>
5:33 pm - Sunday December 5, 3204

ኢትዮጵያ እና ግብጽ (ሳሚ ዮሴፍ)

ኢትዮጵያ እና ግብጽ 

 

የግብጽ መንግሥት ሀገር ለመያዝ እንደሞከረና የወርኔር ሙንዚንጀር ሞት 

ሳሚ ዮሴፍ
የግብጽ መንግሥት የጥንቱን ገናናነት መልሶ ለማቋቋም ወደ ኢትዮጵያም ለመግባት ሲያስብ በፊት የአጤ ቴዎድሮስ ኃይለኝነትና የጀግንነት ስም አግዶ ይዞት ነበር። ከዚያ በኋላ ምንም እንኳን የአጤ ዮሐንስ ጀግንነት ያነሰ ባይሆንም የግብጽ መንግሥት ግዛቱን የሚያስፋፋበት ጊዜ በመድረሱ በዚያ ሰዓት የነገሰው ኢስማኤል የሚባለው የግብጽ ንጉሥ
በሜድትራንያን አጠገብ ከሚገኘው ከራሱ ግዛት ከግብጽ አንስቶ ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያንም ጨምሮ ግዛቱን እስከ ህንድ ውቅያኖስ ለማድረስ ያስብ ነበር። በዚህም ምክንያት በቱርክ መንግሥት እየተገዛ አስቀድሞ ወታደር እየላከ በኢትዮጵያ ሰሜን የሚገኘውን ከረነን፣ በምስራቅ ያለውን በርበራንና ዘይላን፣ ሐረርንም ጭምር ይዞ ሲኖር ቀጥሎ አንዱ ከታጁራ (ከጅቡቲ)፣ ሁለተኛው ከምጥዋ ተነስቶ የኢትዮጵያን የሰሜን ግዛት የሚይዝ ከሁለት የተከፈለ የጦር ሠራዊት አዘጋጀ።
አጤ ዮሐንስ ለአውሮፓ መንግሥታት የግብጽ ጦር ወሰን እያለፈ መሆኑን በተለያየ ጊዜ የስሞታ ደብዳቤ በተለያየ ወቅት ቢጽፉም የአውሮፓ ኃያላን የስሞታው ደብዳቤ የሚያሳስባቸው አልሆነም ግብጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በንግድ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ አስፋፍታ ይዛ ስለነበረ ሁሉም የመንግሥታቸውን ጥቅም መጠበቅ ስለነበረባቸው በዚህ በኢትዮጵያና በግብጽ የወሰን ክርክር ኢትዮጵያን ብንደግፍ የምናገኘው ጥቅም አይኖርም በሚል አቋም ወሰዱ። ለዚሁም ማረጋገጫ የጀርመኑ ጠቅላይ ሚንስትር አቶን ቢስማርክ ለጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት ለዊልሄልም በጻፈው ማስታወሻ ላይ “…በግብጽና በኢትዮጵያ የወሰን ክርክር ለመግባት ለጀርመን ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጥቅም የለም። በዚህ ጉዳይ የከዲቩን ምኞት  የሚጻረር አቅዋም ብንወስድ በእሱ ሀገር ያለንን ቁም ነገር ያለውን የንግድ ጥቅማችንን እናበላሻለን…” ብሎ ያለው የሁሉም አስተያየት ነው። በኦርቶዶክስ እምነቱ የተማመኑበት የሞስኮ መንግሥት ከእንግሊዝና ከጀርመን መንግሥት የተለየ አልነበረም።
በዚህም ምክንያት የምኒልክን ከዮሐንስ ጋር አለመተባበር  እንዲሁም የነ ራስ ወልደ ሚካኤል፣ ራስ ወልደ ስላሴ፣ ራስ ወልደ ማርያም ከአጤ ዮሐንስ መሸፈት የነ አለቃ ብሩ ክዳት  ለሙሲንጀርና በእርሱም ስብከት ለተማመነው ለከዲቭ እስማኤል ኢትዮጵያን ወርሮ ከሱዳን ጋር የመደባለቁ ጉዳይ
ምንም ዓይነት እንከን የሌለበት ጥርጊያ መንገድ መስሎ ታያቸው።
ከታጁራ ለሚመጣው የጦር ጠቅላይ አዛዥ ወርኔር ሙንዚንጀር ፓሻ የሚባለው የስዊስ ተወላጅ ተሾመ።
እሱም በካይሮና በእስክንድርያ የግብጾችን ልማድ ይዞ ካደገ ወዲህ ወዲያው ለግብጽ መንግሥት አገልግሎት ወደ ምጥዋ መጥቶ ከምጥዋ ወደ ከረን፣ ከከረን ወደ በርበራ እየተመላለሰ የኢትዮጵያን ሰሜን ደህና አድርጎ በመመርመሩ ትግርኛ ቋንቋንም ለማወቅ ቻለ። በአንድ ወቅት በሱዳንም ጠቅላይ ሀገር ገዥ ሆኖ ነበር።
የእንግሊዝ ጦር በጄነራል ናፒዬር አዝማችነት አጤ ቴዎድሮስን ለመውጋት በመጣ ጊዜ መንገድ በመምራትና በማስተርጎም ደህና አድርጎ ረድቷል። በዚህ ምክንያት በእንግሊዞችና በፈረንሳዮች ተከብሮ እስከ ቆንስልነት ደረጃ ደርሶ ነበር። ይህንንም ከአጤ ዮሐንስ ጋር የሚደረገውን ጦርነት የተመለከተው በዚያው በመቅደላው ጦርነት ዓይነት ነበር። ከፈረንሳዮች ወደ ግብጾች ዞሮ የምጥዋ ሀገረ ገዥነት ሲሾም የ”ቤት” ማዕረግ ተሰጥቶት የነበረውን አሁን ደግሞ የግብጽ ጦርን በእርሱ አሳሳቢነትና አመራር ቦጎስንና አካባቢውን ሲይዝ ባላባቶቹም ያለምንም ተቃውሞ ተገዥነታቸውን ሲያረጋግጡ በከዲቭ እስማኤል ፈቃድ ከፍ ያለውን የፓሻነት ሹመት አገኘ። ባለቤቱም የቦጎስ ተወላጅ ነበረች። በዚህ ላይ የአጤ ዮሐንስ ታማኝ አገልጋይ አለቃ ብሩ ግብጽ ሀገር ድረስ ሄደው ጳጳሱን አቡነ አትናቴዎስን በማምጣትና አጤ ዮሐንስን በማንገሥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት አሁን ንጉሠ ነገሥታቸውን ከድተው ከሙሲንጀር ጋር በመሆን ስለተባበሩለት ሁኔታው መልካም ነገር የያዘ መሰለው።
ሙንዚንጀር ወታደሮቹን ይዞ ከታጁራ ተነስቶ የአውሳን በርሀ ሲጓዝ ውሎ ከመሐመድ አንፋሪ ግዛት  አሰል የሚባለው ስፍራ ላይ ሲደርስ ስለመሸበት በዚያው ስፍራ ላይ ለሊቱን  ደንከሊዎች አግኝተው ከበቧቸው።
ከእርሱም ጋር  ከአጤ ዮሐንስ የከዱት አለቃ ብሩና ገብረስላሴ ንጉሤ የሚባሉ አብረው ነበሩ። ወታደሮቹም በበረሀ ሲጓዙ ውለው ስለደከሙ የከበደ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበርና ምንም ሳይሰሙ ሙንዚንጀር ፓሻ ከነሚስቱ ወደ ተኛበት ስፍራ ደንከሌዎቹ (ጥልጣሎቹ) ደረሱ። ሙንዚንጀር ከእንቅልፉ ነቅቶ ሦስቱን ደንከሌዎች ከመካከላቸው በጠበንጃ እንደገደለ፤ ወዲያው እነሱም በጦርና በጩቤ ወግተው ገደሉት። ወታደሮቹም ከእንቅልፋቸው ነቅተው እየተደናበሩ ሲሸሹ ደንከሌዎቹ እየተከተሉ ፈጁዋቸው።
በሰሜን በዘይላ በኩል ለሚዘምተው ራውፍ ፓሻና የጠቅላይ ሚንስትሩ የኑፓር ፓሻ የልጅ ልጅ፣ የእርሱ ምክትል ኮሎኔል አራንድሩፕ (የዴንማርክ ተወላጅ) ተመድበዋል።
ዋናውም ሀሳብ በሰሜን ራውፍ ፓሻ በትግራይ ዮሐንስን የከዱትን መኳንንት ከሙስሊሞቹ ባላባቶች ጋር አስተባብሮ በምስራቅ በኩል የወሎንና የአውሳን፣ እንዲሁም የአዘቦ ኦሮሞን ባላባቶች ቀስቅሶና ቢቻል ምኒልክንም ጨምሮ ዮሐንስን በሁለት ወገን አዋክቦና አዳክሞ በመጣል የግብጽን የበላይ ገዥነት በኢትዮጵያ ለመመስረት ነበር።
በ1868 መስከረም 17 ቀን ኮሎኔል አሬን ድሩፕ የጦሩ የበላይ አዝማች ሆነ። የዚህ ጦር ዋና አላማ ከምጥዋ ተነቃንቆ ወደ ደጋው ወደ አስመራ ወጥቶ ሐማሴንን፣ ሰራዬንና አካለ ጉዛይን ወርሮ እስከ መረብ ወይም እስከ አድዋ በመዝለቅ የተያዘውን ሰፊ ግዛት በቀጥታ የማስተዳደሩ ተግባር በግብጽ የበላይ ገዥነት የሚወሰን ጉዳይ መሆኑን እስማኤልና አሬን ድሩፕ ተጻጽፈውበት ይገኛል።
ይህንንም ሀሳብ ዮሐንስ የተቃወሙ እንደሆነ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ በዮሐንስ ላይ የሚነሱበትን መሣፍንት አግዟቸው የሚል ደብዳቤ ከእስማኤል ለአሬንድሩፕ ደርሶታል።
አሬንድሩፕ መስከረም 26 ቀን 1868 ዓ.ም ምጥዋ ገብቶ ሲደራጅ ሰንብቶ ከምጥዋ ተንቀሳቅሶ በጥቅምት 14 ቀን ሰሀጢንና ዶጋሊን አልፎ ጊንዳዕ ደረሰ። ከዚያም የግብጽ ጦር ግማሹ ሐማሴን የቀረው አካለ ጉዛይ ሲገባ…
በንጉሠ ነገሥቱ በአጤ ዮሐንስ ትእዛዝ የሐማሴኑ ገዥ  ደጃች ገብሩ፣ የሰራዬው ደጃች ማሩ ግዛታቸውን ለቀው ንጉሠ ነገሥቱ ወደ አሉበት ወደ ዓድዋ ሄዱ።
በዚህ ጊዜ ለማታለልና ለማዘናጋት በከዲቭ እስማኤል እንደታዘዘው የጦሩ አዝማች “..የግብጽ መንግሥት ሐበሻንም ለመያዝ ሐማሴንንም ለመውሰድ ምኞት የለውም። ነገር ግን
ከእርስዎ በኩል ጀኔራል ኪርክሃም የሚባለው እንግሊዛዊ የአስመራና የጊንዳዕ ሀገር ገዥ ተብሎ መሾሙን እስማኤል ከዲቭ ስለሰማና በወደብ ላለው ግዛቱ ስለሰጋ ደግሞም እንግሊዙ አገዛዙ መጥፎ የሆነባቸው ባላባቶች ለከዲቭ አቤቱታ ስላሰሙ ወደ ደጋው ከፍ አልን እንጂ ከዲቩ እንደ ቀድሞው ከእርሶ ጋር በሰላም ለመኖር እንጂ ለመዋጋት ምንም ዓይነት ምኞት የለውም…”  የሚል ደብዳቤ ጽፎ ላከ።
ይህን የመሰለውን የማዘናጊያ ደብዳቤ ከላከ በኋላ  ኮሎኔል አሬንድሩፕ በ24 ሬጅመንት የተከፈሉ 2,500 የሠለጠኑ የግብጽና የሱዳን ወታደሮች፣ ብዙ የረሜንግቶን ጠበንጃዎች
6 የተራራ መድፎችና 6 ሮኬቶች እንደያዙ  ጉዞቸውን ጀመሩ።
ለተጻፈላቸው የማዘናጊያ ደብዳቤ አጤ ዮሐንስ ምንም ዓይነት መልስ ስላልሰጡ አሁንም አሬንድሩፕ
አብድ ኤልራሂምን (አብዱልራሂም) የሚባለውን ልኮ አጤ ዮሐንስ ስለ ሰላም እንዲነጋገሩ ቢያስጠይቅ አጤ ዮሐንስ መልስ ስለአልላኩ ጦሩ ጉዞውን ወደ ፊት ቀጥሎ መረብ ወንዝ ደረሰ።
ስለዚህ ጦርነትና ወረራ የአጤ ዮሐንስ ዜና መዋዕል እንደዚህ ሲል ያትታል “…አጤ ዮሐንስ በነገሱ በአራተኛው ዓመት ከግብጽ እስማኤላውያን መጥተው የአጋዚ ሀገር የሆነችውን
ሐማሴን የምትባለውን ወረሩ፤ በዚህ ጊዜ እስማኤላውያን የተባሉት ቱርኮች (ግብጾች) ወደ ሰፈሩበት ሄደው ሁኔታቸውን የሚሰልሉ ሰዎች ልከው እነዚህ ሰዎች ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው የቱርኮችን (የግብጾችን) የፈረሶቻቸውን ብዛታቸውን፣ ጽናታቸውን ገለጡላቸው” ካለ በኋላ
 ንጉሠ ነገሥቱ አጤ ዮሐንስ “ኃይለኛ በፈረሱ ብዛት አይድንም ፈረሰኛም በፈረሱ ጽናት አያመልጥም” ብለው ዓይናቸውን ወደ ሰማይ ሰቅለው “ሕዝብህን ከጥፋት አድን፣ ርስትህንም ባርካት፣ ለኛ ለአገልጋዮችህም የማሸነፍ ኃይል ስጠን” ብለው ጸልየው ወደ ጦርነቱ ጉዞ ማድረጋቸውን ያመለክታል።
በሙሴ ሼን የታተመው ሌላው የግዕዝ ዜና መዋዕል በነገሡ በአምስተኛው ዓመት እስማኤላውያን ብዙ መድፍና ጠበንጃ ይዘው ሰራዬ መጥተው ስለ ነበር አጤ ዮሐንስ ይህንኑ ሰምተው መረብን ተሻግረው ከእስማኤላውያኑ ጋር መሬት በደም እስክትታጠብ ድረስ ብዙ እልቂት አድርገው ከጠላቶቻቸው አንድም ሳይተርፍ መፍጀታቸውን ያመለክታል።
በምጥዋ የፈርንሳይ ቆንስል ደሳርዜክ በዚሁ ጊዜ የፈረንሳይ መንግሥት መልእክት ይዞ ወደ ዓድዋ መጥቶ  ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ሆኖ ሁሉንም ይመለከት ስለነበር ስለ ጉዞውና ስለ ጦርነቱ አጀማመር በበኩሉ እንዲህ ይላል…
“ዮሐንስ በ2 ኅዳር 1875 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) ቤተ መንግሥታቸውን በለቀቁ ጊዜ ታላቅ የመሬት መናወጥ ተቀስቅሶ ከሸሎዳ ተራራ ላይ የተፈነቃቀለው የድንጋይ ናዳ እየተንከባለለ ከንጉሡ እግር ሥር ሲደርስ፤ ንጉሡ በግንባራቸው ተደፍተው ለሠራዊት አምላክ ሰግደው ቀና ካሉ በኋላ ” ይህ አስደንጋጭ ምልክት አረመኔዎቹ ግብጾች በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ተቀብረው ለመቅረታቸው አምላክ የሰጠው ምልክት ነው” ብለው ከተናገሩ በኋላ ከዓድዋ የሦስት ሰዓት ጉዞ ራቅ ብለው ንጉሠ ነገሥቱ እንደ ሰፈሩ የጦር ሠራዊቱም ቁጥር ከያለበት ተሰብስቦ በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺ እስከ ሰባ ሺ መድረሱን አቡነ አትናቴዎስም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በመተባበር ጦርነቱ ቅዱስ ጦርነት በማለት ወታደሮቹን ማበረታታቸውን ይገልጻል”
ከዚህ በኋላ የሁለቱም የጦር ሠራዊቶች ጉንደት ላይ ተያዩ።
በዚህ ጊዜ ኤረንድሩፕ ግማሹን ጦር በጉንደት ትቶ ኮንት ዘኪ ወዳለበት ወደ ከሳድ ዒቃ እንደተደባለቀ ኢትዮጵያውያኑ ተጠግተው በኃይል ውጊያ ጀመሩ። እርሱም በመጀመሪያ የወጠነውን የማጥቃት ተግባር ትቶ ምቹ ስፍራ ይዞ መከላከል ጀመረ። ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ በነ ሻለቃ
 (ኋላ ራስ) አሉላ፣ በነ ደጃች ሐጎስ፣ በነ ደጃች ተሰማ የሚመራው ጦር ወታደሩን ስለ ፈጁበት ካለበት ስፍራ ለቆ ወደ ጉንዳጉንዲ ሸለቆ ተዛውሮ የአንድ ሰዓት ጦርነት እንደ ተደረገ ግብጾቹ ሙሉ በሙሉ ተሸነፉ። አሬንድሩፕ ከጦርነቱ ሜዳ ላይ ሞቶ ተገኘ። ግማሹ ሲሞት ወይም ወደ ኋላው ሲሸሽ 150 ግብጻውያንና ሱዳኖች 3 የሀገር ተወላጅ የቅጥር ወታደር ሹማምንት ሲማረኩ አንዳንዶቹ በሽሽት አመለጡ።
ከኢትዮጵያ ወገን መጀመሪያ መረብ አጠገብ በተደረገ ጦርነት 31 ወታደሮች ሲሞቱ 55 መቁሰላቸውን በጉንዳጉንዲው ጦርነት 521 ሞተው 335 መቁሰላቸውን ደሳርዜክ ያመለክታል።
ከዚህም አያይዞ ንጉሠ ነገሥቱ ከዓዲኳላ “የምሥራች ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ፤ በእግዚአብሔር ቸርነት ጠላቶቼን አሸንፍሁዋቸው” የሚል የደስታ ደብዳቤ ለእርሱ እንደላኩለት ደሳርዜክ ይገልጽና፤ የጦርነቱን ሁኔታ ለመንግሥት የጻፈው ራፖር ላይ ከኮሎኔል አሬንድሩፕ ጋር ሆኖ ይዋጋ የነበረው ኮንት ዘኪ የሚባለው የኦስትሪያ ሀንጋሪ ተወላጅ በክሳድ ዒቃ በተደረገው ጦርነት ላይ ክፉኛ ቆስሎ በ8ኛው ቀን የእርሱን የደሳርዜክን ዓድዋ መገኘት ሰምቶ ሳይበላ፣ ህክምና ሳያገኝ ክፉኛ ተጎሳቅሎ ቆስሎና ተልቶ በመዳፉም በጉልበቱም እየዳኸ ሲሄድ ከመንገድ አግኝቶት እንደ ረዳውና በኋላም እንደ ሞተ ይገልጻል።
ክብር ኢትዮጵያን በደማቸው ላቆዩልን ጀግኖቻችን!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic