>

ንዴትና ደስታ - ጃንሆይና አቢሲኒያ - ጎሣዊነትና አህጉራዊነት!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ንዴትና ደስታ – ጃንሆይና አቢሲኒያ – ጎሣዊነትና አህጉራዊነት!!!

አሰፋ ሀይሉ
  * የአፍታ ቆይታ ከማንዴላና ኦሊቨር ጋር በአዲስ አበባ
አሁን የምጠቅሰው ‹‹በ20ኛው ክፍለዘመን ከተኖሩ ህይወቶች ሁሉ ታላቅ ክስተት የተከናወነበት ሕይወት›› በሚል በዋሺንግተን ፖስት የተሞገሰውን የኔልሰን ማንዴላ ግለ ታሪክ የያዘ ‹‹LONG WALK TO FREEDOM›› (‹‹ለነጻነት የተደረገው ረጅም የእግርጉዞ›› እንበለው?) የተሰኘውን የማንዴላ የትግል ሕይወት ድርሳን ነው፡፡
መጽሐፉ ያላችሁ ገጽ 294 ላይ ግለፁልኝ፡፡ ማንዴላ በዚህች ገጽ ላይ በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር አፍሪካዊ የሚመራ የጥቁር አንበሶች ሠራዊት በኢትዮጵያ ምድር ማየታቸው ታላቅ ትንግርት እንደሆነባቸው ይገልጻሉ፡፡ እና በኢትዮጵያው (የአቢሲኒያው) ንጉሠ ነገሥት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የትንግርት ኒሻኖች የተደረደሩበት ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሰው ብቅ ያሉትንና የአፍሪካን ነፃነት ያዋለዱትን፣ ሕይወታቸው ራሱ አንድ ትልቅ ታሪክ የሆነውን ‹‹ግርማዊነታቸውን ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን›› ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያያቸው ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማው፣ ሰውነታቸው ከግምቱ በላይ ደቃቃ እንደሆነበት፣ ነገር ግን በራስ የመተማመን መንፈሳቸው፣ ሁሉም እንቅስቃሴያቸውና ንግግራቸው ክብራቸውን የጠበቀ በመሆኑ ያ የክብር መንፈሳቸው በትክክልም እንደሆኑት ታላቅ ግርማ ሞገሳቸውን አውጥቶ እንደሚያገዝፋቸው ይናገራል ማንዴላ፡፡
ማንዴላ አዲስ አበባ የመጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ተገኝቶ ንግግር ለማድረግ ነው፡፡ ማንዴላ አዲስ አበባ የመጣው ብቻውን አልነበረም፡፡ ከኦሊቨር ጋር ነው፡፡ ኦሊቨር ማን ነው? ኦሊቨር – ኦሊቨር ታምቦ ነው፡፡ በ1936 ዓመተ ምህረት ላይ (በ1943 እ.ኤ.አ.) የደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮችን ብሔራዊ ኮንግረስ የወጣት ሊግ (የኤ ኤን ሲን ዩዝ ሊግ) የመሠረቱ ሶስት የኤ ኤን ሲ መሥራቾች አሉ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ፣ ዋልተር ሲሱሉ እና ይሄ ኦሊቨር ታምቦ፡፡ እና አዲሳባ ከአፍሪካ አንድነቱ ጉባዔ ቀደም ብለው ማንዴላና ኦሊቨር ጃንሆይ ፊት ቀርበው ፍላጎታቸውንና የሚሹትን እገዛ በተመለከተ መከሩ፡፡ እና በቀኃሥ ጋባዥነት ከእርሳቸው ቀጥሎ ለጉባዔተኞቹ ማንዴላ ንግግር እንዲያደርግ ለበነጋው ቀጠሮ ተያዘለት፡፡
ከዚያ በፊት ግን በጉባዔው ተሳታፊ የሚሆኑ ድርጅቶች የመግቢያ ፈቃድ ወደሚያገኙበት የአአድ ቢሮ ሄዶ ለእርሱና ለኦሊቨር የተዘጋጀውን የመግቢያ ካርድ መቀበል ነበረበት፡፡ እና ማንዴላ ከቀኃሥ ቤተመንግሥት ከተሰናበተ በኋላ ካርዱን ሊያወጣ ወደ አፍሪካ አንድነት ተቋም አመራ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን ማንዴላ እጅግ በንዴት ያንጨረጨረውን – እና በዚህ የሕይወት ታሪኩ ድርሳን ገጽ 294 ላይ ያሰፈረውን – ያልጠበቀውን ምላሽ አገኘ፡፡ በጉባዔው ላይ መገኘትም፣ ንግግር ማቅረብም አትችሉም የሚል እገዳ ተጥሎባችኋል የሚል፡፡
እነ ማንዴላና ኦሊቨር ደቡብ አፍሪካን ያናወጠውን ኡምኮንቶ ዊ ሲዝዌ የተባለን የነፃነት ትግል የነውጥ ቡድን መሥርተው በሀገራቸው በጥብቅ የሚፈለጉና በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ወንጀለኞች ሆነዋል፡፡ የሀገራቸውን ድንበር አቋርጠው አዲስ አበባ ለመድረስ ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ እና ባለቀ ሰዓት ላይ – ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባዔ አትገቡም የሚል መርዶ ጠበቃቸው! ምክንያቱስ?
ምክንያቱ ደግሞ በኡጋንዳ ሚኒስትር አማካይነት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቀረበባቸው ተቃውሞ ነበር፡፡ ተቃውሞው፡- እነ ማንዴላም ሆነ ድርጅታቸው ኤ ኤን ሲ (አሊያም የሚሊቴሪ ክንፉ ኡምክዌንቶ) የአንድ ጎሣ – ማለትም የማንዴላ ነገድ የዞሳ ጎሣ – ስብስብ ናቸው፣ ስለሆነም እነዚህ የአንድ ጎሣ ወይም የአንድ ነገድ ተወካዮች በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሀገርን ሕዝብ ወክለው በተቀመጡ የሀገራት መሪዎች ጉባዔ ላይ መገኘትም፣ ተገኝተው ንግግር ማቅረብም አይችሉም – በሚል ምክንያት ነበረ፡፡ እና ለተቃውሞው ምላሻችሁን አቅርባችሁ እንዲታይላችሁ ካላደረጋችሁ – ወደ ተከበረው የመሪዎች ጉባዔ መግባት አትችሉም!
ማንዴላ ክልከላውን ስሰማ በዚያው ቅፅበት የመጣብኝ ሃሳብ ታላቅ የቁጣና የስድብ ናዳ ማውረድ ነበረ – በማለት ሳይደብቅ የተሰማውን ስሜት – በዚህ የህይወት ታሪክ መጽፉ ገጽ 294 ላይ ይናገራል፡፡ ነገር ግና ኦሊቨር አረጋጋኝና መልሳችንን በትህትና አብራርተን ማስገባት እንዳለብን አሳመነኝ፡፡ እና ለቀረበብን መሠረተ ቢስ ውንጀላ መልሳችንን አቀረብን፡፡ እንዲህ በማለት፡-
‹እኛ የአንድ ነገድ ወኪሎች አይደለንም፡፡ ድርጅታችንም የዞሳ ነገድ ወኪል አይደለም፡፡ የድጅርታችን አባላትም  ከአንድ ጎሣ የተውጣጡ ሰዎች አይደሉም፡፡ እንዲያውም  የድጅርታችን ፕሬዚደንት ቺፍ ሊቱሊ ከዞሳ ጎሣ የበቀለ ሰው አይደለም፡፡ ዙሉ ነው፡፡ ድርጅታችን በአባልነት ከማናቸውም የሕብረተሰብ ክፍል ወይም ከማናቸውም ጎሣ ለመጡ ሰዎች ክፍት የሆነ፣ እና ከዚያም አልፎ የመላ  አፍሪካውያንን አንድነት ለመፍጠር ታልሞ የተቋቋመ ባለታላቅ ራዕይ ዘር-አልባ ድርጅት ነው!›
ይህን የእነ ማንዴላን የይግባኝ አቤቱታ የሰማው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት – ማዕቀቡን አንስቶ – ኔልሰን ማንዴላ – በሚኒስትሮቹ ጉባዔ ተገኝቶ ንግግሩንና ተማፅኖውን እንዲያቀርብ ፈቀደለት! እና በማግሥቱ ከመጀመሪያው ተናጋሪ ከጃንሆይ ቀጥሎ – በእርሳቸው ግብዣ – ማንዴላ የአፍሪካውያን መሪዎችን ያስጨበጨበ – እና ለኤ ኤን ሲ እና ለኡምኮንቶ ዊ ሲዝዌ ከፍ ያለ የአፍሪካውያንን ድጋፍ ያስገኘለትን ንግግር ተናገረ፡፡
ማንዴላ በዚያው ገጽ ላይ ያስገረመውን ነገር ሲናገር – በጉባዔው ላይ ቀርቤ በአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ ሁሉም ሠላማዊ የፖለቲካ በሮች ስለተዘጉብን በማንኛውም መንገድ – የኃይልን አማራጭ ጨምሮ – መብታችንን ለማስከበር ቆርጠናል፣ በቅርቡም ደቡብ አፍሪካን ያናወጠው ኡምኮንቶ ዊ ሲዝዌ የእኛ ቁርጠኛ የነፃነት ድርጅት ነው – ብዬ ስናገር – ይላል ማንዴላ – ከፊት ለፊት ተቀምጦ የነበረው የዩጋንዳ ሚኒስትር – ንግግሬን አቋርጦ – እንዲህ ነው እንጂ! ጎሽ! በሏቸው በደንብ አድርጋችሁ! – እያለ በደስታና በአድናቆት ድጋፍ ጮኸ – በማለት ይናገራል ማንዴላ፡፡ ቀድሞ በንዴት ያንጨረጨረችው የክልከላው ምንጭ ዩጋንዳ – ኋላ ደግሞ ዋነኛ አድናቂው ስትሆን  ሲያይ – ከባድ የደስታ ሙቀት ሳይሰማው አይቀርም ማንዴላን! ደስ የሚልህ – ማንዴላ – ንዴቱንም ደስታውንም በሕይወት ታሪኩ ድርሳን ላይ አልሸሸጋቸውም!
ማንዴላ የኖቤል የሠላም ሽልማትን ከአፓርታይዱ ሥርዓት መሪና አፓርታይድ እንዲያበቃ ከፍተኛ ሚና ከተጫወተው፣ ማንዴላንም ከእስር ከፈታው ከፕሬዚደንት ዴክለርክ ጋር በጋራ የተሸለመ ሰው ነው፡፡ ዓለም የደቡብ አፍሪካውያኑን ነጭና ጥቁር ሳይበላላ በመካከለኛ መንገድ ላይ በሠላም አብሮ ለመኖር የእርቅን መፍትሄ ያመጣበትን የደቡብ አፍሪካን የሠላም መንገድ እጅግ ወድዶለታል፡፡ እና ማንዴላ በተቻለው መጠን – በሕይወት ታሪኩ ያንን የተወደደለትን እና ሽልማት የበላበትን ነገር አጉልቶ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ እግረ መንገዱንም የጥቁሮች ደቡብ አፍሪካ ምን እንደምትመስል በዓለም ያገኘውን ታዋቂነት ተጠቅሞ ሀገሩንና ሕዝቦቹን ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥሯል፡፡ ከምንም በላይ የአንድ ጎሣ ጠባብ ወኪል ነበረ የሚለውን የብዙዎች ትችት አስተባብሎበታል ማንዴላ – በሕይወት ታሪክ ድርሳኑ፡፡
ከሠላም የጋራ ኖቤል ተሸላሚው ከማንዴላ እና ከማንዴላዋ ደቡብ አፍሪካ መለስ ብለን – ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ – በቅርቡ – ከኤርትራው ኢሣያስ አፈወርቂ ጋር ሠላምና እርቅ የማምጣት ተስፋ ሰጪ ጅምር አሳይተዋል በሚል ምክንያት – ከአንዲት ግሬታ ተንበርግ ከተባለች የአካባቢ ጥበቃ ሰባኪ የ16 ዓመት ሕፃን ልጅ ጋር ተወዳድረው – የዓለማቀፉን የሠላም ኖቤል ለብቻቸው የተሸለሙት የእኛው የኢህአዴጉ ቀዳማይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትዝ አሉኝ፡፡
አብይ አህመድ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በሚሰጠው የኖቤል የሰላም ሽልማት ንግግራቸው – መብራትና ውሃ የሌለባት ያሏትን ትንሿን የትውልድ መንደራቸውን በሻሻን ደጋግመው በመጥራት መንደራቸውን በዓለም ታዋቂ ለማድረግ የተጉት ትጋት በጣም ያስቀና ነበር በእውነቱ! ያኔ ማንዴላንና ኦሊቨርን የአንድ ጎሣ የዞሣ ተወካይ ናችሁ ብሎ የከለከለ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት – ዛሬ የአፍሪካ ኅብረት ሆኖ – በፕሬዚደንቱ በሙሳ ፋቂ አማካይነት – የአንድ ጠባብ የኦሮሞ ጎሣ/ነገድ ድርጅት ሊቀመንበርና ወኪል የሆኑትን አብይ አህመድ አሊን – ከኖቤል ሽልማታቸው በኋላ ያለምንም ሃተታ – ‹‹ታላቅ የዘመኑ የአፍሪካ የሠላም አምባሳደርና ኩራት›› ሲል ሲገልጸቸው ለተመለከተ – የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት – እና የያኔው የጃንሆይ ዘመኑ የአፍሪካ አንድነት ድጅርት – የቆሙበት ምሰሶ ምን ያህል የተለያየ እንደሆነ የዛሬውን አይቶ መናገር አይከብድም፡፡
ማን ያውቃል? ነገ ደግሞ የኖቤል ተሸላሚው የሕይወት ታሪክ ተብሎ የአንድ ጎሣ ወይም የአንድ ነገድ መሪ አይደለሁም – አፍሪካን በመደመር እሳቤዬ አንድ ላደርግ የተነሳሁ የአፍሪካ የሠላም ጀግና ነኝ ብለው – እንደ ጃንሆይ የኢንሳ የኮሎኔልነት ማዕረጋቸውን ደርድረው – ከፊት ገጽ ላይ በፈገግታ የታጀበ ሩቅ የሚያይ ፎቷቸውን ለጥፈው – ከነወፍራም የግል ሕይወት ታሪክ ድርሳናቸው ብቅ ይሉልንና ጉድ ብለን የምንደመምበትን የነፃነትና የሠላም ተጋድሎ ታሪክ ያስነብቡን ይሆናል! ማን ያውቃል?
‹‹እኩል ይሆናል›› (ከሙሉቀን ሰ.)
 
‹‹አስከበረን ስንል
 ሀገሬ ተዋርዶ ፣
በየቀኑ ሀዘን 
 እለት እለት መርዶ ፡፡
በሜንጫ እና ጥይት
 ሠርክ እየቀነሰው ፣
ስንት ቀርቶ ይሆን
 ከተደመረው ሰው ፡፡››
በማንዴላ ‹‹ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም›› – ገጽ 294 መነሻነት ያጫረብኝን አምሰልስሎት አበቃሁ፡፡ ሠላም!
ፎቶው የማንዴላና የፊደል፡፡ ማንዴላ ከ27 ዓመታት የአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ እስር ተለቅቀው፣ የሁሉም ደቡብ አፍሪካ መሪ ሊሆኑ ገና ሶስት ዓመት ይቀራቸዋል፡፡ ማንዴላ የማንንም የፊደል ባላንጣ የሆኑ የዓለማችንን ጉልበተኛ ኃያላን ቁጣና ተግሳፅ ሳይፈሩ – ‹‹በችግራችን ጊዜ ከጎናችን ሆነው የረዱን የቁርጥ ቀን ደራሽ ወዳጃችን ናቸው›› በማለት ፊደልን ወደ ደቡብ አፍሪካ ጋበዙ፡፡ እና የችግር ቀን ጓዶች ቀን ሲወጣ እንዲህ ተቃቅፈው ፎቶ ተነሱ፡፡ ማንዴላና ፊደል፡፡ ዛሬ ሁለቱም በሕይወት የሉም፡፡ ታሪካቸው ግን ሲወሳ ይኖራል፡፡
Filed in: Amharic