>
5:31 pm - Tuesday November 13, 3455

አይደፈሬው ህገ መንግስት ለሶስተኛ ጊዜ ይደፈር ይሆን??? (በፈቃዱ ኃይሉ ነጋሽ መሐመድ)

አይደፈሬው ህገ መንግስት ለሶስተኛ ጊዜ ይደፈር ይሆን???

በፈቃዱ ኃይሉ ነጋሽ መሐመድ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተከልሷል።( ‘ተሻሽሏል’ የሚል ቃል ያልተጠቀምኩት፣ ሒደቱ ‘መሻሻል’ የሚለውን መሥፈርት ስለማያሟላ ነው።) ክለሳዎቹ በ1990 የተደረገው የአንቀጽ 98 ሦስት ንዑስ አንቀጾች እና በ1997 የተደረገው የአንቀጽ 103/5 ክለሳዎች ናቸው።

አስተያየት

የኢትዮጵያ መሪዎች የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት የማይደፈር ቅዱስ ሰነድ ያስመስሉታል። ነገር ግን እነርሱ በአተገባበር ደጋግመው ይጥሱታል። ከዚህ በፊት ሕገ መንግሥቱ ካንዴም፣ ሁለቴ ብዙኀን ሊመክሩበት ቀርቶ በቅጡ መረጃው እንኳን ሳይደርሳቸው ተከልሷል። አሁን ደግሞ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት «መሥራት ስላልቻልኩ፣ ከዚህ ቀደም ባወጣሁት መርሐ ግብር መሠረት ምርጫውን ማካሔድ አልችልም» ብሎ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ከሰረዘው በኋላ፥ ባለሙያዎቹ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ (constitutional crises) የሚሉት ጉዳይ ተከስቷል። የትኛውም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ለክስተቱ አጥጋቢ መልስ አይሰጥም። ስለሆነም፣ የሕገ መንግሥት ክለሳ ጉዳይ ከአማራጭ መፍትሔዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ተደርጎ በመጠቆሙ አዲስ አጀንዳ ሆኗል። የሕገ መንግሥት ክለሳ ዋነኛው አማራጭ የሆነበት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ይሁን የምክር ቤቱ መበተን በምክር ቤቱ ዘመን የሚፈፀሙ እንጂ ዘመኑን ካጠናቀቀ በኋላ የማይሠሩ አማራጮች በመሆናቸው ነው።

ቀድሞም ቢሆን ገና ሲረቀቅ በብዙኀን ዘንድ በበቂ ሁኔታ አልተመከረበትም በሚል ብዙ ትችት የሚሰነዘርበት ሕገ መንግሥት፣ ለወቅታዊው ሁኔታ ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎ ይከለስ ይሆን? ክለሳውስ ብዙኀኑን ያስማማ ይሆን?

ከቀደምት ክለሳዎች ምን እንማራለን?

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተከልሷል።( ‘ተሻሽሏል’ የሚል ቃል ያልተጠቀምኩት፣ ሒደቱ ‘መሻሻል’ የሚለውን መሥፈርት ስለማያሟላ ነው።) እነሱም በ1990 የተደረገው የአንቀጽ 98 ሦስት ንዑስ አንቀጾች እና በ1997 የተደረገው የአንቀጽ 103/5 ክለሳዎች ናቸው። የመጀመሪያው በክልሎች መካከል የነበረውን ታክስ በወል የመሰብሰብ ድንጋጌ በከፊል ወደ ፌዴራሉ በማዞር፣ የፌደራሉ መንግሥት ግን በውክልና ሥልጣኑን ለክልሎች የሚያስተላልፍበት ድንጋጌ ተደርጎ የተከለሰበት ነው። ክለሳው የፌዴራሉን መንግሥት ሥልጣን በክልሎች ላይ ለማጠናከር ተደርጎ የወጣ ክለሳ ነው። ሁለተኛው ክለሳ ደግሞ የ1997ቱ ምርጫ እና የ1997ቱ ሕዝብ ቆጠራ ሲገጣጠሙ መንግሥት ሁለቱንም ባንዴ የማስፈፀም አቅሙ “ስላልነበረው”፣ እንዳስፈላጊነቱ መንግሥት የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚደረግበትን ጊዜ ገደብ ከ10 ዓመት በላይም ቢሆን ለማስረዘም መብት እንዲያገኝ የተደረገ ክለሳ ነው።

ስለነዚህ ክለሳዎች ያነጋገርኳቸው የሕግ ባለሙያዎች በሙሉ እነዚህን ሁለት የሕገ መንግሥት ክለሳዎች በሙሉ ልባቸው ለመቀበል ይቸገራሉ። አንደኛ በምሥጢር መደረጋቸው ከሕገ መንግሥታዊ ክለሳዎች ፅንሰ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ይገልጻሉ። ዜጎች የመምከር፣ የመማከር እና ስለለውጦቹ በቅጡ የማወቅ መብት አላቸው፤ ነገር ግን ሁለቱም ሒደቶች ገዢው ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የበላይነቱን ብቻ ተጠቅሞ የራሱን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የቀረፃቸው ክለሳዎች ናቸው። ሁለተኛው ምክንያት የተከለሱት አንቀፆች እስካሁን ድረስ በሕገ መንግሥቱ ቅጥያነት፣ ወይም በነባሮቹ አንቀጾች ምትክ ታትመው ለሕዝብ ይፋ አለመደረጋቸውን ነው። የሆነው ሆኖ ክለሳዎቹ በተግባር ላይ ውለዋል። ባለፉት ዓመታት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየጊዜው ሲተላለፍ የቆየው ይህንን የሕግ አግባብ ይዞ ነው። ይህ ክለሳ ሕጋዊ ተቀባይነት ባይኖረው ኖሮ፣ መራዘሙ አሁን በምርጫ ላይ እየተነሳ ያለውን ዓይነት ጥያቄ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ላይ መነሳቱ አይቀርም ነበር።

በጥቅሉ፣ ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት የሕገ መንግሥት ክለሳዎች የተደረጉት ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት እና በበቂ ሁኔታ ንግግር ሳይደረግባቸው ነው። ከዚያም በላይ አሳሰቢው ጉዳይ ግን ገዢው ቡድን ሕገ መንግሥቱን እንደፈለገው እየቀያየረ የሚጠቀምበት ሰነድ አድርጎ ማቆየቱ ነው።

አልቦ-ሕዝብ ዴሞክራሲ

የዴሞክራሲ ቀላሉ ብያኔ ‘ሕዝብ አሳታፊ ስርዓት’ የሚለው ትርጉም ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ወሳኞቹ ቁም ነገሮች ሕዝብ በየጊዜው የሚመርጠው መንግሥት መኖር እና በሁለት ምርጫዎች መካከል ዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎዎችን በነጻነት ማድረጋቸው ነው። አሁን በኢትዮጵያ ያለው አጣብቂኝ የዴሞክራሲ መሠረታውያንን ሁሉ የሚጠይቅ ነው። በወቅቱ መካሔድ የነበረበት ምርጫ ባልተጠበቀ ምክንያት ሊካሔድ አልቻለም። ነገር ግን ለማራዘምም ሕዝባዊ ተሳትፎን የሚጠይቅ ሕገ መንግሥታዊ ክለሳ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

መንግሥት ባለፉት 30 ዓመታት፣ ሕገ መንግሥት «የማደይፈር» ሰነድ አድርጎ የሚስል ፕሮፓጋንዳ ነበረው። ነገር ግን ቀላል  አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ሲያሻው ብቻ ከልሶታል። ይህንን ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የበላይነቱን ተጠቅሞ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በፓርቲው ውስጥ የሚያራምደውን ‘ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት’ ተጠቅሞ ነው። የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ በድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ የወሰነውን በሙሉ፣ ቀሪው አባላት ያለምንም ቅሬታ እንዲያስፈፅሙ ያስገድድ ነበር። ይህ አሠራር አንድ ችግር ሲቀርፉ፣ ሌሎች ችግሮች እና ሕዝባዊ ጥያቄዎችን እየፈጠሩ ነበር።

አሁን ኢሕአዴግ ፈርሶ በምትኩ የበቀለው ብልፅግና ፓርቲ የኢሕአዴግን ያህል ውስጣዊ አንድነት የለውም። ቢኖረውም፣ ተቃዋሚዎች ገዢው ፓርቲ ብቻውን የሚያደርገውን ሕገ መንግሥታዊ ክለሳ ፀጥ ለጥ ብለው አይቀበሉትም። የሕገ መንግሥታዊ ክለሳ ጉዳይ ከተነሳም ብዙ ጥያቄዎች ተከታትለው መምጣታቸው አይቀርም። በዚህ ጊዜ ትክክለኛው እርምጃ ዴሞክራሲያዊነትን የሙጥኝ ማለት ነው። ዴሞክራሲ ያለ ሕዝባዊ ተሳትፎ ባዶ ቀፎ ነው። ስለሆነም፣ ውሳኔው ምንም ይሁን ምን የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ውሳኔ መሆን አለበት። የሕዝብ ይሁንታ ሊገኝ የሚችለው ትርጉም ያለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ሲኖር ነው።

Filed in: Amharic