>

የአገዛዙ አዚም ሰለባዎች (ከይኄይስ እውነቱ)

የአገዛዙ አዚም ሰለባዎች

 

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

 

ከወያኔ አገዛዝ መለያ ጠባዮች አንዱ የግዙፍ ሀብትና ንብረት ዘረፋ ብቻ ሳይሆን የዐዋቂዎችን መልካም ሃሳቦች ያለምንም ኀፍረት መስረቅ ነበር፡፡ ሥርቈት በዓለማዊውም ሆነ መንፈሳዊው ሕግ ወንጀል/ኀጢአት ነው፡፡ የሃሳብ ሥርቈት ደግሞ ቢያንስ ነውር ነው፡፡ በግርድፍ አቀራረብ የአእምሮአዊ ንብረት ሕግ ተብሎ የሚታወቀው ሕግ በማይዳሰሱ/ግዙፍ ባልሆኑ ሀብቶች ላይ ላለ መብት ጥበቃ የሚያደርግ ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ ለ‹ፈጠራ ሥራዎች› የቅጅ መብት ጥበቃ ቢያደርግም ሌጣ/ዝርው ‹ሃሳብ› ፣ ፅንሰ ሃሳብ በራሱ ዕውቅና የሚሰጠውና በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት የ‹ፈጠራ ሥራ› ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ሙያዊ ወደሆነው የሕግ ጉዳይ መግባት የዚህ ጽሑፍ ዓለማ ባለመሆኑ ለዝርው ሃሳብ ወይም ሃሳብ በራሱ የተለየ የሕግ ጥበቃ እንደማይደረግለት ግንዛቤ ይዘን አስተያየታችንን እንቀጥላለን፡፡ 

ወያኔ ኢሕአዴግ የዐዋቂዎችን በተለይም የተቀናቃኞቹን ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ሃሳብ ይወስድና ከራሱ እንዳፈለቀው/እንዳመነጨው አድርጎ ይናገረዋል፡፡ የሃሳቡ አመንጪ ተደርጎ የሚወሰደውም የአገዛዙ አለቃ ሲሆን ካድሬዎቹ እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋቡታል፡፡ ላገር ለወገን የሚጠቅመውን በጎ ሃሳብ ለልማት ሳይሆን ለጥፋት ነው ‹የሚጠቀምበት›፡፡ የወያኔ የሃሳብ ሥርቈት ዋና ዓለማ መነሻውም መድረሻውም ሃሳቡ በሌሎች ሥራ ላይ እንዳይውል ማምከን/ማኰላሸት ነው፡፡ አንድም ሃሳቡን ባለመረዳት በድንቁርና፤ ወዲህ ደግሞ ክፋትና ምቀኝነት ባህርይው በመሆኑ፡፡ በዚህ መልኩ ኮስምነው፣ ደቅቀው፣ ሰልለው የቀን ብርሃን ሳያዩ ጭንጋፍ ሆነው የቀሩ ትላልቅና ማለፊያ ሃሳቦች የትየለሌ ናቸው፡፡ የስንቱ ዜጋ ቅስም ተሰብሯል? የስንቱ ቈሽት ተቃጥሏል? ቤት ይቊጥረው፡፡ ይህ ከይሲ አገዛዝ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ግለሰብ ዜጎችና ድርጅቶች ወደተለያየ ንግድ ለመሠማራት በራሳቸውም ሆነ በባለሙያዎች አስጠንተው ያዘጋጇቸውን የፕሮጀክት ምክረ-ሃሳቦች (project proposals) ከሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች ሠርቀው ለአገዛዙ ደጋፊዎችና ሎሌዎች በብላሽም በሽያጭም ሰጥተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት በተለይ በምርጫ 97 ማግሥት በስፋት ተፈጽሟል፡፡ በሚመለከታቸው መ/ቤቶች ስትሠሩ የነበራችሁና ለኅሊናችሁ ያደራችሁ ዜጎች ካላችሁ ዝርዝሩን በማስረጃ ሥጋ ልታለብሱት ትችላላችሁ፡፡ 

ባንፃሩም የዐቢይ አገዛዝ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት በወሰዳቸው የእርምት ርምጃዎች፣ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችና በገባው ቃል ምክንያት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ቅጥ ያጣ የፈንጠዝያ ስሜት ከመፈጠሩም በተጨማሪ ሕዝብ ነገን በተስፋ እንዲመለከት አድርጎት ነበር፡፡ ይህ ስሜት ትንሽ ትልቁን፣ የወያኔ ወራሽ የሆነውን አገዛዝ ለመደገፍ አነሳስቶት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እንደ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም፣ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ አቶ ማሞ እስመለዓለም የመሳሰሉና ሌሎችም (ቊጥራቸው ጥቂት ቢሆንም) ብዙ ባደባባይ የማይታወቁ ግን በየመስካቸው የተማሩና የተወሰነልምድ ያላቸው የዐቢይ እኩዮችና ጎልማሶችን አሰባስቦ ነበር፡፡ ዛሬ የዐቢይ አገዛዝ የቁልቁለቱን መንገድ በፍጥነት ተያይዞት፣ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ በዐቢይ ‹ፈቃድ› እና በተረኞች ዘመዶቹ ፊትአውራሪነት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ትውፊት፣ እሤቶችና ቅርሶች ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ህልውና እና የሕዝቧን ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ወያኔን በሚያስንቅ ሁኔታ አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡ ቀደም ብዬ በስም የጠቀስኳቸውና በስምም ያልተጠቀሱት አገዛዙ በአማካሪነትና በተለያየ ኃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸውና ወያኔን በማስወገድ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ (አንዳንዶቹም በቅርብ የማውቃቸው እሥር፣ እንግልትና ውርደት የተቀበሉ) ያበረከቱ ግለሰቦች በኦነጋውያኑ (ሌንጮ ለታ፣ ዳውድ ኢብሳ፣ ጀዋር ወዘተ.) ኦሕዴድ ግንባር ቀደምትነት፣ ‹የለውጡ መሪዎች› በተባሉና ባፈነገጡ ግለሰቦች መሠሪነት፣ በዐቢይ የአመራር ጮርቃነት÷ የሚያሰደነግጥ ዝምታና በዚህም ምክንያት በተፈጠረው ሥርዓተ አልበኝነት የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤክ ከወያኔ የቀጠለ ከፍተኛ የጥፋት ዘመቻ ሲካሄድባት፣ ክፍላተ ሀገራቱ አብጠው ሉዐላዊ አገር ሲመስሉ፣ በአገራችን ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ፣ ልጃገረዶች/ተማሪዎች ታፍነው ተወስደው እስካሁን የደረሱበትና በሕይወት የመኖር/ያለመኖር ጉዳይ ሳይታወቅ ሲቀር፣ በዜጎች የውስጥ መፈናቀል በዓለም የመጀመሪያወን ቦታ ስንይዝ፣ ግዙፍ አገራዊ የሀብት ዘረፋ ሲፈጸም÷ ዘራፊዎቹ በዐቢይ ሲሾሙና ከለላ ሲሰጣቸው (ባጫ ጊና፣ድንቁ ደያስ፣ ገምሹ በየነ ወዘተ) ላለፉት 27 ዓመታት ግዙፍ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የነበሩ በአራቱም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛና መካከለኛ አመራር ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች ሲሾሙ ሲሸለሙ (ወርቅነህ ገበየሁን፣ ግርማ ብሩን፣ አባዱላ ገመዳን፣ ብርሃኑ ጸጋዬን፣ ሺፈራው ሽጉጤን ለአብነት ያነሷል)፣ ማዕከላዊው አገዛዝ እንኳን ክፍላተ ሀገሩን አ.አ.ን እና ድሬደዋን ማስተዳደር ተስኖት የተረኞች ሰለባ ሲያደርግ፣ በየክፍላተ ሀገራቱ ያሉ የጎሣ አለቆች የአገር መከላከያ አቋም ያለው ሠራዊት ሲያደራጁና ለጥፋት ሲዘጋጁ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ አፈር ድቤ ሲበላ፣ ወርቅና ሌሎች የሕዝብ ሀብት የሆኑ የከበሩ ማዕድናት የጥቂት ተረኛ ቡደኖች መጫወቻ ሲሆን፣ ከወያኔ ጋር በዝርፊያ የበለጸጉ ‹ወንጀለኛ ነጋዴዎችን› አቅፎ የወንጀል ፍሬአቸው ተጠቃሚ ሲሆን፣ወዘተ. ከሕዝቡ እኩል ወይም በበለጠ ሲከታተሉ ቈይተዋል፡፡ በጽሑፋቸውም ባንደበታቸውም የሚታወቁት ሰዎች የጠቀስኳቸውንና እዚህ ያልተዘረዘሩትን አገራዊ ጥፋቶች በሚመለከት ዝም ማለትን መርጠዋል፡፡ አንዳንዶቹ ብቅ የሚሉት የአገዛዙን ድርጊት/ዝምታ ለመከላከልና ምክንያት ለመስጠት ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተቀባይነታቸውም ሆነ ሕዝቡ ለነሱ ይሰጥ የነበረው ቦታ እንደ አገዛዙ ከሰማይ ወደ ምድር የተፈጠፈጠ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ምንም ማድረግ ካልቻሉና ከኅሊናቸው ጋር ካሉ ቦታውን መልቀቅ እንጂ ለአገዛዙ የሕጋዊ ተቀባይነት ገፅታ ለመፍጠር መቀመጥ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ይሄ የይሉኝታና ካፈርኩ አይመልሰኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ በአገዛዙ ላይ መሠረት ያለው ትችት ያቀርቡ የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍያን አገዛዙን ከተጠጉ ጓደኞቻቸው ወይም ከፍ ብለን ከጠቀስናቸው ሰዎች በሚሰሙት ወሬ ትኩስ ወይም በራድ መሆን አቅቷቸው በለብታ ተሽመድምደው በይሉኝታ እዚህም እዚያም ሲረግጡ ይስተዋላሉ፡፡ የበሬ ምንትስ ይወድቅልኛል ብላ እንደምትከተለው ቀበሮ ጉም በመዝገን ተስፋ ይዋልላሉ፡፡

ወያኔ ታላላቅ ሃሳቦችን ሰርቆ ያመክን ነበር፡፡ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የመከኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ስብስብ የሆነው ኦነጋዊው ኦሕዴድ ግን በጐሣ መሠረታቸው የማይፈልጋቸው ነገር ግን ‹የተሻለ ሃሳብ› እንዳላቸው የሚታመኑ ኢትዮጵያውያኖችን አስጠግቶ የማምከን/የማኰላሸት ተግባር ላይ የተጠመደ ይመስለኛል፡፡ አገርና ሕዝብ የሰጠንን መልሰን ለሕዝባችን እናበረክታለን በሚል መንፈስ ጥሪ የተቀበሉ ግለሰቦች ዛሬ የአገዛዙን ገመና ለመሸፈን ሲሯሯጡ ወይም ደብሸው ይታያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውና የሚረጋገጠው የወያኔን ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ሙሉበሙሉ ሕዝብ በሚመክርበትና በሚያፀድቀው አዲስ ሕገመንግሥት በመተካት፣ ሥር የሰደዱ መዋቅራዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት፣ ዘላቂነት የሚኖራቸውን ተቋማት በመገንባትና አገዛዞች ከሥሩ የሚነቅሉት ሳይሆን ለትውልደ ትውልድ የሚተርፍ የመንግሥት ሥርዓት በመዘርጋት ነው፡፡ ዐቢይ በደም መሥዋዕትነት የተገኘ ያለውን የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገመንግሥት› ከምርጫ በኋላ የሚያሻሽለው ይመስላችኋል? መቼም ሰው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው የሚናገረው፡፡ ከሰሞኑ ሥልጣን የማራዘሚያ አማራጮች ንግግሩ አስተዋይ ሰው ምንድ ነው የሚገነዘበው? ብልጽግና ኢሕአዴግ ነው፡፡ እቅጩን ለመናገር ደግሞ ኦነጋዊ ኦሕዴድ ነው፡፡ የዐቢይ ደጋፊዎች ድጋፋቸው ለግለሰቡ ነው ወይስ ድርጅቱን ይጨምራል? ለነገሩ ከሁለት አንዱንም ሆነ ሁለቱን የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ የዐቢይ ማኅበራዊ መሠረት ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሰየመው ግዛት የሚኖሩ የተወሰኑ የኦሮሞ ተወላጆች፣ የኢሕአዴግ የብሔር ድርጅቶች (ከሕወሓት በስተቀር) አባላትና ካድሬዎች ይመስሉኛል፡፡ በተለይ የኋለኞቹ ድጋፍ የተመሠረተው ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ከለላ ፍለጋ ነው፡፡ እነዚህ ደጋፊዎቹ ደግሞ የ‹ደደቢቱ ሰነድ› አንድ አንቀጽ ከተነካ እንተላለቃለን ባዮች ናቸው፡፡ ስለዚህም ዐቢይ የጐሣ ፌዴራሊዝሙን/የጐሣ ፖለቲካን ወይም የፖለቲካ ፓርቲን በጐሣ ማደራጀት፣ ‹ክልል› የተባለውን ሕዝብን የማግለያ መዋቅር፣ ነፃ አውጭ ድርጅቶች ዋስትናችን ነው የሚሉትን የመገንጠል ድንጋጌ፣ የአ.አ. ልዩ ጥቅም (በጽሑፍ ያልተገለጸው የባለቤትነት) ጥያቄ፣ ድሬደዋ ላይ የነገሠው የጥቂቶች መድሎ ሥርዓት ወዘተ. ሊነካ የሚችልበት ሁናቴ ያለ አይመስልም፡፡ 

ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገዛዙም ሆነ ተቃዋሚ ነን በሚሉ ወገኖች ከአጋንንት መካከል ምርጫ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ሁናቴ ውስጥ ያለ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ለአገራችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚጨነቁ ዜጎች ሁሉን አቀፍ የሆነ አገራዊ የምክክር ጉባኤ እንዲጠራ ሲጮኹ የከረሙት፡፡ ዐቢይ የሚሰማችሁና ለመናገርም ድፍረቱ ያላችሁ ባገር ውስጥም ሆነ ውጭ የምትገኙ አማካሪዎቹ አገር የሚያረጋጋ፣ ለምርጫ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅቶቹ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው ዜጎችን የሚያካትት ከሲቪል ማኅበረሰቡ የተወጣጣ ጉባኤ (ከ1-2 ዓመት የጊዜ ገደብ ተበጅቶለት) አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት እንዲረከብ ብትመክሩት፡፡ ይህ ሃሳብ ለፖለቲከኞች በተለይ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ለማያስጨንቃቸው የዋህነት ሲያልፍም ሞኝነት ሊመስል ይችላል፡፡ 

ሰሞኑን ዐቢይና ጠበቆቹ፣ ተቃዋሚዎች ተብዬዎች እና መደበኛውም ሆነ ማኅበራዊው መገናኛ ብዙኃን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስና ክፍተት እንደተፈጠረ አድርገው ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ አነጋገር የሕገ መንግሥት መኖርን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው ሕገ መንግሥት አለ ብሎ የሚያስብ? ሁሉም ጎራ ድብቅ አጀንዳውን የሚያስፈጽምበትን አማራጭ ሃሳብ ሲያቀርብም ይደመጣል፡፡ 

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ላለፉት 30 ለሚጠጉ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነበር? አሁንስ አለ? በደም የጨቀየችው ምድራችን፣ የፍትሕ ያለህ እያለች የምትጮኸው ምድራችን፣ ባገሩ መድረሻ ያጣው ሕዝባችን፣ ጐሣን መሠረት አድርጎ በየአካባቢው የተፈጸመው እልቂት፣ ገበሬውን የመንግሥት ጭሰኛ በማድረግ የተፈጸመው ግፍና በደል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ገንዘቦች በሆኑት በተፈጥሮ ሀብቶች በተለይም በመሬትና በማዕድናት የተፈጸመው እስከ የሌለው ዝርፊያ፤ ኢሕአዴግ የሚባለው አገዛዝ በሚመራቸው የፀጥታ ኃይሎች (መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ ልዩ ኃይል) የተፈጸመው ግፍና በደል ባጠቃላይ ሥርዓተ አልበኝነቱ የሕገመንግሥት እና ሕገመንግሥታዊነት መገለጫዎች ናቸው? ይሄ ከንቱ የወያኔ ሰነድ ለምን ሥልጣንን እና በሱም የሚገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሲሆን ትዝ ይለናል? አንድ የጋራ አገር አለን ብለን የምናምን ከሆነ፣ ከወያኔ ሰነድ ውጭ አስበን የጋራ መፍትሄ መፈለጉ ላይ ብናተኩር የሚሻል ይመስለኛል፡፡

Filed in: Amharic