>
5:13 pm - Saturday April 19, 8380

ዘመን የገለጣቸው የነብይነት ጭንብሎች (ኢ.ፕ.ድ)

ዘመን የገለጣቸው የነብይነት ጭንብሎች

ኢ.ፕ.ድ
“Prophecy” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “Propheteia” ከሚል የግሪክ ሥርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ይህም “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ የመተርጎም ስጦታ” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑን የዊኪፒዲያ መረጃ ያመለክታል። የትንቢትን ምንነት አስመልክቶ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ማብራሪያም በቀጥታ ከግሪኩ ትርጉም ጋር የሚመሳሰል ነው። “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ይላል ሐዋርያው።
የ“ፍካሬ 666” መጽሃፍ ደራሲ መጋቢ ተኩ ከበደ በበኩላቸው በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 6ሺ 208 ትንቢቶች መኖራቸውን ጠቁመው ከእነዚህም ከ3ሺ300 በላይ የሚሆኑት የተፈጸሙ መሆናቸውንና ወደ 2ሺ908 የሚጠጉት ደግሞ ወደ ፊት የሚፈጸሙ መሆናቸውን አመላክተው “ከተፈጸሙት ውስጥም አንድም ቃል እንኳን አልተሳሳተም” ይላሉ። ይህም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣም የሚለውን የሐዋርያው ቃል ምንጭ በትንቢቱ የማይሳሳተው ሑሉን አዋቂ የሆነው ጌታ መሆኑን ያሳየናል” በማለት ትንቢት እውነት መሆኑን በማስረጃ ያረጋግጣሉ።
በእስልምናውም እንደዚሁ ትንቢት የሚለው ቃል “ኑቡዋ” የሚል አቻ የአረብኛ ቃል ያለው ሲሆን፤ የቃሉ መሰረት ተደርጎ የሚወሰደውም “ነቢ” የሚለው የአረብኛ ቃል ነው። “ነቢ” የሚለው ቃል በበኩሉ “ንበ” ከሚል የአረብኛ ቃል የመጣና ትርጉሙም “የምስራች፣ መልዕክት፣ ከፈጣሪ የተላኩ ህጎችን ተቀብለው በሚገባቸው ቋንቋ መልዕክቱን ለእያንዳንዱ ሙስሊም የሚያደርሱ “የአላህ መልዕክተኞች” የሚል ነው።
ትንቢት የሚለው ቃል በቅዱስ ቁርአን ውስጥ አምስት ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከመፈጸማቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ቀድመው የተነገሩ ሁነቶችን የሚያመላክቱ ትንቢቶችን የያዙ አንቀጾች ቁርአን በውስጡ አካቶ ይዟል። ይህም በአማኞች ዘንድ ቅዱስ ቁርኣን ራሱ ከአላህ ዘንድ የተገኘ ነው የሚለውን አባባል ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
እነዚህ ሁሉ ትርጓሜዎች ተደማምረው ትንቢት ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ በሆነ አምላካዊ ባህርይ ለሰዎች የሚገለጽ መለኮታዊ መልዕክት ነው ወደሚለው እውነታ ያደርሱናል።
ትንቢት ለምን ዓላማ ይነገራል?
በዚህ መንገድ በእግዚአብሔር መንፈስ ቀስቃሽነት በሰው አንደበት የሚነገረው ትንቢት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት። ከእነዚህም ጥቂቶቹ የተደበቁ ኃጢአቶችን ለመግለፅ፣ ለተግሳጽ እና ከቀደሙ ስህተቶች ለመመለስ፣ የሰው ልጅ በፈጣሪው ማዳን ተስፋ እንዲያደርግና በዚህም ምቾትና ደስታ እንዲሰማው ፀጋው በተሰጣቸው ሰዎች አማካኝነት ትንቢት ሊነገር እንደሚችል (Spritualgiftstest.com) ከተባለ ድረ ገጽ ላይ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በበኩሉ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ ላይ “ትንቢት የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር፣ ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል” በማለት ትንቢት ለምን ዓላማ እንደሚነገር ገልጿል። ከዚህ የምንረዳው በእርግጥ ትንቢት የሚነገረው የወደፊቱን ክስተት ቀድሞ ለመተንበይ ብቻ አለመሆኑን ነው። በመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥም መጭውን ጊዜ ከመተንበይ ባሻገር ህዝቡን ከጥፋቱ ለመመለስ ያለመና ለተግሳጽና ለምክር የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች መኖራቸውን እናስታውሳለን።

ነብይስ ማን ነው?

እንግዲህ የትንቢትን ምንነት ካየን የነብይን ማንነት  ማወቅ አያቅተንም። በአጭሩ ነብይ ማለት በትንቢት ትርጉም ላይ እንደተመለከት ነው “በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ትንቢት የሚናገር ቅዱስ ሰው”(2ኛጴጥ.1፡20) ማለት ይሆናል። አሁን በዚህ የትንቢትና የነብይ የትርጉም ሚዛን ላይ የዘመናችን ትንቢቶችና ነብዮች እናስቀምጣቸውና እንመዝናቸው።
በዚህም አብዛኞቹ የዘመናችን “ነብያት” አንዱንም የነብይነት መስፈርት አያሟሉም። በመጀመሪያ “ትንቢት” የሚሉትን ነገር የሚናገሩት በራሳቸው ፈቃድ ሲሆን፤ የነብይነትን ማዕረግ የሚሰጡትም ራሳቸው ናቸው። ሌላው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ የመሰላቸውን ይናገራሉ።
ለአብነት በድህረ ኮሮና ዘመን ያሉ ነብይ ነን ባዮች መካከል አንዳቸውም የኮሮና ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ትንቢት አልተናገሩም። ሲቀጥል ነብይ ሊሆን የሚችለው በግልጽ በመጽሃፍ እንደተነገረው ቅዱስ ሰው መሆን አለበት። እነዚህ ቅዱስ በሚለው በዙሪያው ራሱ አይደርሱም፤ ቅዱስነት ዕምነትን ከምግባር ጋር አስተባብሮ፣ ፈጣሪን መስሎ መገኘትን ይጠይቃልና። ሲሰልስ የሚናገሩት ነገር ህዝብን ከስህተቱ የሚመልስ፣ የሚያንጽና የሚመክር የሚያጽናናም አይደለም። ይባስ ብለው ቀድመው ትንቢት ያልተናገሩትን የኮሮና ወረርሽኝ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ የ“ትንቢት” መዓት እያዥጎደጎዱብን ይገኛሉ።
Filed in: Amharic