>
5:13 pm - Thursday April 19, 9703

ተክለፃዲቅ መኩሪያ -  "የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ" ያስወቃ ድንቅ የታሪክ ዘካሪ!!!  (ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው)

ተክለፃዲቅ መኩሪያ –  “የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ” ያስወቃ ድንቅ የታሪክ ዘካሪ!!! 

ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው

በ1936 ተክለፃዲቅ መኩሪያ የተባለ ጎበዝ በትምህርት ሚኒስትር ውስጥ ይሰራ ነበር። ይህ ወጣት ለታሪክ ልዩ ፍቅር ነበረው። ታዲያ ይህንን የታሪክ ጥማት ለማርካት ወደ ቤተመፅሀፍት ጎራ ብሎ በአማርኛ የተፃፉ የታሪክ መፅሀፍትን ቢያፈላልግም አልተሳካለትም። ቢያገላብጥ ካርሎ ኮንቴ ሮሲኒ ፣ ቢገልጥ ፍራንቺስኮ አልቫሬዝ ፣ አንቶኒቼሊ ፍራንኮ ወይም ዴል ቦካ ናቸው። ታሪካችን በነጮች ተወሯል። የሀገሩ ፣ የወንዙ ልጅ የታሪክ ፀሐፊ አንድም የለም።
ለዚህ ብርቱ ወጣት ይህ አሳሳቢ ነው። የራሳችን ታሪክ እኛው መፃፍ አለብን፤የራሳችንን የቤት ስራ እኛው መስራት አለብን። የታሪክ ጽሑፍ ሊዛባ ይችላል። በተለይ የባእድ ሰዎች ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ ሊጠመዝዙት ይችላሉ። በዚህ ምክንያት የታሪክ ጽሑፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በውጪ ኀይል እንካችሁ ታሪካችሁ ይሄ ነው መባልን አንሻም።
ከዚህ በኋላ ይህ ወጣት ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። የኢትዮጵያን ታሪክ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘመናዊው ግዜ በአማርኛ ለመፃፍ ተዘጋጀ። ለዚህም የሚረዱትን በእንግሊዝኛ ፣ ፈረንሳይኛ ፣ ጣልያንኛ የተፃፉ የኢትዮጵያ የታሪክ መፅሀፍትን ሰበሰበ። እነዚህን ዘጠኝ መፅሀፍትም ፃፈ፦
የኢትዮጵያ ታሪክ ቅፅ ፩ ኑብያ  ( ሜርዌ — ናፓታ)
                             ፪ አክሱም — ዛጉዬ
                             ፫ ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ልብነ ድንግል
                             ፬ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ
                             ፭ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀኃስ
የግራኝ አህመድ ወረራ
አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት
አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት
አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት መፅሀፍትን ጽፏል፦
ጥንታዊት ኢትዮጵያ እና ግብፅ
ከጣኦት አምልኮ እስከ ክርስትና
የተክለፃድቅን ስራዎች ዋጋ የምንሰጣቸው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፦
―ታሪክን ከተተበተበበት ልማዳዊ አጻጻፍ ነፃ አውጥተው በሳይንሳዊ መንገድ መፃፍ በመጀመራቸው
―ሀገራዊውን መረጃም ሳይተው በፈረሳይኛ ፣ ጣልያንኛ እና እንግሊዝኛ ሁሉ ያለውን ተጠቅመው ከስር እስከ ጫፍ የሃገሪቱን ታሪክ በመፃፋቸው
―እነኚህን ሁሉ መፅሀፍት የፃፉት በመደበኛ የቀለም ትምህርት ሳይሰለጥኑ በከፍተኛ የመንግሥት ስራና ሃላፊነት ተጠምደው ያላቸውን የመዝናኛ ግዜ ሁሉ ሰውተው ቁምነገር በመስራታቸው
―በተለይ ከ15 አመታት በላይ የደከሙበት “የግራኝ አህመድ ወረራ” የተሰኘ መጽሐፋቸው በ155 ምእራፎችና በ840 ገፆች በጽሑፍ በካርታ በሰንጠረዥ በፎቶግራፍ መረጃዎች ተሞልቶ ስርአት ባለው መልኩ ታሪኩ ትንትን ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ
ተክለፃድቅ መኩሪያ ― “የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ” ያስወቁ ድንቅ የታሪክ ፀሐፊ ናቸው። አስባችሁታል ግን? ተክለፃድቅ መኩሪያ ባይኖሩ ኖሮ የኢትዮጵያን ታሪክ የምናነበው በጣልያንኛ ነበር። እጣ ፈንታ ተክለፃድቅ መኩሪያን ለዚህ ታላቅ ተልእኮ አጭታቸው ነበር፤እሳቸውም ትከሻቸውን አደንድነው ተልእኮውን ተቀብለው በሚገባ አሳክተዋል።
አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ በህይወት ዘመናቸዉ ለህትመት ካበቋቸዉ የታሪክ መፃሕፍት አንዳንዶቹ። የመጨረሻዉ ”ከሞትኹ በኋላ ይታተምልኝ” ያሉት ግለታሪካቸዉ (Autobiography) ነዉ።
Filed in: Amharic