>
10:52 am - Wednesday December 7, 2022

“ንባብ ይገድላል፤ትርጓሜ ያድናል!!!” (ዉብሸት ሙላት)

“ንባብ ይገድላል፤ትርጓሜ ያድናል!!!”

ዉብሸት ሙላት
በሕግ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች የሕግን አተረጓጎም (Interpretation) ይማራሉ፡፡ በአንዳንድ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች አተረጓጎም ራሱን ችሎ እንደ አንድ ትምሕርት ይሰጣል፡፡ 
 
ትርጉም ማለት ምንድን ነው? 
 
ትርጉም ለምን ያስፈልጋል? 
 
ምን ምን ችግር ሲያጋጥም ነው ትርጉም የሚያስፈልገው?
 
 የአተረጓጎም ኀልዮቶች ምን ምን ናቸው? 
 
የአተረጓጎም መርሖች ምን ምን ናቸው? 
 
የትርጉም ዓላማዎች (ግቦች)  ምን ምን ናቸው? ወዘተ የሚሉ ይዘቶች የትምሕርቱ አካል ናቸው፡
በሕግ ትምሕርት ቤት እንደ ትምሕርቶቹ ዓይነት የአተረጓጎም መርሖቹና ኀልዮቶቹ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ሕገ መንግሥት የሚተረጎምበት ሥልት  የወንጀል ሕግ የሚተረጎምበት ይትባሃል የፍትሐ ብሔር ሕግ ወይም ጉዳይ ከሚተረጎምበት የሚለዩበት ገጽታዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል በወንጀል ሕግ በምስስል () ትርጓሜ መስጠት አይቻልም፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ግን ይቻላል፡፡  በምስስል ትርጉም የሚሰጠው በሕግ በግልጽ የተደነገገ አንቀጽ ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡
በእኛ አገር ዩኒቨርሲቲዎች አተረጓጎም ራሱን ችሎ እንደ አንድ የተለየ ትምሕርት ባይሰጥም ቅሉ፣ በጥቅሉ “Introduction to Law” ከዚያ በመቀጠል የአተረጓጎም ደንብ ያላቸው ሕጎችና ትምሕርቶች (ለምሳሌ፡- የውልና የወንጀል ሕጎች) ስላሉ በእነሱ ውስጥ ተካትቶ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባለፈ ትምሕርትን ወይም የሕግ ዘርፍን ወይም ድንጋጌን መሠረት ያደረጉ ስለ አተረጓጎም የተዘጋጁ ድርሳናት ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ወደ በይነ መረብ ገባ ብሎ ብዛቱን መታዘብ ይቻላል፡፡
ሕገ መንግሥትም እንደ አንድ የሕግ ዓይነት ከሕግ አተረጓጎም ምንነት፣ግብ፣አስፈላጊነት፣ መርሕና ኀልዮት የሚጋራቸው እንዳለ ሁሉ ልዩ ገጽታዎችም አሉት፡፡ የየአገራቱ ሕግ (ሕገ መንግሥትንም ጨምሮ) ከሌሎች አገራት ሕግጋት የሚጋራቸው (በተለይ የሕግ ሥርዓትን መሠረት አድርጎ) ጠባዮች ቢኖሩትም የሚለይበትም ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡
አሁን ያለው የኢትዮጵያ (የፌደራሉ) ሕገ መንግሥትም እንዴት እንደሚተረጎም፣ ማን እንደሚተረጉመው፣ ትርጉም መቼ እንደሚያስፈልግ በራሱ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች አዋጆችም ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥቱ ትርጉም እንደዚህ ነው እንደዚያ ከማለት አስቀድሞ መታወቅ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡
የሕግ ትርጉም ከሚያስፈልገባቸው ጊዜያት አንዱ የሕግ ክፍተት መኖር ነው፡፡ ግልጽ ያልሆነ (Vague)፣አሻሚ (Ambiguous)፣ የሚጣረስ (Inconsistent) ቃል፣ ሥረይ (term)፣ ድንጋጌ ወዘተ ሲጋጥም የትርጉም አስፈላጊነት ብቅ ይላል፡፡ ልክ እንደነዚህ ሁሉ የሕግ ክፍተት (Lacuna) ሲያጋጥምም በትርጉም ይሟላል፡፡ እንዴት እንደሚተረጎምም የሚጣወቁ መርሖች አሉ፡፡
ጃዋርና ልደቱ ባደረጉት ውይይትም ሁለቱም ባወቁትም ባለወቁትም መጠን ሲተረጉሙ ነበር፡፡ የአተረጓጎም ሥልትና ለትርጉም የሚውሉ ይትባሃሎችን ለማንሳት ሞክረዋል፡፡ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ሕገ መንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት አርቃቂዎቹ እነ ክፍሌ ወዳጆ፣ ፓርላማው ከአምስት ዓመት የሥራ ዘመኑ በምንም መልኩ ማራዘም እንደማይችል አስበውበታል እያሉ ተናግረዋል፡፡ እንዳሰቡበትም ወይም እንዳላሰቡበትም በቃለ ጉባኤያቸው ላይ አልገለጹም፡፡ እነ ጃዋር በተረዱት መጠን ትርጓሜ ሰጡት እንጂ፡፡
ይሁን እንጂ፣ ሕገ መንግሥትንም ይሁን ሕግን፣ ለሕግ Ordinary/Lay man የሆነ ሰው ተረጎምኩት የሚለውን እንደ ትክክለኛ ትርጉም መውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕግ ትምሕርት ቤት፣ ድግሪ ለመያዝ፣ አምስት ዓመት መማር የሚያስፈልገው ሕጎቹን ለማንበብ ሳይሆን እየተረጎሙ ለመረዳትና ለማስረዳት ነው፡፡ ጃዋር ሲናገር… የብዙ አገራት ሕገ መንግሥቶችን አንብቤያለሁ እያለ ነበር፡፡ አንብቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ካወራሩ ግን ማንበቡን መገመት አልቻልኩም፡፡ ቢያነብም እንዴት እንደሚነበብ ያወቀ አይመስልም፡፡ አቶ ልደቱም እንደዚያው ነው፡፡ ትሕነግም ባወጣችው መግለጫ የምርጫው መራዘም ወይም አለመራዘምን በሚመለከት ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ አያስፈልገውም በማለት ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም ሞክራለች፡፡
የሕገ መንግሥት ትርጉም የግድ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠን፣በሌላ ሕግ ወይም አሠራር ላይ ያጋጠመን ችግር (ግልጽ ያልሆነ፣አሻሚ፣ የሚጋጭ፣የሚጣረስ) በማብራራት ፍቺ ለመስጠት እንደሚተረጎመው ሁሉ፤ በሕገ መንግሥት ወይም በሕግ የሌለን፣ ነገር ግን ነባራዊ ሁኔታ የወለደውና ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ የሚፈለግን ጉዳይ እልባት ለመስጠት ድርጊቱ ከተከሠተ በኋላ  በ Concrete Review አልበለዚያም አስቀድሞ   በ Abstract Review ትርጉም ይሰጣል፡፡
የሌሎች አገራት ልማድ እንተወውና የእኛኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ታሪክ ለዚህ ዋቢ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የማንነት ጥያቄን ማን ይወሰን የሚለው በግልጽ አልተደነገገም፡፡ በግልጽ ስላልተደነገገ ማን፣ ግልጽ ሕግ ስለሌለ፣ በወቅቱ ጥያቄ የነበረው የየስልጤ የማንነት ጉዳይን እንዴት መወሰን እንዳለበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ግልጽ ድንጋጌ ስለሌለ፣ የስልጤ ብሔረሰብ ለማንነቱ እውቅና የሚያገኝበት ሥርዓት የለም በሚል ጥያቄያቸው ውድቅ አልተደረገም፤ አይደረግምም፡፡
ሌላው ምሳሌ፣ የፌደራሉ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ (በሁሉም ክልሎች) ዘንድ ተፈጻሚ የሚሆን የቤተሰብ ሕግ የሕዝብ ተወካዮች ማውጣት እንደሚችል ወይም እንደማይችል የፌደሬሽን ምክር ቤትን ችግር ከማጋጠሙ በፊት ጠይቆ ነበር፡፡ በከአንድ ሁለት ዓመታት በፈትም ስለ ከተማ መሬት ወይም የከተሞች አዋጅ (እርግጠኛ አይደለሁም) የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ስለ ሕገ መንግሥታዊነቱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መርቶት ነበር፡፡
በአጭሩ፣ የሚጠረስ፣የሚያሻማ፣ ግልጽ ያልሆነ ቃል፣ሥረይ ወይም ሕግ ሲያጋጥም ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት ሲያጋጥምም ቢሆን የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በፍርድ ቤት ወይም በባለ ጉዳዩ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሌሎችም ችግር ከመድረሱ በፊት የሕገ መንግሥታዊነት ማረጋገጫ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሊጠየቅ ይችላል፡፡
በጠቅላላው፡-
መተርጎም ቀለላል ነገር አይደለም፡፡ በአገራችን እንኳን የመጽሐፍት ትርጉም የሚሠጥባቸው በርካታ አብያተ ክርስጢያናት አሉ፡፡ የትርጓሜ ትምሕርት ካላቸው አንዱ ፍትሐ ነገሥት ነው፡፡ ያነበበ ሁሉ የፍትሐ ነገሥት አዋቂ አይሆንም፣አይባልምም፡፡ School of Thoughts (መዝሃብ) ሲለያይ ትርጉሙም ሊለያይ ይችላል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮት የላይ ቤትና የታች ቤት አተረጓጎሞች አሉ፡፡  በእስልምናም ሃናፊ፣ሐንበሊ፣ ሻፊ ወዘተ የሚባሉ አሉ፡፡ አንዱ ንባብ የተለያየ መዛሒብ የሚከተሉ ሊቃውንት  ወይም ፊቅኽ (Fiqh) የተለየ ፍቺ ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ትርጉም ሰጪዎቹ በትምሕርቱ ያለፉና ዕውቀታቸውን ያደላደሉ ናቸው፡፡ ለሕግ ትምሕርት ጨዋ ወይም ጃሂል የሆነው ሳይሆን ሕግ የሚያውቅ ነው፡፡
በሥነ መለኮት ስለ አተረጓጎም/አንድምታ /Hermeneutics/ ትምሕርት ሲሰጥ አብነት ሆና የምትነሳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አለች፡፡ የትርጉምን አስፈላጊነት ለማስረዳት፡፡ ከንግሥተ አዜብ (ሕንደኬ) ጋር በጃንደረባነት ወደ ኢየሩሳሌም ደርሲ ሲመለስ ጃንደረባው ሰረገላ ላይ ሆኖ የኢሳይያስን ትንቢት ገልጦ እያነበበ ሳለ ወንጌላዊው ፊልጶስ “የምታነበው ይገባሃልን?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሳይኖር እንዴት ይገባኛል?” በማለት መለሰለት፡፡ ታሪኩን በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ሥራ ላይ ማንበብ ነው፡፡
ቁምነገሩ ማንበብ ብቻውን በቂ የማይሆንባቸው ጽሑፎች አሉ፡፡ ቢያንስ እንዴት እንደሚነበብ መማር የሚጠይቁ አሉ፡፡ ከእነዘህ መካከል አንዱ ሕግ ነው፡፡ ሕግ ላወጡት የፓርላማ አባላት እንኳን ቢሰጣቸው (በተለይ የሕግ ትምሕርት ከሌላቸው) መተርጎም አይሆንላቸውም፡፡ ምክንያቱም፣ ሕግ እንዴት እንደሚተረጎም ማውቅን ይጠይቃል፡፡ ካልሆነ፣ ንባብ ብቻውን ዋጋቢስ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ እስመ ንባብ ይቀትል፣ የትርጓሜ ይሐዩ ይላሉ ሊቃውንትም መጽሐፉም፡፡ ወደአማርኛ ሲመለስ፣ “ንባብ ይገድላል፤ትርጓሜ ያድናል” ነው፡፡
ለማንኛውም Purposeful Interpretation የሚባል እንዳለም ሌላ ጽሑፍ ማንበብ ለደከመው የዶ/ር ፋሲል ናሆምን መጠየቅ በቂ ነው፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት አተረጓጎም የዛሬ ስንት ዓመት ለኢሕዲጎች የጻፈው article ቢጤ ይመስላል፡፡
(አሳዛኙ ነገር በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ትርጓሚው የወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም ተቋም፣ ገና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተጣበው ጥንተ አብሶ (Original Sin) ያለበት መሆኑ ትርጓሜን ብላሽ ያደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግ በነበረበት ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱ ዋርዲያ/ጠባቂና ተርጓሚ ነው እየተባለ ሲደለቅ ከነበረ አሁን ትሕነግ ከኢሕአዴግ ተባርራ መቀሌ ስትከትም፣ ኢሕአዴግም ወደ ብልጽግና ሲለወጥ፣ የፌደሬሽን  ምክር ቤት ሕገ መንግሥት መተርጎም እንደማይችል ያዙኝ ለቀቁኝ ማለት….. ቸጋራ ነገር ነው፡፡)
Filed in: Amharic