>

ያልተዘመራላቸው ንግሥተ ነገሥታት - ማሚቴ ምኒልክ ርኅሩኋ ንግሥት!!! (ሳሚ ዘ ብሔረ ኢትዮጵያ)

ያልተዘመራላቸው ንግሥተ ነገሥታት – ማሚቴ ምኒልክ ርኅሩኋ ንግሥት!!!

 

 

ሳሚ ዘ ብሔረ ኢትዮጵያ
መሠረታዊ ታሪካቸው እንደሚያሳየው ወ/ሮ ማሚቴ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንግሥት እሆናለሁ የሚል ፍላጎት ወይም ምኞት ኖሮዋቸው አያውቁም፤ አባታቸው አባ-ዳኘው ምኒልክም ልጃቸው ማሚቴ አልጋ ወራሽ ልትሆን ትችላለች ብለው አላሰቧቸውም፤ ማሚቴ እናትና አባታቸው አብረው የኖሩ ባለመሆናቸው የወላጆቻቸውን ወግና ፍቅር እያገኙ የማደግ ዕድል አልገጠማቸውም፤ የማሚቴ እናት ወ/ሮ አብቺው የምኒልክ ወዳጅ እንጂ ሚስት አልነበሩም፤ ስለዚህ ማሚቴ ምኒልክ የልጅነት ሕይወታቸውንና አስተዳደጋቸውን የሚያስታውሱት ከሞግዚቶቻቸው ጋር በመኖር ያሳለፉት ዘመን ነው።
ማሚቴ ዕድሜያቸው ወደ ሰባት ዓመት ከተቀራረበበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ዘመን ከተለያዩ ሦስት ሰዎች ጋር ጋብቻዎች ሲፈጽሙ የታጨላቸውን ሁሉ እሺ ብለው ከመቀበል በስተቀር ስለ ሕይወት ጓደኞቻቸው የሚያውቁት ወይም የሚያስቡት ነገር አልነበረም፤ ታሪኩ እንደሚነግረን ዘውዲቱ ምኒልክ በመጀመሪያ ለንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሃንስ ልጅ ለራስ አርአያ ሥላሴ የተዳሩት ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ ነው፤ ቀጥሎም ከሸዋ መኳንንት ውስጥ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድ የሕይወት ጓደኛ እንዲሆኑ ጋብቻ የፈጸሙት በአባታቸው ትእዛዝ ነው፤ ከዚያ ደግሞ ደጃች ውቤን ፈትተው የብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ የወንድም ልጅ ደጃዝማች ጉግሣ ወሌን(በኋላ ራስ) እንዲያገቡ የተደረገው በጣይቱ ብጡል የጋብቻ ፖሊሲ መሠረት ነው።
በመጨረሻም በ1909 ዓ.ም. ዘውዲቱ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንግሥት እንዲሆኑ ሲወሰን ለአስራ ስድስት ዓመታት አብረዋቸው የኖሩትን ባለቤታቸውን ራስ ጉግሣ ወሌን እንዲፈቱ የተደረገው የሸዋ መኳንንትና የኃይማኖት አባቶች በጠነሰሱት ፖለቲካ ነው።
ማሚቴ ምኒልክ በተፈጥሮ ካላቸው ደግነትና ቅንነት በላይ የንጉሥ ልጅ መሆናቸው የማይሰማቸው ሰውን ሁሉ ትልቅ ትንሽ ሳይሉ በእኩልነት የሚመለከቱና የሚያከብሩ ስለሆነ የምድረ ግቢው ኅዝብ እጅግ አድርጎ የሚወዳቸው ነበሩ፥ እቴጌ ጣይቱ ዘወትር የሚቆጧቸውና የሚጨቀጭቋቸው “የምኒልክ ማሚቴ” ከቤት አገልጋዮች ጋር የምታደርገውን መቀራረብና የምታሳየውን ወዳጅነት ለማስጣል ነበር፤ “ዛሬም ቢነገራት ነገም ቢደገምላት ማሚቴን ከገረዶቿ መለየት አቃተኝ….” ብለው ይበሳጩ እንደነበር ይነገራል።
ዘውዲቱ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንግሥት እንዲሆኑ መወሰኑን በግዞት በሚኖሩበት ቦታ በተነገራቸው ጊዜ ከደግነታቸውና ከየዋህነታቸው የተነሳ እንባቸው በአንገታቸው እየተለካ በመጀመሪያ ያቀረቡት ጥያቄ “እኔ ስነግስ ጌታዬ ኢያሱ ምን ይሆናል…?” የሚል ነበር፤ #ንግሥተነገሥታት #ዘውዲቱ #ወለቱ #ለዳግማዊምኒልክ #ዘኢትዮጵያ ተብለው በአባታቸው መንበር ላይ ከተገኙ በኋላ ማንኛውንም የሀገር አስተዳደርና የባለሥልጣናቱን ጉዳይ የሚመለከቱት በደግነትና በቅንነት መንፈስ ስለሆነ ለፖለቲካው አመራርና አወሳሰን ያጋጠማቸው ችግር ቀላል አልነበረም።
ዘውዲቱ ምኒልክ ዘውዳቸውን እንደጫኑ “…እኔ የዚህ የደጉ የኢትዮጵያ ኅዝብ ወኪሉና ምልክቱ እንድሆን ልጄ ወንድሜ አልጋ ወራሽ ደግሞ የመንግሥቱ አስተዳዳሪና መሪ እንዲሆን በታላላቆቹ የተወሰነውን አክብሬ እከተላለሁ…” ብለው ተዘጋጅተው ነበር።
ለኢትዮጵያ አስተዳደር ለውጡ በተደረገ በዓመቱ በምኒልክና በኢያሱ ዘመን የተሾሙት ሚኒስትሮች በራስ ተፈሪ ላይ አድመው ለመንግሥቱ መሪነት የተሰጣቸውን የባለሙሉ እንደራሴነት ሥልጣን ለመሰረዝና “አልጋ ወራሽ” ብቻ ሆነው ጊዜያቸውን እንዲጠብቁ ለማስደረግ በተነሱ ጊዜ ዘውዲቱ ምኒልክ “…እናንተ ከአባቴ ጋር ለብዙ ዓመታት የሠራችሁ ታላላቆች ሰዎች ስለ ሀገራችን አስተዳደር ከእናንተ የበለጠ የሚያውቅ ስለሌለ እኔና አልጋ ወራሽ እናንተን ከማዳመጥ በስተቀር ምን እንጨንርበታለን?…” ብለው ነበር በቅንነት የመለሱላቸው በኋላ ግን የሚኒስትሮች ተንኮል ስለገባቸው
“…እኔኮ የሚኒስትሮች ምክር ማለፊያ ነው ያልኩት እኔና ልጄ ወንድሜን ራስ ተፈሪን በመንግስት አስተዳደር ጉዳይ እንዳንቸገር ሊረዱን ያሰቡ መስሎኝ ነው እንጂ ሥልጣኑን ወደ እነሱ ለማዞር ማሰባቸውን አላወኩም ነበር…ብለው የልባቸውን ገልጠው ተናገሩ።
ይሁን እንጂ ሚኒስትሮቹ እንዲሻሩና ከዚያም ወደ ርስት ሀገራቸው እንዲሄዱና ከዚያም በግዞት እንዲኖሩ የተጠየቀውን ጥያቄ አንጀታቸው አልችል ብሎ እጅግ ተቸግረው ነበር። “…በእነዚህ አባቴን ሲያገለግሉ በኖሩ ታላላቅ ሰዎች ላይ እኔ እንዴት ጨክኜ እፈርዳለሁ…” በማለት እንዳዘኑ አጠገባቸው የነበሩት ያስታውሳሉ።
ከአራት ዓመት በላይ በየአውራጃው እየተዘዋወሩ በሽፍትነት ሲይስጨንቁ የኖሩትና እርሳቸውንም ከነ ባለቤታቸው በግዞት
አስቀምጠዋቸው የነበረው ልጅ ኢያሱ ሲያዙ የእስረኝነት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ዘውዲቱ ያቀረቡት ሀሳብ ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እና ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ አስቸጋሪ ነበር “…ለጌታ ለኢያሱ በቤተ መንግሥት ውስጥ የተለየ ቤት ተሰርቶለት የታመኑ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ተመድበውለት አባታችንም በየቀኑ ትምህርት እየሰጡት ቢኖር ይሻላል…” ብለው ነበር። በኋላ ግን አሳምነዋቸው
ልጅ ኢያሱ ኮረማሽ በቆዩበት ጊዜ ቀጥለውም ሰላሌ ሲዘዋወሩ ለእስረኛው ለጌታዬ እያሱ ስንቅ መስጠት አልከለክለውም እያሉ ቋንጣውን፣ በሶውን፣ ዳቦቆሎውን እያዘጋጁ ይልኩ ነበር።
ራስ ተፈሪ ንጉሥ በመባላቻው ያመፁትን የቀድሞ ባለቤታቸውን “ራስ ጉግሣ ወሌን” ከጥፋት ለማዳን ከንግሥትነታቸው ፕሮቶኮል ወጥተው ብዙ ጥረት አድርገው ነበር “ራስ ወሌ” ግን አሻፈረኝ ብለው ጦርነት አወጁ።
ዘውዲቱ ምኒልክ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል የእርስ በርስ ደም እንዳይፋሰስ በራሳቸውም በአመጸኛው ላይ ክፉ እንዳይደርስባቸው ወሰን የሌለው ጥረት “ጉግሣ ወሌ” ሳይጠቀሙበት ወደ ጥፋት መዝለቃቸው እጅግ የሚያሳዝን ሆነ። ብዙ ከደከሙ በኋላ “…እንግዲህ የአንተ ነገር በቃኝ ክፉ ነገር ቢደርስብህም፣ ብትሞትም አላለቅስም፣ አልጸጸትም…” ብለው እርማቸውን ስላወጡ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም የራስ ተፈሪ ጦር ድል ማድረጉ በተነገራቸው ጊዜ ጉግሣ ምን ሆነ? የሚል ጥያቄ አላቀረቡም። ዘውዲት በከፍተኛ የትኩሳት እሳት እየተቃጠሉ ሕይወታቸው ከማለፉ ከጥቂት ሰዓቶች በፊት “…ንጉሥ ተፈሪን ድል በማድረግህ እንኳን ደስ አለህ፤ እንኳን እግዚአብሔር ረዳህ በሉት…” ብለው የተናገሯት የመጨረሻ ቃላቸው ለአልጋ ወራሹ ምን ያህል እንደሚያስቡላቸው የሚያስገነዝብ ነው።
ንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ከአባታቸው ቀጥለው በሥነ ሥርዓት ዘውድ ጭነው የነገሡ ንግሥት ናቸው ምናልባትም በንግሥትነት ዘመናቸው የእሳቸው እንደራሴ የነበሩት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጎልተው ስለወጡ የእሳቸውን ንግድትነት ሸፍነውት ሊሆን ይችላል።  ንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ዘውድ ጭነው ለአስራ አራት ዓመት ውሳኔዎችን እየሠጡ ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል። የአባታቸውን ፈለግ በመከተልም ለሀገራቸው ሠርተው አርፈዋል ከንግሥት ዘውዲቱ ሥራዎች ጥቂቱ….
* ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጁን ወደ ቀለም ትምህርት ቤት እንዲልክ የማይልክ የሃምሳ ብር መቀጮ ይከፍላል የሚል አዋጅ አውጥተዋል። ትምህርት ምን ያህል ለሀገር ዕድገት አስፈላጊ እንደሆነ ቀድመው መረዳታቸውን ያሳያል
* ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልን አሠርተዋል
* የበአታ ለማርያምን ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠርተዋል
* በ1917 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን መኖሪያ ቤታቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲቀይሩ ነሥታቶቹ ሲቃወሙ፤ ይሁንታ ሰጥተው ባጀት መድበው እንዲሠራ አድርገዋል።
* የአሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅ (united nation) በቀድም ስሙ የመንግሥታቱ ማኅበር (league of nation
ሲቋቋም አልጋ ወራሽ ተፈሪ ብዙውን ሚና ቢጫወቱም በመኳንንቶቹና በመሳፍንቶቹ ይነሳባቸው የነበሩውን ተቃውሞ በማስቆም ኢትዮጵያ አባል ሀገር እንድትሆን የሆነችው በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ነው።
* አልጋ ወራሽ ተፈሪ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት ጉብኝት አድርገው እንዲመለሱና በኋላም በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ሥልጣኔ በደንብ ወደ ሀገራችን እንዲገባ ፈር የቀደዱት ንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ናቸው አልጋ ወራሹን በተለያየ የአውሮፓ ሀገራት ጉብኝት አድርገው እንዲመጡ ከማድረግ በተጨማሪ በ1916 ዓ.ም በፈረንሳይ የተደረገውን ኦሎምፒክ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ተመልክተው እንዲሙጡና የስፖርት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተደረገው በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከ 32 ዓመት በኋላ በ1948 ዓ.ም ለመጀመርያ ጊዜ በሜልቦርን ኦሎምፒክ ብትሳተፍም አልጋ ወራሹ ስለ ስለ ኦሎምፒክ ግንዝዛቤውን ያገኙትና ኦሎምፒክን የተመለከተቱት በንግሥቷ ሥልጣን ዘመን ነው።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንደነገሡ የነገሥታት ደንብ ነውና በጊዜው የነበረው በዳግማዊ ምኒልክ መልክና ስም የታተመው ገንዘብ ቀርቶ ወደፊት በግርማዊት ንግሥት መልክና ስም ገንዘብ እየታተመ እንዲሠራበት አስፈላጊ ስለሆነ ገንዘቡ የሚታተምበት ቅርጽ በብር፣ በአላድ፣ በሩብ፣
በመሐለቅ ተዘጋጅቷልና እንዲፈቅዱ ብሎ የገንዘብ ሚኒስትራቸው ቢጠይቃቸው “…እኔን የኢትዮጵያ ኅዝብ መርጦ ያነገሰኝ እኔ ምንም የዋልኩለት ውለታ ሳይኖር የአባቴን ውለታ አስቦ ስለሆነ እኔም በበኩሌ የአባቴን ስም ማሰብ ስላለብኝ በአባቴ ስም የታተመው ገንዘብ ተሰርዞ በኔ ስም የተተካው ገንዘብ እንዲተካ አልፈቅድምና በዚያ ይቀጥል። በኔ ስም ገንዘብ ሊታተም የተሰናዳው የመታሰቢያ ስጦታ ብቻ ይታተምበት…” ብለው በአባታቸው ስም የሚታተመው ገንዘብ በሥልጣን ዘመናቸው እንዲቀጥል አድርገዋል።
ለአስራ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት ሆነው በኖሩበት ዘመን ለኅዝቡ ደህንነትና ለሀገሪቱ ሰላም ከማሰብና ከመጸለይ አርፈው አያውቁም። ደግነታቸውንና ሩህሩነታቸውን የሚያውቀው ኅዝብ በሞቱበት ዕለት የገለጸው ኃዘንና ያፈሰሰው እንባ በሀገራችን ውስጥ መቼም ታይቶ የሚታወቅ አልነበረም። መጋቢት 23 ቀን 1922 ዓ.ም  አስክሬናቸው የአባታቸው የአፄ ምኒልክ አፅም ካለበት ከታዕካ ነገሥታት በዓታ ደርሶ ዑደት ተደረገ። እጅግ የተወደዱት ማሚቴ ምኒልክ በዘመናቸው አንድም ጊዜ የግል ደስታና የግል ሕይወት ኖሯቸው አያውቅም። በተወለዱ ልክ በ54 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም  ተለይተው ወደ ዘላለማዊ ቤታቸው ሲሄዱ በዘመናቸው ያሳዩትን ደግነትና ርህራሄ በማሰብ የኢትዮጵያ ኅዝብ የተሰናበታቸው እጅግ በመረረ ሀዘንና በዋይታ ነበር። ከንግሥቲቱ ሞት በኋላ ኢትዮጵያ ከምኒልክ እልፍኝ ወጥታ ወደ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ መንበር መዘዋወሯ በአዋጅ ተገለጠ።
ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የተገጠመ የሀዘን መግለጫ
ዘውዲቱ ምኒልክ የካህናት ተድላ
ሞተች ተቀበረች እ’ሷም እንደሌላ
ምንም እንባ አልወጣኝ እያዘነ ሆዴ
እንዳልጽናናማ ብዙ ነው ልማዴ
መቀነቴ ጠፋ ረሃቤ በልቶታል
ይህን ለግርማዊት ማን ይነግራታል
እንግዲህ አልተክልም የጌሾ አታክልት
“ወይኔ” ይበቃኛል የራሴ ንብረት።
ምንጭ
ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ
አምባሳደር ዘውዴ ረታ
የታሪክ ማስታወሻ
ደጃዝማዥ ከበደ ተሰማ
—————————————//——————-—————-
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic