>
5:13 pm - Sunday April 19, 5029

በ ‘ደም የተገኘ’ ደም አፋሳሽ ህገ-መንግሥት!!! (ታሪኩ አባዳማ)

በ ‘ደም የተገኘ’ ደም አፋሳሽ ህገ-መንግሥት!!!

ታሪኩ አባዳማ 
* ዛሬ በ ‘ደም የተገኘ’ ህግ ጥላ ሥር ህገ ወጥነት የተነሰራፋበት ፣ ፖሊስ እያለ በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ የሰፈነበት ፣ ዳኛ እና ፍርድ ቤት እያለ ፍትህ የጠፋበት ፣ ወታደር እያለ የአገር ህልውና ፈተና ላይ የወደቀበት ምክንያት ምንድነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ህጉ ህገ_ወጥነትን ህጋዊ አድርጓል ቢባል ማጋነን ይሆንብን ይሆን? 
 —
የሰው ዘር ዕድገት ታሪክ እንደሚያረጋግጠው የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት እንዲሰፍን ፣ ጉልበተኛው ደካማውን እንዳያጠቃ ፣ወስላታ የሌላውን ንብረት እንዳይዘርፍ እንዳይመዘብር ፣ መዝጊያ ገልብጥ ከክፉ ዓመሉ እንዲታቀብ እና አጥፊ በጥፋቱ እንዲጠየቅ ፣ ብሎም የሰላም እና ዕድገት ፈር እንዲሰምር በየመስኩ ስርዓት እንዲኖር ህግ እንዲደነገግ እና መንግሥት እንዲቋቋም ግድ ሆኗል። ቅድመ ታሪክ ግኝቶች እንደሚጠቁሙት ማህበራዊ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መንደር በመውረር እና በመቀማት ፣ በመማረክ እና ባርያ አድርጎ በመበዝበዝ ላይ የተመሰረት ነበር —  ለሺህ ዓመታት የዘለቀው ካንዱ ሁዋላ ቀር ግንኙነት ወደ ተሻለ የመሸጋገር ሂደት የሰው ልጅ ከሌሎች እንሰሳት የተሻለ የማሰብ ፣ የማገናዘብ ፣ የማስተዋል ፣ የመተንተን እና የመተግበር ብቃቱን ለራሱ ያሰመሰከረበት ነው።
የዕድገት ሂደቱ በሁሉም ዓለም በተመሳሳይ ደረጃ የተከናወነ ባይሆንም የለውጥ ጉዞ ወይንም እንቅስቃሴ ሁሉም ዘንድ መኖሩ ግን እውነት ነው። ቀድሞ የሄደው ሁዋላ የቀረውን ለማገዝ እና የዕድገቱን እሴት እንዲቋደስ የማድረጉ ሂደትም እንዲሁ የለውጥ ሂደትን ለማቀላጠፍ መርዳቱ እሙን ነው። አውሮፓ በተፃፈ የህግ ጥላ ሥር መኖር ሲጀምር አፍሪቃ በጎሳ እና ጎበዝ አለቆች ፈቃድ ስር ይተዳደር  ነበር –
ሁላችንም የህግ በላይነት ይረጋገጥ ስንል ይሰማል – ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት እስከ ተራ ፖሊስ ፣ ከጳጳስ እና ሸህ እስከ ተራ ምዕመን ፣ ፊደል ከቆጠረው እስከ ተራው ዜጋ ፣ ከህወሃት እስከ ኤጀቶ ፣ ከፋኖ እስከ ቄሮ እና ባለደራስ ፣ ከጠንቋይ እስከ ደብተራ እንዲሁም ከቧልተኛ እስከ ጋዜጠኛ… ሁሉም የህግ በላይነት መረጋገጥ አለበት ሲሉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይሰብካሉ… — ህግ የምናከብር ብቻ ሳይሆን በህግ ጥላ ስር መኖር ሥልጣኔ መሆኑን እንደተረዳን ሥልጡን ዜጋ ሁሉ አበክረን እንናገራለን።
ህግ እና ህጋዊነት – ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ እስከ ዛሬ ድረስ በታላላቅ የትምህርት ተቋማት እንደ መደበኛ የማስተማሪያ መፅሀፍ ሆኖ እያገለገለ ያለውን The Republic የመጀመሪያ ምዕራፍ የከፈተው ‘ፍትህ ምንድነው’ በሚል ጥያቄ ነበር – ጥያቄውን ከተለያየ አመለካከት እና አቋም አንፃር እንዲመልሱለት ገፀ ባህሪያትን ፈጥሮ ጥልቅ የሆነ ሙግት በመቀስቀስ ሁላችንም የምንስማማበት የፍትህ ትርጉም ለመቅረፅ ብርቱ ጥረት አድርጓል – ዛሬ በተለያየ ዓለማት አንዱ የህግ ጥበቃ ያደረገለት ጉዳይ ሌላው ዘንድ እንደ አደገኛ ወንጀል የሚቆጠርበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን — ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ህጋዊ በሆነባት ካናዳ ጉዳዩ ወንጀል መሆኑን የብዙ አፍሪቃ አገሮች ያግዱታል –
ገዢ የሆነ የፍትህ ትርጓሜ በህበረተሰብ ውስጥ ሰርፆ ከሌለ ሁሉም እንዳሻው ለግሉ ወይንም ወክለዋለሁ በሚለው ቁንፅል ማህበረሰብ ጥቅም አንፃር በመተርጎም ምስቅልቅል እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል – ወንጀል ወይንም ፍትህ እንደ ባለጉልበቱ አተረጓጎም ይሆናል – ጉልበተኛ በሄደ እና በመጣ ቁጥር ትርጓሜው ለየቅል እየሆነ ህብረተሰቡ እንደ አለኝታ እንደ ዋስትና እና ታዳጊ የሚቆጥረው ህግ ይጠፋል — ህገወጥነት ይንሰራፋል።
በጥንታዊው የሀሞራቢ ህግ አይን ያጠፋ አይኑ ይጠፋል ሲል ጉልበተኞች በዘፈቀደ በደል እንዳያደርሱ ልጓም ሆኖ የሚገታቸው በሁሉም ላይ እኩል ተፈፃሚነት ያለው ጠንካራ ድንጋጌ እንደነበረው ይታወቃል። ባልተፃፈ የጉልበተኞች ትዕዛዝ እና መልካም ፈቃድ ሥር የሰው ፊት እያዩ ከመሳቀቅ ገዢ በሆነ ሁሉም ይፋ በተቀበለው ሰነድ ጥላ ሥር መኖር ቢያንስ የህግ ዋስትና መኖሩንና እና በደል ቢፈፀም አቤት የሚሉበት ዳኛ መቀመጡን ያረጋግጣል ። የአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ደረጃ ከሚገለፅባቸው አቢይ ጉዳዮች ውስጥ በተፃፈ ህግ ጥላ ስር ማህበራዊ ህይወቱ ዋስትና ማግኘቱ አንዱ ነው። የህግ ዋስትና በማያወላዳ ብቁ አስፈፃሚ ተቋማት ጠንክሮ ካልቆመ ማህበራዊ ህይወት ይናጋል።
ኢትዮጵያ ይፋ በታወጀ እና በተፃፈ ህግ መተዳደር የጀመረችው በአፄ ኋይለሥላሴ ዘመን ይመስለኛል – ንጉሠ ነገሥቱ ለሚወዳቸው እና ለሚወዱት ህዝባቸው ያበረከቱት ስጦታ እንደነበርም ተነግሯል። ከዚያ ወዲህ በማንም ይፅደቅ በማን የተፈራረቁት መንግሥታት የሚያጣቅሷቸው አንቀፆች እና ሰነዶች አሉ – ህግ ይከበር ብለውም ሰነድ ይጠቅሳሉ – በህገ መንግሥቱ መሰረት ሲሉ ይሰማል ፤ የቅርቡን እንኳ ብናስታውስ ህገ መንግሥቱን በሀይል ለመናድ እያሉ ሌሎችን ሲወነጅሉ መስማት የህግ ዋስትና ላጣው ህብረተሰብ እንግዳ ነገር አይደለም– በድህረ ወያኔ የታወጅውን ህግ ቀድም ካሉት የሚለየው ዋና መሰረታዊ ጉዳይ ዜጎችን በጎጥ ግንድ ከፋፍሎ አንዱ ሌላውን እየተጠራጠረ እና እየመነጠረ በስጋት እና በዋስትና ማጣት ሰበብ አገራዊ ማንነት እንዲፈራርስ አመቺ መደላደል ከመፍጠሩ ላይ ነው – እነ አብዲ ኢሌ ከሌላ ዘር መጣችሁ ብለው ዜጎችን በአደባባይ ሲጨፈጭፉ በህሊናቸው ይህንን በደም የተገኝ ህገ መንግሥት ማስከበራቸው መሆኑን መዘንጋት የዋህነት ነው – እነሱም በደም ያገኙትን ‘የክልል ፕሬዘዳንትነት’ ስልጣን በደም በተገኘው ህገ መንግሥት ካላሰከበሩ ክህደት እንደፈፀሙ ይሰማቸዋል…
እኔ የህግ ተማሪ አይደለሁም – ከህግ ተማሪዎች ጋር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የተጋራሁት ቢኖር በጊዜው ፐሮፌሰር ሰምነር ይሰጡ የነበረውን logic የተሰኘ ኮርስ ብቻ ነበር። እንደ ተራ ዜጋ በምሰነዝረው አስተያየት ሙያ ነክ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ማንሳት አይጠበቅብኝም ለማለት ነው። እናም ራሴን ጠይቃለሁ…
በድህረ ወያኔ/ኢህአዴግ ዛሬ በ ‘ደም የተገኘ’ ህግ ጥላ ሥር ህገ ወጥነት የተነሰራፋበት ፣ ፖሊስ እያለ በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ የሰፈነበት ፣ ዳኛ እና ፍርድ ቤት እያለ ፍትህ የጠፋበት ፣ ወታደር እያለ የአገር ህልውና ፈተና ላይ የወደቀበት ምክንያት ምንድነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ህጉ ህገውጥነትን ህጋዊ አድርጓል ቢባል ማጋነን ይሆንብን ይሆን? ለመላ ዜጎች ያለአንዳች አድልዎ እኩል ተፈፃሚነት ያለው የህግ ዋስትና የሚሰጥ ህግ አለ ወይ ብሎ መጠየቅ በራሱ ወንጀል በሆነበት አገር ስለ ህግ ዋስትና እና የህግ በላይነት እንዴት መነጋገር ይቻላል?
አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ‘በህግ አምላክ’ ሲል ብንሰማ ስለየትኛው ህግ ማለቱ እንደሆነ የሚገነዘብ ሰው ካለ ጉልበቱ ሥር ቁጢጥ ብዬ ለመማር ዝግጁ ነኝ – በቅርቡ ሲዳማ ውስጥ ለዘመናት የቋጠሩትን ንብረት በጠራራ ፀሀይ ሲዘረፉ በህግ አምላክ ብለው የተማፀኑ አዛውንት ይህን ለማለት በመድፈራቸው ብቻ በጭካኔ ተገድለዋል — ትንሽ ምሳሌ ናት — ያንድ ዜጋ ህጋዊ ዋስትና ተጣሰ ማለት የሁሉም ዜጋ የህግ ዋስትና ጥያቌ ውስጥ ወደቀ ማለት ነው። ለዚህ ነው በሁሉም ዜጋ ላይ እኩል ተፈፃሚነት ያለው ህግ ገዢ እስካልሆነ ድረስ በህግ የሚያስተዳድር መንግሥት ስለ መኖሩ ጥያቄ የሚነሳው…
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ተናግረው ነበር — በፓርላማ ስብሰባ የመጀመሪያ ሪፖርታቸው ወቅት ከትግራይ ተውክለው በተሰየሙ አንዲት ክብርት ወይዘሮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ያሉትን — ከትግራይ በደም የተገኘ ዲሞክራሲ አግባብ ተመርጠው የፓርላማ አባል የሆኑት ወይዘሮ ጠ/ሚኒስትሩ ‘በደም የተገኘውን ህገ መንግሥት’ እያስደፈሩ መሆኑን በመጥቀስ ወቀሳ ጭምር ነበር ያቀረቡት —
አቢይ አህመድ ሲመልሱ ‘… ህገ መንግሥቱ ዜጎች ብልት ላይ ጠርሙስ እያንጠለጠልክ መረጃ ሰብስብ የሚል አንቀፅ የለውም …’ ነበር ያሉት — የጠ/ሚኒስትሩ መልስ የተሟላ ባይሆንም ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ – ለኔ እንደገባኝ ጠርሙስ ከሰው ብልት ላይ አንጠልጥለው ያሰቃዩ የነበሩ የህግ ጥበቃ ሰራተኞችን ያፈራ ህገ መንግሥት መሆኑን ጥምር መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል። ጠ/ሚኒስትሩ ካንጀታቸው የተናገሩት ከሆነ መልካም ነበር… ግን ይህ ሰቆቃ ለህጉ ጥበቃ ሲባል በተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም መፈፀሙ የህጉን መሠረታዊ ግድፈት አብሮ የሚጠቁም ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ሲናገሩ እንደሰማችሁት ይህ አሁን ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት ህግ በደም የተገኘ ነው። በደም ተገኘ የተባለውን ህገ መንግሥት በተግባር መንዝረን ዝርዝሩን ስናየው ደግሞ በርግጥም ዛሬ ከሀያ ስምንት ዓመታት የደም ህገ መንግሥት አገዛዝ በሁዋላ የት እንዳለን ቁልጭ ብሎ ይታየናል…
እርግጥ ነው ባለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት የሆነውን ስናጤን በደም ያልተገኘ አንዳችም ነገር የለም – በደም የተገኘ ጀነራልነት ፣ በደም የተገኘ ሚኒስትርነት ብሎም ጠ/ሚኒስትርነት ፣ በደም የተገኘ አምባሳደርነት ፣ በደም የተገኘ ‘ክልል’ አስተዳዳሪነት ፣ በደም የተገኘ ፖሊስ አዛዥነት የኮርፐሬት እና ግዙፍ የንግድ እና ማምረቻ ድርጅቶች ዋና ስራ አስኪያጅነት… ዛሬ ዓለም የደረሰበትን ግሥጋሴ እና ምጥቀት ለማምጣት የሰው ልጅ በመደበኛ ትምህርት እና ልዩ ምርምር ተጠምዶ ችሎታውን በሚያስመሰክርበት ወቅት እኛ አገር ማንኛውንም ሁነኛ ሀላፊነት ያለው ሥልጣን ለመጨበጥ ወሳኙ በደም የተገኘውን ህገ መንግሥት ለማወደስ እና የፖለቲካ ሥርዓቱን ተቀብሎ በታማኝነት ማገልገል ሆኖ እናገኘዋለን። ጥያቈው ምን ብቃት እና እውቀት አለህ ሳይሆን በደም ተገኘ የተባለውን ስርዓት ለማቆየት ምን ያህል ታማኝ ነህ የሚለው ነው… በደም ተገኘ የተባለው ህገ መንግሥት ሲቸረቸር ዝርዝሩ እስከ መንደር የደም ባለሥልጣናት ማንነት ዘንድ ያደርሰናል —
ህግ አለ ብለህ ሰነድ ብትጠርዝ በሙያዊ ብቃት የተገነባ ተርጓሚና አስፈፃሚ ተቋማት ከሌሉህ ፌዝ እና ቀልድ ይሆናል። የህግ ተርጓሚ ወይንም አስፈፃሚ ብለህ በብሄር ብሄረሰብ ታማኝነት መለኪያ ያስቀመጥከው ሰው ሲልከሰከስ እና የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ ብታገኘው ጥፋቱ ሙሉ ለሙሉ የግለሰቡ አይደለም። እንደ ሜቴክ ያሉ ትላልቅ የማምረቻ እና ንግድ ተቋማት በዱር የደፈጣ ውጊያ ነፃ አውጪ ነን ባሉ የፍየል እረኞች እጅ ወድቀው ቢሊየን ብር እንዲያሰሉ ፣ እንዲያቅዱ እና ትርፋማ እንዲሆኑ ስትጠብቅ ቤታቸውን ሳይቆልፉ እኔን ሌባ ይላሉ እንዳለችው ድመት መሆን ነው።
ሌቦቹን ነጻ አውጪዎች ተጠያቂነት በሌለበት አሰራር ታፍሶ የማያልቅ የአገር ሀብት እንዲያሰተዳድሩ ስትሾም ያኔ ነው ነገር የተበለሸው … ሹመቱም ዘረፋውም በዘር ማንነት እንዲሆን ያመቻቸው የፖለቲካ ስርዓት ፍፁም ተጠያቂ እና አብሮ ለፍርድ ቀራቢ መሆን አለባቸው። ይሄ ግን ባንድ ጀምበር በደም ፍላት ተነስተው መንጋ ማዝመት ከሚፈልጉ ሀይሎች የሚከናወን ሥራ አይደለም። አሁን የተገኘው ለውጥ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጥቅሞ ቢያንስ ረጋ ብሎ በሁሉም ዘርፍ ከተሰማሩ ዜጎች ጋር ሀሳብ ተለዋውጦ ለዘለቄታው የሚጠቅመውን ማስላት አማራጭ ያለው አይመስልኝም።
እነ ጌታቸው አሰፋ በደም ያገኙትን ሚኒስትርነት እና ጄነራልነት በደም ለመጠበቅ ሲሉ በደም የተገኘውን ህገ መንግሥት መከታ አድርገው ኖረው አሁንም በደም የተገኘውን ህገ መንግሥት ንቀው በደም በተገኘ ህገ መንግሥት በምትተዳደረው አገር በአደባባይ እየተንጎማለሉ ይኖራሉ። በደም ስለተገኘው ህገ መንግሥት ስናወሳ ዝርዝሩ ይከረፋል…
ዛሬ ተንሰራፍቶ የምናየው ህገ ወጥነት የሚመመነጨው በደም ከተገኘው ህገ መንግሥት መሆኑን በጥሞና መቀበል ያሻል። ህወሀት ጫካ ያረቀቀው የከፋፍለህ ግዛ ሰነድ ባለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት ያሰፈነውን የጥፋት ፣ ስደት ፣ ዘረፋ ፣ እስር እና ግድያ ስናሰላስል ህጉ በደም የተገኘ ደም አፋሳሽ ሰነድ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም። የዶ/ር አቢይ የለውጥ ሀይል በደም የተገኘውን ህገ መንግሥት በመመካት ዘርፈው በከበሩ ጥቂቶች እና ተዘርፈው በደኸዩ ብዙሀን ዜጎች መካከል የቆመ መንግስት ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ በደም የተገኘው ህገ መንግሥት በደም ከተገኘው ስልጣን በላይ ሳይሆን እስከ ዛሬ ደርሰናል። በደም በተገኘ ህገ መንግሥት ገደብ የለሽ ስልጣን ገደብ የሌለው ዘረፋ እና ሰቆቃ ሰፍኗል። እንዲያውም በጎጥ ተደራጅቶ የሌሎችን ደም በማፍሰስ ለከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን መብቃት እንደሚቻል ህወሀት በግብር አረጋግጧል። የህወሀት አርአያነት ብዙ ጎጠኞችን አነቃቅቷል ፣ አበረታቷል… ትግራይን ነፃ ለማውጣት ዘገር ሰንቆ በረሀ የገባው ጎጠኛ በደሀው ልጅ የደም ኪሳራ መሪዎቹን በሀብት እና ስልጣን ለማንበሽበሽ ካበቃ የስልጣን ማማ ላይ በማቆሙ የሌሎች መሰል ጎጠኞችን አይን ስቧል። የህወሀት ለስልጣን መብቃት ብቻ ሳይሆን እንደ ባዕድ የወጉትን ህዝብ እና አገር ተቆጣጥሮ ባልተወለደ አንጀት ይሉኝታ ቢስ ዘረፋ ሲያደርግ እስከ ዛሬ መዝለቁ ጎጠኝነት ትክክለኛ አደራጃጀት ስልት ነው ወደሚል ዝንባሌ እየወሰደ ነው። በጎጥ መደራጀት የስልጣን ጥያቄን በተሳካ እና ዘላቂነት ማሳካት እንደሚያበቃም እየታመነበት ይገኛል።
እናም ጠ/ሚኒስትሩ በደም የተገኘ ህገ መንግሥት ማለታቸው እንደምታው ምንድነው ብለን ብንጠይቅ እነሆ ዛሬም ሌላ በደም የሚፃፍ ህገ መንግሥት ሊያስታቅፉን ደም በማፈሰስ ላይ ያሉ ሀይሎች መኖራቸው ነው – በደም የተገኘ የሚለው አነጋገር ሌሎች ደም አፍስሰው የራሳቸውን በደም የተገኘ ህግ እንዲያስታቅፉን የሚያበረታታ ነው። እናም እነሱም ይሉናል – በደም የተገኘ –
የተፃፈ ህግ እንዳለ ቢታወቅም ያንን ህግ ደፍጥጦ ባልተፃፈ ህግ ዕለት ተዕለት መኖርን እንመርጣለን – ህግ የሚጣሰው የህግ በላይነት ይከበር ብለው በሚሰብኩ እና ህጉ እንዲረጋገጥ እና እንዲከበር ሀላፊነት በወሰዱ ዜጎች ጭምር ነው። እናም አገሪቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ በተፃፈ ህግ ጥላ ሥር ማስተዳደር ከተሳነ ህብረተሰቡ የከፋ አደጋ ላይ መውደቁን ቁልጭ አድርጎ ያመለክታል። ይኼ መቆም መቻል አለበት… ይህን በአገር ደረጃ ማስቆም ካልተቻለ አገር ነን ማለቱ ለይቶለት ግንጠላ እስከሚታወጅ የመጠበቅ ያህል ነው።
የህግ በላይነት ትርጉም ከመሰረቱ ተናግቷል – የህግ በላይነትን እንወዳለን ግን በዕለት ተለት ህይወታችን ህግ እንጥሳለን – ሁላችንም። በህገ መንግሥት መገዛት እጅግ የምንፈልግ ይመስል ህገ መንግስቱ ይለወጥ ይሻሻል ይናድ እንላለን – ስለ ህግ እና ሀገ መንግሥት ትንሽ የተሻለ ግንዛቤ እስከሌለን ድረስ ሰነዱ ተለወጠ አልተለወጠ ተሻሻለ አልተሻሻለ ተናደ ወይንም ተነከባለለ ያለንበትን አሳፋሪ ማህበራዊ ግንኙነት የሚቀይረው ነገር የለም። ህግ አልባነት ባህሪያችን በህገ-መንግስት ሰነድ ሸጋ አንቀፆች እና ምዕራፎች መሻሻል የሚለውጥ አይደለም።
አጠር ለማድረግ ያህል – በደም ሳይሆን በህዝባዊ ሙሉ ተሳትፎ እና ጥሞናዊ ውይይት የተጻፈ ህገ መንግሥት እስከሌለ ድረስ ሰላም እና ዕድገት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ጉም እንደ መዝገን ያህል ነው። ፖለቲከኞቻችን በደም ሳይሆን በውይይት እና ሙግት ላይ ተረቆ ግልፅ በሆነ የሁሉም ዜጎች እኩል ተሳትፎ አዎንታ የፀደቀ ህግ እንዲገዛን ይፈቅዱልን ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን — — ሌብነት እና ሰቆቃ መፈፀም አኩሪ ተግባር እነድሆነ ሁሉ የድርጊቱ ፈፃሚዎች አይነኬ እንደምሆናቸው ሁሉ በደም ስለተገኘ ህገ መንግሥት በኩራት መናገር እራሱ አሳፋሪ ሊሆን ይገባል – በደም የተገኘው ህገ መንግሥት በጥሞና ውይይት በሚረቀቅ ህገ መንግሥት ይተካ ዘንድ እንጠይቃለን – ብዬ ሀተታዬን ደመድማለሁ…
እኛ አልኩ እንዴ? – እኛ ማን ነን?
Filed in: Amharic