ኮሮናቫይረስ ሲጠፋ እንጨባበጥ ይሆን? ሳይንቲስቶች “በፍጹም!” ይላሉ
ይታገሱ አምባዬ
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ብዙ ልማድ መጥቶ ሄዷል። መጨባበጥ ግን እነሆ እንዳለ አለ።
መጨባበጥ ከሰው ልጅ ባሕል ጋር እንደተጨባበጠ እነሆ ስንት ዘመኑ!
ሰዎች አዲስ ሰው ሲተዋወቁ ይጨባበጣሉ፤ ከሚያውቁት ሰው ጋር ይጨባበጣሉ። ቢሊየነሮች የንግድ ሥምምነት ተፈጣጥመው ይጨባበጣሉ። አጫራች አሸናፊውን ተጫራች ማሸነፉን የሚያውጅለት እጁን በመጨበጥ ነው። መንግሥታት በጦርነት ከተቋሰሉ በኋላ “ይቅር ለእግዜር” የሚባባሉት በመጨባበጥ ነው።
መጨባበጥ እንደ መተንፈስ ያለ ነው። ሕይወታችንን ተቆጣጥሮታል።
እንኳንስ እኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትም የነጩ ቤተ መንግሥት የግዛት ዘመኑን ሩብ የሚያጠፋው በመጨባበጥ ነው።
አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዓመት በአማካይ ስንት ሰው የሚጨብጥ ይመስልዎታል? 65 ሺህ ሰዎችን!
ታዲያ ከመጨባበጥ ጋር በቀላሉ የምንፋታ ይመስልዎታል?
ለመሆኑ ማን ጀመረው?
እንዴት ይታወቃል ይሄ? አይታወቅም። ኾኖም መላምቶች አሉ።
ጥንታዊ ግሪኮች መሣሪያ ይሸከሙ ስለነበር አንዱ ሌላውን ለማጥቃት እንዳልመጣ ለማሳየት ይጨባበጡ ነበር።
አውሮፓዊያንም ጀምረውት ይሆናል። ድሮ በመካከለኛው ዘመን በነፍስ የሚፈላለጉ የመሳፍንትና የመኳንንት ቤተሰቦች እርስ በርስ የሚጨባበጡበት ዋናው ምክንያት አንዱ ሌላውን ሊጎዳ የሚችል መሣሪያ እንዳልታጠቀ እጁን በማርገፍገፍ ለማጣራት ነበር።
መጨባበጥን እንደ የኮይኮር ክርስቲያኖች ያስፋፋው ግን የለም። ኮይኮሮች በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የክርስቲያን ወንድማችነት ማኅበር አባላት ናቸው። ማንኛውም መልክ ያለው ጦርነትን ይጸየፋሉ።
እነርሱ በሰው ልጆች እኩልነት ከማመናቸው ጋር ተያይዞ ይሆናል ከማጎንበስ ይልቅ መጨባበጥ እኩልነትን ይገልጣል ብለው ያስባሉ። እንዲያ በማመናቸው ነው ሰመል መጨባበጥን አጠናክረው ገፉበት።
ክርስቲን ላጋር በቴክሳስ ኦስተን ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቡና ሳይንስ ፕሮፌሰር ናት።
መጨባበጥ የሰው ልጆች ትሁትነት የሚገለጥበት፤ ልብ ለልብ መናበባቸውን በጥቂቱም ቢሆን የሚንጸባረቅበት ጥበብ ነው።
“የሰው ልጅ በጊዜ ርዝማኔ እንዴት ማኅበራዊ ፍጡር እየሆነ እንደመጣም ማሳያ ነው” ትላለች ፕሮፌሰር ክሪስቲን። በተለይም ሰው በንክኪ ራሱን የሚገልጽ እንሰሳ ስለመሆኑም ሌላ ማረጋገጫ ነው።
ፕሮፌሰር ላጋር እንደምትለው “መጨባበጥ ብቻም ሳይሆን መነካካት ጠንካራው የስሜታችን ቋንቋ ነው፤ ልናጣው አንፈልግም።”
በሳይንስ እኛን ይቀርባሉ የሚባሉት “አጎቶቻችን” እነ ቺምፓዚም ከእኛ የባሱ ናቸው። እጅግ ይተቃቀፋሉ። ሰላምታ ሲሰጣጡ አጠገባቸው ያለውን ዛፍም ቢሆን ያቅፉታል እንጂ የእግዜር ሰላምታን ቸል አይሉም። አንዳንዴ ከመተቃቀፍም አልፈው ይሳሳማሉ።
በ1960ዎቹ ምርምሩን ይፋ ያደረገው አሜሪካዊው የሥነ ልቦና ሳይንስ ሊቅ ሃሪ ሀርሎ የዝንጀሮ ልጆች ለዕድገታቸው እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ መነካት አንደሆነ ደርሶበታል። መተሻሸት፣ መታቀፍ።
ቀጭኔዎችም እንደኛው ናቸው። ሁለት ሜትር በሚረዝመው መቃ አንገታቸው አንዱ የአንደኛውን አንገት ይጨብጣል።
መጨባበጥን ለምን አንተካውም?
ይሄ መጨባበጥ የሚሉት ነገር ምንም ያህል ወሳኝ የስሜት መግለጫችን ቢሆንም አማራጭ አልባ አይደለም።
ለምሳሌ ሁለት መዳፎቻችንን በማገናኘት እጃችንን ከደረታችን አስደግፈን ከወገብ ሸብረክ ብንልስ? ደስ አይልም? ሕንዶች “ናመስቴ” ይሉታል።
ወይም ደግሞ እንደ ሳሞአ ደሴት ነዋሪዎች በዓይን ጥቅሻ ሰላም ብንባባልስ? እነዚህ ከአውስትራሊያ ማዶ በትንሽ ደሴት የሚኖሩ ሕዝቦች ሁነኛ ሰላምታ አሰጣጣቸው ሞቅ ካለ ፈገግታ ጋር የዐይን ሽፋሽፍታቸውን ከፍ ዝቅ በማድረግ ነው።
ወይም ደግሞ በሙስሊም አገራት እንደሚዘወተረው አንድ እጅን ወደ ልብ አስጠግቶ በማሳየት በፈገግታ ብቻ ሰላም ብንባባልስ?
ወይም ደግሞ እንደ ሃዋይ ሰዎች ሦስቱን የመሐል ጣቶች አጥፎ አውራ ጣትንና ትንሽ ጣትን ዘርግቶ እደውልልኻለው አይነት ምልክት በማሳየት ሰላም መባባልም ይቻላል።
ዝርዝሩ ብዙ ነው። አንዳቸውም ግን እንደ መጨባበጥ አርኪ አይመስሉም። የባሕሪና ተያያዥ ጉዳዮች ሳይንቲስት ቫል ከርቲስ እንደምትለው ሰዎችን ስንጨብጥ የጥርጣሬ ግንብን እያፈረስን ነው።
መጨባበጥን መርሳት እንችላለን?
መጨባበጥ ከኮቪድ-19 ወዲህ ብቻ አይደለም ዘመቻ የተከፈተበት።
በ1920ዎቹ በወጡ የጥናት ወረቀቶች መጨባበጥ ክፉ ተህዋሲያንን የምናዛምትበት ሁነኛው መንገድ እንደሆነ ተደርሶበት ነበር።
አሜሪካኖች ታዲያ በዚያ ጊዜ መጨባበጥን ትተን እንደ ቻይናዎች የራሳችንን እጆች በማጨባበጥ ሰላምታን እንለዋወጥ የሚል ዘመቻ ተከፍቶ ነበር።
በፈረንጆች 2015 በሎሳንጀለስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ አንድም ሰው እንዳይጨባበጥ መመሪያ አውጥቶ ነበር። ይህም የተደረገው በተለይ በጽኑ ሕሙማን ሕክምና ክፍል አካባቢ ነበር። ሆኖም ይህ መመሪያ መቆየት የቻለው ለ6 ወራት ብቻ ነበር።
በነገራችሁ ላይ በብዙ የዓለም ክፍል የሚገኙ ሙስሊም ሴቶች በአመዛኙ የቅርብ ቤተሰብ ካልሆነ በስተቀር ወንድ ለመጨበጥ አይፈቅዱም። ይህም ከሐይማኖት መመሪያ ጋር የተያያዘ ምክንያት ያለው ነው።
ይህ ሁሉ ሐይማኖታዊና ሳይንሳዊ ጫና የደረሰበት የመጨባበጥ ባሕል ሁሉን አሸንፎ በመላው ዓለም እጅግ ተመራጩ የሰላምታ መንገድ ሆኖ ለኮሮናቫይረስ ዘመን በቅቷል።
ሰዎች ለምን ይጨባበጣሉ፤ ስሜታቸውስ ምን ይመስላል ሲሉ የጠየቁና መጨባበጥን ያጠኑ ሳይንቲስቶች፤ የሰው ልጆች አእምሮ ልክ አመርቂ ወሲባዊ ተራክቦ፣ ወይም ጥሩ ምግብ አልያም ጥሩ መጠጥ ሲያገኝ የሚሰማው ስሜት ዓይነት በመጨባበጥም ተመሳሳዩ የአእምሮ ክፍል እንደሚነቃቃ ደርሰውበታል።
ወደ ፊት እንጨባበጣለን?
አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች በራቸውን እየከፈቱ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ ቢሆንም መጨባበጥ ግን ከዚህ በኋላ ተመልሶ ስለመምጣቱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ የአሜሪካ ተቀዳሚው የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮች መሪ ናቸው። በአሜሪካ ምድር ከትራምፕ በላይ ይታመናሉ፤ ይሰማሉ። ስለ መጨባበጥ ጉዳይ በተጠየቁ ጊዜ እንዲህ ብለዋል።
“እውነቱን ተናገር ካላችሁኝ ከዚህ በኋላ መቼም ቢሆን ወደ መጨበጥ የምንመለስ አይመስለኝም። ያ ዘመን ላይመለስ አልፏል።”
ዶ/ር ፋውቺ መጨባበጡ ፈጽሞ እንዲቀር የሻቱት ኮሮናቫይረስን ለማቆም ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ በርካታ ሰዎች በኢንፍሉዌንዛ ስለሚሞቱም ጭምር ነው።
ኢንፍሉዌንዛው በዋናነት ከሰው ወደ ሰው እየተላለፈ ያለው ደግሞ በመጨባበጥ እንደሆነ በዘመናት ልምዳቸው ያውቁታል።
ምናልባት በድኅረ-ኮሮና ሁለት ዓይነት ሕዝቦች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የሚጨባበጡና የማይጨባበጡ። መነካካት የሚፈልጉና የማይፈልጉ። ይህ ደግሞ የሰው ልጅን በሥነ ልቦና የሚሰባብር ይሆናል።
ዶ/ር ስትዋርት ዎልፍ በዚህ ረገድ የሰጡት አስተያየት በተለይ በኮቪድ-19 ዘመን ያደጉ ወጣቶች ምናልባት ያለመጨባበጡን ነገር ሊገፉበት እንደሚችሉ የሚጠቁም ነው።
የተቀረው ሕዝብ ግን መነካካት ደሙ ውስጥ የተቀበረ ያህል የተላመደው ስለሆነ በዋዛ እንዲሁ እርግፍ አድርጎ ሊተው አይችልም።
ፕሮፌሰር ክሪስ ላጋር “የዚህ የኮቪድ-19 ዘመን ምጸት ምን መሰላችሁ?” ትልና ትጠይቃለች። “ምጸቱ አትነካኩ የተባልነው እጅግ መነካካት በምንሻበት ወቅት መሆኑ ነው።”
ፕሮፌሰር ላጋር ለዚህ ሐሳቧ ማጠናከሪያ በሐዘን ላይ ያለንን ስሜት እንድንፈትሽ በመጋበዝ ነው።
“እስኪ ሐዘን ላይ ባላችሁበት ጊዜ ማን ስሜታችሁን ይበልጥ እንደሚነካው አስታውሱ። ከልቡ እቅፍ የሚያደርገን ሰው ለልባችን በጣም የቀረበው ነው። ወይ ደግሞ አጠገባችን ሆኖ ትከሻችንን የሚያቅፈንን ወዳጃችን ስሜታችንን እጅጉኑ ይነካዋል። ይህ ስለእኛ የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር እኛ የሰው ልጆች በንክኪ የምንግባባ ዳሳሽ እንሳሳት መሆናችንን ነው።”
ደሊያና ጋሪሺያ በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ የተሰማራች ስለሆነ በተቻለ መጠን ንክኪን ታስወግዳለች። ነገር ግን ልማድ ክፉ ነውና ሰው እቅፍ በማድረግ ሱስ የተጠመደች ናት።
“85 ዓመት የሆነችውን እናቴን ሁልጊዜም ፍቅሬን የምገልጽላት በማቀፍ ነው። እቅፍ ሳደርጋት ነው ደስ የሚለኝ። እቅፍ አድርጋ ነው ያሳደገችኝ። አሁን አትነካኩ ሲባል ከእናቴ ጋር የነጠሉኝ ያህል ነው የተሰማኝ። አሁንም ቢሆን ስትጠጋኝ እቀፊያት እቀፊያት ይለኛል።”
ለማንኛውም ከኮሮናቫይረስ በኋላ መጨባበጥ አይጠፋ ይሆናል፤ እጃችንን ስንዘረጋላቸው ግን የሚያሳፍሩን ሰዎች አይጠፉም።