>

በእውቀታቸው ሃገራቸውን ያገዙ በውጪ ሃገር የተማሩ ኢትዮጵያዊ ምሁራን!!! (ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው)

በእውቀታቸው ሃገራቸውን ያገዙ በውጪ ሃገር የተማሩ ኢትዮጵያዊ ምሁራን!!!


ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው


አስራት ወልደየስ
―የህክምና ትምህርታቸውን በስኮትላንድ ኤደንብራ ተከታተሉ። በከፍተኛ ማእረግ ተመረቁ። በምእራቡ አለም፣ በመረጡት ሆስፒታል፣ በትልቅ ደሞዝ፣ በሰለጠኑ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሰሩ የቀረበላቸውን አጓጊ ጥያቄ ወደ ጎን ብለው ሃገራቸውን በትንሽ ደሞዝ፣ ባልተስተካከለ ሁኔታ፣ በኋላቀር ሴቲንግ ለማገልገል መጡ። እጃቸውም ብዙዎችን ፈወሰ። ለሺዎች መድሃኒት ሆኑ። እልፍ አእላፋትን ቀደው አከሙ። ስለ አስራት አንድ ነገር ልጨምር። አስራት ጋዜጠኞችም ሆነ ሌሎች ሰዎች “ቀዶ ጥገና” ሲሉ አይወዱም። “ቧንቧ አይደለም የምንጠግነው፤ ክቡር የሰው ልጅ ነው። ቀዶ ህክምና በሉ” ይላሉ።
 እሌኒ ገብረመድህን ― የተማረችው ስታንፈርድ ፣ ኮርኔል፣ ሚቺጋን ዩኒቨርስቲዎች ነው። በአለም ባንክ የነበራትን ስራ ትታ ለሃገሯ ቁምነገር ለመስራት ሃገር ቤት ገባች። ያጠናችው ኢኮኖሚክስ የሃገሯ ኢኮኖሚ የተመሰረተው ግብርና ላይ። እሌኒ የእርሻ ምርት ግብይቱን እንዴት ማዘመን እንደሚቻል ማሰብ ጀመረች። የግብርና ምርቱ አንድ ቦታ ወይም ወቅት ላይ ይትረፈረፋል። ሌላ ግዜ እጥረት ይፈጠራል። ምርት ይባክናል። ገበሬ ይከስራል። ሃገር ይደኸያል። ይህንን ለመቅረፍ መፍትሔው የመረጃ መረብ መፍጠር ነው። ኢሴክስ ECX ይባላል። እሌኒ ይህንን ድርጅት መስርታ አዋቅራ ቅርፅ አስይዛ ልምዷን በመላው አፍሪካ ለመድገም እየተንቀሳቀሰች ነው። በነገራችን ላይ እሌኒ ያደገችው በሶስት የአፍሪካ ሃገሮች ውስጥ ሲሆን ስዋሂሊ፣ ፈረንሳይኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ አቀላጥፋ ትናገራለች።
ፍስሐ አጥላው-  አቶ ፍስሐ እዚሁ ኢትዮጵያ በ1955 ተወልደው ለ12 አመታት ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ተምረዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1971 ቢገቡም ወዲያውኑ በመዘጋቱ ለኢንጅነሪንግ ትምህርት ወደ ሰሜን አሜሪካ አቀኑ።
በዚያም ቴሌኮሙኒኬሽን እና ባዮሜዲካል ኢንጅነሪንግ አጥንተዋል። ከዚያም ለአታሪ እንዲሁም ለኤችፒ ለ25 አመታት ሰርተዋል። ፍስሐ አጥላው እራሳቸው ባቋቋሙት ዳሽን ኢንጅነሪንግ ኩባንያ አማካይነት የአማርኛ ኮምፒውተር መፃፊያን ያስተዋወቁ ፈር ቀዳጅ መሃንዲስ ናቸው። ይህንን ለማድረግ ያነሳሳቸው ሁለት ምክንያቶች ናቸው። የመጀመሪያው የራሳቸውን የስነጽሑፍ ዝንባሌ ለማሳደድ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ለኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባይተዋር እንዳይሆኑ የሚናገሩበትና የሚፅፉበት ቋንቋ በዲጂታል አለም ውስጥ ቦታ እንዲያገኝ ማስቻል ነው። ፍስሐ የመጀመሪያውን ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የአማርኛ ኮምፒውተር መፃፊያ ሶፍትዌር ከሰሩ በኋላ ሁለት ነገሮችን አሳክተዋል። በመጀመሪያ የግእዝ ፊደላት በዩኒኮድ ውስጥ ቦታ እንዲያገኙ አድርገዋል። ዩኒኮድ አለምአቀፍ ስታንዳርድ ነው። በዩኒኮድ የተካተተ ፊደል በየትኛውም ፕላትፎርም ላይ ሊፃፍ ሊነበብ ይችላል። ይህ ማለት ፍስሐ አጥላው ከዩኒኮድ ኮንሶርቲየም ሃላፊ ጆ ቤከር ጋር በመሆን ግእዝን በአለምአቀፍ ደረጃ ስታንዳርዳይዝ አድርገዋል። ሁለተኛው የUnicode ንዑስ ኮሚቴ በመደበኛ geez ወይም Amharic በማለት ፈንታ ethiopic ብሎ እንዲጠራው አሳምነዋቸዋል። ይህም ፊደሉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብት መሆኑን አስረግጠዋል።አሁን እኔ ይህንን መልእክት በአማርኛ ለመፃፍ እናንተ ለማንበብ ላስቻላለን ቴክኖሎጂ የፍስሐ አጥላው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ኤርሚያስ አመልጋ― ኤርሚያስ የተወለደው እዚሁ አዲስአበባ ቢሆንም ከተወለደ ከጥቂት ሳምንት በኋላ ቤተሰቡ በሞላ ወደ ግብፅ ካይሮ አቀና። አባትዬው ዲፕሎማት ስለነበሩ ብዙ ይዘዋወሩ ነበር።  በዚህም ምክንያት ኤርሚያስ አፍ የፈታው በአረብኛ ነበር። ቀጥሎ ሃገርቤት ተመልሶ አማርኛ ከዛ ወደ ናይሮቢ አቅንቶ ስዋሂሊ እና እንግሊዝኛ ተማረ። በ1968 ኤርሚያስ እድገት በህብረት ዘመቻ ወደ በደኖ ዘምቶ ነበር። ከዛ መልስ ወደ አሜሪካ አቅንቶ ለ20 አመት ኖሯል። ከዚህ ውስጥ ስምንቱ አመት ለትምህርት የተሰጠ ነበር። ከትምህርት በኋላ ዎልስትሪት ስራ ጀምሮ ኒውዮርክ እና ሎስአንጀለስ ለብዙ የፋናንሽያል ድርጅቶች ሰርቷል። በዚህ ወቅት ኤርሚያስ ወደ ሃገርቤት ለመመለስ ምንም እቅድ አልነበረውም። ቢሆንም በባለቤቱ ጉትጎታ ለአንድ ሳምንት ጉብኝት አዲሳባ መጣ። አንዴ ሃገሩን ከረገጠ በኋላ ግን ሃሳቡን ቀይሮ እዚሁ ለመኖር ወሰነ። ሎስአንጀለስ ውስጥ የነበረውን 2500 ካሜ መኖሪያ ቤት ሽጦ አዲሳባ ከተመ። ኤርሚያስ ሃገር ቤት ከገባ በኋላ ያልሞከረው ቢዝነስ የለም―ዘይት መጭመቂያ፣ ሚነራል ውሃ(ሮያል ክራውን)፣ የታሸገ ውሃ(ሃይላንድ)፣ አክሰስ ሪል ስቴት፣ ዘመን ባንክ እና ሌሎችም ብዙ። ኤርሚያስ በቢዝነሱ የተነሳ ሁለት ግዜ ታስሮ ተፈቷል። ኤርሚያስ በ24 ሰአት የሚመገበው አንዴ ብቻ ነው። ዘወትር የሰውነት ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋል። ከውሃ ውጪ ወደ አፉ የሚያስገባው አልኮል የለም። ይህ የሕይወት ዘይቤው በ63 አመቱ ገና የ30 አመት ጎረምሳ አስመስሎታል። ኤርሚያስ በቢዝነሱም በግል ህይወትም አርአያ የሚሆን ሰው ነው።
Filed in: Amharic