>

የመንታ ትንሳኤዎች ወግ፤  1978 እና 2012!!!! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

የመንታ ትንሳኤዎች ወግ፤  1978 እና 2012!!!!

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
.
.
በመንታነታቸው መሀል ሰላሳ አራት አመታት አሉ፡፡ በ1978 ብሄራዊ ወታደር ነበርኩ፤ ወታደር ብቻ! ዛሬ መምህር፣ ደራሲና ገጣሚ ነኝ፤ ብዙ ነገር ነኝ፡፡ ሁለቱ እኔዎች የሚገናኙት እንደሸረሪት ድር በቀጠነ ክር ነው፡፡ ይህን ቀጭን ክር አንዳንዴ ወቅትና ገጠመኝ ብረት (ያውም ማግኔት) ያደርጉታል፤ ሁለቱን እኔዎች አሳስሞ ይሰፋቸዋል፡፡ አንድ መንታ ያደርጋቸዋል፡፡ የዛሬው ትንሳኤም ያንን ጉልበት አግኝቷል፡፡.
እነዚህ ሁለት ፋሲካዎች ብቻዬን ያሳለፍኩባቸው ናቸው፤ የ1978ቱ በተዘጋ ቤርጎ፤ የ2012ቱ በተዘጋ ጎጆ፡፡ ጎጆ ከቤርጎ ቢሰፋም፣ ነፍስህ ብቻዋን መሆኗን ካመነች ለውጥ የለውም፡፡
.
በ1978 ለትንሳኤ በአል ወር ገደማ ሲቀረው አንድ ኤሮግራም ደረሰኝ፤ ከወንድሜ ፡፡ ሙሉ ኤሮግራሙ ግጥግጥ ተገርጎ ቢጻፍበትም፣ ዋናው ሀሳብ፣ ‹‹ለትንሳኤ በአል ደሎ መና እመጣለሁ፤ ፍቃድ ጠይቅና ና፡፡›› የሚል ነበር፡፡ የቅዳሜ ስኡር በጠዋት ወደ ደሎ መና፡፡ መንገድ ላይ ሶስት ብሄራዊ ወታደሮችና በርካታ መደበኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ወደ አስር ኪሎ ሜትር በእግር ሄደን፣ ከሪራ የመጣ የጭነት መኪና አገኘን ለቀሪው 12 ኪሎ ሜትር፡፡
.
ደሎመና ደረስኩ፤ ወንድሜን  በየሆቴሉ ፈለግኩት የለም፡፡ የምሳ ሰአት እስኪደርስ ከነዚያ ሶስት ብሄራዊ ወታደሮች ጋር ወዲህ ወዲያ እያልን ቆየን፡፡ ከተማዋ ከማነሷና ከአቧራዋ ጋር፣ የወፍጮ ቤት ቋት አራጋፊ መዳፍ ታክላለች፤ ትመስላለችም፡፡ ወታደሮች፣ ባለሌላ ማእረግተኞችና መኮንኖች አጨናንቀዋታል፡፡
.
ሙሉ ሆቴል የጀርባ በረንዳ ላይ አራታችን ምሳ ስንበላ፣ አንድ በቀበቶ ወገቡን ሰርስሮ ሊበጥስ የተወራረደ የሚመስል መደበኛ ወታደር፣
 ‹‹ብሄራዊ ጦር! እንዴት ናችሁ? የአብዮታዊት እናት ሀገር አለኝታዎች፡፡›› እያለ መጣና በቁሙ ለአራት ያዘዝነው 3 ሚስቶ ላይ ወረደበት፡፡ ‹‹ብሉ እንጂ! ወታደሮች አይደላችሁም!››
ባዶ ትሪ ትቶልን ሄደ፡፡
‹‹ቢበላስ፣ ምግብ እንጂ የሰው ነፍስ አይደል!›› ላለማለት የምትችለው፣ ከ20 ብር የኪስ ገንዘብህ ላይ 3 ብር ተቀንሶ 17 ብር በወር የሚከፈልህና እሷን ይዘህ ከተማ የወጣህ ብሄራዊ ከሆንክ ብቻ ነው፡፡
.
ወደ 8 ሰአት አካባቢ፣ የወንድሜ አለመምጣት ቁርጥ ሲሆን፣ ቢታታ የሚባለው ሰፈር የማውቃት ልጅ አለች፤ እሷ ጋ ሄድኩ፡፡ በሳጠራ የታጠረች፣ አነስ ያለች የአሞራ ክንፍ ቤት ናት፡፡ ከምትሸጠው ጠጅ በነጻ ቀዳችልን፡፡ እኔም አሳቅኳት፤ ሞቅ ሲለኝ ሳቋ እየቸመረ መጣ፡፡ ይባስ ብዬ ናፍቃኝ እንደመጣሁ ነገርኳት፤ አሁንም ይባስ ብዬ፣ ፍቃድ ከልክለውኝ የፈለገው ይምጣ ብዬ እንደመጣሁ ነገርኳት፡፡ በጠጅ ድልቅቅ ብዬ፣ ጠጅ መስዬ፣ እስዋ ዶሮ የሚባርክላት ፍለጋ ስትወጣ አብሬያት ወጣሁ፡፡
.
‹‹እንዳታመሽ›› ስትለኝ፣
‹‹ትንሳኤ እኮ ነው›› አልኳት፡፡
የማላውቀው ኩራት ድብልቅ ስሜት ተሰማኝ፤ አሁን ሳስበው የአባወራነት ስሜት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከነዚያ ብሄራዊ ወታደሮች ጋር ቀጠሮ ነበረን፡፡ አገኘኋቸው፡፡ እንደእኔም ባይሆን ጠጅ ጠጥተው ሞቅ ብሏቸዋል፡፡ ጠጅ ጋበዝኳቸው፤ ከመጣሁ ብዙ አላወጣሁም፤ ወደ 14 ብር ገደማ ነበረኝ፡፡ ለሁለት ጠርሙስ ጠጅ 6 ብር ከፈልኩ፡፡
.
ሁለት ሰአት ላይ ቀን ምሳ የበላንበት ሆቴል ለእራት ስንገባ፣ ያ አራዳ ነኝ ባይ ፍልጥ ወታደር ከበርካታ ወታደሮች ጋር ባንኮኒ ተደግፎ ይጠጣል፤ ወገቡ እስካሁን አለመበጠሱ ገረመኝ፡፡ ሁለቱ ይደንሳሉ፤ የተቀመጡትን አልቆጠርኳቸውም፡፡ በጓሮው በረንዳ፣ ቀን ምሳ የበላንበትን ጠረጴዛ ከበን ተቀመጥን፡፡ ሁለት ሚስቶ አዘዝን፡፡ በጠጅ ጥግብ ብለናል፡፡ አንዳንዴ እንደጎረስን፣ ያ ቀን ምሳችንን ጠራርጎ የበላ ወታደር መጣ፡፡
.
‹‹ብሄራዊ ጦር፤ የአብዮታዊት እናት ሀገር መከታ!››
እጁን አሹሎ መጣ፡፡  ተበሳጨሁ፤ ነጠቃው ሳይሆን፣ እርድናው አበሳጨኝ፡፡ በእሱ ቤት በቃ እኛን ጨላ ባላገር አድርጎናል፡፡
.
ጠረጴዛው ላይ ውሀ የተሞላ አናናስ የመሰለ ጆግና አራት ኒኬል ብርጭቆዋች ከትሪው እየተገፋፉ ተቀምጠዋል፡፡ አንዴ ጎርሶ ሁለተኛውን ሲሰነዝር . . .
‹‹አንተ እናትክን . . . አራዳ መሆንህ ነው!››
ጆጉን አነሳሁና ውሀውን ከክንዱ ጀምሬ ከለበስኩበት፡፡ ትሪው በማእበል ተመታ፡፡ ተጥለቀለቀ፡፡ እሱ ወደኋላው ተፈናጠረ፡፡ ሌሎቹ እጃቸውን ሰበሰቡ፤ መቀመጫዎቻቸውን ስበው ገለል አሉ፡፡
ወዲያው ሳቅ ፈነዳ፡፡ ቀጥሎ የወታደር ጫማ ፊቴ ላይ ፈነዳ፡፡
‹‹የእኔን እናት? . . . የእንጭቅ ልጅ፣ . . ›› (ይህቺን ስድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማኋት የዚያን እለት ነው)፡፡
ካልገደልኩት አለ፡፡
አልሞትም አልኩ፡፡
ተደባደብን፡፡
በጂን የሰከሩ ገደኞቹ ተንጋግተው መጡ፡፡
‹‹ምን ተፈጠረ?››
ጠየቁ፡፡
‹‹ይሄ ኩታራ የእኔን እናት . .  .››
የጸባችን ዋና ምክንያት የእሱ ሌማታችንን በተደጋጋሚ መድፈር መሆኑ ቀርቶ፣ የእኔ  እናቱን በስድብ መድፈር (ያውም በደምፍላት) ሆነ፡፡
ፈረዱብኝ፡፡
‹‹ጠጅ አሳስቶኝ ነው›› ብል የሚሰማኝ አጣሁ፡፡
‹‹የት ይሄድብናል፤ የእኛው ነው፡፡ በዚህ በር አይደል የሚወጣው፡፡››
ጓደኞቹ አባብለው ይዘውት ገቡ፡፡
.
ላልበላነው 2 ሚስቶ 3 ብር ከፈልን፡፡
እንዴት እንውጣ?
ተመካከርን፡፡
እነሱ ያሉበት የሆቴሉ ሳሎን፣ የፊት ለፊት በርና መስኮት ወለል አድርጎ የግቢውን የብረት አጥር ያሳያል፡፡ በዚያ ላይ ለበረንዳው መብራት የገጠሙለት አምፑል ሳይሆን ጨረቃን ራሷን ነው፡፡
.
‹‹አንተ እዚሁ አልጋ ያዝ፡፡ እኛ በውጭ በኩል ወደ አጥሩ በር ተጠግተን፣ ወጥተን እንሩጥ እንሩጥ፡፡ አይዙንም፣ ከያዙንም አንተ ትድናለህ፤ እኛን ምን ያደርጉናል፤ አባረው ከያዙን እሱ ቀድሞን ሮጧል እንላቸዋለን›› አለ አንዱ ብሄራዊ፡፡ አብዛኛው ብሄራዊ ወታደር፣ በተለይ አንደኛው ዙር፣ እራሱን እንደወታደር አይቆጥርም ነበር፡፡ ተስማማን፡፡ አንዱ ቤርጎ ገብቼ ቆለፍኩ፡፡ ወደ በሩ ተጠግተው ሸመጠጡ፡፡
.
ጠጅና ድብድቡ አካሌን እንጂ ህሊናዬን አላደከመውም፡፡ አስብ ነበር ስለዘመኑ . . . ኢትዮጵያውያን ‹‹አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!›› ብለው፣ እጃቸውን እየወነጨፉ፣ ከአስገንጣይ ወንበዴው ወያኔ እና ከገንጣይ ሻእቢያ ሀገራቸውን ሊጠብቁ ይዘምሩ ነበር፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ውትድርና ፈቅደው ይሸኛሉ፤ አኩርፈው ያሳፍሳሉ፡፡ . .  . ኪነት ለአብዮቱ ትዘምራለች፤ ጦር ሜዳ ገብታ ታዋጋለች፤ ከተማ ገብታ ታደራጃለች፣ ታስታጥቃለች፡፡  . . ግዳጅ ይታወጃል፤ የጭነት መኪና ግዳጅ፣ . . . አውቶቡስ ግዳጅ፣ . . .
.
ድንገት ዶሮ ጮኸ!
እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ! ትንሳኤም ሆነ፡፡
በጠባብ ቤርጎ ውስጥ የህይወቴን የመጀመሪያውን የብቻ ፍሲካ ተቀበልኩ፡፡
.
.
ከ34 አመት በኋላ 2012 ሆነ፡፡
በ1978 እርስ በርስ ይዋጉ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ከኮቪድ -19 ጋር ውጊያ ገጠሙ፡፡ እጃቸውን ለመፈክር እየወነጨፉ ወደ ጦር ግንባር አልዘመቱም፡፡ እጆቻቸውን እየታጠቡ ወደቤታቸው ገቡ፡፡ መንግስት አዋጅ አወጀ፣ ግዳጅ ጣለ፤ ቲቪውና ራዴዮው በውሀና ሳሙና ተዘፈዘፈ፡፡ ኪነት እጅ ማስታጠብን፣ ሳኒታይዘር ማደልን፣ እርዳታ ማሰባሰብን . . .  ተያያዘችው፡፡  በ1978 በህግ ያስቀጣ የነበረው፣ የፈሪ ታቴላ የነበረው እቤት መደበቅ፣ ዛሬ የጀግንነት መለኪያ፣ አሸናፊነት ሆነ፡፡
.
አሸናፊነት የሰው ልጅ አራተኛ መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ የዛሬ 34 አመት በውትድርና ክላሽንኮቭ አንግቼ የአሸናፊነት ሰዋዊ ፍላጎቴን (ቢያንስ ባለመሞት) ለማሳካት ሁለት አመት ተኩል ስታገል፣ አንድ ፋሲካ በባዶ ቤርጎ ውስጥ አለፈች፡፡ በዚያ ትግል አሸንፌ ይሁን ተሸንፌ እስካሁን አልገባኝም፤ ቢሆንም ግን አስከ ዛሬ አሸናፊነቴን ለማረጋገጥ እየታገልኩ ነው፤አልታከተኝም፡፡ ይኸው ዛሬም በክላሽ ምትክ ሳኒታይዘርና አልኮል፣ በኮሾሮና ዝግኒ ምትክ ፓስታና የቲማቲም ድልሄን ይዤ፣ ጎጆዬን ዘግቼ ትግል ገጥሜያለሁ፤ ዛሬም አሸናፊ ልሁን አልሁን አላውቅም፤ ትግልን መርሄ አድርጌዋለሁ፤ ትግል ላይ ነኝ፡፡ . . .
ድንገት ዶሮ ጮኸ!
እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ!
ትንሳኤም ሆነ፡፡
በተዘጋ ጎጆ ውስጥ የህይወቴን ሁለተኛ የብቻ ፍሲካ ተቀበልኩ፡፡  ሶስተኛ፣ አራተኛ . . . ይኖረው እንደሁ ማን ያውቃል!
 (ሰኔ 1978)…………………….…… (ሚያዝያ 2012)
Filed in: Amharic