>

"የኢትዮጵያ መሬት... ህዝቡም... አይገዛላችህ ! ውጉዝ ከመ አርዮስ!!!' (አቡነ ጴጥሮስ)

“የኢትዮጵያ መሬት… ህዝቡም… አይገዛላችህ ! ውጉዝ ከመ አርዮስ!!!’ አቡነ ጴጥሮስ

በሳሚ ዮሴፍ
በ1885 ዓ.ም ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ስማቸው ኃይለማርያም ነበር። አቶ ኃይለማርያም በ1909 ዓ.ም መለኮሱ።በ1910 ዓ.ም በወላይታ የደብረ መንክራት ገዳም መምህር ተብለው ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም በዝዋይ ደሴት የገዳሙ መምህር ሆኑ። በ1921 ዓ.ም በእስክንድርያ ቅዱስ ማርቆስ ከአራት ጳጳሳት ጋር ጵጵስና ሲሾሙ ስማቸው ጴጥሮስ ተባለ።
    የኢጣልያ ፋሺስት  ጦር በኢትዮጵያ ላይ በተነሳ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘምተዋል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ሆኖ ከተመለሰ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ሚያዝያ 24 ቀን
ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ። ከዚያም ሆነው በስብከት የሰላሌን አርበኞች ያነቃቁ ጀመር። በዚህም ለኢጣልያ የገቡና በኢጣልያ አገዛዝ ያመኑ የኢትዮጵያ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣልያ እንዲገቡና በኢጣልያ ላይ የሚነዙትን አጉል ስብከት እንዲተዉ በደብዳቤም በቃልም ይመክሯቸው ጀመር። አቡነ ጴጥሮስ ግን ማንኛውንም ልመና አልተቀበሉም።
ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በኢጣልያ ወታደሮች ከተያዘች ጀምሮ ሰላም አልነበረችም። አርበኞቹ አንድ ቀን ከተማዋን ይይዟታል ተብሎም ይፈራ ነበር። በተለይ የመጀመሪያው ወራቶች ለኢጣልያን የጭንቅ ነበሩ።
ማሪያ ጃኮኒያ ላንድ በመጽሐፍዋ ውስጥ “…ሐምሌ 18 ቀን የያዝኩት ማስታወሻ ብላ ስትገልጽ በየቀኑ ከተማዋ እንደምትጠቃ ይነገራል። እንደሚወራው የክረምቱ ወራት እስከሚያልቅ ሰላም የለም ይላሉ። ሐበሾች ባልታሰበና ባልታወቀ ቀን ገበያውን ሁሉ እንደሚወሩት ይነገራል…” ብላለች። እንደ ተፈራውም አልቀረ ተወረረ።
ላ ኮንኮይታ ዴል ኢምፔሮ በሚል ርእስ ዞሊ ባሳተመው መጽሐፉ “…በሰሚናዊ ምዕራብ በኩልና ቡደቡባዊ ምስራቅ በኩል አዲስ አበባ ከተማ ሐምሌ 28 ቀን በሁለቱ አቅጣጫ በኢትዮጵያውያን ተወረረች ብሏል።
በእንግሊዝ ሌጋሲዮን የነበረው ፓትሪክ ሮበርትስ ሐምሌ 30 ቀን እ.ኤ.አ. ባስተላለፈው ሪፖርት “…የኢትዮጵያውያን ኃይል በምዕራብ በኩል አጠቃ። ኢትዮጵያውያኖቹ ከባድና የሚያስገርም ውጊያ አደረጉ። ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ያለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣልያ ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው። ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያውያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ። አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ ከአርበኞቹ ጋር የመጡ ናቸው። የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ነው…” ብሏል።
ፓጃሊ የተባለ በዚያ ዘመን የኮሪዬር ዴላ ሴራ ጋዜጠኛ የነበረው ድአሪዮ አ.ኦ.ኢ. በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ
“…ሐምሌ 30 ቀን እ.ኤ.አ. በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበት እንዲገደሉ ፈረደ። ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ፈጠረ። ጉዳዩም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሺስቶች ከባድ ቁጥጥር አደረጉ። ለእኛም ትእዛዝ ተሰጠን። ማንኛውም ጋዜጠኛ አቡኑ ተገደሉ ብሎ ወደ ኢጣልያ ቴሌግራም እንዳይደርግ ክልክል ነው። አቡኑ ታሰሩ ብላችሁ ግን ዜናውን ማስተላለፍ ትችላላችሁ አሉን”
ፓጃሊ በመቀጠል “… አቡኑ ሲገደሉ እዚያው ነበርኩ። ጴጥሮስ ረዥምና ብሩህ ገጽታ ያላቸው ናቸው። ጥቁር ካባ ለብሰዋል። በጉዞው ምክንያት ልብሳቸው ሁሉ በጭቃ ተበላሽቷል። የሆቴል ቤቱ ጌታ ግሪካዊው ማንድራኮስ የአቡኑን ንግግር ለጋዜጠኞች ያስተረጉም ነበር። አቡኑ የመከላካያ ሀሳባቸውን በሚገባ ሰጡ።
የሞት ፍርድ በተፈረደባቸው ጊዜ በፀጥታ አዳመጡ። በቀኝ እጃቸው በሰማያዊ ጨርቅ የተሸፈነ መስቀል ይዘዋል። የሞት ፍርዱ ከተፈረደ በኋላ ኢጣልያኖች የመግደያውን ቦታ ለማዘጋጀት ወደ ገበያ ሄዱ። የመግደያው ቦታ ተዘጋጅቶ ጴጥሮስ ተወሰዱ። ፊታቸውን ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ አድርገው ቆሙ። በጴጥሮስና በሕዝቡ መሀል የሀገር ተወላጅ ወታደሮች ቆመው ሕዝቡ እንዳይጠጋ ይከለክላሉ።
ጴጥሮስ ሰዓታቸውን አዩ ወዲያውም አጠገባቸው ያለውን ኢጣልያዊ ለመቀመጥ እንዲፈቅድላቸው ጠየቁት። ቀና ብለው ሰገነት ላይ ወደ ተቀመጥነው ጋዜጠኞችና መኳንንት አይተው የመቀመጥ ጥያቄያቸውን ትተው ቀጥ ብለው ቆሙ። ከፊታቸው ለቆሙት ገዳዮቻቸው ተመቻቹላቸው።
አቡኑ ረጋ ብለው ተራመዱ ካራሚኚዬሮቹም ከመግደያው ቦታ እስኪቆሙላቸው ጠበቁ። ከቦታው ሲደርሱ አንድ አስተርጓሚ ተጠግቶ ‘ዓይንዎ እንዲሸፈን ይፈልጋሉ?’ አላቸው። እሳቸውም ሲመልሱ ‘የእናንተ ጉዳይ ነው፤ እንደ ወደዳችሁና እንደፈለጋችሁ አድርጉ ለኔ ማንኛውም ስሜት አይሰጠኝም’ አሉ።
ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ፊታቸውን ወደ ግድግዳው እንዲያዞሩ ተደረገ። እሳቸውን ቀድሞ በመግደል ክብር የሚፈልጉት ስምንት ካራሚኚዬሮችም ከጴጥሮስ 20 እርምጃ ያህል ርቀው በርከክ አሉ። በአስተኳሹ ትእዛዝም ተኮሱ። ጴጥሮስ ጀርባቸው በጥይት ተበሳሳና ከመሬት ላይ ወደቁ። ወዲያው አንድ ኢጣልያዊ ካፒቴን ሐኪም ሬሳቸውን መረመረና ይሄ ቄስ አልሞተም ብሎ ተናገረ። የካራሚኚዬሮቹ መኮንን ተጠግቶ ሦስት ጥይት ተኩሶ ራሳቸውን ደበደበና ጨረሳቸው። አስገዳዩ ኮሎኔልም የጴጥሮስን ሬሣ ማየት ቀፎት እንደ እብድ ሆኖ ከመቀመጫው ተነሳና “የት ነው የሚቀበረው” ብሎ ጮኸ። ሬሣቸውም በሚስጥር ከከተማ ውጭ ተወስዶ ተቀበረ…” በማለት ጽፏል።
ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ እንደጻፈው “…ከሚገደሉበት ስፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ ” ፋሺስቶች አርበኞቹን ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ። ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰው ሀገርን የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመው አረመኔው የኢጣልያ ፋሺስት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእሱ እንዳይገዛ ውግዝ ነው። የኢትዮጵያም መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች  ትሁን” ብለው ተናገሩ።
አቡነ ጴጥሮስ ላይ የሞት ፍርድ ሲፈረድ ችሎቱን የመራው ኢጣልያዊው የመሀል ዳኛ ኮንቴ ዴ ላ ፖርቶ ሲሆን የቀኝ ዳኛ
ብላታ አየለ ገብሬ፣ የግራ ዳኛ ነጋድራስ ወዳጆ አሊ ነበሩ የተሰየሙት ዳኞች በአንድ ድምፅ ነው የፈረዱባቸው።
ምንጭ:- ጳውሎስ ኞኞ
የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ
ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ
Filed in: Amharic