>

እውን ኢትዮጵያ ባለቤት አላትን? (አምባቸው ደጀኔ - ከወልዲያ)

እውን ኢትዮጵያ ባለቤት አላትን?

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


  1. ሱዳን ባቅሟ የኢትዮጵያን መሬት እንደፈለገች በመውረር ላይ ትገኛለች፡፡ ፊጂና ማልታ፣ ከኛ የባሰች ድሃዋ ኒጀርም ጭምር ኢትዮጵያ ስለራቀቻቸው እንጂ “የድርሻችንን!” ብለው እነሱም የፈለጉትን ያህል መሬት ከየትኛውም የኢትዮጵያ ይዞታ ሊወስዱ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡ ኢትዮጵያ  እንደጠፍ አህያ ማንም ያሻውን የሚጭናት የጋማ ከብት ከሆነች ሰነበተች፡፡ ይገርማል፡፡ በአቢይ አህመድ አስተዳደር ይህን መሰል ቅሌት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ እንደ ዳያስፖራ ሰልፍ ለአቢይ “Shame on you!” ማለት አሰኝቶኝ ነበር፤ ብቻ ይቅር ግዴለም፡፡ “በባዳ ቢቆጡ፣ በጨለማ ቢያፈጡ” ይባል የለም?

… እናስ ኢትዮጵያ የማን ናት? የምን ዝምታ ነው – መልሱልኝ’ይ፡፡ መንግሥቷስ የት አለ? በመንግሥቱ ኃ//ማርያም ይቅርና በመለስ ጊዜ እንኳን ይህን ያህል ተደፍራ አታውቅም (ምርጫ አጥቼና ለሥነ ጽሑፋዊ ውበት ስል መለስን በበጎ ላነሳ ገና ሳስበው ጀምሮ እንዴት እንደሚዘገንነኝ እኔና አንድዬ ብቻ ነን የምውቀው! ቀዳሚን ሰይጣን ከተከታይ ሰይጣን ማወደዳር ግድ ሲሆንብህ መታመምህ አይቀርም)፡፡ ግን ግን ምን እስክንሆን እየተጠበቀ ይሆን? አምባሣደርም በሉት ሚኒስትርና ኮሚሸነር የሚሾመው ደግሞ በትውውቅ እንጂ በሙያና በችሎታ አይደለም፡፡ የዕድሜማ ነገር አይነሣ! ‹ተረከዙ›ን ያልጠረገ ውርጋጥ፣ ንፍጧን ያልጠረገች ያላገባች ሣዱላ ወይንም የቅርብ ጊዜ ፈት ጋለሞታ ሚኒስትርና አምባሣደር ሲሆኑ ስታይ እነ አምባሣደር አሃዱ ሣቡሬ፣ አምባሣደር ዘውዴ ረታ፣ አምባሣደር ዕምሩ ወንዴ … ፊትህ ድቅን ሊሉብህ ይችላሉ፡፡ እንደታዘብኩት በዘመነ አቢይ ሥልጣን ልክ እንደቡና ቁርስ ሆኗል – ስትፈልግ ለምትፈልገው የምትሰጠው – ሳትፈልግ ከሰጠኸውም ሰው ላይ አለምክንያት የምትነጥቀው የግል አንጡራ ሀብት፡፡ ሥልጣን የቡና ቁርስ ከሆነ ሀገር ጠፋች፡፡ “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” ይባል የነበረው ቀርቶ በዘርና በጎሣ ልክፍት ተቃኝተህ ታዛዥ ውጫጮችን በመሰብሰብ የምትሾም የምትሽር ከሆነ አዲዮስ ሀገር! በታላላቅ ነገሥታት ዘመን የተጣሉትንና በእጅጉ የተቀያየሙትን ሰው ሳይቀር እያባበሉ ይሾሙ ነበር፤ ምክንያቱም ቅድሚያ የሚሰጡት ለሀገራቸው እንጂ ለግል ፍላጎታቸውና ለቂም በቀል ጥማታቸው አልነበረም፡፡ የአሁን ዘመን መሪ ግን አስተሳሰቡም ዕውቀቱም ከአፍ እስካፍንጫው ነውና ሹመቱም ሆነ ሽረቱ ልክ እንደዛፍ ላይ ዕንቅልፍ ሆነና ከመሾሙ መሻሩ፣ ከመሻሩ እሥራቱና እንግልቱ ይቀድም ጀመር፡፡ … በእውነቱ ታዲያን ኢትዮጵያን ምን በላት? የምሬን እኮ ነው – ወዴት ተደበቀች? ማንም የሞቀውና አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት ዕድሉን ያገኘ ሁሉ እንዲህ እንዲጫወትባት ከላይ የተፈቀደው በየትኛው ኃጢኣታችን ይሆን? ይህ ዓይነቱ ባለቤት አልባነትና ዝርክርክነት እንዲሁም የብሔራዊና ሕዝባዊ ስሜት መጥፋት፣ ወገን በወገን መጨካከን፣ ወደ ዐውሬነትና ወደ ለዬለት ዞምቤነት መለወጥ… ለግብጽና መሰል የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? ድንበር አስደፍሮ ውይይትና ድርድርስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? አገርን እያስወረሩና በጎሣና በዘር እየሸነሸኑ ችግኝ መትከልና ከተማን ለማስዋብ መሮጥስ ማንን ይጠቅማል? ምን ዓይነት ግንጥል ጌጥ ነው? አቢይ አህመድ ሆይ ወዴት አለህ? ኧረ ተፈጥሮህ ከምን ይሆን? ከገበያ ገዝቶ ለባለቤቱ የሰጣት እህል “እንጀራ ላርግህ እምቢኝ፣ ቂጣ ላርግህ እምቢኝ፣ ቆሎ ላርግህ እምቢኝ፣ ንፍሮ ላርግ እምቢኝ…” እያለ ሲያስቸግራት የታዘበ ባል “ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት!” ያለው ወዶ አልነበረም ለካንስ፡፡ በስመ አብ! 

  1. አቢቹን ካነሳን ዘንዳ አንድ አስገራሚ ነገር ልጠቁም፡፡ እንዲያው በአላህ ይሁንበትና አቢይና የሚመራው መንግሥት መዋሸት የሚሰለቻቸው መቼ ነው? በውሸት መርካትስ ምን ዓይነት መረገም ነው? ባለፈው ስንት ቢሊዮን ችግኝ ተከልኩ አስተከልኩ ብሎ አቢይ ለዓለም እምቢልታውን ነፋ፡፡ ከቁጥሩ መጋነን የተነሣ ብዙዎች ተጠራጠሩት፡፡ ከእኛም ብዙዎቻችን አላመንነውም፡፡ ቁጥር አያውቁም ብለንም ተሳልቅንባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ጊነስ ቡክም ሳያምናቸው ቀርቶ የመዘገበላቸው አይመሰለኝም፡፡ እንዴ! ሲዋሽ እኮ ትንሽ ይሉኝታ ያስፈልጋል – አለበለዚያ እኮ ሌላ ጊዜ የሚያምንህ አይኖርም፤ ልክ እንደውሸታሙ እረኛ ነው የምትቆጠረው፡፡ ዝም ብሎ እንደጣቃ መቀደድ ከየት ያመጡት ፋሽን ነው? እነዚሁ የቁጥር ደናቁርት አሁንም እኛንም ዓለምንም በሣቅ ሊገድሉን በመጪዎቹ የክረምት ወራት አምስት ቢሊዮን ችግኝ እንደሚተክሉ ቅንጣት ሳያፍሩ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህ ዜና በራሱ የምርጫ መራዘምን ለሚቃወሙ ሰዎች ትልቅ የወሬ ሲሳይ ነው፡፡ ምርጫን በኮሮና ምክንያት አዛውረህ ስታበቃ በማግሥቱ – ጥቂት የማረሳሻ ጊዜ እንኳን ሳይኖርህ – አምስት ቢሊዮን ችግኝ እተክላለሁ ማለት ለኔ ዕንቆቅልሽ ወይም የፕሮፓጋንዳ ዕጦት ያመጣው ችግር ይመስለኛል – ይታይህ፡- መራጩም ሕዝብ – ችግኝ ተካዩም ሕዝብ፤ ወቅቱም ክረምት – አስፈጻሚ አካሉም መንግሥት – አይደለም እንዴ? ለነገሩ ውሸታም መዋሸቱን እንጂ ስለውሸቱ የዞረ ድምር አያውቅም፤ ማወቅም አይፈልግም – አይችልምም፡፡ ለምን ቢባል ውሸታም ማለት በተፈጥሮው እንደ አቃቂ ፈረስ ወዲያና ወዲህ እንዳያይ ግራ ቀኙን ራስ ወዳድነትና ስስታምነት በወለደው የሥልጣን አምሮት ሱቲ የተሸፈነ ነው፡፡ ሲጀመር አምስት ቢሊዮን ችግኝ ከየት ይመጣል? ማንስ ይተክለዋል? የት ይተከላል? ለመሆኑ አምስት ቢሊዮን ስንት ነው ኧረ? አምስትን ጽፈህ ስንት ዜሮ ይከተላል? እንዴ! አቢይን ምን ነካው? በቅጡ ቢዋሽ ምን አለበት? ( በ”ዋ” ምክንያት ይቺ ዐረፍተ ነገር ሁለት መሆኗን ልብ ይሏል!) ዋጋን በተመለከተ አንድ ችግኝ በትንሹ በሦስት ብር ሒሣብ ቢገመት 15 ቢሊዮን ብር ከየት መጥቶ ችግኙ ተዘጋጀ? ነው እንደቡሃቃ የሰጡንን ሁሉ የምንውጥ ጅሎች መሰልናቸው? … ካለፈው ተከላ 84 በመቶው እንደጠደቀ ደግሞ ሲናገሩ ሰማሁ – ሀፍረት የለሾቹ ኢቲቪዎችና መንግሥታችን፡፡ በየትኛው ጥናት? ማንና መቼ አጥንቶት? ቀልድ ሲበዛ ያንገሸግሻል፤ ይመራል፡፡ እንደምንሰማው ከሆነ – መድረቃቸውን አጥብቀን ብንጠላውም – ብዙዎቹ ተክሎች ተንከባካቢ በማጣታቸው ሳቢያ እየደረቁ ነው ይባላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሜጋ ፕሮጀክት በሆይ ሆይታ አይደለም የሚሠራው – ወይም ለታይታና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መሆን የለበትም፤ ትልቅ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ ጥበቃና ተንከባካቢ ያስፈልገዋል፤ ብዙ ግብኣትን ይሻል፡፡ ግን አቢይና መንግሥቱ ሕዝብን ስለሚንቁ ሚዲያውም የነሱ በመሆኑና ቆንጣጭ ገልማጭም ስለሌላቸው እንደፈለጉ የፈለጉትን የውሸት ወሬ ያቀረሹብናል – እንዲህ ስል በጣም አዝናለሁ፤ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያዊ ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባልሆን እመርጣለሁ – ምርጫ አጣሁ፡፡ “ጥሎብኝ” አለች ያቺ ትንሽዬ ዘፋኝ!” የት ሄጄ ልኑር እባካችሁ? ይህን የመሰለ ሀገራዊ የቁጭ በሉ ድርጊትና ተደራራቢ የሀሰት ቱማታ እያዩ ከመኖር ሞትና ስደት በስንት ጣሙ፡፡ የነአቢይን ሜጋ ውሸት በሚመለከት ግን … የማያውቁትን ቁጥር አምስት ቢሊዮን ከማለት ይልቅ ሁለት መቶ ሽህም፣ አንድ ሚሊዮንም፣ ሃያ ሚሊዮንም ማለት እኮ ይቻል ነበር፡፡ “በትንሹ ያልታመነ በትልቁም አይታመንም” ወገኖቼ፡፡ በነአቢይ ውስጥ ጎልቶ የሚታየኝ ትልቅ ነገር ቢኖር የኃጢኣታችን ክርፋትና የክፉ ሥራችን ደለል ነው፡፡ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡- “ፈጣሪ ክፉ ሕዝብን ሊቀጣ ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥን ያነግሣል፡፡” አቢይ በራሱ ጨካኝ ነው ማለት ቢከብደኝም ከነባራዊ ሁኔታዎች ተነስቼ ውክልናው ግን ጭካኔን ስለመሆኑ አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ጣፋጭ ፍሬ ከዛፍ ላይ እንዳለ ይታወቃል መባሉስ ለዚህም አይደል?
  2. አገር ምድሩ በርሀብ እየተንጠራወዘ ሳለ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ሃይ የማይለው ለምን ይሆን? የተራበና የጠወለገ ሕዝብ መምራት ለሥልጣን ዕድሜ መራዘም ጥሩ መሆኑ በቀደምት ደናቁርት አገገዛዞች የሚነገረው በዚህ የዕውቀት ዘመን እንዲሠራ ይፈለግ ይሆን? ሰብኣዊነት የት ጠፋ? ሃይማኖታዊ መልካም ሥነ ምግባር ወዴት ኮበለለ? የአቢይ መንግሥት ስለኑሮ ውድነቱ አንድም አይተፍስም፡፡
  3. የሃይማኖት ሰባኪ ነኝ ባይ ሁላ እንደፈለገው እየተነሣ አንዱ የአንዱን ሃይማኖት በሚዲያ ማንቋሸሹ ምን ይባላል? ለምን ራሱን ችሎ በራሱ ግዛት አይሰብክም? በቀደም ለታ በዋልታ ቲቪ ትልቅ ብልግና አየሁ – ትልቅ ድፍረት፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ፡፡”

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የሙስሊሙ ሰባኪ በኮሮና ምክንያት መንግሥት የፈቀደለትን የጸሎትና ምህላ ፕሮግራም ገልብጦ ክርስትናን መሳደቢያ አደረገው፡፡ ህግም መንግሥትም የሌላት የምትመስለው ኢትዮጵያ ደግሞ ዝም አለችው፡፡ ምክንያቱም ባለቤት የላትማ! ያ ስብከት እኮ የሚያሳስር ነው፡፡ ስብከቱ በአጭር ትርጓሜ “ከእስልምና በስተቀር የሌላው ሃይማኖት ተከታይ ሁላ ወዮልሽ! ወደ እሳት ነው እምትጣይው፤ በዚያ ዘላለምሽን በእቶን ስትለበለቢ ትኖሪያለሽና በቶሎ ወደ አላህ ነይ!” የሚል ነው፡፡ እኔ የፈለግሁትን ባመልክ ወይም ምንም ባላመልክ ስለኔ ማን ምን ጥልቅ ያደርገዋል? ክርስትናም ሆነ እስልምና ወይም ሌላ ሃይማኖትም ይባል እምነት በራሱ የአምልኮት ቦታ ወይም በራሱ ሚዲያ ብቻ እንጂ በየገበያውና በየመንደሩ ወይም በየአደባባዩና በሕዝብ ሚዲያ እንዲህ ዓይነት መስፈራርቾ ማሰራጨት አይኖርበትም፡፡ ነውርም ነው፡፡ ብሂሉም “ሃይማኖት የግል ሀገር ግን የጋራ “ ነው የሚለው፡፡ ታዲያ አጋጣሚ ተገኘ ተብሎ እንዲህ ያለ የጦርነት ዐዋጅ ሲታወጅ መንግሥት ወዴት አለ? ሰውዬው የሚለው ነገር ካለቀበት ወይም ተዘጋጅቶ ካልመጣ “ታረቀን አላህ፤ ታረቀን አላህ” የሚለውን ቆንጆ መንዙማ ከፍቶ አያሰማንም ነበር? የት የሚያውቀውን እሳትና ውኃ ነው የሚቀባጥረው? የሃይማኖት ሰባኪ ማስፈራራት ካበዛ እንደየጁ ደብተራ ቅኔው አልቆበት ወደ ቀረርቶው ገባ ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ልማዳዊ አካሄዶችን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ በዓለማችን ጥቂት ሽህ ሕዝብ በነበረበት ዘመን ጥቅም ላይ ይውል የነበረ የስብከት ሥልት አሁን ላይሠራ እንደሚችል መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ መጻሕፍትን ከዳር እዳር መመርመርና ምርቱን ከግርዱ፣ ጭማሪውን ከነባሩ፣ ውሻሉን ከቋሚው… መለየትም አግባብ ነው፡፡ የእውር ድንብር ሞሼዲያኛ ጉዞ አያዋጣምና ነገርን ከሥር መሠረት መመርመር የሚያዛልቅና አዋጭም ነው፡፡ ጥፋት ሰውኛ ሲሆን ምሕረት ደሞ እግዜርኛና “ሕዝብኛ፣ አንባቢኛም” ጭምርት ነውና ባጠፋሁ ይቅርታ፡፡

በሽዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ – ምንም እንኳ መሠረታውያኑ ሦስት ቢሆኑም፡፡ እርግጥ ነው ከሦስቱ አንደኛው በቅርቡ የዛሬ 1400 ዓመታት በፊት ገደማ ነው የተመሠረተው፡፡ የትኛውም ሃይማኖት በማንም ይጀመር፣ መቼም ይመሥረት፣ ስንትም ያህል ተከታይ ይኑረው …. ለክፋትና ለክፉ ሥራዎች ጥብቅና እስካልቆመ ድረስ እንደአካሄድና እንደመብት የሁሉም ሰው ሃይማኖት ሊከበር ይገባዋል – ህገ መንግሥታዊም ነው፡፡ ሃይማኖት የሌለውም ስላለ እርሱም ይህ መብቱ ሊጣስበት አይገባም፡፡ አንድ ሰው የሚያዋጣውንና የሚያከስረውን ንግድ ራሱ ብቻ ነው የሚያውቀው – ሃይማኖትም “ንግድ” ነው – ነፍስን ከዘላለማዊ ጉስቁልና ስለማትረፍ አስበውበትና ፈቅደው የሚገቡበት “ንግድ”፡፡ ከኪስህ “መዥርጠህ” ለኔ ቢጤ አንድ ብር የምትሰጠው በነፃ እንደሆነ የምታምን ከሆነ ጅል ነህ፡፡ ሰው  አምስት ሣንቲም ከኪሱ አውጥቶ ለሰው በነፃ አይሰጥም – የሚሰጠው አንድም አዝኖ ነው(ነግ በኔን ፈርቶ)፣ አንድም ሊጸድቅ ነው (ለነፍሱ ሳስቶ)፣ አንድም ተርፎት ነው (“መጣያ” አጥቶ – ምናልባት)፣ አንድም ፈርቶ ነው – (ባልሰጥ ይቀሙኛል ብሎ) …፡፡ እንደማንኛውም የሥራና የሥምሪት ዘርፍ በሃይማኖትም አንድ ሰው ምክርና አስተያየት እንዲሰጠን መጠየቅ ግን ይቻላል፡፡ ያ ምክር እንዲሰጥ የሚጠየቅ ሰው የተጠየቀውን ምክር ቢሰጥ ልክ ነው፤ በምክሩም ሰውዬውን ሊጠቅመው ወይም ሊጎዳው ቢችል በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ስለሆነ የሁለቱ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ እንጂ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ” እንዲሉ ሁሉም በዘፈቀደ ብድግ እያለ “የኔ ካንተ ይበልጣል!” ቢል አንኗኗርም፡፡ የዓለማችንን ቅርጽ አስጠሊታ ካደረጓት መካከል አንዱ ይህ ችግራችን ነው፡፡

ማንኛውም ዓይነት አክራሪነት ጎጂ ነው፡፡ አክራሪነት ደግሞ ገደቡን ያለፈ ፍቅር ወይም ጥላቻ ነው፡፡ ምክንያታዊነት የሚጎድለው አንዳች ውሳኔ ታላቅ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ሚዛናዊነት የሚጎድለው አንድ ነገር ጠንቁ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ከስሜትና ከሞቅታ ወጣ ማለትና በትክክለኛ የአእምሮ ሚዛን መፍረድ ለዘለቄታዊ መልካም ተራክቦ ጠቃሚ ነውና በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም፡፡ “አሥሬ ለካ አንዴ ቁረጥ” ይባላል፡፡ ከኋላ ጸጸት የፊት ብስለትና አስተዋይነት ይሻላልና ሁላችንም አደብ እንግዛ፡፡ 

ሀገራችን ግን መንግሥትና ሕዝብ ማለትም ለኮሮና እጁን የማይሰጥ ሕዝብ የሚኖራት መቼ ይሆን? ይሄ ኮሮና የሚሉት ደግሞ… ለነገሩ እርሱስ ገር ነው፡፡ አሉ እንጂ ከኮሮና የበላለጡ ትላልቅ በጥባጭ ኮሮናዎች ማለቴ ከነአልሲሲ ቀለብ የሚሰፈርላቸው ኮርማዎች፡፡ ሀገርን ለማፈራረስ ከሕወሓት ቀብድ የተሰጣቸው አያሌ ልደታዎች!   ፐ! ቅኔ ብሎ ዝም ነው …

martyrof2011@gmail.com

Filed in: Amharic