>
5:13 pm - Friday April 19, 9033

ሚያዚያ 30 እና አሰፋ ማሩ (ብሩክ አበጋዝ)

ሚያዚያ 30 እና አሰፋ ማሩ

ብሩክ አበጋዝ
ከቤቱ በጧት ወጥቶ በመለስ ዜናዊ አፋኝና አልሞ ተኳሽ ገዳዮች በጥይት ተመትቶ በዚያው ያሸለበው፣ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ከሰሜን ወሎ መቄት ወጥቶ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ዋና ጸሀፊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ የቦርድ አባል እስከ መሆን የደረሰው፣ ለኢትዮጵያውያን መብት ተሟጋች የነበረው አሰፋ ማሩ አገዳደል ሁኔታ፤ የትህነግን ቅጥ ያጣ እበሪት ከሚያስረዱ እና በግሌ በጣም ከሚያንገበግቡኝ መካከል ነው።
አቶ አሰፋ ማሩ በጊዜው በወሎ ክፍለሀገር በላስታ አውራጃ መቄት ወረዳ በ1951 ተወለደ። በመምህርነት ሙያ ከማገልገሉም ባሻገር በሙያ ማህበሩ የአመራር አባል በመሆንም የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ፣ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል በግምባር ቀደምትነት ከሚታገሉት አንዱ ሆኖ ሕይወቱ በግፈኞች እስካለፈበት ዕለት በጽናት ቆሞ ቆይቷል። በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የላቀ ድርሻ አበርክቷል።
ስለ አሰፋ ማሩ ድሮ ከነበረኝ በላይ ይበልጡን ያንገበገበኝ የዛሬ 2 ዓመት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ስድስት ኪሎ፣ ኬነዲ ላይብረሪ ስለ ላስታ የመሬት ስሪት ጉዳይ ያጠናውን ማለፊያ የሆነ ጥናቱን ካየሁ በኋላ ነው። አሰፋ መብት ተሟጋች ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተመራማሪ ሙህር ነበር።  ሚያዚያ 30ን ስናስብ ይህንን በጠራራ ፀኃይ በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ  በወንበዴ ጥይት ተደብድቦ ህይወቱ ያለፈችውን ውዱን ኢትዮጵያዊ እናስታውሰው።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፀሀፊና የቀድሞው ኢሰመጉ ስራ አስፈፃሚ አባል የነበረው አቶ አሰፋ ማሩ ሚያዝያ 30 1989 ዓም ማለዳ የዓመት ከምናምን የሆነው እምቦቃቅላ ልጁን፤ ደሟ ጠፈፍ ያላለ አራስ ሴት ልጁንና የሚወዳት የህይወት አጋሩን ተሰናብቶ ከእጁ የማይለየውን ሳምሶናይት አንጠልጥሎ ለስራ ወጥቷል።
ከቤቱ እስከ ታክሲ መያዣው ድረስ ያለችውን መንገድ ሲያሻው ከመንገደኛ ጋር እያወጋ አልያም በሀሳብ እየቆዘመ መጓዝ ልምዱ ነበር። በዚህች ቀንም በዝምታ ድባብ ውስጥ ሆኖ እየተጓዘ ነው። አሰፋ ስለሀገራቸው እንቅልፍ አጥተው ይባዝኑ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መኃከል አንዱ እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ለዜጎቿ ሁሉ ምቹ የሆነች ሀገር መገንባት አለበት የሚል ታላቅ ህልም አንግቦ ነጋ ጠባ የሚታትር ብርቱ ሰው ነበር።
አሰፋ በዚህች ቀን በጉዞው ላይ እያለ በዙሪያው ምን እየተሸረበ እንደ ነበረ ያስተዋለ አይመስልም። 100 ሜትሮች ያህል ከፊቱና ከኋላው መንገድ ሲዘጋ አላስተዋለም ወይ ደግሞ ለኔ ይሆናል ብሎ አልጠረጠረም። ለነገሩ የመከላከያ ሰራዊትን የሚያክል የሀገር ድንበርና ሉዓላዊነትን ማስከበርን የሚያክል ታላቅ ኃላፊነት የተሸከመ ተቋም ለአንድ ግለሰብ ሲል ኃይል መድቦ መንገድ ያዘጋል ብሎ እንዴት ያለ ባለጤነኛ ዓዕምሮ ሊያስብ ይችላል?
አሰፋም በሃሳብ እየቆዘመ ጉዞውን ቀጥሏል። ከሱ በኋላ ሰዎች በዚያ መንገድ እንዳይሄዱ መከላከያ መንገድ ዘግቷል ከፈት ለፊቱም እንደዚያው ተደርጓል። መንገዱ ላይ ብቻውን መሆኑን የተረዳው ድንገት “እንዳትንቀሳቀስ” የሚል የሚያንባርቅ ድምፅ ሲሰማ ነው። የሀገር መከላከያ ንብረት የሆነ መኪና ሙሉ ሰራዊት መሳሪያ ደቅነው በተጠንቀቅ ቆመዋል። ግርታ፣ ግራ መጋባት፣ መደናገጥ፣ ….. ወድያው የጥይት እሩምታቸውን ያዘንቡበት ያዙ። አሰፋም ለምን እንደሚገድሉት ሳይነግሩት፣ የመጨረሻ ቃሉን እንኳን ለመናገር ሳይፈቅዱለት እንደውሻ ሬሳ መንገድ ላይ ጥለውት ሄዱ።
የአሰፋ ባለቤት እሱን ሸኝታ አራስ ልጇን ጡት በማጥባት ላይ እያለች ነበር የጥይት ድምፅ የሰማችው። ወዲያው ቤቷና ግቢዋ የመከላከያ ካምፕ እስኪመስል ሰራዊት ይተራመስበት ያዘ። ይሄኔ ውስጧን አንዳች ነገር ወረራት። ባሏ ከቤት የወጣበትን ሰዓትና ተኩስ የሰማችበትን እንዲሁም ቤቷ እየተካሄደ ያለውን ነገር ሁሉ አስባ መጀመርያ ሽብር ነገር ውርርር አደረጋት።
ከዚያ በኋላ ግን ፍፁም ድንዝዝ የማለትና ምን እንደምታደርግ አለማወቅ ነገር ታየባት። ይህ ሁሉ ግን ለገዳዮቹ ጉዳያቸው አልነበረም። እሷን ከነህፃናት ልጆቿ ከቤት አስወጥተው ጓዳ ጎድጓዳውን ሁሉ ያምሱት ያዙ። ከሰዓታት ብርብራ በኋላ ያሰቡትን ባለማግኘታቸው በንዴትና ግራ በተጋባ ስሜት ግቢውን ለቀው ወጡ።
.
የአሰፋ ማሩ እናትና አባቱን ቤተሰቦቹን የሚያውቅ ወንድሜ ደግሞ በጊዜው የነበረውን የቤተሰቡን ሁኔታ እንደዚህ ይገልጠዋል <<የአባቱ እና የእህት ወንድሞቹ  ሃዘን አሳዛኝ ነበር። ጎረቤቶቻችን ነበሩ መቄት/ፍላቂት። አሰፋን በአካል አላዉቀዉም ግን በቤተሰቦቹ ሀዘን ምክነያት የማቀዉ ያህል ነዉ የሚሰማኝ። አባቱን ከዓመት በፊት አይቻቸዋለሁ አሁንም በህይወት አሉ፤ እስካሁን ሀዘን የወጣላቸዉ አይመስለኝም።”ልጃቸዉን ኢህአዴግ የገደለባቸዉ ሰዉዬ” ነው የሚባሉት ለማያቃቸዉ ሰዉ ማሩ በጊዜዉ!>>።
የወልዲያ ከተማ ነዋሪው ጋሽ ይመር በሪሁን ደግሞ ስለ አሰፋ ማሩ እንዲህ ይለናል
«በ1984 ወልዲያ ፒያሳ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ሆቴል በር አቶ አሰፋ ማሩ በእድሜ እኩዮቻቸው ከሚሆኑ ሰወች ጋር ቆመው፣ ብዙ ሆነን በአድናቆት አይተናቸዋል። መገደላቸውን የሰማሁ ጊዜ አሞኛል፤ በአካል ከአየኋቸው በላይ ታሪካቸውን ስለሰማሁ ተንገብግቤያለሁ። የሚገርመኝ በ አሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ስለ እርሳቸው ስሰማ “ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው በራሷ ጊዜ አጣች፣ የአቶ አሰፋ ማሩን ዓይነት 5 ሰው ብታገኝ ከአደጉት አገሮች ጋር ትደርስ ነበር።” ተብሎ ሳዳምጥ የባሰ ተርመጠመጥኩ። እግር ጥሎኝ በአጋጣሚ መቄት የእናትና አባቱ ቤት ስገባ የቤተሰቦቹንና የእርሱን ፎቶዎች ሳይ ደነገጥኩ፣ ከእኔ በእድሜ የሚያንስ የመጨረሻ ወንድሙ ጋርም ተዋወቅኩ። የተማሩና የተከበሩ ቤተሰቦች ውስጥ የወጣ እንደሆነም ተረዳሁ። ይህ ስነምግባሩ፣ ጨዋነቱም የዲሞክራሲ ትግሉ እንዳልተፈለገ ገባኝ። ለዚህም ኋላ እንደቀረን ገባኝ፣ ፈጣሪ  ፍርድ ይስጥ!»
የአሰፋ ባለቤትም ልጆቿን ይዛ ሀገሯ በብዙ ማይልስ ርቃ የፍትህን ቀን እየናፈቀች የስደት ኑሮን ትገፋለች ። ቢያንስ ለምን እንደገደሉት የማወቅ ረሀብ እየቦረቦራት ትኖራለች፤ ግን አሁን ለአሰፋ ሞት ማን ይጠየቅ ይሆን? ማን ያውቃል ሌላኛው ሚያዝያ 30 ምን ይዞላት እንደሚመጣ። በይቅርታ ትሻገረው ወይስ ገዳዮቹ ይጠየቁ ይሆን አሁንም እድሜ ይስጠን ብቻ። ኢትዮ ሪፈረንስ (ጽሁፉን የላኩልን ሰው የጸሃፈውን ስም አላኩልንም።ከወዲሁ ጸሃፊውን እያመሰገንን ¨ጽሁፉየኔ ነው¨ የሚሉን ጸሃፊ ስማቸውን ለማሰቀመጥ ዝግጁ መሆናችንንም ስንገልጽ በታላቅ ትህትና ነው።
Filed in: Amharic