>

ከ60ሺ በላይ ሴቶችን ሕይወት  የታደጉ የማህጸን ስፔሻሊስቷ ዶክተር ካትሪን ሐምሊንን እንዘክር... (ልዑል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

ከ60ሺ በላይ ሴቶችን ሕይወት  የታደጉ የማህጸን ስፔሻሊስቷ ዶክተር ካትሪን ሐምሊንን እንዘክር…

ልዑል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ዛሬ፣ ግንቦት 15 (May 23) ዓለም አቀፍ የፀረ-ፊስቱላ ቀን (International Day to End Obstetric Fistula) ነው፡፡
 
ይህን ምክንያት በማድረግም በ61 ዓመታት ወርቃማ የኢትዮጵያ ቆይታቸው በፊስቱላ ላይ ዘመቻ አካሂደው ከ60ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሕይወት የሰጡትን አንጋፋዋን የፅንስና የማህጸን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊንን ማስታወስ ይገባል፡፡
ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን በ1916 ዓ.ም ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ውስጥ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኒው ሳውዝ ዌልስ (New South Wales) ግዛት ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ገብተው የሕክምና ትምህርት አጠኑ፡፡ የልምምድ ቆይታቸውን ቅዱስ ዮሴፍ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባሉ ሆስፒታሎች አጠናቀቁ፡፡ ከዚያም ክራውን ስትሪት ወደተባለው የሴቶች ሆስፒታል (Crown Street Women’s Hospital) ገብተው የሁልጊዜም ምኞታቸው የነበረውን ሴቶችን የመርዳት ተግባራቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ከዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን ጋር የተዋወቁትና ትዳር የመሰረቱት፡፡
በ1951 ዓ.ም ጥንዶቹ ዶክተሮች የኢትዮጵያ መንግሥት የአዋላጅነት ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ለመክፈት ያለውን ፍላጎት የሚገልፅ ማስታወቂያ ተመለከቱ፡፡ ሪቻርድ ከተባለው የስድስት ዓመት ልጃቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተቋሙን የማቋቋም ኃላፊነትን ተረከቡ፡፡ ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እነዚህ ጥንዶች እስከዕለተ ሞታቸው ድረስ በኢትዮጵያ ይቆያሉ ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡
ጥንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ስራቸውን የጀመሩት በልዕልት ጸሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ እነካትሪን የተመለከቱት በወሊድ ወቅት በሚከሰት ችግር (ፊስቱላ) ምክንያት የሚሰቃዩ ሴቶች መከራ ፈፅሞ ያልጠበቁት ሆኖባቸው ነበር፡፡ እነርሱ ኢትዮጵያ ከመድረሳቸው በፊት የፊስቱላ ችግር ያለባቸው ሴቶች፣ እንኳን ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ይቅርና እንደሰው የሚቆጥራቸው አጥተው የሚደርስባቸው መገለል እጅግ በጣም አስከፊ ነበር፡፡
እንዲህ ዓይነት ስቃይ ከዚህ ቀደም አጋጥሟቸው የማያውቁት ጥንዶቹ ዶክተሮች የራሳቸውን የሕክምና መመሪያ በማዘጋጀት የኢትዮጵያውያኑን ሴቶች ሕይወት የመታደግ ተግባራቸውን ጀመሩ፡፡ ተግባራቸው በሰዎች ዘንድ ሲሰማ በርካታ ሴቶች ለሕክምና መጉረፍ ጀመሩ፡፡ በመጀመሪያ ልዕልት ጸሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ 10 አልጋዎች ያሉት ክሊኒክ አቋቋሙ፡፡ በግንቦት 1968 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል (Addis Ababa Fistula Hospital)ን ከፈቱ፡፡
እ.አ.አ በ1993 የዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለባለቤታቸው ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ከባድ ፈተና ሆነባቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ስቃይ ከሁሉም ነገር በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የተረዱት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሐዘኑን ተቋቁመው ሴቶችን የመርዳት ተግባራቸውን ቀጠሉ፡፡
የዶክተር ካትሪን ሴቶችን የመርዳት ተግባራቸው ሴቶቹን በማከም ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ አዋላጅ ነርሶችን የማሰልጠን ሕልማቸውን ለማሳካት በ2000 ዓ.ም የሐምሊን አዋላጅ ነርሶች ማሰልጠኛ ኮሌጅ (Hamlin College of Midwives) እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ አዋላጅ ነርሶቹ ስልጠናቸውን ካጠናቀቀቁ በኋላ በገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ ክሊኒኮች ተመድበው ያገለግላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የፊስቱላ ችግር ተጠቂዎች ካሉባቸው አገራት የሚመጡ ሰልጣኞችንም ያስተምራል፡፡ ከነዚህም መካከል የኬንያ፣ የኮንጎና የባንግላዴሽ ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ዶክተር ካትሪን ለታማሚዎቻቸው በሚሰጡት የህክምና ዓይነት (Hamlin Model of Care) በእጅጉ እንደሚኮሩና እንደሚደሰቱ ይናገሩ ነበር፡፡ ‹‹ … ችግሩ የተከሰተበትን/ሕመም የሚሰማበትን ቦታ ብቻ አናክምም፤ሕክምናችን ለታማሚው ሙሉ ፈውስ የሚሰጥ የፍቅር፣ የእንክብካቤና የግንዛቤ ሕክምና ነው …›› ብለዋል፡፡ በዚህ ሕክምናቸውና በአጠቃላይ የበጎ አድራጎት ስራዎቻቸው ምክንያት ከፊስቱላ ችግር ተላቀው መደበኛ ሕይወታቸውን የሚኖሩት ብቻም ሳይሆኑ ዶክተር ካትሪንን የሚያውቋቸው ሁሉ ‹‹እማዬ›› እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡
ዛሬ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ (Hamlin Fistula Ethiopia) በመባል የሚታወቀው ማዕከል ከ550 በላይ ሰራተኞችን (አብዛኞቹ በዶክተር ካትሪን ሐምሊን የሰለጠኑ)፣ ስድስት ሆስፒታሎችን፣ ‹‹ደስታ መንደር›› የተባለ የማገገሚያ ማዕከልን፣ የሐምሊን አዋላጅ ነርሶች ማሰልጠኛ ኮሌጅን እንዲሁም በሐምሊን የሚታገዙ 80 የማዋለጃ ክሊኒኮችን አስተሳስሮ የያዘ ተቋም ሆኗል፡፡ ማዕከሉ ፊስቱላን ከማከም በተጨማሪ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከልና ከችግሩ የተላቀቁ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና የበቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ ስድስት የሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡ ይህም ብዙዎቹ የፊስቱላ ታማሚዎች በገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን የችግሩ ተጠቂዎች በተነፃፃሪነት በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ምስጋና ለእነዶክተር ካትሪን ሐምሊን ይሁንና ባለፉት 61 ዓመታት ከ60ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በወሊድ ወቅት በሚከሰት ችግር (ፊስቱላ) ምክንያት ከገቡበት መከራ ውስጥ ወጥተው አንገታቸውን ቀና አድርገው ለመጓዝ/ለመኖር በቅተዋል፡፡
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን እ.አ.አ በ2001 ጆን ሊትል ከተባለ አውስትራሊያዊ ጋዜጠኛ ጋር በመተባበር ‹‹The Hospital By the River: A Story of Hope›› በሚል ርዕስ የሕይወት ታሪካቸውን ጽፈው አሳትመዋል፡፡ በዚህ መጽሐፋቸው ላይም የእርሳቸውና የባለቤታቸው ተግባር ‹‹በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ከሚደረጉ እርዳታዎች መካከል አንዱ ነው›› በማለት ገልጸውታል፡፡ እ.አ.አ በ2016 የታተመው የመጽሐፉ ሁለተኛ እትም ቀዳሚ ቃል የተፃፈው በወቅቱ በአውስትራሊያ የንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ወኪል በሆኑት ኩዊንቲን ብራይስ ነው፡፡
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በዋጋ ለማይተመነው አበርክቷቸው በርካታ ሽልማቶችንና ክብሮችን ተቀዳጅተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
🔯 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሰብዓዊነት ሽልማት
🔯 የኦርደር ኦፍ አውስትራሊያ (Member of the Order of Australia – AM) ሽልማት
🔯 የአውስትራሊያና ኒው ዚላንድ ጦር ዘማቾች (ANZAC) የሰላም ሽልማት
🔯 የታላቁ የቅዱስ ጊዮርጊሥ የላቀ የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት
🔯 የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ኮሌጅ የክብር የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት
የዞንታ ዓለም አቀፍ ሽልማት
🔯 የሮተሪ ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ የሰላም ሽልማት
🔯 የአሜሪካ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ኮሌጅ የክብር ሽልማት
🔯 የአውስትራሊያ ከፍተኛ ብሔራዊ ሽልማት
🔯 የዓለም አቀፍ የጤና ምክር ቤት የላቀ አፈፃፀም ሽልማት
🔯 የኤደንብራ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ኮሌጅ የክብር ሽልማት
🔯 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስነ ሕዝብ ሽልማት
🔯 የአሜሪካ ሕክምና ማኅበር/የዶክተር ናታን ደቪስ ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ሽልማት
🔯 የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሽልማት
🔯 የአውስትራሊያ አስተማሪዎች ኮሌጅ የክብር ሽልማት
🔯 የእንግሊዝ ሕክምና ማኅበር ሽልማት
🔯 የምርጥ የሰብዓዊና የማዕበራዊ አገልግሎት ሽልማት (ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝደንት)
🔯 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሽልማት
🔯 የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የሕይወት ዘመን ሽልማት
🔯 የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የላቀ አፈፃፀም ሽልማት (ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝደንት)
🔯 የዓለም የስርዓተ ፆታ ማኅበር የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት
🔯 የአውስትራሊያ ሕክምና ማኅበር ሽልማት
🔯 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውስትራሊያ ማኅበር ሽልማት
🔯 የ2009 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት … ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከነዚህ ሽልማቶች በተጨማሪም ዶክተር ካትሪን ሐምሊን እ.አ.አ የ1999 እና የ2014 የኖቤል የሰላም ሽልማት እጩ ሆነው ቀርበው ነበር፡፡ እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም ‹‹ተለዋጭ ኖቤል (Alternative Nobel Prize)›› በመባል የሚታወቀውና አስቸኳይ ምላሽ ለሚሹ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች/ችግሮች ተግባራዊና ተምሳሌታዊ የሆኑ መፍትሄዎችን ላፈለቁ አካላት የሚሰጠው የ‹‹ራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት (The Right Livelihood Award)›› ዓለም አቀፍ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፓስፖርትና የክብር ዜግነት የምስክር ወረቀት ለዶክተር ካትሪን የሰጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹በኢትዮጵያ የፊስቱላ ሕመም ሰለባ ለሆኑ ሴቶችና እናቶች የተለየ ፍቅርና ሕክምና በመስጠት ለረጅም ዓመታት የሚደነቁ ተግባራትን ያከናወኑት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ከኢትዮጵያውያን አንዷ መሆን መቻላቸው የሚያኮራ ነው›› ብለው ነበር፡፡
ዶክተር ካትሪን በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ባልወለድባትም ከትውልድ አገሬ የበለጠ እወዳታለሁ … አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለአገሪቱና ለሕዝቧ ያለኝን ፍቅርና አክብሮት ተገንዝቦ የክብር ዜጋ እንደሆን ስለፈቀደልኝ ከምንም ነገር በላይ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል … የተሰጠኝ የክብር ዜግነት የጀመርኩትን የሰብዓዊና የሕክምና አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያደርግ ኃላፊነት ጥሎብኛል …›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
እ.አ.አ በ2011 በእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ የክብር የምሳ መርሃ ግብር ላይ እንዲታደሙ ከተደረጉ 50 ታላላቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ አውስትራሊያውያን መካከል አንዷ የኢትዮጵያውያን ባለውለታዋ ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ነበሩ፡፡ በ1996 ዓ.ም በኦፕራ ዊንፍሬይ የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ቀርበው ተሞክሯቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም ዝነኛዋ አሜሪካዊት ኦፕራ ዊንፍሬይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታልን እንድትጎበኝና ‹‹A Walk to Beautiful›› የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እንድትሰራ አስችሏታል፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያ ከፍተኛ ቦታ ካላቸው ሽልማቶች መካከል አንዱ የሆነው የፑሊትዘር ሽልማት (Pulitzer Prize) አሸናፊው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኒኮላስ ክሪስቶፍ ዶክተር ካትሪን ሐምሊንን ‹‹የወቅቱ እናት ቴሬዛ›› በማለት ገልጿቸዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በግንቦት 2011 ዓ.ም የዶክተር ካትሪን ሐምሊንና የባለቤታቸውን የዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን የመታሰቢያ ሐውልትን በመረቁበትና ለዶክተር ካትሪን ሐምሊን የወርቅ ሽልማት ባበረከቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ‹‹ … ዶክተር ካትሪን ከእኔ ዘር ውጪ አላይም የሚል አመለካከት በበዛበት በአሁኑ ወቅት ከዘር፣ ከቀለም፣ ከጾታ በላይ ሰውነትንና ሰውን ማዳን ያሳዩ እናት ናቸው። ህዝቡ ከእርሳቸው ተግባር መማር ይገባዋል፤ እኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ባለሥልጣናትም እንደዚህ ዘመን የማይሽረው ለትውልድ የሚጠቅም አሻራ ለማስቀመጥ መስራት ይጠበቅብናል … ዶክተር ካትሪን እ.አ.አ ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ስልሳ ዓመታት ከስልሳ ሺ በላይ እናቶችንና ሴቶችን መታደግ ችለዋል። ይህ ደግሞ 60ሺ ተገድሎ በሚጨፈርበት ሀገር 60ሺ ያዳኑ የድሀ እናት የሚያስብላቸው መልካም ስራቸው ነው … ›› ብለው ነበር፡፡
የካትሪን ሐምሊን ፊስቱላ ፋውንዴሽን ሊቀ መንበር ጁሊ ዋይት ‹‹ … ካትሪን በበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ የፈጠሩና አስደናቂና ሰብዓዊ የሆነ ሕይወት የኖሩ ሰው ናቸው፡፡ ሴቶችንና እናቶችን ለማገልገል ያላቸው በፍቅር የተሞላ የአገልግሎት ተነሳሽነትና ጠንካራ ጥረት/ስራ ሁላችንንም የሚያኮራና ልንማርበት የሚገባ ታላቅ ገድል ነው …›› ብለዋል፡፡
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩላቸው ዶክተር ካትሪን በምድር ላይ ከኖሩባቸው 96 ዓመታት መካከል አብዛኛዎቹን በወሊድ ምክንያት ችግር ለገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች በፍቅርና በትጋት እንዳዋሏቸው ገልጸው፤ ‹‹ … ዶክተር ካትሪን ላበረከቱት የሕይወት ዘመን አስተዋፅዖ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ እርሳቸው የጀመሩትን ፊስቱላን ከኢትዮጵያ ምድር ጨርሶ የማጥፋት ርዕይ እውን ለማድረግ ተግተን እንደምንሰራ ቃል እንገባለን›› በማለት ተናግረዋል፡፡
– – –
በ61 ዓመታት ወርቃማ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከ60ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወት የሰጡት አንጋፋዋ የፅንስና የማህጸን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን በ96 ዓመታቸው፣ በዕለተ ረቡዕ፣ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከ60 ዓመታት በላይ በኖሩባትና ባገለገሏት በኢትዮጵያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት አንጋፋዋ የፅንስና የማህጸን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሰሯቸው በጎ ስራዎች እንዲሁም ያሳዩት ፍቅርና ክብር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነው፡፡
Filed in: Amharic