>
5:13 pm - Sunday April 19, 1676

ጦቢት ተላሊት (መስፍን አረጋ) 

ጦቢት ተላሊት

 

“ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆችሚንህ እንደ ቸጉቬራ”::

ለምን ይሰማራል እንደ ቸጉቬራ

በላይ እያለለት የፋኖወች አውራ?

መስፍን አረጋ


ጀግኖቿን እያዋረደች ባንዶቿን እንደምታከብረው እንደ ጦቢያ ያለ ተላላ አገር ባለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡   እንዲህም እያደረገች የጀግና ማሕፀኗ ጨርሶ አለመንጠፉንና አሁንም ድረስ አንዳንድ ጀግኖችን እያፈራች መሆኗን ሳስበው ደግሞ ታምር ይሆንብኝና ዕደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር የሚለውን አስባለሁ፡፡  

ጦቢያ ማለትኮ የታላቁን ቀያኔ የክቡር ከበደ ሚካኤልን ቤት መሸታ ቤት አድርጋ ምንም ላልተከሩላት ለእስክንድር ፑሽኪን (Alexander Pushkin) እና አርተር ሪምባው (Arthur Rimbaud) አደባባይ የምትሰይም፣ ቤተመዘክር የምትሠራ አገር ናት፡፡  ጦቢያ ማለትኮ ያፍሪቃ መዲና በሆነችው ባዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘውን ዋና ጎዳና ባጸያፊው ዘረኛ በዊንስተን ቸርችል (Winston Churchill) ስም የምትሰይም አገር ናት፡፡  የዚህን እኩይ ግለሰብ አራዊታዊ አስተሳሰብ ለመረዳት ስለ ኦምዱርማን ውጊያ (Battle of Omdurman) የጻፈውን ሰቅጣጭ ዘገባ ቀንጭቦ ማንበብ ይበቃል፡፡    

Thus ended the Battle of Omdurman – the most signal triumph ever gained by the arms of science over barbarians. Within the space of five hours the strongest and best-armed savage army yet arrayed against a modern European Power had been destroyed and dispersed, with hardly any difficulty, comparatively small risk, and insignificant loss to the victors.“, Winston Spencer Churchill, The River War: An Historical Account of The Reconquest of the Soudan, page 164 ).

“ስልጡን የሰገል (science) ጦር በኋላቀር አረመኔወች ላይ የመጀመርያውን አስደናቂ ድል የተጎናጸፈበት የኦምዱርማን ጦርነት እነሆ ተጠናቀቀ፡፡  ያውሮጳን ዘመናዊ ሠራዊት የገጠመው ያረመኔወች ጠንካራ ሠራዊት ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳያደርስ ባምስት ሰዓት ውጊያ ብቻ በመትረየስ እየተቆላ ተረፍርፎ፣ እንደ ጉም በኖ፣ እንደ ጤዛ ተኖ ድምጥማጡ ጠፋ፡፡”    

በዚህ አጭር ጥቅስ ላይ ቸርቺል ራሱን በራሱ መቃረኑን እናስተውል፡፡  ባፍሪቃውያን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በማድነቅ አወድሶ፣  ተጨፍጫፊወቹን አረመኔወች ይላቸዋል፡፡  ዓለምን ከሂትለር አምባግነት (dictatorship) የታደገ የቻራስፍና ድባብ (bulwark of democracy) እያሉ ምዕራባውያን የሚያወድሱት እንዲህ ያለውን ሐሳበመፃጉ ነው፡፡

በነገራችን ላይ አውሮጳውያን እኛን አፍሪቃውያንን ቅኝ ሊገዙንና በሕዝባችን ላይ ያን ሁሉ ውርደት፣  በቅድስት አህጉራችን ላይ ደግሞ ያን ሁሉ ውድመት ያደረሱብን፣ ቸርችልን መሰል ዘረኞቻቸው እንደሚታበዩት ጀግኖች ወይም በጦርነት ጥበብ የተካኑ የጦርነት ሊቆች ሁነው ሳይሆን፣ በጊዜው ጨፍጫፊ ጦሳር (የሕዝብ መጨፍጨፊያ ጦር መሣርያ፣ weapon of mass destruction) ወይም ባጭሩ ጨጦ (WMD) የነበረውን መትረየስን በሰይጣናዊ መንፈስ በስፋት በመጠቀማቸው ብቻና ብቻ ነበር፡፡  ለዚህ ምሳሌ ደግሞ የቅርቡን የማይጨውን ውጊያ ትተን፣ ከታላቁ ያድዋ ውጊያ ስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ ነሐሴ 28፣ 1890 ዓ.ም ላይ የተካሄደውን የኦምዱርማን ውጊያ (Battle of Omdurman) መጥቀስ እንችላለን፡፡   

በኦምዱርማን ውጊያ ላይ፣ በጀነራል ሆራቲዮ ኪችነር (Horatio Kichener) የተመራው ቁጥሩ አስር ሺ ገደማ የነበረው፣ እንዲሁም ሃያ ሺ ገደማ በሚሆኑ የሱዳንና የግብጽ ባንዳወች ይታገዝ የነበረው የእንግሊዝ ወራሪ ጦር፣ በዳርፉራዊው አብዱላ ወልደሙሔ (Abdullah Ibn-Mohammed) በተመሩ፣ ጦርና ጋሻ ብቻ ባነገቱ ጥቁሮች ድባቅ ከመመታት የዳነው በደቂቃ ስደስት መቶ ጥይት የሚተፋውን ማክሲም መትረየስ (Maxim machinegun) የተሰኘውን የጊዜውን ጨጦ (WMD) ያለምንም ርህራሄ በመጠቀሙ ብቻና ብቻ ነበር፡፡   

ስለዚህም በታሪክ የመጀመርያወቹ የጨጦ (WMD) ሰለባወች ጃፓኖች ሳይሆኑ አፍሪቃውያን ነበሩ፣ ጨጦ ለመጠቀም የመጀመርያወቹ አሜሪቃኖች ሳይሆኑ እንግሊዞች ነበሩ፣ እነዚህ እኩይ ጦሣሮች የሚያስከትሉትን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ባድናቆት ለመዘገብ የመጀመርያው ደግሞ ካመታት በኋላ የእንግሊዝ ቀሎ (ቀዳሚ ሎሌ፣ prime minister) ለመሆን የበቃው ዊንሰት ቸርችል (Winston Churchill) ነበር፡፡  

ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ከፈጸሟቸው አያሌ ስተቶች ውስጥ አንዱ አሰበተፈሪ፣ ተፈሪበር፣ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ተፈሪመኮንን ትቤት … እያሉ ለራሳቸው ብቻ ራሳቸው መታሰቢያወችን ማቆማቸው፣ ይባስ ብለው ደግሞ ዊንጌት ትቤት፣ ደጎል አደባባይ፣ ቸርችል ጎዳና … እያሉ ላገራችን ለጦቢያ ምንም በዛ ቢባል ደግሞ እምብዛም ያልተከሩላትን ባዕዳንን መዘከራቸው ነው፡፡ 

ወጣት ሲባል እያደነቀውና እያወደሰው ፈለጉን ለመከተል አጥብቆ የሚመኘው አርአያ (role model) አፈንፍኖ መፈለጉ የተፈጥሮ ባሕሪው ነው፡፡  በትምህርት፣ በሐውልት፣ ባደባባይ፣ በመንገድና በመሳሰሉት ስለራሱ ጀግኖች እንዳይማርና እንዳያውቅ የተደረገው የኛ ወጣት ደግሞ አርአያወችን ከባዕዳን መፈለግ ግዴታ ሆነበት፡፡  ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ራስ አሉላን፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን፣ ፊታውራሪ ገረሱ ዱኪን፣ ጠቅል ጃጋማ ኬሎን … ከስማቸው ያለፈ እምብዛም ስለማያውቃቸው፣ ለሱነቱ ምንም አስተዋጽኦ ያላደረጉትን፣ ከራሱ ፋኖወች (ወዶ ዘማቾች) ጋር ሲነጻጸሩ ኢምንት ፋኖወች የሆኑትን ባዕዶች ሆችሚን፣ ቸጉዌራ (ቸጉቬራ) እያለ ከማድነቅ አልፎ ለማምለክ ዳዳው፡፡  የበላይ ዘለቀን ልጆች በሆችሚን ዝና ሊያስፎክራቸው፣ በቸጉቬራ ገድል ሊያስቀራራቸው ፈለገ፡፡   

 እኛ ጦቢያውያን ጀግንነትን ካብናቶቻችን (ካባቶቻችን እና እናቶቻችን) እንጅ ከማንም (በተለይም ደግሞ ከምዕራባውያን) መቅሰም አያስፈልገንም፡፡  ጦርነትን በተመለከተ አብነቶቻችን አብናቶቻችን ብቻ ናቸው፡፡  የየጊዜውን ዘመናዊ ጦሣር (ጦር መሣርያ፣ weapon) እስካፍንጫው እየታጠቀ በየጊዜው ይከታተል የነበረውን ወራሪ ሠራዊት፣ አብናቶቻችን በጦር፣ በጋሻና በጎራዴ ብቻ እያከታተሉ ድባቅ የመቱት በጦርነት ጥበብ የተራቀቁ የጦር ገበሬወች ስለነበሩ ነበር፡፡  አቶ ጸጋየ መብራቱ የሚባሉ ጦማሪ ‹‹ካድዋ ያልቀሰምነው ትምህርት›› (The Unlearned Lessons of Adwa) በተሰኘው ድንቅ ጦማራቸው በስፋት እንዳብራሩት፣

“The genius of Ethiopians was that they succeeded finally in developing a rectangular form of fighting …while the fitawrari breaks into the enemy’s defence system, the kegnazmach and grazmach could attack on the right and left side of the enemy with view to encircling it. The role of the Azmach was then to help the fitawrari while the rear guard was ready to come to the help the azmach, the kegnazmach and the grazmach” 

(Tseggai Mebrahtu, “The Unlearned Lessons of Adwa”, Ethiomedia Website).

‹‹ጦቢቾወች (ጦቢያውያን) ወደር የሌለው አራት ማእዘናዊ የውጊያ ስልት የቀመሩ የጦርነት ሊቆች ናቸው፡፡  ፊታውራሪው ጠላትን በግንባርጌ እንደ ተርብ እየተወረወረ ሲነድፈው፣ ቀኛዝማቹና ግራዝማቹ ደግሞ በቀኝጌና በግራጌ እየተገተጉ መፈናፈኛ ያሳጡታል፡፡ የደጃዝማቹ ሚና ውጊያውን ማስተናበር ሲሆን፣ የደጀኑ ሚና ደግሞ ፊታውራሪውን፣ ቀኛዝማቹንና ግራዝማቹን ለመርዳት የደጃዝማቹን ሚና በተጠንቀቅ መጠባበቅ ነው››     

በሌላ በኩል ግን ከምዕራባውያን ልንቀስማቸው የሚገባን አያሌ ቁምነገሮች አሉ፡፡  ከነዚህም ውስጥ አንዱ ከተሞቻችንን፣ ኑስተሞቻችንን (towns)፣ አደባባዮቻችንን፣ ተራሮቻችንን … በታላላቅ ሰወቻችን ስም መሰየም ነው፡፡  ኑስተማ (town) ማለት አነስተኛ ከተማ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ንዑስ እና ከተማ ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡  

ከተሞችንንና ኑስተሞችን በታላላቅ ሰወቻችን ስም ለመሰየም ደግሞ የሚከተሉትን ፊልጡፍ (prefix) እና ኋልጡፍ (suffix) መጠቀም እንችላለን፡፡  ፊልጡፍ ማለት በቃል ፊትጌ (በስተፊት) የሚለጠፍ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ፊት እና ልጡፍ ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡  ኋልጡፍ ማለት ደግሞ በቃል ኋልጌ (በስተኋላ) የሚለጠፍ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ኋላ እና ልጡፍ ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡  ፊልጡፍ እና ኋልጡፍ በተንዛዛ አጠራር ባዕድ መነሻ እና ባዕድ መድረሻ የምንላቸው ናቸው፡፡  

መዲና ከሚለው ቃል ዲና (-polis,-city, -grad, -ville) የሚለውን ኋልጡፍ (ባዕድ መድረሻ፣ suffix) እናገኛለን፡፡  ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ (Constantine) የመሠረታትንና በእንግሊዘኛ constantinople የምትባለውን፣ አሁን ደግሞ ቱርክ ከያዛት በኋላ ኢስታንቡል (Istanbul) ያላትን ከተማ ቆስጠንዲና እንላታለን፡፡   በተመሳሳይ መንገድ ጀፈርሰንዲና (Jefferson City)፣ ቮልጋዲና (Volgograd)፣ ናሽዲና (Nashville)፣ እስክንድርዲና (Alexanderia) ይሆናሉ፡፡   

 ደብር (ተራራ) ከሚለው የግእዝ ቃል ደግሞ ደብረ (-berg, -burg, -brugh) የሚለውን ለከተሞችና ኑስተሞች የሚያገለግል ፊልጡፍ (prefix) እናገኛለን፡፡  ለምሳሌ ያህል ሩሲያን ባጭር ጊዜ ውስጥ ታላቅ ባደረጋት በታላቁ ጴጥሮስ (Peter the Great) የተመሠረተችው ሴንት ፒተርስበርግ (Saint Petersburg) የምትባለው ታላቋ የሩሲያ ከተማ ባማረኛ ስትጠራ ደብረጴጥሮስ ትሆናለች፡፡  በተመሳሳይ መንገድ ደብረዮሐንስ (Johannesburg)፣  ደብረካትሪን (Yekaterinburg, Ekaterinburg) ይሆናሉ፡፡     

   ወደኛ ስንዞር ደግሞ ሮሃን ላሊበላ እንዳልን ሁሉ፣ ዙር ዐምባን ያሬዲና (ያሬድ-ዲና)፣ አድዋን ምኒሊክዲና፣ መቅደላን ደብረቴድሮስ፣ መተማን ዮሐንስዲና፣ ባሕርዳርን በላይዲና፣ የላኮመልዛዋን ኮምበልቻን ደግሞ እያስዲና (እያሱዲና) ልንላቸው እንችላለን፡፡ 

አዲስ አበባን ደግሞ ጣይቱዲና በማለት ሲሆን፣ ሲሆን በብቸኛ ስም፣ ሳይሆን፣ ሳይሆን ደግሞ በሁለተኛ ስም ብንጠራት የምናከብረው እቴጌ ጣይቱን ሳይሆን ራሳችንን ነው፡፡  ሌላው ቢቀር ግን ያዲስ አበባው ኔፋል ወደብ (air port) ፋይዳዊ ትርጉም በሌለው ቃል ቦሌ (የተሰነጣጠቀ መሬት፣ መረሬ አፈር) መባሉ ቀርቶ በእቴጌ ጣይቱ ስም ሊጠራ ይገባዋል፣ እቴጌ ጣይቱ ቤንበራዊ ኔፋል ወደብ (Etege Taitu International Airport)፡፡  ኔፋል (air) ማለት አየር ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው እንፋሎት ከሚለው ቃል ነው፡፡  ቤንቤራዊ (international) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ በይነ (መካከል) ከሚለው የግእዝ ቃልና ብሔራዊ ከሚለው ቃል ነው፡፡    

በተመሳሳይ መንገድ ሻሸመኔ የሚለውን ሸሞነ (አሽሞነሞነ፣ በሸማ ሸፈነ፣ አከናነበ፣ አሳመረ) ከሚለው ቃል የተገኘ የሚመስለውን ስም ትተን ለጥቁር ሕዝብ ልዕልና ታላቅ አስተዋጽኦ ባደረገው በሮበርት (ቦብ) ማረሌ (Robert Nesta Marley) ስም ማርሌዲና ወይም ደግሞ ይበልጥ በማሳመር ማርየ ልንለው እንችላለን፡፡

ከተሞቻችንን እና ኑስተሞቻችንን በሁሉም መስኮች ጀግኖቻችን በሆኑት በታላላቅ ሰወቻችን ስም ለመሰየም እንደ መንደርደርያ ይሆኑ ዘንድ ባማረጭነት የነየምኳቸው (suggested) ስሞች በሚከተለው ሰንጠረዥ ላይ ተዘርዝረዋል፡፡  ነየመ (suggest) ማለት ሐሳብ አቀረበ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ነየተ (ሰጠ) እና ጠቆመ ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡  ግሱም ሲረባ ነየመ (suggest)፣ ንይም (suggested)፣ ነያሚ (suggester, suggestive)፣ ንየማ (suggesting) እያለ ይሄዳል፡፡  ነይም (suggestion) ማለት ደግሞ የተነየመ (እንደ አማራጭ የቀረበ) ማለት ነው፡፡  ነይም (suggestion) ከሚለው ቃል ደግሞ ተነያሚ (suggestible)፣ ተነያሚነት (suggestibility) የሚሉትን ቃሎች እናገኛለን፡፡    

የተወሰኑ ከተሞች ንይም ስሞች
ያሁን ስም ንይም ስም ያሁን ስም ንይም ስም
ዙር ዐምባ ያሬዲና ጉንደት አሉላዲና
አድዋ ምኒሊክዲና ወልወል አፈወርቅዲና
መቅደላ ደብረቴድሮስ ኮምበልሻ እያስዲና
መተማ ዮሐንስዲና አዲስ አበባ ጣይቱዲና
ባሕርዳር በላይዲና ሻሸመኔ ማርሌዲና (ማርየ)

ከነዚህ ንይም ስሞች በተጨማሪ ገበየሁዲና፣ ባልቻዲና፣ ገረሱዲና፣ ጃገማዲና፣ ባዕሉዲና (ደራሲ ባዕሉ ግርማ)፣ ከበደዲና (ቀያኒ ከበደ ሚካኤል)፣ ጥላሁንዲና (ከያኒ ጥላሁን ገሠሠ) … እያልን ታላላቅ ጀግኖቻችንን ብንዘክራቸው ጥቅሙ ለነሱ ላለፊት ሳይሆን ለኛ ለቀሪወቹና እኛን ለሚከተለው መጭው ትውልድ ነው፡፡    

መስፍን አረጋ 

mesfin.arega@gmail.com

                   

Filed in: Amharic