>
5:13 pm - Wednesday April 19, 0744

የዛሬው ቅዳሜ የወፎች ቀን ብለን ሰይመነዋል! የወፎች ቀን!!! (ዘመድኩን በቀለ )

የዛሬው ቅዳሜ የወፎች ቀን ብለን ሰይመነዋል! የወፎች ቀን!!!

ዘመድኩን በቀለ 
 
 ( ህንዳዊውን ፒኮክን ግን  አይመለከትም!!!) 
•••
በአዲስ አበባ ፥ በዳግማዊ ሚኒልክ ቤተ መንግሥት መግቢያ በራፍ ላይ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ህንዳዊውን ፒኮክ የተባለ የህንዶችን ብሔራዊ አርማና መለያ ምልክት የሆነ ወፍ በእንግድነት አምጥቶ በኢትዮጵያ ካቆመ በኋላ ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ስለዚህች ወፍ አጭር ማስታወሻ ጽፎ ነበር። እናም ዳኒም ለፒኮክ ጥብቅና በቆመበት ማስታወሻው ላይ ወፏ በጥንት ሰዎች ዘንድ የትንሣኤ ምልክት ሆና ትታመን እንደነበርም ገለጸ።
•••
ከዚህ በኋላ ከዚያኛው መንደር አቧራው ጨሰ። ጃወርም አለ። ተቆጣም። “ ነው እንዴ? ፥ ነገሩ እንደዚያ ነው ለካ? እኔኮ ጌጥ መስላኝ ነበር ብሎም ሄጵ አለ”። ዳንኤልም ወደ ጦማሩ ተመለሰ። ተመለሰና ነገረ ትንሣኤውን ያመላክታል፣ የቤተ መንግሥቱም ሰዎች ከኢትዮጵያ ትንሣኤ ጋር አያይዘው የሠሯት ናት የሚለውን አንቀጽ አጥፍቶ ለማምለጥ ሞከረ። ጃዋር ግን ኤዲት ያልተደረገውን የቀደመ የዳኒን ሥራ አስቀድሞ ሴቭ አድርጎ ይዞ ስለነበር አቧራው መጨሱ እንደቀጠለ ነው።
•••
የሆነው ሆኖ ከጌታ ትንሣኤና ከነገረ ክርስቶስ ጋር ተያይዘው ምሳሌም ሆነው በቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉት አእዋፋት መካከል ከፒኮክ በቀር ለዛሬ ጥቂቶቹን እናያለን። ( ጣኦስና ፒኮክ ግን አልተካተቱም ) የሉማ። የሌሉትን ከየት አመጣለሁ።
በቅድሚያ ፥ ፊንክስ / phoenix / 
•••
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥነ-ፍጥረትን ተንትኖ ባስተማረበት  በአክሲማሮስ መጽሐፉ እጹብ ድንቅ ስለምታሰኝ ስለ ፊንክስ ወፍ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ (ስለዚህ ወፍ በፊሳልጎስ (ፊስአልጎስ) Pysology /Bestiary/ እንዲሁም በሃይኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ላይ ተነግሯል አባታችን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ “Panarion” በሚባል መጽሐፉ ሳይጠቅሰው አይቀርም) ፦ ስሙ ፊንክስ / phoenix /  የሚባል ወፍ አምስት መቶ ዘመን ይኖራል። የሚሞትበት ቀን እንደደረሰ በአወቀ ጊዜ ወደ ሊባኖስ (ወደ ደጋ ዛፎች) ይገባል የዛፎቹንም ቅርንጫፎች ይሰብርና በክንፎቹ ይሸከማቸዋል፡፡
ብዙ ጭቃም ሰብስቦ ሙቀት ወደ ሚፀናበት ወደ ግብጽ ይወርዳል። ኹለቱንም ክንፎቹን አብድ በሚባል ሽቱ ያጥናቸዋል። አብድ መልካም ሽቱ ያለው ጭቃ ነው ስሙም በግብፅና በዕብራዊያን ቋንቋ አብዱ ይሉታል።
•••
ፊንክስ ይኸን ጭቃ ይዞ ከላዩ ላይ ቆሞ ደረቱን በክንፉ ያጣፉል። ደረቱንም በክንፉ ይመታዋል። እሳትም ከአካሉ ወጥቶ ሥጋውን አጥንቱን ሁሉ ያቃጥለዋል በከበረ በተመሰገነ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ዝናብን የያዘ ደመና ይመጣል ይዘንባልም። ከዚያ ወፍ አካል የወጣውን እሳትም ያጠፉዋል። ከአጥንቱም ጥቂት ይቀራል። በአንድ ቀንም ይጠፋል። ከዚኸም በኋላ ከእርሱ ትል ይገኛል። ለዚያ ትል ክንፎች ይበቅልለታል። ትንሽም ወፍ ይሆናል። በሦስተኛው ቀን ያድጋል ይበረታል። ለሚያርሱ ለሚቆፍሩ ይታያል ቦታውንም መርምሮ ለሚያውቅ የቀና ነው። ከዚህ በኋላ ወደ መጣበት ከዚያ ይኖራል።
•••
አንድም ደግሞ ይኸ ፊንክስ አምስት መቶ ዓመት ሲሆነው ወደ ሊባኖስ ዛፎች ይገባል። ኹለት ክንፎቹን አብድ በሚባል ሽቱ ያጥናቸዋል። በሃገረ ፀሐይ (ሄልዮፖሎስ) ይህች ከተማ ግብፅ ውስጥ ዛሬ “ዓይን ሻምስ”፣ በሶርያ ደግሞ የጥንቷ ፊንቂ ዛሬ “ባአልቤክ” በዚህ ስም የፀሐይ ከተማ በመባል ይጠራሉ። ካህኑም ከአጸደ ወይን እንጨት ሞልቶ ወደ መሠዊያው ይገባል። ወፋም እራሱን በእሳት ያቃጥለዋል። ዐመድ ይሆናል። በማግስቱም ካህኑ መሰዊያውን ሲፈልግ ዐመዱ ላይ ትል ያገኛል። በሦስተኛው ቀን ትንሽ ወፍ ይሆናል። ካህኑም ጫጩት ያያል። በአራተኛው ቀን ታላቅ ወፍ ሆኖ ካህኑ ያገኘዋል። ፊንክስም እጅ ነሥቶ ወደ ቀድሞ  ቦታው  ይሄዳል። ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲኸ አለ “ፍጡራንን መርምሮ ማወቅ ካልተቻለ ሁሉን የፈጠረ እርሱን መርምሮ ማወቅ እንደምን ይቻለናል?” …በአርምሞ እናድንቅ እንጂ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል ”  ነፍሴን ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሳት “.ዮሐ 10፥18 ያለውን አስቀድሞ በተፈጥሮ  አስተማረን። በማለት ፍቅር ዘብሩክ ዘመዴ ይህችንም ጨምርባት ብሎ ከአዲስ አበባ ቂርቆስ የላከልኝን ጨመርኩት።
•••
የሌላኛውም አስደናቂ ወፍ ታሪክ ይቀጥላል። ህንዳዊውን ጋሽ ፒኮክን ግን አባቴ ይሙት አላገኘሁትም። ጋሽ ጃዋርም ነገር አብርድ። ዳኒም ነገር አታወሳስብ። ምክሬ ነው።
••• 

ከራድዮን !!!]

 ፀዓዳ ዖፍ ከራድዮን !! ኦርቶዶክሳዊ የተዋሕዶ ልጅ ሆኖ መፈጠር እኮ መታደል ነው። ዕድለኝነትም ይጠይቃል። ሃቅ።
•••
•••
በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉን ነገር ለኢሉሚናቲ የምትሰጡትን ነገር ግን አቁሙ። ኢሉሚናቲ የመጣው ትናንት፣ ሥነ ፍጥረት የነበረው ጥንት። ምልክቱን ሁሉ ለሰይጣን ሰጥተን የምን ሽባ ሆኖ መቀመጥ ነው። ኢሉሚናቲዎቹ ነገ መስቀል፣ ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያን ዓርማቸው ቢያደርጉ አውጥተን ልንጥላቸው ነው ማለት ነው? ኧረ ተረጋጉ ጎበዝ። የምን ሳይተኮስ፣ ውጊያ ሳይጀምር እጅ መስጠት ነው። ነቃበል። ምድረ ፈዛዛ ሁላ። 
• አሁን ደግሞ ስለ ከራዲዮን ወፍ ደግሞ እናወሳለን
•••
ከራድዮን የሚባል ነጭ ወፍ አለ። ጠቢባን በድካም አድነው ይይዙታል። ይዘውም ከቤተ መንግሥት ወስደው ያኖሩታል። ሰው ሲታመም ወስደው ያቀርቡታል። ያ ሰው የሚሞት የሆነ እንደሆነ አያየውም ፊቱን ይመልስበታል። የሚድን የሆነ እንደሆነ ግን ያየዋል። ቀርቦም አፉን ከአፉ አድርጐ የህምተኛውን እስትንፋሱን ይቀበለዋል። በእስትንፋሱ ምክንያት ደዌ ከሰውዬው ወደሱ ይመለሳል። ታማሚው ይድናል ወፉ ይታመማል። ነጭ የነበረው ይጠቁራል። ብርድ ብርድ ይለዋል። ዋዕይ ሙቀት ሲሻ ወደ አየር ይወጣል። ዋዕይ ሙቀቱ ሲሰማው ሲያይልበት ከባህር ይገባል። 3 መአልት 3 ሌሊት በባህር ኑሮ የቀደመ ጠጉሩን መልጦ በአዲስ ተክቶ እንደ አዲስ ታድሶ ኃያል ሆኖ ይወጣል።
•••
ወፉ በዕለተ ሐሙስ የተፈጠረ ፍጥረት ነው። እግዚአብሔር ወፉን በዚህ መልክ ስለምን ፈጠርው ቢሉ በኋለኛው ዘመን የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማያምኑ ሁሉ ትምህርትና ምሳሌ አብነትም ይሆን ዘንድ ሥላሴ ይህን ወፍ የማዳን ኃይል ሰጥተው ፈጥረውታል።
•••
ይኸውም የጌታ ምሳሌ ነው!
ከራድዮን የጌታ ምሳሌ ነው!
 
ህመምተኛው የአዳም ምሳሌ ነው። በአይነ ምህረቱ አይቶ በእስትንፋስ ምክንያት ደዌ ወደሱ እንደተመለሰ በአዳም የተፈረደውን መከራ ጌታ ለመቀበሉ ምሳሌ ነው፡፡ ወደ አየር እንደመውጣት ከመሬት ከፍ ብሎ በመስቀል ተሰቅሏል፤ ከባህር እንደመግባት ከመቃብር ወርዷል፡፡ 3ት ቀን 3ት ሌሊት በከርሰ ባህር ኑሮ የቀደመ ጠጉሩን ትቶ እንደመነሣት ጌታም እንዲሁ 3ት መአልት 3ት ሌሊት በከርሰ መቃብር ኑሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ለመነሣቱ ምሳሌ፡፡
•••
እግዚአብሔር ፍጥረታትን ግሩምና ውብ አድርጐ ፈጠራቸው፤ የሰው ልጅም እንደነዚህ ያሉ የእግዚአብሔር ሥራዎችን እያየ እግዚአብሔር ድንቅ አምላክ እንደሆነ የእጆቹም ሥራ ግሩም እንደሆኑ ይመሰክራል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም የእሳት እራት፣ ፍልፈል፣ የእሳት ትል፣ ፊንክስ… በራሳችንም ፀጉር ሳይቀር እየመሰለ የትንሣኤ ነገር ያስረዳናል።
እነዚህ እንኳን ሞተው የተነሡ ከእንስሳ ሁሉ የከበረ የሰው ልጅማ እንዴት አይነሣም ? ስለዚህም ይህ ቅዱስ ሲያጠቃልል እንዲህ ይላል “ የሥጋችንን ትንሣኤ አንካድ በምድር ላይ የወደቀው እርሱ እንዲነሣ እንመን እንጂ፡፡” እያለ ያብራራል። በተለይ የሥነ ፍጥረት አንድምታ፣ መጽሐፈ አክሲማሮስን ብታነቡ የአስደናቂ ፍጥረታትን ታሪክና ሥነ ተፈጥሮ ትገበዩበታላችሁ።
•••
እያየሁ ደግሞ እጨምርላችኋለሁ።
•••
ሻሎም  !  ሰላም  !
Filed in: Amharic