>

ቻይና እና ለአፍሪካ የሰጠችው ብድር !!! ቅዱስ ማህሉ

ቻይና እና ለአፍሪካ የሰጠችው ብድር !!!

ቅዱስ ማህሉ
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር፣ የደቡብ ካሮላይና ገዥ፣ደራሲ እና ፖለቲካኛ የነበሩት አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከኮሮና ቫይረስ ውጥን ጀርባ የቻይና እቅድ እዳ የከመረችባቸውን ታዳጊ የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚ የበለጠ በማዳከም ያላቸውን ንብረት(አሴት) ወደራሷ መጠቅለል መሆኑን ዋልስትሪት ጆርናል ያወጣውን ዘገባ ተንተርሰው ጽፈዋል። አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ ” ይህ እንደሚሆን ለሃገራቱ አስጠንቅቀን ነበር።” ብለዋል። ከሁለት ወር በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ያቁም እየተባለ አስተያየት በሚሰጥበት ወቅት እኔ ሙሉ ለሙሉ አየር መንገዱ ወሳኝ ሊሆን የማይችልበት እዳ ውስጥ እንዳለ እና ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ እንዳለበት ወደፊትም አየር መንገዱ ሲሸጥ ቻይና ዋነኛ ባለድርሻ እንደምትሆን ጽፌ ነበር። በዚህ ረገድ ከአንድ ወር ከሃያ ቀናት በፊት ፌብሩዋሪ 29 የጻፍኩትን ጽሁፍ እንዲመለከቱ ሊንኩን ከታች አያይዤዋለሁ። አሁን አምባሳደሯ እና ዋል ስትሪት ጆርናል ቻይና እንዴት የአፍሪካን ወሳኝ አሴቶች ልትጠቀልላቸው እንደምትችል ማሳያ ሲሆን እኔም ለምሳሌ የተጠቀምኩት ለጽሁፌ አጀንዳ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበር።  የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያን በየሰበቡ እና ጠብ በማይል ረብ የለሽ ፕሮጀክቶች ለድግስ፣ለዛፍ መትከያ እና በየመንደሩ እየዞሩ ለማስመሳያ ፎቶ መነሻ የግብር ከፋዩን ህዝብ ገንዘብ እሴት በሌለው ትርኪምርኪ የታይታ ስራ በሚሰሩ “ወሬ ብቻ” በሆኑ ባለስልጣናት መዳፍ ወድቃ ይቅርና ቀንና ሌት የሚያሰራ ፖሊሲ ቀርጸው ሰርተው የሚያሰሩ መሪዎች ቢተኩ እንኳ ያለባትን የእዳ ቁልል ለመክፈል በትንሹ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስፈልጋታል።
ቻይና ደግሞ ያን አትታገስም።
ቻይና ገንዘብ እየሰጠች በእጅ አዙር መሬት ያጋበሰችባቸው እና ኢንዱስትሪ ን የተቆጣጠረችባቸውን ሃገራት የሚፈጠርን ማንኛውም ችግር በኢንዱስትሪዎቿ ላይ የሚቃጡ የአፍሪካዊያን ጥቃቶች በጦር ሃይል ሳይቀር ለመመከት ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ በአፍሪካ የወታደሮቿን ቁጥር ስታሳድግ ቆይታለች። አሁን በአፍሪካ ጸረ ቻይና እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው። ቻይናም ሃገራቱን በኢኮኖሚ አዘቅት ከታ ንብረቶቻቸውን ለመረከብ አቆብቁባለች። ኢትዮጵያ ላይ ያ ፍላጎቷ ነገ እና ከነግ ወዲያ ከሆነ ቻይና የምትነጥቀን የመጀመሪያው ተቋማችን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ከዚያ ቴሌ እያለ ይቀጥላል። ይህን እዳ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትንም በህግ እና በግድ ጭምር ልታስከፍል ትችላለች።
መብቱም አላት። አንድ ቤቱን አሲዞ ከባንክ ብድር የወሰደ ሰው ገንዘቡን መመለስ ሳይችል ሲቀር ገንዘቡን ከነወለዱ የመክፈሉ ጉዳይ አይቀሬ ነው። አለዚያ ንብረቱ ተሸጦ ይከፈላል ወይም ንብረቱን አበዳሪው ይወስዳል። ቻይና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከሌሎች ተቋሞቻችን እንደ በአበደረችን ብድር እና በወለዱ መጠን ድርሻዋን ልትወስድ ትችላለች። ይህን ለማድረግ ካልተሰማማን እና እንቢ ብንል የአርጀንቲና አበዳሪዎች እንዳደረጉት የዓለማቀፍ ፍርድ ቤት መሄድ ሳትሄድ አለማቀፍ የባህር ወሰን ላይ እየጠበቀች በጦሯ የንግድ መርከቦቻችንን መንጠቅ ትችላለች። የአርጀንቲና የጦር መርከብ በጋና ለእረፍት በቆመበት አበዳሪዎቿ የዓለም አቀፍ ፍርድቤት ውሳኔ ለጋና መንግስት አቅርበው ተሳፋሪዎቹን አውርደው መርከባቸውን ይዘው ሂደዋል። ቻይና በጉልበቷ ይህን ማድረግ ትችላለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚበርባቸው ሃገራት ጋር በመደራደር አውሮፕላኖቹን በየሄዱበት ሲያርፉ መንጠቅም ትችላለች። ዓለም አቀፍ ፍርድቤት ከሄደች ደግሞ የጉዳዩን ውስብስብነት በአጭሩ በመቅጨት ሌሎች ሃገራት የፍርድቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ጀርመን የአርጀንቲና አውሮፕላን ሃገሯ ላይ  ሲያርፍ ለአበዳሪዎቿ ይዛ ሰጥታ ነበር። በአጋጣሚ አውሮፕላኑ የተረፈው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት መጓጓዣ ስለነበር እና የዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲ ስላገኘ ነበር። በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ የአርጀንቲና መንግስት ንብረቶች በሙሉ ለአበዳሪዎቹ ተላልፈው ተሰጥተዋል። ቻይና ከነዚህ የግል ባለሃብት እና ገንዘብ አበዳሪዎች የሚለያት ጦሯን በአበደረቻቸው የአፍሪካ ሃገራት አቅራቢያ ማስፈሯ ነው። የቻይና ጦር ዋና ቤም ጅቡቲ ነው። አንድ ሃገር እዳ ተቆልሎበት አልከፍልም ሲል የት ድረስ ሊኬድ እንደሚቻል ለመረዳት ጀርመን እዳ መቅከፈል በማቆሟ ፈረንሳይ እና ቤልጀም በየአቅራቢያቸው የሚገኙትን የጀርመን ግዛቶች ወረው ግብር ይሰበስቡ እንደነበር እና ኢንዱስትሪዎቹን ይጠቀሙባቸው እንደነበር ታሪክን የኋሊት መቃኘት እንችላለን። እዚህ ላይ ቁልፉ ጉዳይ ቻይና የት ድረስ እና መቼ ትገፋናለች ወይም እንዴት ትጋፋናለች የሚለው ነው።
Filed in: Amharic