>

ልደቱ እስከ ዓለም ፍጻሜ የእርሱን "እውነት" ለማወቅ የምንጨነቅ የሚመስለው ለምንድን ነው?  (መስፍን ነጋሽ)

ልደቱ እስከ ዓለም ፍጻሜ የእርሱን “እውነት” ለማወቅ የምንጨነቅ የሚመስለው ለምንድን ነው? 

መስፍን ነጋሽ
አቶ ልደቱ አያሌው የፖለቲካ ህይወቱን አሀዱ ብሎ የጀመረው   1983ዓ.ም. #ህወኃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ  በኋላ የከተማዋን ወጣቶች የማደራጀት ስራ ላይ ከተሰማሩ ወጣቶች አንዱ ሆኖ ነው፡፡ በዚያ ወቅት ወጣቱ ልደቱ ለወያኔ መንግስት የመወገን ጫና በነበረበት የወጣት ማህበር ምስረታ ሂደት ንቁ ተዋናይ ነበረ፡፡ በመሆኑም የማህበሩ ሊቀመንበር የመሆን ፍላጎት እንደነበረው በወቅቱ አብረውት የነበሩ የመሰከሩት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በ1990 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በይፋ ሲመሰረት ወጣቱን በማደራጀት ምንም ተሳትፎ ያልነበረው #የዳዊት_ዩሃንስ (አፈጉባዔ የነበሩት) ሚስት ወንድም የሆነው ወጣት ታጠቅ ካሳ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ፡፡
ይሄኔ ነው እንግድህ የልደቱ የመጀመሪያው የፖለቲካ አቋም እጥፋት የተጀመረው፡፡ የታጠቅን በሊቀመንበርነት መመረጥ አሚን ብሎ መቀበል አልፈለገም፡፡ የተመሰረተው ማህበር ግን እንደታሰበው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ እንደማይሆን እና ይልቁንም የኢህአዴግ የወጣት ክንፍ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ያዛኔው ልደቱን ያበሳጨው ጉዳይ የወያኔ አገልጋይ ለመሆን አለመታመኑ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ቀጥሎ የሄደው አዲስ ወደ ተመሰረተው የፕ/ር አስራት ወልደየስ ፓርቲ #መአሕድ ነው፡፡ ልደቱ በይፋ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ ሲወጣ ኃላፊነቱን የጀመረው በተመሳሳይ የመአሕድ ወጣት ክንፍ አመራርነትን ሲቀላቀል ነው፡፡
ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ጥሎ ወጥቶ እስከ አሁን ድረስ የሚመራውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን(ኢዴፓ) መሰረተ፡፡ ፓርቲው በታሪካዊው ምርጫ-97 ወቅት #ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የተባለውን ዋነኛ የተቃዋሚ ጎራ ከመሰረቱት አምስት ድርጅቶች አንዱ ነበር፡፡ በቅድመ-ምርጫ የክርክር መድረኮች ላይ አንደበተ-ርቱዕው #ልደቱ_አያሌው በተለየ ሁኔታ ጎልቶ ወጣ፡፡ ከአዲስ አበባ አልፎ የወጣቱ ፖለቲከኛ ስምና ዝና በመላ ኢትዮጵያ ገነነ፡፡
ሆኖም ግን መጨረሻው እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ የድህረ-ምርጫ ኩነቶች በህዝባዊ አመፅ እና የመንግስት የፀጥታ ኃይል በወሰዳቸው ዘግናኝ እርምጃዎች በውዝግብ የተሞላ ሆነ፡፡ ከዚህ ሂደት ጋር በተያያዘ የቅንጅት አመራር ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብቶ ተከፋፈለ፡፡ አብዛኛዎቹ የምርጫውን ውጤት ባለመቀበል ፓርላማ ላለመግባት ከህዝብ የተደረገባቸው ግፊት ተቀብለው አሻፈረን ሲሉ አቶ ልደቱ የቅንጅትን ማህተም ይዞ በተቃራኒዉ ቆሞ፡፡ ይሄን የቅንጅት አመራር አቋም ተከትሎ ፓርላማ አልገባም ያሉት ወደ ማረሚያ ቤት ሲላኩ አቶ ልደቱ ከተራው የድርጅቱ ተመራጮች ጋር ፓርላማ ገባ፡፡
#የቅንጅት_መፍረስ እስከ አሁን አነጋጋሪ እና የአቶ ልደቱን የፖለቲካ ስብዕና የቀበረ ሆኖ በማለፉ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ካላስረዳሁ በማለት ዛሬም ላይ ታች ሲል ይታያል፡፡ ቅንጅቱን በመበተኑ የማን ሚና የጎላ ነበር? ለሚለው ጥያቄ ህዝብ በአገኘው መረጃ ልክ ብያኔ ሰጥቶበት ያለፈው ምናልባትም በሀገራችን ታሪክ ከፍተኛ የህዝብ ትኩረት አግኝቶ የነበረ ክስተት ነው፡፡ ቢሆንም ልደቱ እስከ ዓለም ፍጻሜ የእርሱን “እውነት” ለማወቅ የምንጨነቅ የሚመስለው ለምንድን ነው? መጻሕፍት ጽፎ፣ መቶ መግለጫ ሰጥቶ ወዘተ እውነቱን ያስረዳ ካልመሰለው እስኪ ምናልባት እነዚህ ስድስት ነገሮች ሆነው ይሆናል በሉት።
👉#ይሆናል1፤ ምናልባት የምታስረዳው “እውነት” የለ ይሆናል፤ ወይም ከሌላ አንጻር ቆመው ሲያዩት የሚጠቅም ታሪክ እና እውነት አይደለም ይሆናል። እርግጠኝነትህን ተጠራጠረው።
👉#ይሆናል2፤ “እውነቱ” ባንተ ብቃት/ቁመና ሊገለጽ፣ ሊሰበክ የማይችል ሆኖ ይሆናል። እስቲ ሌሎች ይህንን እውነት እንዲያስረዱት ተውላቸው። መለኮታዊ ተልእኮ ተሰጥቶህ እንኳን ቢሆን ለላከህ አካል “አልቻልኩም፣ አልሰሙኝም” ብለህ ንገረው። ነቢያት አድርገውታል።
👉#ይሆናል3፤ እንዲሰሙህና እንዲለወጡ የምትፈልጋቸው ሰዎች ያንተን “እውነት” ለመስማት ወይም/እና ለመቀበል አይፈልጉ ወይም አልበቁ ይሆናል። ተዋቸው። ግዴታ አታድርግባቸው። ያንተን እውነት ማወቅም ሆነ መቀበል አንተ የምታስበውን ያህል ጠቃሚ ላይሆን ይችላል። አይደለምም።
👉#ይሆናል4፤ ሕይወትህን ወይም ትርጉሟን በአንድ ያንተ እውነት ላይ ብቻ አንጠልጥለሃት፣ እረፍት ነስቶህ ይሆናል። የፖለቲካም ሆነ ሌላ ሕይወትህን (ወይም ትርጉሙን) ከዚህ ከምትለው እውነት/ትርክት ለማፋታት ሞክር። ሌላው ቀርቶ፣ የፖለቲካ ሕይወትንም ጭምር ከዚህ ከምትለው “እውነት” ውጭ እንደ አዲስ ልትገነባ ትችላለህ፤ ከፈለግህ። እውነት የምትለው ጉዳይ/ትርክት እስረኛ አትሁን። ራስህን ፍታ።
👉#ይሆናል5፤ ፖለቲካ ጨዋታ መሆኑን ረስተኸው ይሆናል። በማንኛውም ጨዋታ መብለጥ፣ መበለጥ ያለ ነው። አንድ ግጥሚያ በፍትሕ በርትእ ይዳኝም አይዳኝም  አጠቃላይ ጨዋታው ይቀጥላል። ያለፈውን ግጥሚያ ወደኋላ ተመልሶ መቀየር አይቻልም። ስላለፈው ግጥሚያ ስሕተቶች ያልካቸውን ለማስረዳት ሞክረሃል። ከዚያ በላይ ማድረግ አትችልም። ጨዋታው ካንተ የግል ውጤትና ስሜት ይበልጣልና መቀጠሉ አይቀርም። ወደ ጨዋታው ተመለስ፤ ወይም ጨዋታ ቀይር፤ ወይም ጨዋታ ተው።
👉#ይሆናል6፤ ስፖርተኛ ሆነህ ከተጎዳህ ቢያንስ ሕመምህ እስኪድን ጉዳት ካደረሰብህ ጨዋታ ማረፍ አለብህ። አንተ ከፖለቲካ በቂ እረፍት ሳትወስድ እየተመላለስክ ሕመምህ እንዳይሽር አድርገኸው ይሆናል። ካስቻለህ በቂ እረፍት አድርግ። ካላስቻለህ፣ ለቅሶህን አቁመህ፣ ወደምትወደውና ወደምትችለው የፓርቲ ፖለቲካ በቀጥታ ግባ። አለዚያም ከፓርቲ ፖለቲካ ውጭ ባለ መድረክ ለምሳሌ ትንተና ወደ መስጠት፥ ወደ ማጥናት ወዘተ ዙር። በአንድ ነጠላ ጉዳይ ላይ ጊዜህን፣ ስሜትህን እና አቅምህን አታባክን።
ነገሩ እንዲህ ነው።
(ይህን አስተያየቴን የሆነ ባንተ ላይ የተሸረበ ሴራ አካል አድርገህ እንደማታየው ተስፋ አደርጋለሁ። ያው ተስፋ ነው።)
Filed in: Amharic