>
5:13 pm - Friday April 18, 8200

አገሪቷ የገጠሟትን ችግሮች ሁሉ ጠቅሎ ሕገ መንግስቱ ውስጥ መክተት ለምን አስፈለገ? (ያሬድ ሀይለማርያም)

አገሪቷ የገጠሟትን ችግሮች ሁሉ ጠቅሎ ሕገ መንግስቱ ውስጥ መክተት ለምን አስፈለገ???

ያሬድ ሀይለማርያም
 

* የአትኩሮት አግጣጫ ለማሳት ወይስ ለመፍትሄ?


ሕገ መንግሥቱን ብቸኛ የችግር መፍቻ መንገድ አድርጎ መውሰድ ሌላ ዙር ችግር ውስጥ ሊከተን የሚችል ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ችግር ከሕገ መንግስታዊ ቀውስ በላይ ነው። የችግሮቻችን ምንጭ ከሆኑት በርካታ ጉዳዬች አንዱም ራሱ ሕገ መንግስቱ ነው። አንዳንዱ ችግር ከሕገ መንግሥቱ ጋር አብሮ የተወለደ እና አብሮ የጎለመሰ ነው። ሌላው ቀርቶ ካለፋት ሦስት አመታት ወዲህ ሲንከባለል የመጣውን የአገሪቱን ችግሮች ሁሉ ሰንካላ በሆነው ሕገ መንግስት እና ግልጽ ባልሆኑት ድንጋጌዎች ብቻ ለመፍታት መዳከር አንድም ከቅን ልቦና የራቀና አቋራጭ መንገድ መፈለግ ነው። አለያም አገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ እውነታ ላለመጋፈጥ የተመረጠ የሽሽት እስራቴጂ ነው። ይህን ስል ገዢውን ፖርቲ ብቻ ሳይሆን በተቃርኖ የቆሙትንም ጭምር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ መንግስት በሁለት መንገድ እውነተኛ እና ዘላቂ የሆነ አገራዊ መፍትሔ የሚገኝበትን አቅጣጫ መንገዱን እንዲስት እያደረገ ይመስለኛል።
፩ኛ/ አገሪቱ የተጋፈጠችውን ችግር ያስቀመጠበት ወይም የሳለበት መንገድ ፍጹም በተሳሳተ ትርክት ወይም እጅግ በተጋነኑ ኩነትች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረጉ ነው። ቀደም ሲል በአንድ ጽሁፌ ላይ እንደገለጽኩት አራት የመፍትሔ ሃሳብ እና ስድስት ማስፈራሪያዎች ይዘው ብቅ ያሉት ጠቅላዮ ብልጽግና በስልጣን ካልቆየ ወይም እኔ ማለታቸውም ነው፤ ግብጽ ትወረናለች፣ የአባይ ግድብ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፣ የአንበጣ መንጋ ያጠቃናል፣ ኮሮና ቫይረስ ይጨርሰናል፣ ምርጫው ይደናቀፋል፣ ወዘተ የሚሉ አደጋዎችን አመላክተዋል። እነዚህ ማስፈራሪያዎች የእወነተኛ የአደጋውን ትርክት አዛብተውታል። ሕዝብ ቢያንስ ከውጪ ወረራ ለመዳን እሳቸው የሚመሩትን መንግስት የሙጥኝ እንዲል ያደርገዋል። ከወረርሽኝ ለመትረፍ ቤሳቤስቲ ከሌላቸው ተቃዋሚዎች ይልቅ የሳቸውን ልግስና ይመኛል። በሁዋላም ይዘውት ለሚመጡት ማንኛውም ውሳኔ እንቅፋት አይሆንም። ይህ ደግሞ የሕዝብን ስነ ልቦና መስለብ ስለሚሆን የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የምርጫውንም ነጻነት ከወዲሁ ያዛባዋል።
፪ኛ/ መንግስት በተሳሳተ ትርክት ላይ ተመስርቶ ላስቀመጣቸው አገራዊ ችግሮች ሕገ መንግስቱን ብቻ እንደ ዋነኛ እና ብቸኛ የችግሩ መፍቻ አድርጎ በማቅረብ የፖለቲካ ፖርቲዎችን እና የምሁራንን የአትኩሮት አቅጣጫም ማሳት ችሏል። ሁሉም ተለክታ በተሰጠቻቸው አጀንዳ ላይ ግራ ቀኝ ተቧድነው እንዲጯጯሁ አድረጓል።
ይህ የማህበረሰብን ስነ ልቦና ወይም የአስተሳሰብ አቅጣጫ ማሳት በምዕራቡ አለም የተለመደ የፖለቲከኛች ቁማር ነው። Manufacture consent ይሉታል። ሲተረጎም፤ to create a system in which citizens become willing and obedient, consenting and unquestioning, obeying certain principles and paradigms, all by way of corporate-sponsored propaganda through mass media and commercialism, as opposed to obedience achieved through strongman tactics.
አብይ ሕገ መንግስቱን የሙጥኝ ማለቱን ተከትሎ ሙሁራኖችም የሕገ መንግስቱን አንቀጾች መፈተሻቸው አግባብ ነው። ይሁንና በሚያስተዛዝብ ደረጃ ሕገ መንግስቱ ያላሰበውን እና ያላለውን ሁሉ ብሏል ወይም ሊል ፈሎጎ ነው እያሉ አንቀጽ ፈለጣ እና ብለታ ውስጥ እስከ መግባት መድረስ ግን ከአካዳሚ እውቀት መፈተሻነት ባለፈ አገሪቷ የተጋፈጠችውን ችግር አይፈታም። ከእውነታውም ያርቃል። የሕግ እውቀት የሌለውን ሰፊውንም ሕዝብ መደናገር ውስጥ ይከታል። እርግጥ ነው ከምሁራኖቹ ውይይቶች ትምህር ይገኛል፣ ለወደፊትም ለሚቀረጸው ሕገ መንግሥት ግብአት ይገኛል። ለዛሬው ችግራችን መውጫ መፍትሔ ማመንጨቱን ግን እንጃ።
በእኔ እምነት ይች አገር ከሕገ መንግስት ትርጓሜም ሆነ ማሻሻል በላይ በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ፣ የገዢውን ፖርቲ እና ሌሎች ባለድረሻ አካላት ግልጽና ሰፊ ምክክር፣ መቀራረብ እና የጋራ መፍተሄ ለማምጣት አብሮ መስራትን ትፈልጋለች።
የሚታዩኝ የመፍትሔ ሃሳቦች፤
1. የምርጫውን ጊዜ እንደተባለው ቢያንስ ለአሥር ወር ቢበዛ ለአንድ አመት ማራዘም፣
2. በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ የሽግግር መንግስት ተብሎ እራሱ እንዲቀጥል ማድረግ። ይሁንና ሥልጣን እና ተግባሩን ግን በልዩ ሁኔታ የሚገድብ የሕግ ማእቀፍ በማዘጋጀት አንድ በሽግግር ላይ ያለ መንግስት የሚኖሩት ሥልጣናት እና ባህሪያት እንዲኖሩት ማድረግ፣
3. የተለየ የፖለቲካ ሥልጣን የሌለው እና ከመንግስት መዋቅር ውጪ የሆነ የመማክርት ጉባዔ እንዲቋቋም በማድረግ በሃሳብ እና ምክረ በማቅረብ የሽግግሩን ሂደት የሚደግፍ አካል መፍጠር። በአወቃቀሩም ባለሙያዎችን፣ የፖለቲካ አመራሮችን፣ የሲቪክ ተቋማትን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ ምሁራንን እና የማህበረሰብ ተወካዮችን የያዘ ይሆናል። ዋና ሥራው የሽግግሩን መደገፍ ይሆናል።
4. የእርቅና እውነት አፈላላጊውን ኮሚሽኑ በአዲስ መልክ አዋቅሮ እና ዝርዝር የአፈፃፀም ጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዬችን ከምርጫው በፊት አከናውኖ የፖለቲካውን ውጥረት እንዲያረግብ እና መለስተኛ ጉዳዬችን በቀጣይ ከምጫው በኋላ እንዲያከናውን ማድረግ።
ሕገ መንግስቱን በትርጉም ስም ከአቅሙ በላይ መለጠጥ እና አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ሥልጣን ለማራዘምም ሆነ፤ ሥልጣን ከመንግስት ለመንጠቅ የሚደረጉ ሙከራዎች አገሪቱን ሌላ ዙር ጥፋት ውስጥ ሊከታት ይችላል። የመጣንበትን መንገድ ባንመለስበት ጥሩ ነው።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic