>

ጂ ጂ ዬ ን  ፍ ለ ጋ … !!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጂ ጂ ዬ ን     ፍ ለ ጋ … !!!

አሰፋ ሀይሉ

 

 የጂጂ የውበት ወጥመድ… ምኗ ላይ ተፈልጎ ይገኝ ይሆን?

• እኔ የምለው ጂጂ እንደ ትልልቅ የተከበሩ አባቶቻችን ትንቢተኛ ናት እንዴ? ከሚያስደንቁኝ ብቃቶቿ አንዱ አሁን ላይ ካለው ነገር ተነስታ የወደፊቱን የማየትና የመተንበይ ችሎታዋ ነው!
—               
በህይወት ስንኖር ብዙዎቹ የምንወዳቸው ነገሮች ምክንያት የላቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ ምክንያት ደርድረን ሳይሆን ዝም ብለን ነው የምንወደው፡፡ መውደድን በቀመር አታመጣውም፡፡ በሚዛን አትለካውም፡፡ ዝም ብለህ ትወዳለህ፡፡ ዝም ብለህም ትወደዳለህ፡፡ ጂጂንስ ምናልባት እንደዚያ ዝም ብለን ይሆን የወደድናት? የጂጂን ሙዚቃዎች እንዲህ እጅግ ተወዳጅ ያደረጉላት ነገሮች ምንድናቸው? የሚለው ጥያቄ በብዙዎቻችን ልብ አንዳንዴ የሚያቃጭል ጥያቄ ነው፡፡
ፈገግተኛ፣ በብዙዎች ቤተሰብ ውስጥ ተፈልጎ የማይታጣ፣ መልከ ቀና፣ ትሁት፣ የዋህ፣ ነቄ፣ መልክ ስላላት ይሆን ልባችንን ባንዴ በፍቅር የነደፈችው ጂጂ? ወይስ ድምጿ ውስጥ ያለው ይሄ ከምንም ዓይነት ማስመሰልና ሜካፕ የፀዳ እውነተኛ ቃና? ከእውነተኛ ሰው፣ በእውነተኛ ስሜት የሚወጣው ያ እውነተኛ ያልተቀባባ ድምጿ ይሆን የሚማርከን? ወይስ ሸግዬ ተክለሰውነቷ? ስርጉድ ያለው ጉንጭ፣ ግጥም ያለው ቅንድብ፣ ስልክክ ያለው አፍንጫ፣ ልቅም ያለው ሽፋሽፍት፣ ወይ እርሷ ራሷ ‹‹ባቴን ነው ባቲን ነው›› እንደምትለው ያ በጨዋ ደንብ ሽፍን አድርጋ የምታኖረው ባቷ ይሆን? ወይስ ምኗ? አካላዊ መግነጢስ ይሆን ለብዙዎች በጂጂ ፍቅር መውደቅ ምክንያቱ? ያም የጂጂ ተፈጥሯዊ አካላዊ መስህብ በብዙዎች ዓይን እንድትገባና በስስት እንድትታይ እንዳደረጋት በእርግጥ አይካድም፡፡ ግን ያ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ጂጂ ‹‹መልክ ብቻ›› አቀንቃኝ አይደለችም! ሌላም አላት፡፡
ምናልባት ለየት ያሉ – ከተለመደው ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ስልት ወጣ ያሉ – ግን ደግሞ መልሰው ወደ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልቶች የሚጠልቁ ውብ የሙዚቃ ቅንብሮቿ የተነሳ ይሆን? በአንድ ወቅት የ2ኛ አልበሟን የሙዚቃ ቅንብር የሠራላትና አሁን በሕይወት የሌለው ደረጀ መኮንን በህይወት ሳለ ስለ ጂጂ በሰጠው ቃለመጠይቅ ገና ሙዚቃ ስቱዲዮ ሳልገባ – ገና ዘፈኖቿን ስሰማቸው – በዚህ አልበም ትታወቂበታለሽ – ይሄ አልበም አንቺ በሙዚቃ እንደ አብሪ ኮከብ ደምቀሽ የምትወጪበት አልበም ነው – ብዬአት ነበር – በማለት ነበረ የተናገረው፡፡ ቅንብሩን ሲሰራም በፍፁም ተመስጦና ፍሰት የፈጠራ አኪሩ እንደልብ እየመጣለት በደስታ እንደሠራላት ነበረ የተናገረው፡፡
ባለቤቷ ደግሞ በአንድ ወቅት ሲናገር – የጂጂ ሙዚቃ ቅንብሮችን ልብ ብለህ ከሰማሃቸው በኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ድምጾችና ውሁዶች ብቻ የተገደቡ አይደሉም – የጂጂ ሙዚቃዎች የብዙዎቹን እንደነ ኦሞ ሳንጋሪ የመሳሰሉ አፍሪካውያን አቀንቃኞችን ሙዚቃዎችም ይመስላሉ – የብዙ አፍሪካውያን – የህንዳውያንንም ሙዚቃ የሚመስል ነገር አላቸው – እኔ ይህን ነገር ከመነሻው ቀን ጀምሬ ብዙ ጊዜ ነው የምናገረው – የጂጂ ሙዚቃዎች – ሀገራዊ ብቻ አይደሉም፣ አህጉራዊም አይደሉም፣ ዓለማቀፍ ድምፀት ያላቸው የጥበብ ውጤቶች ናቸው – በማለት ሲናገር ተደምጧል፡፡
በእርግጥ ጂጂ – ከባህል መሣሪያዎች እስከ ጊታር፣ ከኬንያ እስከ አሜሪካ ድረስ ባሳለፈቻቸው የሙዚቃ ህይወቶችና ተሞክሮዎች – እንዲሁም ሙዚቃዎቿ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉት በርካታ ዓለማቀፍ የሙዚቃ ወዳጆችና ባለሙያዎች አንፃር ስትታይ – ሙዚቃዎቿ ልክ በፍቅር እንደምታቀነቅንለት ሀገር ተሻጋሪው አባይ – የእርሷም ሙዚቃዎች – ሀገርን፣ አህጉርን አቋርጠው ዓለማቀፋዊ ማንነትን እንዲላበሱላት አስችለዋት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ኳሊቲዋ ይሆናል የጂጂን ሙዚቃዎች በሁሉም ዘንድ ተወዳጅና ድንበር የለሽ ፍቅርና አድናቆትን እንዲቀዳጁ ያስቻላቸው ጥበባዊ ተፈጥሮ!
እኔ ደግሞ እንደ አንድ በጂጂ ሙዚቃዎች ፍቅር እፍፍ እንዳለ አድማጯ – ከሌሎችም ከብዙዎች ቀደም ካሉ የጂጂ ሙዚቃ ተከታታዮችና አድናቂዎች ጋር አብሬ የምጋራው ምክንያት አለ፡፡ የጂጂ ሙዚቃዎች ውስጥ የሚገኙት የዜማ ስንኞች – ፍፁም ተፈጥሯዊ መሆን፣ ፍፁም ቤተኛ መሆን፣ ፍፁም ከእውነተኛው ኢትዮጵያዊ ማጀት የፈለቁ፣ ከእውነተኛው የኢትዮጵያዊ ልጅ አስተዳደግ፣ ከእውነተኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮና አካባቢ የፈለቀ – ‹‹ኦተንቲክ›› የሚሉት ዓይነት – ፍጹም ኦሪጂናሌ ህይወትን የምትገልጽባቸው ስንኞቿ – ከደመግቡ ተክለሰውነቷም፣ ከግሩም ቅንብሮቿም፣ ከአስገምጋሚ ያልተቀባባ ድምጿም፣ ከዓለማቀፋዊ የሙዚቃዎቿ አድማስም – ከሁሉም በላይ ልቆ – አድማሳትን እየሰነጠቀ – የጂጂ ሙዚቃ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ታትሞ እንዲቀር ያደረገው ዓይነተኛው ምክንያት ይመስለኛል!
ልብ ብሎ ላያት – ጂጂ – ስለ ፍቅር፣ ስለ መንደር፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ውበት፣ ስለ ሰው፣ ስለ ምንም ነገር – የምታሰናዳቸው ስንኞች – የምትደረድራቸው ቃላት – እነዚያን የምታወጣባቸው ቅላፄዎች ሁሉ – ፍፁም ቤተኛ (‹‹ሎካል ኤንድ ኦሪጂናል›› ወይም ‹‹ኦተንቲክ›› የምንለውን ዓይነት) – ከእውነተኛ ኢትዮጵያዊ የህይወት ምንጭ፣ ከእውነተኛ የኑሮ ምንጭ፣ ከእውነተኛ ኢትዮጵያዊ ልቦና – ከእውነተኛ መረዳትና – ለህልም እውነተኛ ህልም ካለው – ከእውነተኛ ኢትዮጵያዊ ህልሞች የፈለቁ – እውነተኛ ባለቀለማት ውብ ህልሞች የመሰሉ ኢትዮጵያዊ ስንኞች ናቸው – የጂጂ ዋነኛ የውበት ምንጭ የሚል የቆየ ሃሳብ አለኝ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የጂጂን ሙዚቃ ስንኞች ምንነትና ኢትዮጵያዊ ዳራ በሚገርም ሁኔታ ተንትኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ – በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አማካይነት – በማቅረብ ለብዙዎች በጂጂ ስንኞች ውስጥ እዚህም እዚያም ለምናገኛቸው ኦርጂናል ቃላት እንግዳ ለሆንን ሁሉ – ዜማዋን ከስንኟ አሰናኝተን ከጂጂ ዜማዎች ጋር በፍቅር እንድንግባባ ያደረገ አንድ የጋዜጣ አምደኛ ሁሌም አይረሳኝም፡፡ እርሱም የማንኩሳው ሰለሞን አበበ ቸኮል ነበረ፡፡ በምኅፃረ ቃል ‹‹ሰአቸ›› በሚል ስም በየሳምንቱ በዚያው ጋዜጣ ይጽፍ የነበረ ጉምቱ ሐያሲ ነበረ፡፡ ያ የሰአቸ የጂጂን ‹‹ውሃ ጃሪ›› ‹‹ውሃ ኮሉ›› ወዘተ እያለ.. እነዚያን ስንኞች ያስተነተነበት መንገድ – ከዚያም በኋላም ሆነ፣ ከዚያም በፊት በጂጂ ዘፈኖች ውስጥ የማገኛቸውን ስንኞች ልብ ብዬ እንዳደምጥ ታላቅ በር ከፋች ሆኖልኛል፡፡ እና ሁሌም አስታውሰዋለሁ፡፡
እና ባጠቃላይ ስለምንም ነገር አቀነቀነች – ጂጂ – ሁልጊዜም (በራሷ አነጋገር) ስንኞቿ – ልክ ተጠብሰው እንሚበሉ እንደ ትኩስ እሸት ናቸው – ትኩስ ነፍስን የሚያሞቁ፣ ደስ የሚል ቃና ያላቸው፣ በቀላሉ ወደ ውስጣችን የሚሰርጉ – ፍጹም ኢትዮጵያዊኛ ስንኞች! ምናልባትም ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደማምረው – በጂጂ ፍቅር የጣለኩን ዋነኛ መስተፋቅሮቿ – እነዚያ ነፍስ የሆኑ እውነተኛ ስንኞቿ ይመስሉኛል!!
ጂጂ ስለ ሀገር ስታቀነቅን እንዲህ እያለች ፍጹም ለነፍሳችን ቅርብ የሆኑ – ልክ እንደ ልጅ የገዛ እናቷን ደገፍ ብላ የምትናገር የሚመስሉ አጽናኝ ስንኞቿን ታንቆረቆርልናለች፡-
“እምዬ እናት ዓለም እስቲ አንቂኝ ከእንቅልፌ
እምዬ እናት ሃገር እስቲ አንቂኝ ከእንቅልፌ
ሁሉም ይሄዳሉ እንዳመጣጣቸው – ሳቅና ለቅሶሽን አይገዙትምና
አትፍሪ እናት ዓለም ኑሪልኝ በጤና”
ጂጂ ስለ ሀገር ናፍቆት ስንኝ ስትደረድር – አጉል አትራቀቅም፡፡ ሌላ ትርፍ ነገር አታወራም፡፡ በቀጥታ እና ልክ እንደተሰማት አድርጋ የሚገርም ተፈጥሯዊ የናፍቆት ስሜቷን በስንኞቿ በኩል በቀስታ አንካችሁ ትልሃለች፡፡ ጂጂ “ናፈቀኝ” ውስጥ የምትናገራቸው ቀላል የሚመስሉ ነገሮች – ልክ እኔ አሁን ከሀገሬ ወጥቼ ሩቅ ሆኜ የሚሰሙኝን ዓይነት፣ ከቤትህ፣ ከመንደርህ፣ ከሀገርህ ውጭ የትም ልታገኛቸው የማትችላቸውን የናፍቆት ስሜቶች ነው፡ የሀገር ናፍቆት ከዚህ በላይ በምንስ ሊገለጽ?፡-
“የቤቱ ጫወታ የመንደሩ ወሬ
ናፈቀኝ ናፈቀኝ – ናፈቀኝ ሀገሬ
እህህ እየየ ኦዉዎ – እይይይ
ናፈቀኝ ናፈቀኝ ናፈቀኝ ሀገሬ…
ስም የለኝም ስም የለኝም በቤቴ
አንዱ እምዬዋ ሲለኝ፣ አንዱ ሲለኝ አከላቴ
ጎኔ ስኳሬ ሲሉኝ፣ በፍቅራቸዉ ሲጠሩኝ…
ናፈቀኝ ጎረቤቱ… ናፈቀኝ ጨዋታው..
እምዬ እናት ዓለም ….”
ጂጂ በሌላ ተወዳጅ ዜማዋ እንዲሁ ናፍቆትን የምትገልጽበት ጥበባዊ ስዕል ከሳች እና ፍፁም ግልጽ እውነተኛ መንገድ እጅግ ያስደምማል፡-
“የሽመል አጓራ አይችልም ገላዬ፤
የኔሆድ አኔዋ ናቁም ከኋላዬ፤
አያና ደማሙ አያና ደማሙ፤
አያና ደማሙ አያና ደማሙ
ከአባይ ወዲያ ማዶ – አንዲት ግራር በቅላ
ልቤን ወሰደችው – ከነሥሩ ነቅላ…”
ጂጂ በሌላ ስለ ምንጃር በምትሰንቃቸው – እና የተለመዱ የሚመስሉ ስንኞች ውስጥ ራሱ የምትከስታቸው ምስሎች – እጅግ ‹‹ጀንዩን›› (ፍጹም ለራስ ሃቀኛ) የሆኑ ምስሎች ናቸው፡፡ እዚህ ሀገርህ ላይ ካልሆነ የትም የማታገኛቸው፣ ምትክ የማታገኝላቸው ስዕላዊ መግለጫዎችና ስንኞችን ነው የምትሰጥህ ጂጂ፡-
“አንቺ የምንጃር ልጅ የተጉለቲቱ
የመንዜዋ ሎጋ ነይ እመቤቲቱ
ምንጃር ምንጃር ሲሉ በጣም ደስ ይለኛል
ስም ይወጣል እንጂ ምትክ የት ይገኛል
የሸኖ ብርቱካን ቢጠይሙ አሶች
አሁን የት ይገኛል እነ ምንጃሮች…”
(እንግዲህ ያገርህን ምንጃሮች አሜሪካ አታገኛቸውም! አውስትራሊያ አታገኛቸውም! የትም አታገኛቸውም፣ ከነጥይምናቸው፣ ቢቀሉ ብርቱካን፣ እንደ ራሷ እንደ ጂጂ መልክ – ቢጠይሙ ደሞ አሳ ከነሚመስል ጥይምናቸው – እዚህችው ሀገርህ ኢትዮጵያ ብቻ ነው የምታገኛቸው – እና እነሱንም እንዴት እንዲናፍቁህ እንደምታደርግህ እኮ ነው የምልህ – የስንኞቿ ቅለትና የፈጠራ አቅም በቃ ልዩ ነው!)
ሌላ ከጂጂ ዜማዎች ውስጥ ደጋግሜ ያገኘሁትንና በጣም ፈገግ ያሰኘኝን ነገር ለዛሬ ተናግሬው ልሰናበት፡፡ ያም ጂጂ ስለ ፍቅር ስታወራ፣ ስለ ፍቅረኛ ስታነሳሳ፣ የምታነሳው ነገር ነው፡- በእጅ መነካካት! ለእናት ሲሆን ‹‹ዳበሳ›› ይባላል አይደለም? ፈረንጆቹ ‹‹ካሬሲንግ›› ይሉታል፡፡ ኢትዮጵያዊ ልጅ ሁሉ ገና ከህጻንነቱ በእቅፍ ገብቶ በእናቱ ፀጉሩ እየተዳበሰለት፣ ና እስቲ ምን ሆነሃል አባዬ? እየተባለ በፍቅር እጆች እየተነካካ እየተፈተሸ ነው የሚያድገው ኢትዮጵያዊ ልጅ – ፍቅር ፍቅሩን ልብ ብለን ካነሳነው፡፡ እና ይመስለኛል ጂጂም – ይሄ ኢትዮጵያዊ መሠረቷ – ለፍቅር ስንኞቿ ሁነኛ እሳቤን ሳያቀብልላት አልቀረም! ስለ ፍቅር ስታሰናኝ – ጂጂ – የምትለውን ልብ ብለን ከሰማናት – ለምሳሌ – “ጉድፈላ” በሚለው ድንቅ ዜማዋ ላይ እንዲህ ስትል እናገኛታለን፡-
“እስቲ በጆሮዬ ፍቅርን ይድገም ያነብንብልኝ
ከትንፋሹ በልጦ የሚደመጥ ምን ሙዚቃ አለኝ
በእጁ ቢነካካኝ ድምጽ አወጣሁ እኔም እንደ ጊታር
ጉድ አረገኝ መዉደድ የዚህ ሰዉ ፍቅር
አቤት አቤት አቤት አቤት
ፍቅሬን ላንተ ሰጥቻለሁ – አርገኝ የቤት እመቤት
አረ ጉድ አረ ጉድ ፈላ…”
በሌላ “የአፋፍ ላይ አደይ” በሚለው አባይ ዙሪያን በሃሳብ እየቃኘች ስለምትናፍቀው ፍቅር በምታንጎራጉርበት ቆየት ያለ ዜማዋ ደግሞ ጂጂ ስለመዳበስ እንዲህ ስትል እናገኛታለን፡-
“እኔም ጎፈሬ ባላገር
ውሰደኝ ካባ ጎጆህ ስር
የመስኩ ሽታ አደስ አደስ
እቅፍ እቅፍቅፍ አርገኝ ዳበስ
መውደድ ዓለም
ያላንተ አልሆነም
እንዲያው ፍርጃ
የነካኝን እንጃ…”
ሌላውማ የጂጂ ‹‹እምቢ አሻፈረኝ›› የሚል ዜማዋ – በቃ ብዙዎቹ ስንኞች ስለመነካካት ናቸው፡፡ እና ያ የሀገራችን ሰው – በቃል መናገር ስለሚያፍርና ስለሚተፋፈር – በመንካት እና በመነካካት ፍቅሩን የሚነጋገረው – የሚገልጸው – በመንካት ያለ ቃላት ፍቅሩን የሚቀባበለው ነገር – ከሀገሯ ርቃ ያለችውን ጂጂን ትዝ እያለ ፈገግ ሳያሰኛት – አለፍ ሲልም ሳያስደምማት የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እኔን ራሴ ስንኞቿን እየመረጥኩ ስሰማቸው – ደስ የሚል ትዝታ የተቀላቀለበት ፈገግታን ያጭርብኝና ነፍሴ በሀገሬ ትዝታ ሀሴት ሞቅ ትላለች! ጂጂ በእምቢ አሻፈረኝ ስለመነካካት ነው የምታንጎራጉረው፡፡ ግን አትንካኝ! አትነካካኝ! እያለች ፡-
“እምቢ አሻፈረኝ እምቢ እንጃ
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ ተወኝ ተወኝ
ባልፈለግኩት ነገር አታግደርድረኝ
አትንካኝ አልኩት እጄን ልቀቀኝ
ለትንሽ ሰዓት ፈቀቅ አለና
ፈራ ተባ ሲል ትንሽ ቆየና
ይነካኝ ጀመር ደሞ እንደገና
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ እንጃ
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ ተወኝ ተወኝ
ባልፈለግኩት ነገር አታግደርድረኝ
ውሉን አይደብቅም ይሄ ሰው ጅል ነው
አልፎ ይነካኛል….. “
ጂጂ እንደ ትልልቅ የተከበሩ አባቶቻችን ትንቢተኛ ናት እንዴ?
* ከሚያስደንቁኝ ብቃቶቿ አንዱ አሁን ላይ ካለው ነገር ተነስታ የወደፊቱን የማየትና የመተንበይ ችሎታዋ ነው!
 
አንዳንዴማ “ጂጂ እንደ ትልልቅ የተከበሩ አባቶቻችን ትንቢተኛ ናት እንዴ?” ታስብለኛለች፡፡ እስኪ አሁን አገራችን ያለችበትን ውጥንቅጡ የጠፋውን የዘር ጥምዝምዝ ተመልከትና “አንድ ኢትዮጵያ” ከሚለው አልበሟ ላይ ሁለት ሙዚቃዎችን አድምጣቸው፡፡ ይሄ ከባድ ችግር ገና ያኔ በእንጭጩ እያለ ባለ ብሩህ አይምሮዋ ወጣት ታውቋት በቁጭትና ተስፋንም በሚሰጥ መልኩ እንዲህ ብላ ታንጎራጎር ነበር….
“እህህ እስከመቼ እህህ ያዘላልቀናል..???
ገና ብዙ መንገድ ብዙ ይቀረናል..
እስኪ ፈጠን ፈጠን እግር ተራመድ..
ምን ያኳትንሀል አመድ ለአመድ..???”
“ልቤ በፍርሀት እጅግ ተበክሏል..
በርሀብ በጥማት ሰውነቴ ዝሏል…
እግሬ አልንቀሳቀስ እጄ አልሰራም ብሏል..
ጆሮዬም አልሰማ አይኔም አላይ ብሏል..”
በነዚህ ጠንካራ ስንኞች ላይ እኛን ዘግይቶ ገብቶን አሁን ላይ በፍርሃት የምንማቅቅበትንና ያለንበትን አስፈሪና መጥፎ ሀገራዊ ሁኔታን በፍርሃትና በሽብር ትገልፅልናለች፡፡ ምን ያህል ጊዜ ልንቆይበት እንደምንችልም ትጠይቀናለች፡፡ በአስቸኳይ ከዚህ አስፈሪ አጣብቂኝ መውጣት እንደሚገባንም ጭምር በደንብ ትጠቁመናለች፣ ትጠይቀናለችም…?
“የራበኝ እንጀራ ወይኑ መስሏቸው..
የጠማኝ ወተቱ ወይ ጠጁ መስሏቸው..
ችግሬ ጭንቀቴ ምንጩ ያልገባቸው…
ያቺ ሰው ተራበች ሲሉኝ ሰማዋቸው..
እኔን የራበኝ ፍቅር ነው…”
ወረድ ብላ ደግሞ በነዚህ ስንኞች ለሷ የታያትን ፍርሃትና መሸበር ያላስተዋሉና ያልገባቸው፣ ጥያቄዋን በምን አይነት እሳቤ እንደሚመለከቱት ትገልፅልናለች… (ልክ እንደ ዘመናችን ፖለቲከኞች እኛ “ታላላቅ አባቶቻችን ያስቀመጡልንን የአንዲት ኢትዮጲያን ጥያቄና አብሮ የመኖር ህልውናችንን አስቀድሙልን” ብለን ስንጠይቅ.. “እንደዛ አይደለም እኔ አውቅልሃለሁ” ብለው ስለ አንዲት መፅሐፍ፣ ስለ ልዩ ጥቅምና ስለ ችግኝ ደጋግመው እንደሚደሰኩሩልን)፡፡
እና ጂጂ ከዚህ የመውጫ መንገዱን ታመላክተናለች፡፡ የራባትና አብዝታ የምትመኘው ታላቁን የሁሉ ነገር መጀመሪያና አስፈላጊ የሆነውን ፍቅር እንደሆነ በአንክሮ አስረግጣ ትናገራለች፡፡ ያው ፍቅር ቢሉ የታላቋን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ፍቅር ስጡኝ ብላ ትለምናለች…….!
“እኔስ የራበኝ ፍቅር ነው… የራበኝ
ፍቅር.. ነው የራበኝ
ፍቅር.. ነው የራበኝ
ፍቅር.. እየራበኝ…”
የቀሩት ስንኞችም ብዙ ብዙ ይናገራሉ፡፡ እኔ መግለፅ ከምችለው በላይ ይሄ ዘፈኗ ለኔ “ትንቢተኛ” ያስብላታል፡፡ ይሄ “አንድ ኢትዮጵያ” አልበም የተለቀቀው ካልተሳሳትኩኝ በ1990 ይመስለኛል፡፡ ያኔ አገራችን የነበረችበትን ሁኔታ መለስ ብለህ ስታስበው ጂጂ ለኔ የመጪውን ዘመን የመገመትና የመጠቆም፣ የማስጠንቀቂያ ደውል የማሰማት አቅሟ… እጅግ ይደንቀኛል…፡፡
የዚህ አልበም መጠሪያ በሆነው “አንድ ኢትዮጵያ” (“ONE ETHIOPIA”) ሙዚቃዋ ላይም ብዙ ነገር ትለናለች፡፡ ይሄን ሙዚቃ በጥልቀትና በሰፊው የመዳሰስ ሀላፊነቱን በአደራ መልክ ለአንተ ልስጥና.. ግን አንድ የምትመቸኝን ምርጥ የተስፋ ስንኝና አንገብጋቢውን እኛ አሁን ላይ የምንጠይቀውን ከዘር በፊት አንዲት ኢትዮጲያ ጥያቄ ባማረ መልኩ ታቀርብልናለች…
“ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ..
መድሀኒት አለው የማታ ማታ…
አገር በወገን እንዴት ይረታ…?
ፍቅር በነገር እንዴት ይፈታ..?
ዘር ሳይለያየን ወይ ሀይማኖት..
ከጥንት በፍቅር የኖርንባት..
እናት ኢትዮጵያ ውዴ ውዲቷ..
በጎጆ አያልቅም ሙሽርነቷ..!”
በምንም ልንገልፃት ይከብደናል፡፡ በጣም የተለየች ናት ጂጂ፡፡ አንደኛ ነች!!! በተከታይም ስለዚህች ምርጥ ሙዚቀኛ ጥሩ ገለፃና መረጃዎችን እንደምታስኮመኩመን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ ስለሰራችው “ወርቅና ሰም” አልበሟ ጥቆሟ ብታደርግልን ደስ ይለኛል፡፡ ሥራው ምርጥና መደመጥ የሚገባው ሆኖ ሳለ ለምን እንደሆነ አይገባኝም ብዙም ሲነገርለትና ሰውም ሲያደምጠው አልመለከትም፡፡
* * *
“ገዢ አጣሁ ገዢ አጣሁ ኧረ ፍቅር ግዙ፤ ቢጠቅም እኮ ነው ከእግዜር መታዘዙ” እያለች ለምታቀነቅነው የፍቅር ንግሥት ለጂጂዬ (በወዳጄ አጠራር “ለታላቋ በአባቶቻችን አምሳል የተከሰተች የጥበብ ትንቢተኛ” ለእጅጋየሁ ሽባባው) የበዛ ዕድሜ፣ ጤና፣ ፍቅር… እና ግርማ-ሞገስን… ከልብ ተመኘሁ፡፡
ለመውጫ ይችን …ተጋበዙ ዜማው ከናንተ
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ እንጃ
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ ተወኝ ተወኝ
ባልፈለግኩት ነገር አታግደርድረኝ
አትንካኝ አልኩት እጄን ልቀቀኝ
ለትንሽ ሰዓት ፈቀቅ አለና
ፈራ ተባ ሲል ትንሽ ቆየና
ይነካኝ ጀመር ደሞ እንደገና
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ እንጃ
እምቢ አሻፈረኝ እምቢ ተወኝ ተወኝ
ባልፈለግኩት ነገር አታግደርድረኝ
ውሉን አይደብቅም ይሄ ሰው ጅል ነው
አልፎ ይነካኛል….. “
እኔም በዚሁ የጂጂ ዜማ ተሰናበትኩ! ለስንኝ ፈታይዋ፣ ለዜማ ንግሥቷ፣ ለቅንብር መጢቃዋ፣ ለውቢቷ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ ለጂጂዬ (ለእጅጋየሁ ሽባባው) – እንደ ልማዴ ዝልዝል ያለ ረዥም ዘልዛላ ዕድሜን ከበዛ ጤና፣ ከበዛ ውበት ጋር ከልቤ ተመኘሁ፡፡
ለሁላችንም መልካም ጊዜ፡፡
ፈጣሪ ውብ ኢትዮጵያችንን፣ ከነውብ ሰዎቿ አብዝቶ ይባርክ!
Filed in: Amharic