ታዋቂው አክቲቪስት ገዛኸኝ ነብሮን ማን ገደለው?…..
ታምሩ ገዳ
የደቡብ አፍሪካው ታዋቂ ጋዜጣ፣ ዘ ሜል ኤንድ ጋርዲያን ከዛሬ ሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያዊው የመብት አቀንቃኝ /አክቲቪስት ገዛኽኝ ገ/መስቀል በቅጥረኞች መገደል፣ እና በአሟሟቱ ዙሪያ ሰፊ እና ጥልቅ ዘገባ አስነብቦ ነበር።
በሚያዚያ 21 ,2018 እኤአ እለተ ቅዳሜ ከቀኑ 5pm(በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ 11 ) ብዙ ሰው በሚያዘወትርበት የመሃል ጆሃንስበርግ ጎዳና ላይ ከጓደኞቹ ጋር በሽርሽር ላይ የነበረው ዛግቦ ፖስካል አንድ የጥይት ድምጽ ይሰማል፣በአካባቢውም ሲያማትር አንድ ስው ከአንገቱ ላይ ደም እይፈሰሰው ከመሬት መውደቁን ፣በአቅራቢያውም እንድ ቀጠን ያለ እና ማንነቱን በምናቡ ሊቀርጸው ያልቻለ ሰው ተልእኮውን ፈጽሞ፣ ሽጉጥ እያወናጨፈ ከስፍራው ለመሰወር ሲጣደፍ እርሱ እና ጓደኞቹ ተመልክተዋል።
ምንም እንኳን የአገሬው ፖሊስ ከግማሽ ሰአት በሁዋላ ወደ ስፍራው ቢመጣም አስክሬኑንም ከሰአታት በሁዋላ ቢያነሳውም ያ ህዝብ በተሰበሰበት ስፍራ የተገደለው ግለሰብ ተራ ሰው ባለመሆኑ፣ ግድያውም ተራ ወንጀል ስላልነበር በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰባሰቡ። የአይን እማኙ ፖስካል ” ደም እይፈስሰው እያየን ምንም ልንረዳው ባለመቻላችን አዝነናል ፣ግድያውንም ለተመለከተው ዘግናኝ እና አሳዛኝ ነው” ብሎታል። ስለ ግድ ያው ምንነትም ፓስካል እና በአካባቢው የነበሩት ሁለት እማኞች ለጋዜጣው ዘጋቢ ግምታቸውን ሲናገሩ ” ተራ የዝርፉያ ወንጀል ላለመሆኑ የሟቹ ንብረቶች የሆኑ ሁለት ዘመናው የእጅ ስልኮች ፣በኪሱ ውስጥም የነበረ በጥሬ ገንዘብ አንድ መቶ ሀምሳ ሽህ የደቡብ አፍሪካ ራንድስ(ስምንት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም ወደ ሁለት መቶ ስድሳ ሺህ ብር) አንድም ሳይነኩ ቦርሳው ሳይበረበር መገኘቱ ግድያው የወረበላዎች ጥቃት ያለመሆኑን ያመላክታል” ብለዋል።
ወደ ስፍራው ለምርመራ ተሰማርትው ከነበሩት የፖሊስ ባልደረቦች መካከል አንድ ማንነቱን ለጊዜው መግለጽ ያልፈለገ የፖሉስ አባል ከአስር ቀናት ምርመራ በኃላ የደረሱበት ድምዳሜ ሲናገር “ገዳዩ ተልእኮውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ግድያውም ታቅዶ እና ተወጥኖ የተፈጸመ ነው።” በማለት ሙያዊ ድምዳሚውን ለጋዜጣው ዘጋቢ ሰጥቷል።በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሀላፊ እና የገዛኸኝ ነብሮ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ ታምሩ አበበም”ግድያው ተራ ግድያ ላላመሆኑ እና በእቅድ ለመከናወኑ ምንም አያጠራጥርም”በማለት ለ ሜል እና ጋርዲያን ዘጋቢ በወቅቱ አረጋግጠዋል።
ሟች ገዛኸኝ ነብሮ ማን ነው?፣ለምንስ ተገደለ?…
በቀድሞው መንግስት የአየር ወለድ አባል ሆኖ አገሩን እና ልጇቿን በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገለው የአርባ ስምንት አመቱ የሃምሳ አለቃ ገዛኽኝ ገ/መስቀል (ነብሮ) በአገሩ ኢትዮጵያ የነበረውን ጭቆና እና በደል በመቃወም ከሁለት አስር አመታት በፊት ወደ ደ/አፍሪካ በመሰደድ ፣በላቡ ጥሮ ግሮ፣ የራሱን የንግድ ተቋም በማንቀሳቀስ ከራሱ ተርፎ ለበርካታ ወገኖቹ ተርፏል።እንደ ጋዜጣው ቅኝት ገዛኽኝ ነብሮ ለ በርካታ አዳዲስ የደ/አፍሪካ ተሰዳጅ የአገሩ ልጆች የገንዘብ ፣የሞራል እና የማቴሪያል እገዛ በማድረግ በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት ይታወሳል። ለዚህም ይመስላል በቀብሩ ስነስርዓት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ በመውጣት ገሚሱ የኢትዮጵያ ሰንደቅን በመልበስ የተቀረው የሟች ነብሮ ምስል ያለበት ቲሸርት በማጥለቅ መሪር ሀዘናቸውን ልዩ ፍቅራቸውን የገለጹት፣ቀብሩንም ከአንድ ታላቅ ሰው ሽኝት ያልተናነሰ ያደረጉሉት።
ገዛኸኝ ነብሮ ከለጋስነቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይ በስብአዊ መብት ረገጣ የሚደረጉ በርካታ ተቃውሞዎችን በፊት አውራሪነት ሲዘውሩ ፣ድምጽ ለሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ድምጽ ከነበሩ ፣አይን ግቡ ፣ በጣት የሚቆጠሩ አክቲቪስቶች መካከል ይጠቀሳል። ይህም አገር እና ህዝብ ወዳድነቱ በወቅቱ በፕሪቶሪያ ከሚገኘው የህዋት/ኢህአዲግ መራሹ ኢምባሲ በኩል ከጥርስ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን ጋዜጣው መጠቆሙ አልቀረም።
ምንም እንኳን ኢምባሲው በወቅቱ ወቀሳውንም ሆነ “ከግድያው ጀርባ እጆቹ እንደሌሉ ቢያስተባብልም “እንደ ሜል ጋርዲያን ዘገባ ግን ገዛኽኝ ነብሮ ከመሞቱ አንድ ቀን ቅደም ብሎ ኢምባሲው አስተናግዶት በነበረው አንድ ንግድ ተኮር ስብሰባ ላይ ተገኝቶ በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ጭቆና የተቃውሞ ድምጹን ሊያስማ ቢሞክርም ቀድሞውንም የሚያውቁት የኢምባሲው የጸጥታ ኃይሎች ከስፍራው እንዳባረሩት፣ ፣በተመሳሳይ ምሽት ማንነታቸውን የደበቁ ወገኖች በማህበራዊ መረብ አማካኝነት “ለምን አትተወንም፣ዝም ብለህ ስለቤተሰብህ ብትጨነቅ ይሻላል ፣አለበለዚያ ግን መላ እንቀይስልሃን”የሚል ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደ ደረሰው፣ በበነጋታውም ገዛኸኝ ነብሮ በአደባ ባይ እንደ ተገደለ ጋዜጣው ዘግቧል።
ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህምድ እና አስተዳደራቸው ” አሸባሪዎች ነበርን ያሉት ስርዓት ተገፍትሮ” ወደ ስልጣን እንዲመጡ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ አክቲቪስቶች ፣ ቄሮዎች ፣ፋኖዎች እና ዙርማዎች…ወዘተ እንደሆኑ በተለያዩ መድረኮች ላይ እማኝነት መስጠታቸው ይታወሳል። ገዛኸኝ ነብሮም ከእነዚህ የለውጥ መንገድ ጠራጊ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ለመሆኑ ገድሉ ያስረዳል።
የደቡብ አፍሪካው ዘ ሜል እና ጋርዲያን ጋዜጣ በወቅቱ አንድ ቁልፍ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። እርሱም :-” ኢትዮጵያዊው አክቲቪስት ገዛኸኝ ነብሮን ማን ገደለው?/ Who killed the Ethiopian activist?”የሚል ነበር። ምንም እንኳን የጀግና ገድሉ ከቶ ባይሞትም ፣ያ የጋዜጣው ሙያዊ፣መሰረታዊ እና የሰብአዊ መብት ጥያቄ ዛሬም የአክቲቪስት ገዛኸኝ ነብሮ ሁለቱ ታዳጊ ልጆቹ፣ባለቤቱ፣ደካማ እናቱ፣ቤተሰቦቹ እና አፍቃሪ ዲሞክራሲዎች የዶ/ር አብይ አስተዳደር ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርብላቸው ዘንድ ፣የቀድሞ የኢምባሲው ሹማምንቶችም በገዛኸኝ ነብሮ ግድያ ዙሪያ ግልጽ እና ሙሉ መረጃ እንዲሰጡበት መጠየቃቸው አይቀርም።