>

"እንወያይ እንደራደር ማለት ከመቼ ወዲህ ነው የጦርነት ግብዣ የሆነው?" (ጃዋር ለጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጠ - ህብር ራድዮ)

እንወያይ እንደራደር ማለት ከመቼ ወዲህ ነው የጦርነት ግብዣ የሆነው?”
ጃዋር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጠ 
ህብር ራድዮ
 
* “ሊታረም የሚገባው እና የማይሰራ ወታደራዊ ማስፈራሪያ ነው!”
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አዳመጥኩት።  በግሌም ሆነ እንደ ፓርቲ መባል ያለበትን ከዚህ በፊት ስለተናገርን አጭር አስተያየት ብቻ ልስጥ
1. ነገሮችን ከሚገባው በላይ ማጋጋል (escalate ማድረግ) ለማንም የሚጠቅም አይደለም። አሁን የተከተልነውን ህገመንግስታዊ ትርጉም የመጠየቅ መፍትሄ የመረጥነው የተለያዩ የድርሻ አካላትን ካሳተፍንና ካወያየን በኋላ ነው የሚለው እውነት እንዳልሆነ እራሳቸውም ያውቁታል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጀንዳ ሳይነገራቸው ተጠርተው  በተሳተፉበት  ስብሰባ መንግስት የራሱን አማራጮች አቀረበ እንጂ ሌሎች አማራጭ ሃሳቦችን ለመመልከት ፍቃደኛ አልነበረም፤ በተጨማሪም ስብሰባውን የጠራው አሁን ገሃድ ያደረገውን መፍትሔ የገዢው ፓርቲ ማዕከላዊ ከወሰነ በኋላና ይህን ውሳኔውን በይስሙላ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ በእውነት ትክክለኛ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረው የተሻለ የሚባለውን አማራጭ ለመከተል አልነበረም። ይህም የቀድሞውን የኢህአዴግ ”ወስኖ የማሳወቅ” (fait accompli) ባህል ያስቀጠለ ነው።
2) በኮቪድ-19 ምክንያት የምርጫን መተላለፍ የተቃወመ የፖሊቲካ ድርጅትም ሆነ አመራር እስካሁን አልሰማሁም (በህወሃት በኩል ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸው እንደጠበቀ ሆኖ)።
3) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዛኛው ንግግራቸውን ያሳለፉት የሽግግር መንግሥትን ሀሳብ በመተቸት ነው። አከራካሪው ጉዳይ ሕገመንግሥቱ ስለምርጫ ማስተላለፍ እና ማራዘም ምንም ያለው ነገር ስለሌለ ምርጫው እንዴት መተላለፍ እንዳለበትና አዲስ ምርጫ ማካሄድ እስኪቻል መንግሥት እንዴት መተዳደር እንዳለበት ድርድር እና ውይይት ያስፈልጋል ነው። እንደ መፍትሔ አንዳንድ ድርጅቶች የሽግግር መንግሥት፣ ሌሎች የባላደራ መንግሥትን ሲጠቅሱ ሰምተናል። አብዛኞቹ ግን እስካሁን በዚህ ላይ አቋማቸውን አልገለፁም። ሁሉም ድርጅቶች በጋራ እየጠየቁ ያሉት የምክክር እና የድርድር መድረክ ይዘጋጅ ነው። እዛ መድረክ ላይ የየድርጅታቸውን ፕሮፖዛል አቅርበው አስማሚ የሆነው ይተገበራል።
4) በሕገመንግሥት ጉዳይ ላይ ምንም ምርምር ያላደርጉ ሰዎች ናቸው የገዢውን ፓርቲ የሕገመንግሥት መተርጎም አካሄድ የተቃወሙት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። አዎ አብዛኞቻችን የሕገመንግሥት ጥናት ባለሙያዎች አይደለንም። ነገር ግን ልክ እንደ ገዢው ፓርቲ የሕግ አማካሪዎች አሉን። የያዝነውም አቋም የባለሙያዎችን ምክር ሰምተን የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ እና የድርጅቶቻችንን ፖሊሲ አገናዝበን ነው። የውይይቱ ቀን አጀንዳ አስቀድሞ ቢነገረን ኖሮ እኛም እንደ ገዢው ፓርቲ የህግ አማካሪዎቻችንን ይዘን ለመምጣት ያስችለን ነበር። በነገራችን ላይ የሕግ ባለሙያዎች የተስማሙበትን ጉዳይ የፖለቲካ መሪዎች ለውይይት መቅረባቸው ስህተት ነው እንዳሉ ተደርጎ መቅርቡ ትክክል አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ባለፉት ሳምንታት በእውቅ የሕግ ባለሙያዎች ሰፊ ክርክር በማኅበራዊ ሚዲያ እና በጋዜጦች ሲካሄድ ከርሟል አሁንም ቀጥሏል። Addis Standard, Ethiopia-Insight, Addis Fortune, etc ማየት ይቻላል። ገዢው ፓርቲ ያቀረባቸው አራት አማራጮች ከመቅረባቸው በፊት ሰፊ ክርክር ሲካሄድባቸው ነበር። ሆኖም ግን በአንዱም ላይ ስምምነት አልተደረሰም። እኛም አስማሚ የሆነ አንቀጽ በሕገመንግሥቱ ስለሌለ የፖሊቲካ አመራሩ መግባባት አስፈላጊ ነው ያልነው ለዚህ ነው።  አይደለም ግልጽ እና አስገዳጅ ለሆነም የህገመንስት ቀውስ፤ የሀገራችንን ፖሊቲካ ሁኔታ ባጠቃላይ ከአዙሪት ለማውጥት ሀገራዊ ውይይት እና ድርድር ወደር የለሽ አማራጭ ነው።
5) ጠቀላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ስልጣን ሀገመንስታዊ ባለሆነ መንገድ መያዝ ፈጽሞ የተከለከለ ነው  ብልዋል ። ትክክል ነው። በተመሳሳይ መልኩ ህገመንስታዊ ባልሆነ አሰራር የስልጣን ጊዜን ማስረዘምም  የተከለከለ ነው። ህገመንስቱ ምርጫን ስልማስተላለፍ እና የስልጣን ዘመንን ማራዘም ምንም ያለው ነገር በሌለበት በገዢው ፓርቲ በተሞሉ ምክርቤቶች ‘ህገመንስት አስተርጉሞ’ የስልጣን ዘመንን ማራዘም ኢሀገመንስታዊ ነው የምንለውም ለዚሁ ነው።
6) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው መንግስት ቅቡለንት ያለው ነው ሲሉ አንድ የዘነጉት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። ይሄውም ይህ ገዢ ፓርቲ ቅቡልነት ማጣት ብቻ ሳይሆን በህዝብ አመጽ ተሽነፎ፣ ቅቡልነት ማጣቱን አምኖ፤ ከንግዲህ እለወጣለሁ ሀገርምን ወደዲሞክራሲ አሻጋግራለሁ በሎ ቃል የገባ ነው። አሁን ያለው ፓርቲ ለ 27 አመታታ ህዝብን ያሰቃየ አምባገናዊ  ‘ አሸባሪ’ መንግስት  እንደነበር እኮ በግልጽ በፓርላማ የነገሩን እኝሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ታዲያ ከዛ ወዲህ ምርጫ ተካሂዶ ነው አዲስ ቅቡልነት የተጎናጸፈው? አሁን ያሉን የፌደራል እና የክልል ምክርቤት አባላት እኮ የዛው ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም በማያሻማ መልኩ ቅቡልነት የነፈጉት ፓርቲ ተመረጮች ናቸው።   ልድገመው ይህ ፓርቲ በተጨበረበረ ምርጫ በተመረጠ በወራት ውስጥ ህዝብ አምጾበት ለ4 አመታታ ከፍተኛ መስዋትነት ያስከፈለ ትግል ተሸንፎ፤ እጅ ጸጥቶ ከጊዜው   ነበራዊ ሁኔታ አንጸር እስከ ምርጫው ድረስ በባለደራነት እንዲቀጥል  የተፈቀደለት መንግስት ነው። ይህን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቱን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት በተደጋግሚ ሲሉት የነበር ነው።
7)  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻ ላይ ስለ ወጣቶች ደም መፍሰስ እና መንግሥት አስፈላጊውን የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ መግለፃቸው ምንም አይነት አግባብነት የሌለው እና አፍራሽ አባባል ነው። ለምንድነው የወጣቶች ደም መፍሰስ ጋ የሚኬዴው? ምንስ ሲሆን አሰቡት? የተጠየቀው ለተፈጠረው ቀውስ በውይይት እና ድርድር መፍትሔ እንፈልግ ነው። እንወያይ እንደራደር ማለት ከመቼ ወዲህ ነው የጦርነት ግብዣ የሆነው? ይህ አካሄድ ትችትን እና ክርክሩን ለማስቆም የተደረገ ማስፈራሪያ ከሆነም ትክክል አይደለም። ሊታረም ይገባል። አይሰራምም።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲሞክራሲ እሴቶችን ማጎልበት አስፈላጊ እንደሆነ በአጽዕኖት ተናግረዋል። እነዚያን እሴቶች ማዳበሪይው ዋናው መንገድ በዜጎች እና አመራር መካከል የሚደረግ ትችት፣ ክርክር እና ድርድር ነው። ትችት እና ክርክርን ለማስቆም የሚደረግ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እነዚያን የዲሞክራሲ እሴቶች ለማቀጨጭ እንጂ ለማጎልበት አይረዳም። ይህ ለውጥ ሺዎች ህይወታቸውን ገበረው ያስገኙት ወደ ተሻለ ነጻነት እና ዲሞክራሲ እንድነሸጋገር መሆኑን ሁሉም ለ አንዲት ሰኮንድ  መርሳት የለበትም።
 8) ፓርቲያቸው ሰፊ ቅቡልነት እንዳለው እና የሚቀጥለውን ምርጫ እንደሚያሸንፍ ጥርጥር የለውም ብለዋል። ከሆነ እሰየው ነው። እንደዚያ ዓይነት በራስ መተማመን ካለ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማሰር፣ ማሳደድ፣ ማስፈራራት እና ማፈናቀልን ምን አመጣው? ነፃ እና ሰላማዊ በሆነ ምርጫ እንወዳደር፤ በዝረራ አሽንፉን እና ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን እንደተቃዋሚ እንቀጥላለን። ምርጫው እስኪካሄድ ግን ምርጫውን በማስተላለፊያ እና የመንግሥትን የሥራ ዘመን ማራዘሚያ ጉዳይ ላይ አሁንም ተወያይተን መግባባት አለብን እንላለን።
Filed in: Amharic