>

የወደብ ከተማዋ ምፅዋ/ባፅዕ/ እንዴት ተያዘች?!? (ዳንኤል እንግዳ)

የወደብ ከተማዋ ምፅዋ/ባፅዕ/ እንዴት ተያዘች?!?

ዳንኤል እንግዳ
የኢህዲሪ መንግሥት በኤርትራ ምድር በሚደረገው ጦርነት ምጽዋን የመከላከሉን ተግባር በአንደኛ ደረጃ እንዳስቀመጠው በዘመኑ የነበሩት ወታደራዊ አዛዦች ይናገራሉ፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምም ይህንኑ ሐሳብ ይጋራሉ ። በዚህም መሰረት ምጽዋ ከዋና ከተማዋ ከአስመራም ሆነ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አላቸው ከሚባሉት የከረንና የተሰነይ ከተሞች በበለጠ ሁኔታ ትታይ ነበር ማለት ነው ፡፡
ሰራዊቱ የመጨረሻውን መከላከል የሚያደርገው በምጽዋ ነው ተብሎ ተወስኗል ። ምጽዋን ለዚህ ደረጃ ያበቃት የወደብ ከተማ መሆኗ ነው፡፡ለሰራዊቱ የሚያስፈልገው ቀለብ ፣ ጦር መሳሪያ፣ መጓጓዣ፣የግንኙነት መሳሪያዎች፣የመለዋወጫ ቁሳቁሶች ወዘተ… ወደ ኤርትራ የሚገቡት በምጽዋ በኩል ነው፡፡ይሁንና የሰራዊቱ የመጨረሻ የመከላከያ ወረዳ ትሆናለች ተብላ የታሰበችው ምጽዋ ከሌሎቹ ከተሞች አስቀድማ በሻዕቢያ እጅ ወደቀች፡፡በዚህም ሁኔታ በሰራዊቱም ሆነ በመንግሥቱ ውስጥ ታላቅ ምስቅልቅል ተፈጠረ ፡፡
ለመሆኑ የምጽዋው ጦርነት ምን ይመስል ነበር? የአብዮታዊ ሰራዊት ሽንፈትስ እንዴት ተከሰተ? ከልዩ ልዩ ምንጮች በተገኘው መረጃ ላይበመመርኮዝ ታሪኩን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡ በቀይ ኮከብ አብዮታዊ ዘመቻ ወቅት የአስመራን ከተማ ዙሪያ ይጠብቅ የነበረው የመክት እዝ የስምሪት ጠገጉ ሰፍቶ ከአስመራ በስተ ምስራቅ ያሉትንም አውራጃዎች እንዲያካልል ተደርጓል፡፡
የመጠሪያ ስሙም “606ኛ ኮር” በሚል ተቀይሯል፡፡ በዚህ ኮር ስር አራት ክፍለ ጦሮችና ሶስተኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ይገኙ ነበር፡፡ የኮሩ ዋና መምሪያ የሚቀመጠው በአስመራ ከተማ ነው ፤ ሆኖም ዋነኛ ትኩረቱ የምጽዋን ከተማ ከጥቃት  መከላከል ነው፡፡ ታዲያ አብዮታዊው ሰራዊት ምጽዋን የሚጠብቃት በከተማው ብቻ በመመሸግ አልነበረም፡፡በከተማው ዙሪያ ከ50-80 ኪ.ሜ. ራዲየስ ላይ የሚገኘውን መሬት በድርብርብ ተዋጊ ክፍለ ጦሮች በማጠር ነው ከተማዋን ከሻዕቢያ  ለማትረፍ የተሰናዳው፡፡
በዚህ መሰረት ከምጽዋ በስተደቡብ ባለችው “ዙላ” የተሰኘች ጥንታዊት ወደብ አቅራቢያ ሁለት ተዋጊ ብርጌዶች ነበሩ፡፡ከምጽዋ ወደ አስመራ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለችው “ጋህተላይ” የተሰኘች መንደር ላይም ሶስትእግረኛ ብርጌዶችና አንድ ሜካናይዝድ ብርጌድ ነበር ፡፡ከምጽዋ በስተሰሜን ባሉት ሸዒብ እና “ሰለሙና” የተሰኙ ኩታገጠም መንደሮችም ላይ አራት ብርጌዶችና የ6ኛው ነበልባል ክፍለጦር ቀዳሚ መምሪያ ሰፍሯል፡፡በምጽዋ ከተማ ውስጥ ከአራት ብርጌድ የማያንስ ተዋጊ ጦር ነበር፡፡በዚህ ግንባር በርካታ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ተሰልፈው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ኃይልም በብዙ ባህር ወለድ ተዋጊዎችና የጦር ጀልባዎች ተጠናክሮ በምጽዋ ዙሪያ ከትሟል፡፡የ606ኛው ኮር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል እንግዳ ወልደአምላክ በግንቦት 8/1981 በተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል ተብለው በመከሰሳቸው ከቦታው ተነስተው ነበር ፡፡ በርሳቸው ምትክ የተሾሙት ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ነበሩ።የ3ኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ በነበሩት ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ ምትክም ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላሂ ተተክተው ነበር፡፡
606/ኛ ኮር በአዲስ ሁኔታ ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ግዳጅ አላጋጠመውም ፡፡ ሻዕቢያ በባህር ወለድ ኮማንዶዎቹ ምጽዋ ላይ አልፎ አልፎ ጥቃት እየከፈተ ጦሩን ለማስደንገጥ ያደረጋቸው ሙከራዎችም በባህር ሃይሉ እየከሸፉ ተመልሰዋል፡፡የካቲት8/1990 (ጥር 30/1982) ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡የወደብ ከተማዋ ምጽዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ እንቅልፍ ላይ ነበሩ፡፡በከተማዋና በከተማው ዙሪያ የሚገኙ የአብዮታዊ ሰራዊት አባላትም ሀገር ሰላም ብለው ሌሊቱን በጸጥታ እያሳለፋ ነው፡፡
የስድስተኛው ክፍለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ግን ሁኔታው ከብዶአቸዋል፡፡ከምጽዋ በስተሰሜን ባለው የሸኢብ ግንባር ሻዕቢያ አዘናግቶ ጥቃት ይከፍት ይሆናል የሚል የዘወትር ስጋት ነበራቸው፡፡ታዲያ በዚያች ደረቅ ሌሊት የፈሩት ነገር ደረሰ፡፡ ሻዕቢያ ከአፍአቤት ድል በኃላ ለአስራ ስምንት ወራት በቂ ቅድመ ዝግጅት ያደረገለትን ጥቃት በሸኢብ ከፈተ ያንን ተከትሎ የሬድዮ መልዕክት መጣላቸው፡፡ወዲያውኑ ወደ ማዘዣ ጣቢያቸው ሄደው ከግንባሩ አዛዥ ጋር ግንኙነት ፈጠሩ፡፡ ያለውን ሁኔታ ከተረዱ
በኋላ ረዳት ሀይል እስከሚላክላቸው ድረስ ጠንክረው እንዲዋጉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ከዚያ በመለጠቅም አስመራ ለሚገኙት የ606ኛው ኮር አዛዥ ለብ/ጄ/ጥላሁን ክፍሌ ስልክ ደወሉ፡፡ ሆኖም ጄኔራሉን ሊያገኟቸው አልቻሉም ፡፡ በርሳቸው ፈንታምለሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ ለነበሩት ለሜ/ጄ/ ሑሴን አሕመድ በመደወል ሁኔታውን አስታወቁ፡፡
ጄኔራል ሑሴንም ረዳት ጦር እስከሚላክላቸው ድረስባለው ሀይል ሁኔታውን ለመቆጣጠር እንዲሞክሩም አዘዙ ፡፡ጀኔራል ተሾመ በዚያች ቅጽበት በምጽዋ ዙሪያ የነበሩት የብርጌድ አዛዦች ጦሯቸውን ለጠዋት እንዲያዘጋጁ ነገራቸው ፡፡ንጋት ላይም ከረዳቶቻቸው ጋር ወደ ውጊያው ቦታ ተንቀሳቀሱ፡፡ሆኖም ያዩት ነገር ከጠበቁት ውጪ
ሆነባቸው፡፡ሻዕቢያ የሰለሞና ግንባር ከፍተኛ ጥቃት በመክፈቱም በአካባቢው በነበሩት ተዋጊ ብርጌዶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ተረዱ ፡፡የሰራዊቱ ብርጌዶችም ከሰለሞና በማፈግፈግ በምጽዋ አስመራ መንገድ ላይ ወደምትገኘው ጋህተላይ እያፈገፈጉ እንደሆነ ለማወቅ ቻሉ፡፡
ጄኔራል ተሾመ ከቃኚዎች በደረሳቸውም መረጃ የሻዕቢያ ግብ የምጽዋ-አስመራን መንገድ መቁረጥ ሊሆን እንደሚችል ገመቱ ስለዚህ ሻዕቢያን በዚህ መስመር ገትረው ለመያዝ ወሰኑ፡፡በአካባቢውም የነበሩት ብርጌዶች ለመከላከል ቢሞክሩም የሻዕቢያን የግስጋሴ ፍጥነት ለመቆጣጠር ሳይቻል ቀረ፡፡ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ቀኑ10፡00 ድረስ ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ሻዕቢያ “ጋህተላይ”ን ተቆጣጠረ፡፡የአስመራ-ምጽዋ መንገድም በእጁ ወደቀ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ለሁለት ተቆረጠ፡፡ የሰራዊቱ አዛዦች ሻዕቢያ በያዘው ይዞታ ብቻ ተብቃቅቶ የሚገታ መስሎአቸው ነበር፡፡በዚህም የተነሳ ረዳት ጦር እስከሚደርስላቸው ድረስ “ዶጋሊ” የተሰኘችውን ታሪካዊ አምባ በመያዝመከላከልን መረጡ፡፡
ሆኖም ሻዕቢያ ግስጋሴውን አልገታም፡፡ዋናውን ጎዳናተከትሎ ሰራዊቱን ከኋላው እየተከታተለ ወጋው፡፡ሰራዊቱ በዶጋሊ ላይ እልህ አስጨራሽ ትንንቅ አደረገ፡፡
ሻዕቢያም በዚያች ቀን ምጽዋን ከመያዝ ተገታ፡፡ ከጋህተላይ ወደ ምዕራብ የተንቀሳቀሰው የሻዕቢያሰራዊት ግን ምሽቱ ከመድረሱ በፊት የደንጎሎን አነስተኛ መንደር ተቆጣጠረ ከዚያም አልፎ ወደ አስመራ የቀረበችውን የጊንዳዕ ከተማ ለመያዝ ከፍተኛ ውጊያ ከፈተ። ይቀጥላል …..
Filed in: Amharic