>
5:18 pm - Wednesday June 15, 6033

የብርሃኑ ዘሪሁን 33ኛ እና የደበበ ሰይፉ 20ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ!!! (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የብርሃኑ ዘሪሁን 33ኛ እና የደበበ ሰይፉ 20ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ!!!

 

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
፩). ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ያረፈው ከዛሬ 33 ዓመታት በፊት (ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም) ነበር፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን «የታንጉት ምስጢር»፣ «ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ››፣ ማዕበል የአብዮት ማግስት»፣ ‹‹የቴዎድሮስ እምባ››፣ ‹‹ጨረቃ ስትወጣ››፣ ‹‹የእንባ ደብዳቤዎች››፣ ‹‹ድል ከሞት በኋላ ነው››፣ ‹‹የበደል ፍፃሜ››፣ ‹‹አማኑዔል ደርሶ መልስ››፣ ‹‹ብርአምባር ሰበረልዎ››፣ ‹‹ባልቻ አባ ነፍሶ››፣ ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ››፣ ‹‹የለውጥ አርበኞች››፣ ‹‹ሞረሽ›› በተባሉት የልብ ወለድና የተውኔት ስራዎቹ ይታወቃል፡፡
፪). ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ያረፈው ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት (ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም) ነበር፡፡
ደበበ የተዋጣለት ገጣሚ ነበር። የግጥም ትሩፋቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ‹‹የብርሐን ፍቅር›› በሚል ርዕስ ታትመዋል። በ1992 ዓ.ም ደግሞ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ‹‹ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነ-ግጥም መፅሐፉ ታትሞ ለንባብ በቅታለች።
– – –
ደበበ ከገጣሚነቱ ባሻገር ሐያሲም ነበር፡፡ ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳና የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሒስ ጥበብን ከታደሉትና በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነበር።
ደበበ የትያትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሠሩ ቴአትሮችንና የቴአትር ጽሑፎችን የያዟቸውን ሐሳቦች በመተንተንና ሒስ በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
– – –
ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው። ለአብነት ያህል በትያትርና በሥነ-ጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትንና ‹‹ገፀ-ባህርይ››፣ ‹‹ሴራ››፣ ‹‹መቼት››፣ ‹‹ቃለ-ተውኔት›› … እየተባሉ የሚገለፁትን መጠሪያዎች የፈጠረው ደበበ ሰይፉ ነው።
– – –
ደበበ ለትያትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም. ‹‹የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር›› የሚል ርዕስ ያላት መጽሐፍ ማሳተሙ የሚጠቀስ ነው።
– – –
ደበበ ጸሐፌ ተውኔትም ነው። በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለበርካታ ጊዜያት ያህል በቴሌቪዥን ታይተውለታል፡፡ ደበበ ከጻፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል ‹‹ከባህር የወጣ ዓሳ››፣ ‹‹እናትና ልጆቹ››፣ ‹‹እነሱ እነሷ››፣ ‹‹ሳይቋጠር ሲተረተር››፣ ‹‹የሕፃን ሽማግሌ››፣ ‹‹ማክቤዝ››፣ ‹‹ክፍተት››፣ ‹‹እድምተኞቹ›› እና ‹‹ጋሊሊዮ ጋሊሊ›› ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
– – –
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በነበረባቸው ዓመታት በርካታ ከሰራቸው የምርምር ስራዎችን አከናውኗል፤ብዙ መጽሐፍትንም ጽፏል፡፡ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የቋንቋዎች ተቋም የጥናት መጽሔት አሳታሚ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስፋፋት ሰፊ እገዛ አድርጓል።
Filed in: Amharic