>

እብድነቱን እንጂ ነብይነቱን ያልተቀበልንለት የአንድ ዕብድ ትንቢት !!! (ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት)

እብድነቱን እንጂ ነብይነቱን ያልተቀበልንለት የአንድ ዕብድ ትንቢት !!!

 ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት 
  «… የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ይከፈላል፣ በስድስት ይከፈላል – የሚበላ፣ የሚበላ /’በ’ ይጠብቃል/፣ የማይበላ፣ የሚያባላ፣ የሚያስበላ፣ የሚያብላላ ተብሎ ይከፈላል» 
አንድ ዕብድ አራት ኪሎ ላይ ጆሊ ባር ፊት ለፊት ቆሞ «ወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ይከፈላል፣ በስድስት ይከፈላል» እያለ ቡትቶውን እየጎተተ ይጮኻል፡፡ አጠገቡ የነበሩ ጋዜጣ ሻጮች «ዝም በል፣ ዕብድ፣ ተነሣብህ ደግሞ፤ማን ይከፍለዋል ደግሞ፤ መዓት አውሪ» አሉና ሊያባርሩት እጃቸውን ወነጨፉ፡፡ እርሱም በተራው ከት ብሎ ሳቀና «የዕውቀት ማነስ ችግር አለባችሁ፡፡ ኩላሊታችሁ ችግር አለበት፡፡ የኛ ሰው መከፋፈል ልማዱኮ ነው፡፡ በዝባዥ እና ተበዝባዥ፤ አድኃሪ እና ተራማጅ፤ ፊውዳል እና ፀረ ፊውዳል፤ ኢምፔሪያሊስት እና ፀረ ኢምፔሪያሊስት፤ አብዮተኛ እና ፀረ አብዮተኛ፤ ሕዝባዊ እና ፀረ ሕዝብ፤ ልማታዊ እና ፀረ ልማት፤ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ኪራይ ሰብሳቢ» መልሶ ከት ብሎ ሳቀ፡፡
ቀጠለ «ወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ይከፈላል» አለና የቀኝ እጁን መዳፍ ጠቅልሎ እንደ ጡሩንባ ነፋው፡፡
«ምን ተብሎ ነው የሚከፈለው» አሉት አንድ ጋዜጣ የሚያነበቡ አዛውንት፡፡
«ጥሩ ጥያቄ ነው» አለና ጉሮሮውን በስላቅ እንደመጠራረግ ብሎ «የሚበላ፣ የሚበላ /’በ’ ይጠብቃል/፣ የማይበላ፣ የሚያባላ፣ የሚያስበላ፣ የሚያብላላ ተብሎ ይከፈላል» ይህንን ሲናገር በአካባቢው የሚያልፉትን የብዙዎችን ጆሮ ለመሳብ ችሎ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም መንገዳቸውን ገታ አድርገው ያዳምጡት ጀምረዋል፡፡
«እስኪ ተንትነው» አሉት እኒያ አዛውንት ጋዜጣቸውን አጠፍ አድርገው፡፡
«’የሚበላ‘ ማለት ጤፍ መቶም መቶ ሺም፣ መቶ ሚሊዮንም ቢገባ መገዛቱን እንጂ የተገዛበትን የማያውቅ፤ በጋዜጣ ካልተጻፈ፣ በሬዲዮ ካልተነገረ በቀር የኑሮ ውድነቱ የማይነካው፤ የውጭ ምንዛሪ ቢጠፋም ባይጠፋም ዶላር የማያጣ፣ ወረፋ ቢኖርም ባይኖርም ባንክ እምቢ የማይለው፣ ጨረታውን ሁሉ ለማሸነፍ የሚያስችል ድግምት ያለው፤ ተራራ ቁልቁለት መውጣትና መውረድ ሳያስፈልገው ቤቱ ቁጭ ብሎ ሚሊየኖችን የሚያፍስ፤ ሰው ሁሉ በእጁ የጠቀለለው በእርሱ ጉሮሮ የሚያልፍለት፤ ሰው ሁሉ የጎረሰው በእርሱ ሆድ የሚቀመጥለት፣ ሰው ሁሉ ሮጦ እርሱ ሜዳልያ የሚሸለም፣ ለመብላት እንጂ ለመሥራት ያልተፈጠረ ማለት ነው፡፡
«’የሚበላ‘ ማለት ደግሞ ጉቦ ለመስጠት፣ ኪራይ ለመክፈል፣ ግብር ለመክፈል የተፈጠረ፡፡ ምንም ሕግ አክብሮ ቢሠራ አንዳች ጉርሻ ካላጎረሰ ሥራው የማያልቅለት፤ ለመጋገር እንጂ ለመብላት ያልታደለ ማለት ነው፡፡ ‘ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት’ ሲባል አልሰማችሁም፡፡ የርሱም ነገር እንደዚህ ነው፡፡ ለመበላት የተፈጠረ ነውና ሕገ ወጦቹ ተቀምጠው እርሱ በሕጋዊ መንገድ እየሠራ እና እየኖረ እርሱ ነው የሚከሰሰው፤ እርሱ ነው የሚጉላላው፡፡ እዚህ አንዳንድ ሠፈር ያሉ ቀበጥ ወላጆች ለልጆቻቸው ሁለት ሁለት ሞግዚት ነው አሉ የሚቀጥሩት፡፡ አንዷ አሳዳጊ ናት፡፡ አንዷ ደግሞ ልጁ ሲያጠፋ የምትመታ ናት፡፡ ልጃቸው እንዳያመው እርሱ ባጠፋ ቁጥር እርሷ ትመታለች፣ እርሷ ታለቅሳለች፡፡ እነዚህም እንደ እርሷ ናቸው፡፡
«’የማይበላ‘ የሚባለው ለቁጥር የሚኖረው ነው» አለና ወደ ሕዝቡ ዘወር ብሎ «አሁን ለምሳሌ እኔ እና እናንተ ጥቅማችን ለቁጥር ነው» ሲል ብዙዎች በፈገግታ አዩት፡፡ «አዎ እኛኮ ቁጥሮች ነን፡፡ ቁጥር ደግሞ ምዝገባ እንጂ ምግብ አያስፈልገውም፡፡ የኛ ሥራ መመዝገብ ነው፤ መብላት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲቆጠር እንካተታለን፤ ሲበላ ግን አንካተትም፤ ርዳታ ለማግኘት እናስፈልጋለን፤ እርዳታውን ለመቀበል ግን አናስፈልግም፡፡ ስለዚህ ቁጥር ነን ማለት ነው፡፡ ወደፊት እንጀራን በቴሌቭዥን ዳቦንም በፊልም ነው የምናየው፡፡ ወደፊት ምግብ ቤቶች ሁለት ዓይነት ክፍያ ያዘጋጃሉ፡፡ አንዱ ለሚበላ፣ አንዱ የሚበላውን ለሚያይ፡፡ እኔ እና እናንተ ገባ ብለን ምግብ እና አመጋገብ አይተን እንወጣለን፡፡
እንጀራ በሰማይ እኔ በእግሬ ሆኜ
አልደርስበት አልኩኝ ባክኜ ባክኜ 
የተባለው በ’ፍካሬ ሕዝብ መጽሐፍ’ ላይ የተጻፈው ትንቢት ይፈጸማል፡፡
«’የሚያባላ‘ የሚባለው ደግሞ ከሚበላው ተጠግቶ ለበይዎች እንደ ‘ሀፒታይዘር’ የሚያገለግል ነው፡፡ አያችሁ የሚበሉት መንቀሳቀስ አይወዱም፣ ውቃቢያቸው ይጣላቸዋል፤ ስለዚህም የሚያባላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ የሚቀበሉ፣ የሚያቀባብሉ፣ የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ እንደነዚያ ጠግበው ባይበሉም ትርፍራፊ ግን አያጡም፡፡ እነዚያ ግንድ እነዚህ ሥር ናቸው፡፡ እነዚያ ሆድ እነዚህ ግን እጅ ናቸው፡፡ የነዚህ ጥቅማቸው ከምርቱ ሳይሆን ከቃርሚያው ነው፡፡ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በአፍ ቅልጥፍናቸው፣ በመመቻመች ችሎታቸው ከሚበሉት ይጠጉና ‘እባክህ ጌታዬ እንዲበላ ብቻ ሳይሆን በልቶ እንዲያተርፍም አድርገው’ እያሉ እየጸለዩ ይኖራሉ፡፡ እነዚያ የሚበሉት ምግብ ሲዘጋቸው የሚያባሉትን ይሰበስቡና ይጋብዟቸዋል፡፡ ታድያ እነዚህ መታ መታ እያደረጉ ሲበሉ የነዚያም የምግብ ፍላጎታቸው ይከፈትላቸዋል፡፡ ምናልባትም የሚበሉት ካልተስማማቸው የሚያባሉት ይታመሙላቸዋል፡፡
«አንድ ጊዜ አንድ ገበየሁ የሚባል ሰው በምኒሊክ ጊዜ ነበር አሉ»
«እ…………..ሺ» የሚል የቀልድ ምላሽ ከከበበው ሰው አገኘ፡፡
«እና ገበየሁ በወቅቱ ለነበሩት አቡን አገልጋይ ሆነና የተጣላውን ሰው ሁሉ እያስገዘተ እጅ እግሩን አሣሠረው፡፡ ይህንን ያዩ ያገሩ ሰዎች
ገብሽ መች ቀሰሰ ከየትስ አምጥቶ
ይወጋናል እንጂ ካቡን ተጠግቶ
ብለው ገጠሙለት አሉ፡፡
«’የሚያስበላ‘ የሚባለው ደግሞ የተሰጠውን ሥልጣን፣ ዕውቀት እና ኃላፊነት ተጠቅሞ የሚበሉትም እንዳይራቡ የማይበሉትም እንዲጠግቡ ማድረግ ሲገባው ‘ላለው ይጨመርለታል’ እያለ መሬቱን ሲቸበችብ፣ ግብር ሲቀንስ፣ ያልተፈቀደ ዕቃ ሲያስገባ፣ ሕገወጥ የሆነ መመርያ ሲያስተላልፍ፣ የሚውል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሀገር የሚያስበሉ ናቸው፡፡ ስሕተቱን፣ ጥፋቱን፣ ሕገ ወጥነቱን፣ ጉዳቱን፣ በኋላ ዘመን የሚያመጣውን መዘዝ እያወቁ እኔን ምን ቸገረኝ ብለው ለበይዎች የሚስማማውን ብቻ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነርሱም አይጠቀሙም፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሀገራቸው ማረሚያ ቤት ነው፤ እነሆ ነገ ግዳጃቸውን ሲፈጽሙ እንደ ሸንኮራ ተመጥጠው፣ እንደ ሙዝ ልጣጭ ተልጠው ይወድቃሉ፡፡»
የሚያብላላ‘ ይህ ደግሞ ለመብላት የሚያመች ሕግ ፣መመርያ፣ አሠራር እንዲዘረጋ የሚያደርግ፣ የሚበሉት አጋጣሚዎችን ሁሉ እንዲጠቀሙ መንገድ የሚያመቻች፤ ከበሉም በኋላ በተቻለ መጠን የበሉትም ፣አበላላቸውም ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው የሚያመቻች ነው፡፡ መንግሥት ለበጎ ብሎ የዘረጋውን አሠራር፣ ያወጣውን መመርያ እና ያዋቀረውን መዋቅር እርሱ እንዴት ለበይዎች እንደሚስማማ ያጠናል፣ ያመቻቻል፣ ያስፈጽማል፡፡ ከመመርያው እና ከአሠራሩ ጋር የሚሄድ ደረሰኝ፤ ዶክመንት፣ ማስረጃ፣ ያዘጋጃል፤ አበላሉን ያሳልጠዋል፡፡ እነዚህ የጨጓራ አሲድ ናቸው፡፡ የጨጓራ አሲድ የበላነውን እንዲዋሐደን አድርጎ ይፈጨዋል፣ያስማማዋል፡፡ እነዚህም እንደ ጨጓራ አሲድ ይፈጩታል ያስማሙታል፡፡
«አንተ ይህንን ትንቢት ከየት አመጣኸው» አሉት አንዲት እናት ገርሟቸው፡፡
«በዕብድነቴ ነዋ እናቴ፤ አዩ እዚህ ሀገር ካላበዱ በቀር ብዙ ነገር አይገለጥልዎትም፡፡ እንዲገለጥልዎት ከፈለጉ እንደ እኔ ማበድ አለብዎ፡፡ ለነገሩ እዚህ ሀገር ዕብዱ ብዙ ነው ግን ዓይነቱ ልዩ ልዩ ነው» አላቸው፡፡ «ደግሞ የዕብድ ምን ዓይነት አለው፤ ሁሉም ያው ነው» አሉት እኒያው እናት የነጠላቸውን ጫፍ ወደ ትከሻቸው እየመለሱ፡፡
«ተሳስተዋል፤ አዩ ይህም ቢሆን ካላበዱ በቀር አይታይዎትም፡፡ ብዙ ዓይነት ነው ዕብዱ፡፡ የመጀመርያው ያበደና ማበዱን እንደኔ የተረዳ ነው፡፡ ሁለተኛው አብዶ ማበዱን እያወቀ ግን ማመን የማይፈልግ ነው፣ እንደ ብዙዎቻችሁ፤ ሌላው አብዶ ግን ማበዱን ባለማወቁ የተምታታበት ነው፡፡»
«ቆይ አንተ ችግሩ ብቻ ነው የተገለጠልህ፤ መፍትሔውን አልገለጠልህም፤ ማበድህ ካልቀረ ለምን ከነ መፍትሔው አታብድም ነበር» አሉት እኒያ አረጋዊ፡፡
Filed in: Amharic