>

ፒኮክና አንበሳ (ሲናጋ አበበ)

ፒኮክና አንበሳ      

ሲናጋ አበበ

       ሁለቱ ግዙፎች የፒኮክ ቅርጾች በቤተመግሥት መግቢያ ላይ ዘብ እንዲቆሙ ከተደረገበት ወቅት ጀምሮ፤  የብልጽግና ፓርቲ ልበል የኢህዴግ የአመራር አባሎች የፒኮክን ማማር የላባዎቹ ደማቅ ቀለማት በኢትዮጵያ ያሉትን ከ80 ያላነሱ ብሄረሰቦች ሊወክል እንደሚችል ለማሳመን ሲሞክሩ፤

       በተቃራኒው በሺ ዘመናት እንደአርማ ስንጠቀምበት የነበረው የአንበሳ ሃውልት መተካቱ ታሪክን ከማውደም የማይተናነስ ሥራ ነው ሲሉ ሙግት ሲያቀርቡ እንሰማለን፡፡ ዝርዝሩ ውስጥ መግባት ሚዛን ስለማይደፋ አልፈዋለሁ፡፡

         ሁሉም ይቅርና እንዲያው ለነገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረውን እንዲያጣና በሌላ እንዲተካለት የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የግል ፍላጎታቸውን ሲጭኑበት ሕዝቡን ከምን ቆጥረውት ነው ? ኢሕአዴግ እንኩዋን በሰንደቅ ዓላማችን ላይ ኮከቡን ሲጭን በቀቀኑን ፓርላማ አስወስኖ ነበር፡፡

         ክቡር እምክቡራን ዶክተር አቢይ የኢትዮያን ሕዝብ ምን ያህል ቢንቁት ነው በግል አንበሳ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ቀደም ሲል በጻፉት መጽሀፋቸው የገለጡቱትን በተግበር ሊያውሉት የቻሉት፡፡

          ሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠ ሁሉ ሕዝብን እንደጌኛ መንዳት ለምን እንደማይቀፋቸው ይገርማል ፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመናት ባካበተው ልምድና በወረሰው ትወፊትና እውቀት የፈረንጅ ቁዋንቁዋ ባለማወቁ ብቻ እንደአላዋቂ ተቆጥሮ እንደ ግዑዝ እቃ የሚቆጠረው ማብቂያ መቼ ነው፡፡

          በዚህ ጉዳይ ሕዝብ ይምከርበት ተብሎ የሚጠየቀው መቼ ነው ? እንደ ክብር ነክ የሚታየው ማቆሚያው መቼ ነው ?

           የጠቅላይ ሚኒስትራችን ትልቁ ደካማ ጎናቸው ሁሉንም እኔ አውቃለሁ ማለታቸው ነው፡፡ ለነገሩ የእውቀት አድማሳቸው ሰፊ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ግን የሰው ልጅ የፈጣሪን እውቀትና ችሎታ ሊፈታተን ስለማይችል፤ አገራችን ደግሞ የጋራችን እንደመሆኑዋ መጠን ሁሉም ዜጋ ያገበዋልና የመሰማት ዕድል ሊነፈግ አይገባም፡፡

       ያገሬ ሰው አልሰማ  ለሚል ሰው “ምከረው ምከረው ካልሰማ መከራ ይምከረው” ይላል፡፡ ብዙ አዋቂዎች ምክራቸውን ከመሰንዘር አልቦዘኑም፡፡ ግን አልተሰሙም፡፡

       መከራውን እየጠበቁ ይሆን ?

       የቀድሞ መሪዎች ቅምአያቶቻችን “ሕዝብ ምን አለ?” “እረኛ ምን አለ? አዝማሪ ምን አለ?” ብለው ይጠይቁና ከዚያ ተነስተው እርምጃ ይወስዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡

        አገር በመምራት ላይ ያላችሁ ሁሉ፤  በሕዝብ ላይ አትቀልዱ፤  የአገርን ሀብት አትመዝብሩ፤   ቀለብ ለሚሰፍርላፍሁ ታማኝ ሁኑ፤  ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን ፍሩ፡፡

        ይህን በቅንነት ካልተገበራችሁ የመጨረሻው እጣ  ፈንታችሁ አያምርም፡፡ 

                                           

Filed in: Amharic