>

እ ን ደ   ቼ ጉ ቬ ራ  -  “ ቼ!  ቼ!  ቼ!  ቼ!… ቼ! ” (አሰፋ ሀይሉ)

እ ን ደ   ቼ ጉ ቬ ራ  –  “ ቼ!  ቼ!  ቼ!  ቼ!… ቼ! ”

አሰፋ ሀይሉ
 
“ቼ!” ቼ ምንድነው? ቼ ፊደል ነው፡፡ የፊደል የልብ ወዳጅ፡፡ የኩባውያን የትግል አጋር፡፡ የብዙዎች የዓለማችን ነፃነት ፈላጊ ወጣቶች መፈክር፡፡ ራስን በግብታዊነት ለሌሎች አሳልፎ የመስጠት – የክብር መጠሪያ ቃል ነው ቼ!
*  ቼ “እንደ ሆቺ ሚንህ፣ እንደ ቼ ጉቬራ፣ ፋኖ ተሰማራ!” የተባለለት ቼ! ቼ አንድ ሰው ነው! ቼ አንድ መፈክር ያነገበ ደመ ሙቅ፣ ደመ ግቡ ወጣት ነው፡፡ ግን ደግሞ ብዙ ሰው ነው፡፡ ብዙ፡፡ ልክ እንደ ብዙ ሰው ዓለምን የወጣ የወረደ፣ ብዙ የምድሪቱን ጥጎች በሁለመናው ያዳረሰ – አንድ ሆኖ – ግን ብዙ – ብዙ ልባም ሰው ነው ቼ!!!
ስለ ቼ ለመናገር የሚነሳ ሰው ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ ስለ የትኛው ቼ ይናገር? ካስታኔዳ የቼን የሕይወት ታሪክ መርምሮ፣ አስሶ ጽፎት – ዓለም ቼን አወቅነው ብሎ ነበር፡፡ ግን የቼን ሁሉን ህይወት አልጨረሰውም፡፡ ታዪቦ ደግሞ ሌላ የቼን ታይተው ተሰምተው የማያውቁ ነገሮች የተካተቱበትን የቼን የሕይወት ታሪክ አሳተመ፡፡ ተጨበጨበለት፡፡ ዓለም ቼን ሙሉውን አገኘሁት አለ፡፡ ግን እርሱም አልጨረሰውም፡፡ ሩሲያኖች ደግሞ እኛጋር ማንም ያላያቸውን የቼን ምስሎች የያዘውን የቼን የሕይወት ታሪክ አሳተሙ፡፡ እነዚህ የቼ የሕይወት ታሪክ መድብሎች ሲገጣጠሙ የቼ የሕይወት ጉዞ አንድም ሳይቀር በመላው ዓለም ለሚገኙ አክባሪዎቹና አድናቂዎቹ ዘንድ የታወቀ አስመሰሉት፡፡
ነገር ግን ቼ ብዙ ሰው ነውና ብዙ ብዙ ድብቅ በጠላቶቹ ዘንድ የተያዙ ምስጢራዊ ሰነዶችና መረጃዎች፣ የኑዛዜ ቃል እማኝነቶች፣ ፈቃደኛ ሰዎች ሁሉ እየወጡ ስለ እርሱ ዓለም ያልሰማው የሚያውቁት ነገር እንዳላቸው ይገልጹ ጀመር፡፡ እና ለእነዚህ ጆን ሊ አንደርሰን መጣላቸው፡፡ ይሄን መጽሐፍ ይዞ፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት ገደማ፡፡ እና በዓለም እስካሁን የማይጠገብ የቼ የሕይወት ድርሳን ሆኖ ቀረ፡፡ ግን የቼ ታሪክ – የእልፍ የሰው ልጆች ታሪክ መሆኑን የተገነዘበው ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተመራማሪ – ጆን ሊ አንደርሰን – የዚህን መጽሐፉን ማጠንጠኛ የሪቮሉሽነሪውን – የአብዮተኛውን ቼ – አነሳስና ፍጻሜ ነው የምነግራችሁ – ብሎ እውነቱን ተናገረ፡፡
በዚህ መጽሐፍ – ከልጅነቱ እስከ ፍጻሜው ህልሙን ሊኖር የተጣጣረውን ቼ፣ ጀብደኛውን ቼ፣ ታታሪውን ቼ፣ የማይሆን ይሆናል ብሎ የሚያምነውን ህልመኛውን ቼ፣ መራሩንና ቁርጠኛውን ቼ፣ እና አሳዛኙን ሰማዕት ቼ – ደራሲ ጆን ሊ አንደርሰን – እንደማይረሳ ታላቅ የሰው ልጆች ሰማዕት – እንደ ሮቢንሁድ – ስጋን ለብሶ ሃቫና እያጨሰ ቢራውን ፉት እያለ በ20ኛዋ ክፍለዘመን ዓለማችን – በሰው ልጆች መካከል የሰው ልጆችን ከመከራ ቀንበራቸው ሊያድን እንደመጣ – እንደ ዳግማዊ ክርስቶስ አድርጎ ተረከው፡፡ እንዳይረሳ አድርጎ ብዙውን ቼ – በአንድ መጽሐፍ ገለጠው፡፡ ሲሉ ብዙዎች አሞካሹት፡፡
አንዳንዶች እንዲያውም – ቼጊዮሎጂ – ወይም የ20ኛው ክፍለ ዘመን የቼ ሳይንሳዊ ምርምር ኢንስቲትዩት ቢከፈትና የቼ ኮርሶች እንደ ዩኒቨርሲቲ በየደረጃው ለተማሪዎች የሚሰጡ ቢሆን – የዚህ መጽሐፍ የክስተቶች ሰንጠረዥ ብቻውን ራሱ – “ቼ-101” ለሚባል ኮርስ በቂ ማኑዋል ይወጣዋል! በማለት እስከማሞካሸት ደርሰዋል – ቼን እንደ ታላቅ ሰብዓዊ ፍጡር ከቤተሰቡ ጉያ እስከሞተላቸው ሕዝቦች ጉያ ድረስ ፈልፍሎ ላሳየን ለደራሲው ጆን ሊ አንደርሰን – አድናቆታቸውን ሲገልጹ፡፡
እና እኛስ – ስለ ቼ እናውራ ስንል – ስለ የትኛው ቼ እናውራ? ሙሉውን ቼ ይቅርና – ሙሉውን ወጣቱን ቼ መጻፍ ይከብዳልና፡፡ ቼ ብዙ ነውና፡፡ ስለ እርሱ ለማንሳት መምረጥ ግድ ይሆናል፡፡ ደፋሩ ቼ፡፡ ተጓዡ ቼ፡፡ ሃኪሙ ቼ፡፡ ዶክተሩ ቼ፡፡ ጉደኛው ቼ፡፡ አሸናፊው ቼ፡፡ የአርጀንቲናው ዕፀ-በለስ ቼ፡፡ የኒካራጓው ወዳጅ ቼ፡ የፓናማው ተቆርቋሪ ቼ፡፡ የፖርቶሪኮው ተገዳዳሪ ቼ፡፡ የጓቴማላው ተስፈኛ ቼ፡፡ የሜክሲኮው አሳቢ ቼ፡፡ የቬንዙዌላው መጻተኛ ቼ፡፡ የሆንዱራሱ አቡካቶ ቼ፡፡ የፔሩው ባለሟል ቼ፡፡ የቦሊቪያው ሰማዕት ቼ፡፡ የዶሚኒካን ሪፐብሊኩ እንባ ጠባቂ ቼ፡፡ የሄይቲው ተሟጋቹ ቼ፡፡ የላቲን አሜሪካው የትግል ወንጌል ሰባኪ ቼ፡፡ ቼ! ቼ አንዱ ሰው፡፡ እና ብዙው ሰው ቼ!
የኮንጎው አርበኛ ቼ፡፡ የአልጄሪያው አነጣጣሪ ቼ፡፡ የአፍሪካው ተወርዋሪ ኮከብ ቼ፡፡ ጀብደኛው ቼ፡፡ ምስኪኑ ቼ፡፡ ባለ ዳያሪው ቼ፡፡ ተጫዋቹ ታናሽ ወንድም ቼ፡፡ የእናቱ ስስት ቼ፡፡ የእህቶቹ የወንድሞቹ የሳቅ ምንጭ ቼ፡፡ የአባቱ የስለት ልጅ ቼ፡፡ የአንድ ፍሬ ለጋ ህጻናት አባቱ ቼ፡፡ አፍቃሪው ቼ፡፡ ቃል ጠባቂው ቼ፡፡ ቃል አባዩ ቼ፡፡ ገንዘብ ቀፋዩ ቼ፡፡ የጉልበት ሠራተኛቸው ቼ፡፡ የፈጠራ ፓተንት ባለቤቱ ቼ፡፡ የአለርጂ ተመራማሪው ቼ፡፡ የኬሚካል መሃንዲሱ ቼ፡፡ ህልመኛው ቼ፡፡ መከረኛው ቼ፡፡ የጓደኞቹ አዲስ ዓለም አሳሹ ቼ፡፡ ቼ፡፡ ቼ፡፡
ቼ ፊደል ነው፡፡ ቼ የአንድ እንደ አዳኝ መልዓክ ስሙ በዓለም የናኘ የአንድ ዓለማቀፍ በጎ አድራጊ መጠሪያ ቃል ነው፡፡ ቼ ለሰው ልጆች ነፃነት ሲል ነፍሱን ሳይሳሳ የሰጠ፣ በአንድ ዘመን በሆነች ሥፍራ ላይ የበቀለ፣ የአንድ ራሱን ለታላቅ መስዋዕትነት ያቀረበ አሳዛኝ ሰው ታሪክ ነው፡፡ ቼ፡፡ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ ዴላ ሳርና፡፡ ቼ፡፡ አንዱ ሰው ቼ፡፡ ብዙው ሰው ቼ፡፡
በበኩሌ ዓለም ሁሉ ከሚያውቀው የ“ፀረ-ኢምፔሪያሊስት” የነፃነት ትግል ታሪኩ ፈቀቅ ብዬ ቼን እስከ ሁሌውም አለፍ አለፍ እያልኩ ሰብዓዊውን ነገሩን – እንደኛው ተራው ሰውነቱን የሚያሳየውን የቼን ገጽታ ማነሳሳቱን መረጥኩ፡፡ እስቲ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስቱን ለአሁን ለቅምሻ እነሆኝ!
አንዴ ቼ በአርጀንቲና ቦኖስ አይረስ ከተማ በሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ቼ ሁሌ የማይችለውን ነገር እሠራለሁ ብሎ የሚነሳ መሆኑን ሁሉም የቤተሰቡ አባሎች ያውቃሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ቼ የሆነ ነገር ካሰበ ተባባሪ የሚሆነው ጓደኛ አያጣም፡፡ ምክንያቱም የቼ ሃሳቦች ምንጊዜም በእርሱ አንደበት ሲነገሩ የማይሳኩ መስለው ታይተው ስለማያውቁ ነው፡፡ እና ቼ የህክምና ፋከልቲ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለ አንዴ ምን ሆነ? ገንዘብ በምን ላግኝ እያለ አዲስ የፈጠራ ሃሳብ በጭንቅላቱ ማውጠንጠን ጀመረ፡፡ በሰው ዘንድ መፍትሄ ቢገኝላቸው የብዙ ሰውን ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ ያላቸውን የሰዎች ችግሮች እያሰሰ ብዙ ሪሰርቾችን አደረገ፡፡ እና በመጨረሻ የሆነ አይዲያ መጣለት፡፡
አይዲያው በረሮን ከሰው ቤት ውስጥ ጠራርጎ የሚያጠፋ ኃይለኛ ፀረ-ተኃዋስያን መድኃኒት ቢፈለስፍ – ብዙ ሰው እንደሚገዛውና ለመላው ላቲን አሜሪካ ራሱ እንደሚያሰራጨው ነበረ፡፡ ብዙ ጊዜ አሰበ ቼ፡፡ እና ሃሳቡን ሁሌ ለእርሱ ሃሳብ ተባባሪ ለነበረው አብሮአደግ ጓደኛው (እና በወቅቱ የኮሌጅ የሕግ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የነበረውን) ካርሊቶስ ፊጌራ ነገረው፡፡ ፊጌራ እንደወትሮው ሳያቅማማ ተቀበለው፡፡ የቼ ሃሳብ የነበረው ጋሜክሴን (GAMEXENE) የተሰኘውን የአንበጣ ማጥፊያ ፀረ-ነፍሳት መድኃኒት በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር በማደባለቅ – ፍቱን የበረሮ ማጥፊያ ለማድረግ ነበረ፡፡
ከዚያ ቼ እና ፊጌሮ ለፕሮጀክታቸው ገንዘብ ያልተበደሩት ዘመድ አዝማድ አልነበረም፡፡ እና ቼ የራሱን ክፍል ወደ ምርምር ላብራቶሪ ቀይሮ ብዙ ጊዜ በበረሮዎች ላይ ሙከራ ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ ተሳካለት፡፡ እና ወደ ማምረት ሥራ ገባ፡፡ የበረሮ ማጥፊያን በቤት ውስጥ፡፡ ደግሞ የሚገርመው ደንበኛም ያገኝ ጀመር፡፡ የቼ ከአንበጣ ማጥፊያ ጋሜክሴን ላይ የሆኑ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተፈበረከው የበረሮ ማጥፊያ መድኃኒት ‹‹ቬንዳቫል›› ይሰኛል፡፡ ይሄ የቼ የፀረ-በረሮ ግኝቱም እስከ ዛሬ ድረስ በቦኖስ አይረስ በስሙ በፓተንት መዝገብ ሰፍሮለት ይገኛል፡፡
ችግሩ ግን የእነ ቼ ቤተሰብ የበረሮውን ሽታ መቋቋም አለመቻሉ ነው! ከሶስት ወራት በኋላ አባቱ ጉቬራ ሊንች የምበላውን ነገር ሁሉ ይሄ ልጅ መርዝ መርዝ እንዲለኝ አደረገውኮ ብሎ ማማረር ጀመረ፡፡ እናቱ ሲሊያም ተከተለች፡፡ እህቱ አና ማሪያም ከአቅሟ በላይ መሆኑን ተናገረች፡፡ እና ቤተሰቡ ሁሉ ባንድ ላይ አመፀበት፡፡ ይሄንን ነገር ወደምትጥልበት አውጥተህ ካልጣልክ ሁላችንንም በመርዝ ልትጨርሰን ነው – የምንጎርሰው፣ የምንተነፍሰው፣ ሁሉ ጋማክሴንን ሆኗል ብለው ነገሩት፡፡ ብዙ ተሟግቶ – እንደማይሆንለት ሲያውቀው እንዳሉት ጋማክሴኑን እርግፍ አደረገው፡፡ ኋላ ግን ሲናገር ጋማክሴኑ ከሁሉም የቤተሰቡ አባላት መካከል እጅጉን የጎዳው እርሱኑ ነበረ – በመጨረሻ ቼ – “ችዬው ነው እንጂ .. ጋማክሴኑ ስንቴ አስም በሽታዬን እንደቀሰቀሰብኝ ማን በነገራችሁ?” ብሏቸው እርፍ!
(በነገራችን ላይ የአንበጣ መንጋ ሀገራችን ገባ፣ ሚሊዮኖች ለረሃብ ተጋለጡ፣ ነዋሪዎች አንበጣውን ለማባረር ጥይት እየተኮሱ ነው የሚል ዜና ከተደመጠ ወራት አይዘልም… እና ያኔ በ1950ዎቹ ቼጉቬራ ያገኘው ጋማክሴን – እኛ ጋር በ70 ዓመቱም አልደረሰም? ወይስ ሳይንቲስቱን ቼን ከሞት እንቀስቅሰው ይሆን? የሚል ሃዘን ያጠላበት ስላቅ ማጫሩ አይቀርም ዜናው)፡፡ የሆነ ሆኖ – ሳይንቲስቱ ቼ – እና ያልተሳካው ወደ ሃብት ጉዞ እንዲህ ባጭር ተቀጨ!
ሌላ ጊዜ ደግሞ ቼ አሁንም ከፈረደበት ጓደኛው ጋር ሆኖ አንድ የቢዝነስ አይዲያ ያገኛሉ፡፡ ይሄኛውን ደግሞ ያመነጨው “ኤልጎርዶ” ማለትም ፊጌራ ነበረ፡፡ ያም ምንድን ነበር? ጫማ በጣቃ (በቦንዳ) ከሚሸጥበት ቦታ ሄዶ መጫረትና – ከዚያ እነዚያን ጫማዎች በየሰዉ ቤት እያንኳኩ የመሸጥ አዲስ ሃሳብ! ምክንያቱም ሱቅ ሄደህ እንጂ ጫማህን ቤትህ አምጥቶልህ፣ በርካሽ የሚሸጥልህ ቸርቻሪ ያኔ በአርጀንቲና ዋና ከተማ እምብዛም አልተለመደም ነበረና ነው፡፡ እና ቼ እና ጓደኛው እንደለመዱት ወደ ብድር ተሰማሩ፡፡ አያቶቻቸውን፣ አክስቶቻቸውን ሁሉ ተበድረዋል፡፡ ለጫማው ጨረታ፡፡ የቼ ቤተሰብ ሲበዛ ፎታች ስለነበረ ቼ – በነገራችን ላይ የጨረታው ቦታ የት እንደሆነ እስከ መጨረሻው አልናገርም ብሎ ፀንቷል ቼ፡፡
ለማንኛውም ቼ እና ፊጌሮ ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ አሟጠው ጫማውን በቦንዳ ተጫርተው ገዙ፡፡ እና ወደ ፈረደበት ወደ ቼ ቤተሰቦች ቤት አመጡት፡፡ ወጤቱስ ምን ሆነ? የሚያሳዝነው ነገር – ከጫማዎቹ ገሚሶቹ አጣማሪ መንታ የሌላቸው ባለ አንድ እግር ጫማዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በዚህ መቅሰፍት እነ ቼ ክፉኛ ቢያዝኑም – ልክ እንዳሰቡት ግን – ጥንዶቹን ጫማዎች በየቤቱ እያንኳኩ ሸጡ፡፡ የቀሩትን የሚመሳሰሉትን እያጣመሩ ለብዙ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች በርካሽ ዋጋ ሸጡት! የቀሩትስ?
የቀሩትን ባለ አንድ እግር ጫማዎች እነ ቼ ምን እንደሚያደርጓቸው ግራ ገብቷቸው ለተወሰነ ጊዜ ቆዩና ድንገት አንድ ቀን ቼ የሆነ ሃሳብ መጣለት፡፡ ከሰፈራቸው ብዙም ሳይርቅ የሚኖር አንድ ደህና ገቢ የነበረው ባለ አንድ እግር ሰው ነበረ፡፡ እና ቼ ባለ አንድ እግር ጫማዎቹን በሻንጣ ሞልቶ ተሸክሞ ወደ ሰውየው ሄደ፡፡ በግማሽ ዋጋ ግዛኝ ብሎ፡፡ እና ሰውየው ደሞ ሁሌ ለአንድ እግር ጫማ ሙሉ ዋጋ መክፈሉ የመረረው ሰው ነበረና ከቼ ላይ ባለ ቀኝ እግር የነበራቸውን ብዙ አንድ አንድ እግር ጫማዎች ከቼ ላይ ገዛው፡፡ ጉዱ የወጣው አንድ ቀን የቼ አባት ጉቬራ ሊንች – ቤት ውስጥ ያየውን አንድ እግር ጫማ – በሰውየው እግር ላይ ካየው በኋላ ነበረ!
ያ ወሬ ቤተሰቦቹ ለራት በተሰበሰቡበት ጠረጴዛ ላይ ሲፈነዳ – ቤተሰቡ በነገሩ በሳቅ ፈነዳ፡፡ እነዚያ ባለ አንድ እግር ጫማዎች እስከ መጨረሻውም የእነ ቼጉቬራ ቤተሰብ ጆክ ሆነው ቀሩ፡፡ ድንገት አና ማሪያ ከኮንስትራክሽን አርኪቴክቸር ኮሌጇ ከሚያጅቧት ጓደኞቿ ጋር ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ስትመጣ ቼ ጉቬራን በመተላለፊያው ላይ ካገኘችው – ወደ ጆሮው ጠጋ ብላ “የተረፉ ጫማዎች አሉህ አይደል? አዲስ ባለ አንድ እግር ሰው አይቼልሃለሁ፣ አሳይሃለሁ የት እንደሚገኝ! ” (እና ረዥም ሳቅ!) ይሄ የጫማ ጆክ እኮ – ጆክነቱ ያልቀረው – ቼ የሜዲካል ስኩል እየተማረ ሳለ ራሱ – ልክ እንደ ፋሽን – ሁለት ዓይነት ቀለም ያላቸውን ጫማዎች እያጣመረ መጫማቱን ስለቀጠለ ጭምር እኮ ነው! (ጫማዎቹ ሳያልቁማ አይላቀቃቸውም ቼ! ሃሃሃሃ..!!)
ብዙ ነገሮችን ላነሳሳ ነበር አፒታይቴን ከፍቼ የጀመርኩት – ግን አሁን ራሱ 3ኛ ገጼን እያጋመስኩ ራሴን አገኘሁት፡፡ እና በቃ ሌላ ጊዜ፡፡ ቼ አፍሪካ ውስጥ መጥቶ – ኋላ የሀገሩን በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች አሽሽቶ በአምባገነንነት ለአሰርት ዓመታት የሰነበረውን  – የያኔውን የቤልጂያን ኮንጎ ነፃ አውጪ – ሎሬት ካቢላን አግኝቶታል፡፡ አግኝቶታል ብቻ ሳይሆን አንድ የኩባ የሻለቃ ጦር እየመራ ከኮንጎያውያኑ ጎን ተሰልፎ የአሜሪካኖች ኢምፔሪያሊዝም ያለውን ኃይል ተፋልሟል ቼ!
በዚያ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ አዝማችነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባንዲራ ሥር ወደ ኮንጎ የዘመቱበትን የሰላም ማስከበር ጦርነት ቼ ከደቡብ አሜሪካ ድረስ አህጉር አቆራርጦ መጥቶ ከእነ ሎሬት ካቢላ ጋር ረዥም ታሪክ ያለው የጀብዱ ጊዜ አሰልፏል፡፡ (ኋላ ቦብ ማርሌይ ሠላም በጉልበተኞች ጦርነት አይከበርም እያለ ያቀነቀነው ከዚህ ተነስቶ ሳይሆን ይቀራል? የሠላም ማስከበር ጦርነት ሲባል ይገርማል አይደል? ሠላም እንዴት በጦርነት ይከበራል? የሚል ጥያቄ ስለሚያጭር! እውነቱ ግን ይከበራል! ምኑ? ጦርነቱ ነዋ! አሳዛኝ አያዎ!)
በነገራችን ላይ ቼ በቦሊቪያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ – አሳዛኙ ርሸና ሲፈጸምበት – እና ህልፈቱን አስመልክቶ ፎቶዎቹና አገዳደሉ ለዓለም ይፋ ሲሆን – የቼ አስከሬን ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ ሰው እየመጣ እንዲያየው፣ ከፈለገም እንዲነካው ሲደረግ፣ ቼ በመላው ዓለም በአስከፊ የኑሮ ትግል ውስጥ በሚገኙ ሕዝቦች ዘንድ ሁሉ ስሙ ላይረሳ – እንደ ሰው ሳይሆን – መንፈስን በታላቅ የጽናትና የመስዋዕትነት መንፈስ እንደሚያቃና መንፈሳዊ ቃል ሆኖ – ስሙ እና ጀብዱው እና መስዋዕትነቱ እና ምግባሩ በዓለም ላይ ናኘ፡፡ ቼ በህይወቱ ሁሉ የእረፍት ቀኑን እሁድ ጠዋትን የበጎ አድራጎት ዕለት ብሎ በመሰየም ለሌሎች አርአያ ለመሆንም ጭምር ከጉልበት ሠራተኞች ጋር አብሮ ይሰራል፣ የአሮጊቶችን ቤት ጭቃ ይለስናል፣ ውሃ ከጉድጓድ ይቀዳል፣ የምስኪኖች እርሻ ገብቶ ላቡን በነፃ ያንጠፈጥፋል፡፡
እና የሚገርመን በአሰቃቂ ሁኔታ በኩባዊ አሜሪካዊውና በአሳዳጁ የሲአይኤ ሰው በፌሊክስ ሮድሪጌዝ እጅ ገብቶ የተረሸነባትን ያቺን ክፉ ዕለት ተከትሎ አስከሬኑ ለህዝብ ክፍት ሲደረግ – ብዙ የቦሊቪያ እናቶች ከየአቅጣጫው እየመጡ ከፀጉሩ አንድ ዘለላ እየመዘዙ ይወስዱ ነበረ፡፡ በእነርሱ እምነት በሞት የተለዩዋቸውን የውድ መዋቲዎች ቀን ሲያከብሩ – የቼን የፀጉር ዘለላ ከያዝን – አማልክትን ያማልደናል ብለው እስከማመን ደርሰው ማለት ነው፡፡ ኦሆሆ! ወደው ግን አይደለም! አሳዝኗቸው! ያደረገላቸው፣ የሰጣቸው፣ እና የመጨረሻ ሽንፈቱ ልባቸውን ነክቷቸው!
በኦክቶበር 9 ቀን 1967 ዓመተ ምህረት የቼ ሞት እንደተሰማ – ፎቶው በትልቁ በኩባ ሃቫና በረዥም ጊዜ የትግል አጋሩና – ከቼ ጋር ሶስቱ የኩባ ነፃነት አዕማዶች እየተባሉ በሚታወቁት – በፊደል ካስትሮ እና በወንድሙ ራውል ካስትሮ የእንባ ዘለላዎች ታጅቦ በአደባባይ ተሰቀለለት፡፡ የቼ የህይወት ህልፈት ዜና – ቼን ትቢያ አድርጎ እንደማንኛውም ሟች የሚረሳ ሰው አድርጎት ከማለፍ ይልቅ – በመላው ዓለም ዝናው የናኘ – ዘላለማዊ የነፃነት መንፈስ አድርጎ እንደማይረሳ የድል ዓላማ ሰንደቅ – በግብዓተ መሬቱ – በሰዎች ልብ ውስጥ – ሽቅብ ወደ ሠማይ ከፍ ብሎ ተሰቀለ!
ማነው እንደ ቼ ስልጣን ገደል ይግባ ብሎ በየሀገሩ እየሄደ ከጭቁኖች ጋር ተሰልፎ የተዋጋ? ማነው እንደ ቼ ሁሉ ነገሩን ሳይሳሳ እስከ ፍጻሜ ህይወቱ ከእርሱ ለማይዋለዱ ሰብዓውያን የሰው ልጆች እንዲሁ የሰጠ? ማነው? ቼ ልጆቹን በጣም ይወዳል፡፡ በእርሱ ዘመን የህክምና ትምህርት ብቻ ተምረህና ተፈትነህ የህክምና ዶክተር አትሆንም፡፡ የህክምና ዶክተር ሆነህ ራስህን ችለህ በሽተኞችን ለማከም የሚፈቀድልህ ከምርቃትህ በኋላ 30 የህክምና ኮርሶችን ተፈትነህ ስታልፍ ነው፡፡ ያኔ ነው ላይሰንስድ ህጋዊ ሃኪም መሆን የምትችለው፡፡
ቼ እኮ 14ቱን ተፈትኖ አልፎ፣ ቀሪዎቹን ሊፈተን ሲል – ራሱን አስቶ ከጣለው የወባ ህመሙ – ሃኪሙ፣ ነርሱ፣ ቤተሰቡ፣ ሰዉ ሁሉ ጉድ እያለው፣ ተው እያለው – እርሱ እንደ ቀውስ ሰው ከአልጋው በጠዋት ዘልሎ ልብሱን ለባብሶ ወጥቶ ተፈትኖ ያለፈ በታላቅ ፅናት የህክምና ዶክትሬት ዲግሪውን የተቀበለ – ግን ያን መስዋዕት የከፈለለትንና ሃብታም የሚያደርገውን፣ እርሱን ሙያውን ለሰው ልጆች ነፃነት ሲል እርግፍ አድርጎ በመተው ታላቁን የግል ዋጋ የከፈለ እውነተኛ የሰው ልጆች ሃኪም ነው – ዶክተር ቼ!
ቼ እኮ እንደ ብዙዎቻችን እንቅልፉን እየተኛ ሳይሆን እንቅልፉን አጥቶ ነው ያን ሁሉ ሩጫ በዓለሙ ሁሉ የሮጠው፡፡ ይገርመኛል በጣም፡፡ ምን ዓይነት የዓላማ ፅናትና ምኞት ወይም ህልም ቢያድርብህ ነው ግን… እንደ ሰው ሳይሆን እንደማይሰበር ብረት በቀን ውስጥ ከ16 እስከ 22 ሰዓታትን በትትርና እያሳለፍክ፣ እሁድህን ለሰዎች ግልጋሎት እየሰጠህ፣ እንዲያም ሆኖ ከሚስትህና ከልጆችህ ጋር በአካል ባትችል መንፈሳዊ ህብረት ፈጥረህ በሰላም፣ ሳቂታ፣ ደስተኛ፣ ተጫዋች፣ በኃይል የተሞላህ የጀብድ ሰው ሆነህ መቀጠል የምትችለው?
ቼ በሆነ ወቅት ላይ ከጓደኛው ጋር በሳህን አጣቢነት ራሱን ለመደገፍ እስከደረሰበት ጊዜ ባሳለፈበት በጓቴማላ እያለ ለአባቱ ደብዳቤና ፎቶውን ይልክለት ነበር፡፡ ነገር ግን አባቱ አንድም ቀን ቼ እንደ ዶክተርነቱ ሱፍ ልብስ ለብሶ በፎቶው አይቶት አያውቅም፡፡ እና አንዴ አዲስ የሃር ልብስ አሰፍቶ በአድራሻው ላከለት ለቼ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ቼ ለአባቱ የምስጋና ደብዳቤ ሲልክለት እንዲህ ይላል፡-
“አባቴ ስለ ሥጦታህ በጣም አመሰግናለሁ፣
የቦነስ አይረስ ሃር እንዲህ እንደረከሰ አላውቅም ነበር፣
ለመኖሪያችን ገንዘብ ስላልነበረን ልሸጠው ገበያ ስወጣ
100 ፔሴታ ሲሉኝ ጊዜ ነው ያወቅኩት፣ ይገርማል፣
ቢያንስ ለ15 ቀን እንደልብ አኑሮናል ስጦታህ፣
እና አመሰግናለሁ!››፡፡
የአባቱን ስጦታ በክብር ሸጦታል ማለት ነው፡፡ ከምስጋና ጋር፡፡ በነገራችን ላይ ቼ እንደ ዶክተር፣ እንደ ተከበረ ሙያና ሰብዕና ባለቤት እንኳ – እስቲ የክብር ሱፍ ልብስ ከነክራቫቴ ልልበስ ብሎ አያውቅም፡፡ ሁሌ ተጓዥ ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከአርጀንቲና ጠቅልሎ ሊጓዝ የተነሳው በሐምሌ ወር 1953 እ.ኤ.አ. ላይ ነበረ፡፡ እንደ ተመረቀ ከህክምና ፋከልቲ፡፡ ቀድሞ ካቋረጠ የልብ ጓደጃው ከካሊካ ጋር፡፡ ወጣቱ የ25 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ዶክተር ቼ ያለውን ሁሉ ገንዘብ (300 የአሜሪካን ዶላር! እና ጓደኛውም እንዲሁ 300 ዶላር የሚገመት ብር – የሁለቱም ብር የተቀከረው በጓደኛው ፓንት ውስጥ የጓደኛው እናት ለመቀከሪያ በሰፉላቸው የጨርቅ ቀበቶ ውስጥ ተከትቶ ነበረ!)፡፡ እና ያን በዓለም ላይ ያለውን ሃብቱን ሸክፎ ነበረ ጉዞ የጀመረው ካገሩ ቼ፡፡ ያልለመነው የለም፡፡ ያልተደገሰለት መልካም ህይወት አልነበረም፡ እርሱ ግን እምቢ አለ፡፡
እና ለማይቀረው ጉዞው ሊሰናበተው ባቡር ጣቢያ ድረስ ቤተሰቡ ሁሉ ተገኝቶ ሸኘው፡፡ የዚያን እለት እናቱ ሲሊያ የሆነ ነገር ታውቋት ነበር መሰለኝ፡፡ አጠገቧ እጇን ለያዘቻት የቼ ወንድም የሮቤርቶ እጮኛ ለማቲልዳ በተሰበረ ልብ እንዲህ ማለቷን ኋላ ከእናትየው ህልፈት በኋላ ማቲልዳ ለደራሲው ጆን ሊ አንደርሰን እንባዋን እያረገፈች ነግራዋለች፡-
‹‹ዛሬ ልጄን ከአጠገቤ አጣሁት፣
ከእንግዲህ ወዲያ ተመልሼ ለማየት
እንደማልታደል ዛሬ ቁርጤን ተረዳሁት!››
ነበረ ያለቻት – የቼ እናት ሲሊያ፡፡ እንደ መታደል ሆኖ ግን – ኩባ በእነ ቼ እና ፊደል ተጋድሎ ከባቲስታ መንግሥት ነጻ በወጣችበት ዓመት ማግስት ማለትም በ1960 ላይ – እና እነ ቼ የስኬታቸውን የመጀመሪያ በለስ በደስታ እያጣጣሙ ባሉባት ቅፅበት – እናቱ ሲሊያ – እህቱን አና ማሪያን እና አባቱን ጉቬራ ሊንችን አስከትላ ከቦኖስ አይረስ ወደ ሃቫና እንደ ወፍ እየበረረች የልጇን ዓይን ልታይ ደረሰች፡፡ እና በሃቫና አላየውም ያለችውን ልጇን አየች፡፡ ከዚያ በኋላም ለጥቂት ጊዜያት ልጇን ቼን በሕይወት ለማግኘት ታድላለች ሲሊያ፡፡
ለአባቱ ግን ያለመታደል ነገር ሆኖ ያ የሃቫና ግንኙነታቸው ዕለት የሚወደውን ልጁን ቼን ያገኘበት የመጨረሻው ዕለት ነበረ፡፡ ከሞቱ በኋላ የቼ አባት የቼን ለብዙ ዓመታት የተጠራቀመ የጉዞ ዳያሪ እና ሌሎችንም የቤተሰብ ታሪኩን አካትቶ አንድ መጽሐፍ አሳትሞለታል፡፡  ‹‹ሚ ሂጆ ኤል ቼ›› ይሰኛል መጽሐፉ፡፡ የእንግሊዝኛ አቻ ትርጉሙ፡- ‹‹ማይ ሰን ቼ››፡፡ በአማርኛ፡- ‹‹ቼ! የኔ ልጅ››፡፡ ፍቅር በአማርኛ፡፡ እንዲህ አንድ ሆኖ ብዙ በሆነው በቼ ውስጥ ሆነው ሕይወትን ሲተርኳት ብዙ አድቬንቸር ነች፡፡ እና አስከፊ ትራጀዲም ነች፡፡ ግን ግን ደግሞ የበዛ ፍቅር የሞላባት ትራጀዲ፡፡ ሴ ላ ቪ!  ሕይወት እንዲህ ነች…!
ፈጣሪን ለማታውቅ፣ ግን ፈጣሪ ለፈጠራት የሰው ልጆች መንፈስ መቃናት ሁለመናዋን ለሰጠችው የቼ ነፍስ – ፈጣሪ አምላክ የበዛ ምህረትን፣ ሠላምን፣ ፀጋውን ያውርድላት!
ፈጣሪ እናት ምድሬን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያን ያሉትን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ!
Filed in: Amharic