>
5:16 pm - Sunday May 24, 5361

አቶ ልደቱ አያሌው የጣሉት ነጥብ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

አቶ ልደቱ አያሌው የጣሉት ነጥብ…!!!

አቻምየለህ ታምሩ
አቶ ልደቱ አያሌው  ከአንዳፍታ ሜዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኢሳያስ አፈወርቂ ይልቅ ጃዋር መሐመድና ደብረ ጺዮን ገብረ  ሚካኤል እንደሚቀርቡት ተናግሯል። ይህ የአቶ ልደቱ አስተሳሰብ በምክንያታዊነት ሲፈተሽ ትክክል አይደለም። በጃዋር ልብ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ በኢሳያስ አፈወርቂ እእምሮ ውስጥ ካላችዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ አይነት ናት፤ በደብረ ጺዮን ልብ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያም  በኢሳያስ አፈወርቂ  አእምሮ  ውስጥ ካለችዋ  ኢትዮጵያ ጋር አንድ አይነት ናት።
ኦነግ የሚባለው አሸባሪ ድርጅት መሪ የሆነው ዳዎድ ኢብሳ በሻዕብያ ተመልምለው ለኦነግ ተዋጊነት በኢሳያስ ቅርብ  ክትትል ከሰለጠኑት  የኦነግ የመጀመሪያ ዙር ታጣቂዎች መካከል ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ የጃዋር የመንፈስ አባቶች [Godfathers] አባትና አሳዳጊ ነው። ለነደብረ ጺዮንም ደግሞ ኢሳያስ አፈወርቂ የመንፈስ  አባት፣  አሳዳጊና  ሱሪ ያስታጠቃቸው ብቻ ሳይሆን ፈጣሪያቸውም ጭምር ነው። ባጭሩ ጃዋርና ደብረ ጺዮን ልብ ውስጥ የተተከለችው ኢትዮጵያ በኢሳያስ አፈወርቂ አእምሮ የተፀነሰችው ኢትዮጵያ ናት።
ስለዚህ አንድ ሰው ነገር አለሙ ካልተምታታበትና  ከምክንያታዊነት ውጭ ካልሆነ  በስተቀር በምክንያታዊነት እየተመራ  ለሚያስብ ሰው አባትዮውን ወይም ፈጣሪውን  ጠልቶ የመንፈስ ልጆቹንና ፍጡራኑን ሊወድ ወይም ሊመርጥ አይችልም። አቶ ልደቱ  በጣለው ነጥብ ያደረገው ይህንን ነው። አቶ ልደቱ ጃዋርና ደብረ ጺዮን ይቀርቡኛል ያልሁት  በጥላቻ ሳይሆን በምክንያታዊነት የሚል ከሆነ  የመንፈስ አባታቸውንና ፈጣሪያቸውን ኢሳያስ አፈወርቂን ጠልቶ የመንፈስ ልጆቹንና ፍጡራኑን እነ ጃዋርንና ደብረ ጺዮንን የወደደበትን ምክንያት ማስረዳት ይኖርበታል።
ሌላው ቢቀር አቶ ልደቱን ያህል  ፖለቲከኛ  በቅርቡ  እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. ጃዋር  መሐመድ  «የኦሮሞ  ምሁራንና ብሔርተኞች ጉባኤ» በሚል በአትላንታ ጆርጅያ ባካሄደው ጉባኤ  ኢሳያስን መሆን እንደሚመኝ ያወጣውን መግለጫ  ከመቼው  ረሳውና ነው ከኢሳያስ ይልቅ ጃዋር ይቀርበኛል ሊል የቻለው? ጃዋር ጽፎት በአትላንታው ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የቀረበው የአቋም መግለጫ ላይ ስለ ኦሮሞ ትግል ግብ ሲያብራራ “ኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለነጻነት የሚበቃ፤ እንደኤርትራ፤ ትግሬና ደቡብ ሱዳን መሆን አለበት!” ብሏል። ጃዋር በወቅቱ ይህንን መግለጫ ሲያወጣ “ቸር ተመኝ! ቸር እንድታገኝ!”  ብለነው ነበር። ይህ ፈረንጆቹ “ለከዋክብቱ አነጣጥር ብትስት እንኳን የባሕር ዛፉን አናት ትመታለህ!” (Aim to the Stars! If you miss, You Will Hit the Top of the Tree!” እንደሚሉት አይነት ነው። ጃዋር ለመሆን የተመኘው ኢሳያስ ኢሳያስ መላው ዓለም ማዕቀብ አድርጎበት፣ ከዛሬ ነገ የዓለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባል እየተባለ የሚባንነውን ጉድ ነው። ጃዋር ለመሆን የተመኘው ደቡብ ሱዳን የሚባለው አገርም  የከሸፈ አገር (failed State) ነው።  እንግዲህ አቶ ልደቱ ከኢሳያስ ይሻለኛል የሚልለት ጃዋር ኢሳያስን  አፈወርቂን ለመሆን የሚመኘውን ጉድ ነው።
ወሎዬው አቶ ልደቱ ከኢሳያስ ይልቅ ጃዋር ይቀርበኛል ያለው በአገር ልጅነት ከሆነ ከአርሲው ጃዋር መሐመድ ይልቅ የወሎየዋ የተመኙ ሚካኤል የልጅ ልጅ ኢሳያስ አፈወርቄ ይቀርበዋል። የተመኙ ሚካኤል የንጉሥ ሚካኤል ልጅና የልጅ ኢያሱ እኅት ናቸው። የኢሳያስ አያት፣ የአፈወርቂ አብርሃ አባት ደጃዝማች አብርሃ የኢሳያስን አባት አቶ አፈወርቂን የወለዱት የልጅ ኢያሱን እኅት ወሎዬዋን ወይዘሮ የተመኙ ሚካኤልን አግብተው ነው።
ስለዚህ ኢያሳይ ባይቀበለውና ልክ እንደ ጃዋር ኢትዮጵያዊነት ተጭኖብኛል ብሎ የታገለ ቢሆንም  አቶ ልደቱ ጃዋርን ለማቅረብ የተጠቀመበት መመዘኛ የአገር ልጅነት ከሆነ  ለወሎዬው አቶ ልደቱ ከአርሲው ጃዋር መሐመድ ይልቅ የወሎዬዋ የተመኙ ሚካኤል የልጅ ልጅ ኢሳያስ አፈወርቂ ይቀርበዋል። በነገራችን ላይ የኢሳያስ ቅድመ አያት የደጃዝማች አብርሃ አባት ደጃዝማች ሐጎስ ምርጫ የደጃዝማች ካሳ ምርጫ ታላቅ ወንድም ናቸው። ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የኋላው ዐፄ ዮሐንስ እንደሆኑ ልብ ይሏል! ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብሎ የታገለው ኢሳያስ አፈወርቂ ከሁላችንም በላይ  በሁለቱም  በኩል ኢትዮጵያን ከመሩት  ነገሥታት  ተወልዶ ነው።
Filed in: Amharic