‹ከግብፅ ጋር ከነበራት ዘላቂ ጉዳትና ከኢትዮጵያ ጋር ከሚኖራት ዘላቂ ጥቅም የሚሻለውን መምረጥ የሱዳን ፋንታ ነው!!!››
– ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ
በአአዩ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ
‹‹ከግብፅ ጋር ከነበራት ዘላቂ ጉዳትና ከኢትዮጵያ ጋር ከሚኖራት ዘላቂ ጥቅም የሚሻለውን መምረጥ የሱዳን ፋንታ ነው›› ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም
አቀፍግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪና ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በያዘችው ወቅታዊ አቋም ዙሪያ በተለይለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ትናንት እንደገለጹት፤ በጠቅላላው በናይል ውሃ ልማት ጉዳይ የሱዳን ዘላቂ ጥቅም የሚገኘው ከኢትዮጵያና ከሌሎች የውሃ አመንጪ አገሮች ጋር በመተሳሰር እንጂ ለዘመናት ስትጫናትና በብዙ ጣልቃ ገብነት ስትጠቀምባት ከነበረችው ከግብፅ ጋር መሆን አልነበረበትም፡፡
ሱዳን ከግብፅ ጋር ከነበራት ዘላቂ ጉዳትና ከኢትጵያ ጋር ከሚኖራት ዘላቂ ጥቅም የሚሻለውን መምረጥ የእርሷ ፋንታ ነው፡፡የህዳሴ ግድብ ሲጀመር የሱዳን መንግስት በአባይም ሆነ በአጠቃላይ በናይል ውሃ ጉዳይ ከግብፅ ጋር አባሪ ተባባሪ እንደነበረ ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ ፤ በተለይም በትብብር ማዕቀፍ ድርድር ወቅት እውነታው በግልፅ የታየ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴግድብ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ግድቡ ለሱዳን በብዙ መልኩ የሚጠቅማት መሆኑን የሱዳን መንግስት ካረጋገጠ በኋላ የግድቡን ግንባታ ሲደግፍ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ የመርህ መግለጫ ድርድር ወቅት (ODP) ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን ሆና ድንበር ተሻጋሪ ውሃ አጠቃቀም በፍትሀዊና በተመዛዘነ መርህ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው አስረግጣ መከራከሯንም አስታውሰዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የመርህ ስምምነቱ ይህንኑ ሀሳብ ያካተተ ብቻ ሳይሆን ግብፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም መርህ ተቀብላ እንድትፈርም ሆኗል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሱዳን ሚና ጉልህ ነበር:: በአሁኑ ወቅት ግን የሱዳን መንግስት የመዋወላወል ሁኔታ እያሳየ መጥቷል፡፡ የወቅቱ የሱዳን መንግስት ጊዜያዊ ብሄራዊ ጥምረት መንግስት እንደመሆኑ ብዙ የውስጥ ተቃርኖና የውጭ ተፅዕኖ እያስተናገደ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የሱዳን መንግስት ይህንን ውስጣዊ ተቃርኖዎችና ውጪአዊ ጫና ከዘላቂ ብሄራዊ ጥቅም አንፃር እየመዘነ ካልሄደ መልካም ውጤት አይኖርም፡፡ለአብነት ሱዳን ከግብፅ የቅርብ ጉርብትና ብቻ ሳይሆን የረጅም ዘመን ትስስር እንዳላት የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፣ ሱዳን በታሪኳ የግብፅን ቅኝ ገዥነትና ባለብዙ እጅ ጣልቃ ገብነት ማሳተናገዷን ፤ ዛሬም ቢሆን የሱዳንን መሬት ግብፅ በሀይል ይዛ እንደምትገኝም ገልጸዋል:: ሱዳን አገሯን አቋርጦ የሚሄደውን የናይል ውሃ በእኩልነትና በፍትሀዊነት እንዳትጠቀም ግብጽ ጫና ስታሳርፍባት መኖሯንም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የናይል ውሃ አመንጪ አገሮች ግዛታቸው ውስጥ የናይልን ውሃ እንዳያለሙ አባሪ ተባባሪ ለማድረግ ተጽዕኖም ስትፈጥር መቆየቷን አስረድተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለጻ፤ ሱዳን ከግብፅ ጋር ያላት የረጅም ጊዜ ትስስር ለዘላቂ ብሄራዊ ጥቅሟ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ በግልፅ የታወቀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሱዳን አብዛኛውን ውሃ የምታገኘው ከኢትዮጵያ መሆኑን በመገንዘብ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚሰጣትን በርካታ ጠቀሜታ በማመዛዘን እኤአ 2013 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጎን ሆና የግድቡን ግንባታ ስታበረታታና ስትደግፍ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን በቅርብ መሙላት እንደምትጀምር ሱዳን ታውቃለች፡፡ ይህን አካሄዷን በሚቃረን መልኩ ‹‹ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ከመጀመርዋ በፊት ከግብፅ ጋር ስምምነት ያስፈልጋታል›› በሚል መግለጫ ማውጣቷ አፍ ማበላሽት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ግድቧን ከመሙላት የሚያግዳት አለመኖሩን መገንዘብ ነበረባት፡፡ ይልቅስ የሱዳን ብሄራዊ ጥቅም የሚገኘው በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላል ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችውን ትብብር መቀጠል ስትችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡የታላቁ የህዳሴ ግድቡ ስራ በአሁኑ ወቅት 73 በመቶ መድረሱ፤ የውሃ ሙሊት ስራውም በመጪውሐምሌ ወር እንደሚጀመር ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012 – አስቴር ኤልያስ