>

"አስቀድማችሁ የሕዝቡን ትግል ተርጉሙልን !"    (ጠበቃ ተማም አባቡልጉ)

“አስቀድማችሁ የሕዝቡን ትግል ተርጉሙልን !”    

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ
               ክፍል አንድ
* ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ
* ለወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ
* ለወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ
 ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ . . .
ይህ ጽሑፍ እንደ መጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ይወሰድልኝ. . .
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ2007 እስከ 2010 ዓ/ም ያደረገዉ መራር ትግል አብዮት ወይስ ሪፎርም እንደሆነ መጀመሪያ ይተርጎምልኝ፤ ለምን ነበር ወገኖቻችን ያለቁት? የትግሉ መሰረታዊ ዓላማ እና ጥያቄ ምን ነበር? ህገ-መንግሥት ህዝብ ከመንግሥት እና መንግሥት ከህዝብ ጋር የሚያደርጉት {Social Contract} ማኅበራዊ ውል ነው፡፡ ህዝብ ፍላጎቱን በህገ-መንግሥት ውል ያስራል ተብሎ ስለሚታመን ህጉ በጥንቃቄ የሚተረጎመው የህዝቡን ፍላጎት አውቆ ለማስተግበር  ነው፡፡ ህጉን የመተርጎም ዓላማ የመጨረሻ ውጤት የህዝብ ፈላጎት እውን ማድረግ ከሆነ መጀመሪያ መተርጎም ያለበት ህዝብ ህገ-መንግሥቱን ንዶ መራር መስዋዕትነት የከፈለው ምን ፈልጎ ነው ? መጀመሪያ የህዝቡ ፍላጎት ይተርጎም የጠቅላይ ሚንስትሩ ወይም የመንግሥት የስልጣን ዘመን የሚመለከተው ጉዳይ ከዚያ በኋላ ይተረጎማል?
እንደ መንደርደሪያ
‹‹አዲስ አበባ ሚዲያ ኔት ወርክ›› የሚባል አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በታህሣሥ 09 ቀን 2012 ዓ/ም ምሽት ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲከናወን ማድረግ ባለመቻሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በጉዳዩ የሕገ-መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት ህግ ተርጓሚ ተብሎ ለተሰየመው የፖለቲካ ተቋም የፊደሬሽን ምክር ቤት እንደ ላከው ይህንን ተንተርሶ በፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገራችን ጉዳይ ያገባንል በሚሉ ዜጎች እቀረቡ ያሉ ተቃዎሞ እና ውዝግቦችን በተመለከተ ከአንድ የዶ/ርነት ማዕረግ ካላቸው ኢትዬጵያዊ ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ በስክነት አዳመጥኩ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ያገባኛል የሚሉ ዜጎች እና የመንግሥት አካላት የውዝግብ ማዕከል የሆነው ለሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አንዲላክ ፓርላማው ወሰነበት የተባላው ጥያቄ ‹‹ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ-19 ምክንያት
ምርጫዉን ማድረግ አልቻልኩም በማለቱ (ምርጫ ተደርጎ የተመረጠው መንግሥት ሥልጣን እስኪቀበል ድረስ) ሀገሪቷ
በምን ሁኔታ መመራት እንዳለባት ትርጉም ይሰጥበት›› የሚል ነዉ፡፡
ዶክተሩ ህግ የሚተረጎምባቸውን ሦስት አመክንዮዎች እንዲህ ሲሉ ዘረዘሩ . . .
1ኛ.  ሕጉ ግልፅ ያልሆነ እንደሆነ ግልፅ ለማድረግ
2ኛ. የህግ ክፍተት ያለ እንደሆነ ክፍተቱን ለመሙላት
3ኛ. ህጉ ግልፅ ሆኖ ለመተግበር የማይቻል ወይም የሚጎዳ ከሆነ
     እንዲሠራ ለማስቻል ወይም ጎጂ እንዳይሆን ለማድረግ ሕግ እንደሚተረጎም  በማብራራት የኔ ያሉትን ነጥብ ካስቀመጡ በኋላ በሕገ-መንግስቱ ላይ ትርጉም የመጠየቅን አካሄድ ለተቃወሙ ወገኖች የመልስ ምት በሚመስል ንግግራቸው ያሳምናል ያሉትን ደጋፊ ምክንያት አጽዖት ሰጥተው ዘረዘሩ . . .
በምክንያት አንድ ‹‹ወረራ ቢመጣስ ?›› የሚለውን ጥየቄ አዘል ምክንያት ካስቀደሙ በኋላ ‹‹ለአንድ መለስተኛ መብት (የመምረጥ መብት) ተብሎ ሀገር መታመስ የለበትም›› በማለት ሉዓላዊ የህዝብ መበት ከሚባሉት ቀዳሚውን አንቀፅ አርመጥምጠውት ወደ ሦስተኛው ነጥባቸው በመሻገር አሜሪካ እና ኢትዮጵያን አስተሳስሮ ያስረዳል ያሉትን ምሳሌ ጠቀሱ፡፡
እ.ኤ.አ ከ1861-1865 ዓ ም በተደረገዉ የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አብርሃም ሊንከን በኮንፌዴሬቶች (ደቡቦች) ላይ ያደረገውን ጦርነት ለዛሬዋ ኢትዮጲያ የማዕከላዊ መንግሥትና ክልሎች ግንኙነት ሁኔታ በምሳሌ መልክ ጠቅሰው ያንን ከዚህ እያጣቀሱ ‹ማዕከላዊው መንግስት እምቢ ባለው ክልል ያሉትን መሪዎች ከሥልጣን አስወግዶ (በኃይል መሆኑን ምሳሌያቸው ይጠቁማል) ክልሉን እራሱ በሚፈልጋቸው መሪዎች (ባስወገዳቸዉ ቦታ በመተካት) መምራት ይችላል› ሲሉ የሰነዘሩት በተለየ ሁኔታ ቀልቤን ሳበው፡፡
‹‹ወረራ ቢመጣስ›› ሲሉ በጥያቄ የሰነዘሩትን ሃሳብ በዚያው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃላ በሚል ምላሽ አጣፋሁት፡፡ ይሁን እንጂ ያለቦታው  መጠቀሱ በራሱ ግን እንደከነከነኝ አለ፡፡ ጎበዝ እንኳን ያለቦታው መጥቶ የሚሰነቀርን አንቀፅ ይቅርና በቦታው ቢሆንም ይሄን ሕገ መንግስት አስረጂ አርጎ መጥቀስ በህግ በኩል ከሞራል ሚዛን ሳይጎል እውነትን  ለሚያፈላልግ በእጅጉ ፈተና ነው፡፡ በጥቅሉ ይሄን ህገ-መንግስት መጥቀስ ደስ አይልምኮ ጓዶች፡፡
እውነት ለመናገር ትኩረቴን የሳበው የአብርሃም ሊንከን ምሳሌያቸው የትግራይ ክልልን እያሰቡ እንደተናገሩት በጣም ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡ ያልገባቸው ነገር ግን የትላንቱ የአብርሃም ሊንከን እርምጃ ኢትዬጵያውያን ዛሬ ለገጠመን ሁኔታ ጥሩ ምሳሌ አለመሆነ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ወደፊት የምለው ይኖረኛል ‹‹ለአንድ መለስተኛ (የመምረጥ) መብት ተብሎ ሀገር መታመስ የለበትም›› ላሉትም እንደ አንደ የህግ ባለሙያ መለስተኛ/ ከፍተኛ ወ.ዘ.ተ . . . የሚባል መብት መኖሩን ስለማላውቅ ዶ/ሩ መለስተኛ (ከፍተኛ) የሚባል መብት ስለመኖሩና በምን መነሻና መለኪያ እንደዚያ ተብሎ መብት እንደሚከፋፈል አለኝ የሚሉትን ማስረጃ ወይም የህግ ፍልስፍና ሊጠቅሱ ይገባ ነበር፡፡ የሌለ ነገር ሌኖራቸው አይችልምና  ምንም ስላላቀረቡ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለዉ አይኖርም፡፡ ነገር ግን ሕገ-መንግስት በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለንና የሚኖርን ግንኙነት የሚፈጥርና የሚመራ ሲሆን ደግሞ ይህ እውን የሚሆንበትና ሥራ ላይ የሚውልበትን ዋነኛው መንገድ የመምረጥ መብትን በመጠቀም (ምርጫ) ማከናወን ነውና ከዚህ አንፃር ምርጫና የመምረጥ መብት ዋናውና መሠረታዊው እንጂ ‹‹መለስተኛ መብት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የሚራከስ ጉዳይ አይችልም ፡፡
እዚህ ጋር አንድ ማስታወሻ ልተው ይህ ጽሑፍ ዶ/ሩን ለመዳኘት ወይም ስህተታቸውን ለማሳየት ሳይሆን እሳቸው እንዲናገሩበ ወይም እንዲናገሩለት የተፈለገውን ናሬቲቭ በመቃወም ስህተትነቱን ለማሳየት የቀረበ መሆኑን ተረዱልኝ፡፡ ይህም ማለት አሁን የገጠመን ችግር መንግሥት አልነጋገርበትም እያለ ያለው ጉዳይ የአጠቃላዩ የአገሪቷ ፖለቲካ ችግር አካል እንዳልሆነ አስመስሎ ለማቅረብ እየተሄደበት ያለውን ሁኔታ ስህተትነት ማለት ነው፡፡
‹‹ህግ ግልጽ ካልሆነ ይተረጎማል›› ለተባለው ምላሹ ‹ሕጉ ግልፅ ነው› እየተባለ ነው፤ ህግ ክፍተት ካለበት ይተረጎማል ያሉት ደግሞ እራሱን ችሎ የማይቆም ደካማ ሃሳብ ነው፡፡ ‹‹ክፍተት ካለበት›› የሚለው ቃል በራሱ ግልፅ አይደለም፤ ‹ክፍተት ለመሙላት› ማለት አዲስ አንቀፅ መፃፍን መፍጠርን (መጨመርን) ያጠቃልላል ይህ ደግሞ በህጉ ያልተገለፀ ሌላ አንቀጽ መጨመር ሕግ ማውጣት እንጂ ህግ የመተርጎም ሥራ አይደለም፡፡
ግልፅ ሆኖ ለመተግበር የማይቻልና ቢተገበር ጉዳት የሚያመጣ ሕግ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላልን፤ ምሳሌ ቢጠቅሱ፤ ግልፅ ሆኖ የማይሠራ ወይም ለመተግበር የማይቻል ወይም ቢተገበር ጉዳት የሚያመጣ ሕግ አውጪዎቹ እንዳይሠራ ወይም እንዳይተገበር ወይም ቢተገበር ጉዳት እንዲያመጣ ፈልገዉ ያወጡት ነው ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ግን አንድ ሕግ ግልፅ ሆኖ የማይሠራ ወይም ለመተግበር የማይቻል ወይም ቢተገበር ጉዳት የሚመጣ የሚሆነው እንዴት ነው ? እንዴት ሊሆን ይችላል? በህግ ፍልስፍና ዓለም ይህ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊከሰትልኝ አልቻለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን መልሳቸዉ ይህንንና ቀጥሎ ያሉትን ስላልመለሰልኝ የሚከተሉትን ለማለት ወደድሁ፡፡
አንድ
ውል (ሕግ) ግልፅ በሆነ ጊዜ ዳኞች በትርጉም ስም ተጨማሪ (ሌላ) ሕግ (ውል) መፍጠር አይችሉም የሚለዉ ተቀባይነት ያለው የሕግ መርህ ነው፡፡ ታዲያ ሕገ መንግስቱ ሕግ ከሆነ በነዚህ ግልፅ በሆነባቸው ቦታዎች ለምን መተርጎም አስፈለገ? ምን እንዲል ተፈልጎ? ያስ ሕግ ማውጣት አይሆንምን? ለምን? የ5 ዓመት የሥልጣን ጊዜው ያለቀን መንግሥት ለመተካት የሚያስችል የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ በደረሰ ጊዜ ምን መደረግ አለበት? (የሚለው ጭብጥ ምላሹ) አዲስ የሕግ አንቀጽ ጨምሩልኝ ማለት ማለት ነው፡፡ የሌለን ነገር (በመጨመር የሚገኝ) ውጤት  ሕግ በማውጣት እንጂ በመተርጎም የሚሸፈን አይደለም፡፡
ለምሳሌ ፡- ውሳኔዉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ወይም ሳያውጅ በሥልጣኑ ላይ ይቆያል የሚል ከሆነ (ለስንት ጊዜና ለዚያን ያህል ጊዜስ ለምን)? የሚለው የቆይታና የገደብ ጊዜ በአንቀጽ መቀመጡ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ አንቀጽ በራሱ ያልነበረ አዲስ ህግ ተጨመረ (ህግ ወጣ) ማለት ይሆናል እንጂ ተተረጎመ ሊባል አይችልም፡፡
አንድ መንግሥት ሥልጣኑን የሚያገኘው በሕዝብ ስለተመረጠ ነውና ይህ በሕዝብ ያልተመረጠና በሥልጣኑ የቀጠለ መንግሥት የሚኖረው ምን ዓይነት ሥልጣን ነው? ሥልጣኑ እንዲቀጥል ለተደረገበት ጉዳይ መልካም አፈፃፀም የሚረዳውን ብቻ ሥልጣን ይሠጠዋል ቢባል እንኳ እነዚህ ምንን ማጠቃለል (መያዝ) እንዳለባቸው በምንና በማን ይወሰናል? ያስ ለምን ሕጋዊ (ተቀባይነት ያለው) ይሆናል? እነዚህ በሙሉ ምላሽ ይጠይቃሉ፡፡
እንደሚባለው ጠንካራ መንግሥት ይሁን ቢባል ደግሞ ጠንካራ መንግሥት ሲባል በራሱ ምንድንነው?  የሚለውና ለምንና በምን ጠንካራ ይደረጋል? ይወሰናል? የሚሉት ሊነሱ የሚችሉ ቢሆንም እነዚህን ሁሉ የሚያስነሳ ሕግ መኖሩ ግን ግዴታና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው፡፡
ምክንያቱም ሕግን የመተርጎም ሥልጣን በዚያ ጉዳይ ላይ ሌላ አዲስ የሕግ አንቀጽ እስከ መጨመር ሊደርስ (ዳኞችን ያንን እስከ ማድረግ ሊያደርሳቸው) አይችልምና ነው፡፡ ህጋዊ ሊሆን የሚችለው ሕጉን ለማሠራት የተጨመረን (የወጣን) ሕግ ሕገ-መንግስታዊነት መተርጎም ነው፡፡ የወጣው ህግ ህገ-መንግሥታዊ ነው አይደለም ተብሎ ከመተርጎም በቀር ያልወጣ እና የሌለ ህግ ሊተረጎም አይችልም፡፡
ስለሆነም ፓርላማው በኮቪድ-19 ምክንያት የተፈጠረን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችለውን ሕግ (በዚህ ረገድ ሕገ-መንግስቱን ለማሰራት በሚል ወ.ዘ.ተ) ህግ በማውጣት እንጂ ለሕገ መንግሥት አጣሪው የሌለ ህግ እንዲተረጎም በመጠየቅ መጀመር አልነበረበትም፡፡ ስለዚህ ፓርላማው በህጉ ላይ የሌለውን የመንግሥትን ሥልጣን የሚያራዝም ህግ አውጥቶ  ያወጣሁት ህግ ሕገ-መንግስታዊ ነው ወይስ አይደለም ብሎ ለትርጉም ቢልከው ኖሮ ሕገ-መንግስታዊ ነው ወይም አይደለም የሚለው ክርክር መልክ ይዞ ይቀርብ ነበር፡፡
አሁን የገጠመን ችግር ምንድንነዉ?
እንደ አገር አሁን የገጠመንን ጭግር ምንድነው የሚለውን በሦስት ነጥቦች አሥቀምጠን ለያይተን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡
1ኛ. በኮረና ችግር (ወረርሽኝ) ምክንያት ‹‹ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ስለገጠመው›› ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ አልችልም
     ማለቱ ፤
2ኛ. አሁን ያለው መንግሥት የሥልጣን ጊዜው ከጥቂት ወራት በኋላ የሚጠናቀቅ መሆኑ
3ኛ. በአገሪቷ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተፈቀደው በሕገ መንግሥቱ መሠረት (በምርጫ) ብቻ መደረጉ ናቸዉ፡፡
ጭብጡ (ያላግባባው) ምንድን ነዉ?
ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማድረግ ያለመቻሉ የገጠመው ሁኔታ ከአቅም በላይ የመሆኑ ፍፁምነት (ሁሉንም አላግባባምና) መረጋገጥ አለበት፤ ፓርላማው ምርጫ ቦርድን ምርጫ ማድረግ የማትችለው ለምንና እስከ መቼ ነው ? ብሎ ጠይቆ በማስረጃና በበቂ ማብራሪያ ካረጋገጠ በኋላ ለምሳሌ (ምርጫ ማድረግ የምችለው የኮረና ቫይረሱ መድኃኒት ከተገኘለት ጀምሮ ባሉት 6 ወራት ውስጥ ነው) ሊል ይችላል፡፡  የገጠመው ሁኔታ ከአቅም በላይ ነው ወይስ አይደለም በሚለዉ ላይ ድምፅ በማሰጠት ውሳኔ አልተደረገም ፤ የዓዋጁ አካል አልሆነም፡፡
ቀጥሎም ከአቅም በላይ የሆነው ሁኔታ ቀርቶ የምርጫ ቦርድ ይህንን አቅሙን መልሶ እስኪያገኝ ድረስ ምን ዓይነት መንግሥት እንዴት ሊፈጠር ይችላል ወይም ይገባል? የሚለውን ከሕገ- መንግሥቱና ከሕግ ውስጥ ፈልጎና አስፈልጎ ውሳኔ ማሳለፍ (ሕግ ማውጣት) ይኖርበታል፡፡ ይህንን አላደረገም፤ ምክር ነው የጠየቀው፡፡ በዚህ መንገድ የተባለውን ሕግ ያለማውጣት ከሕገ-መንግስቱ ከሰው ሕሊና፤  ከአገር አንድነት፤  ከአገርና ከሕዝብ ሠላምና ደህንነት ጋር የሚጋጭ ነው ከሚል እምነት መነሳትና ያንን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡
ፓርላማው መነሳት ያለበት ከዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥራ አሥፈፃሚ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ከፍተኛውን የመንግሥት ክፍል በጋራ አቋቁሞ  የታችኛውን የመንግሥት መዋቅር በራሱ ያሉትን ተቋማት እየተጠቀመ እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ ይሥራ የሚል ሕግ አውጥቶ ራሱ ቢበተን ይህ አዋጅ ሕገ-መንግሥታዊነቱ በተርጓሚዉ አካል ሊረጋገጥ ይችላል፡፡
የጨነቀ ዕለት
ምክረ ሃሳብ . . .
1ኛ. ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ…እንዲል አበሻ የማላምንበትም ቢሆን ከሕገ-መንግስቱ አንፃር ለዛሬዉ የሚሆን አዋጅ
ናሙና እነሆ፤ የሕጉን ርዕስ ፡-
‹ሕገ-መንግሥቱ ሥራ ላይ እንዳይውል ያደረገው ሁኔታ እንዲወገድ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ሕገ-መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል እስከሚችልበት ጊዜ የሚቆይ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ብቻ ሥልጣን መያዝ እንዲቻል የሚያደርግ መንግሥት ለመመስረት የወጣ አዋጅ› ማለትም ይቻላል፡፡
በመግቢያው ላይም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9 መሠረት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫና በሕገ-መንግሥቱ መሠረት መሆኑ መደንገጉን፤ ምርጫ የሚያካሂደዉ ምርጫ ቦርድ መሆኑን፤ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ ስላለመቻሉና ምክንያቱም ከአቅም በላይ መሆኑን የነሱ (የፓርላማውና የመንግሥቱ) የሥልጣን ጊዜ ማለቁንና ከነሱ ሥልጣን መረከብ የሚችል በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትም ስለማይኖር መንግሥት የማይኖርበት ክፍተት ሊፈጠር መሆኑንና ይህ ቢፈጠር የሕገ- መንግሥቱ ብቻ ሣይሆን የአገሪቷና የሕዝቧም ሕልውና አደጋ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረግ (ሕገ መንግሥቱ ሊከበር የሚችለው አገር ሕዝብና እራሱ መቀጠል ከቻሉ ብቻ ስለሆነ)፤  ሕገ-መንግሥቱን የአገርንና የሕዝብን ደህንነት መጠበቅና መከላከል በመሆኑ ይህንን ማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ብቻ ሣይሆን ሰዋዊም አገራዊም ግዴታችን ስለሆነ ይህንን ያለማድረግ ሕገ-መንግስቱ ሀገርና ሕዝብን የመጥፋት አደጋ እንዲያገኛቸዉ የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን መፍቀድ ደግሞ ሕገ-መንግሥቱን መናድና የአገርን መፍረስ መፍቀድ ስለሚሆንና ስለማይቻለን፤
የሕገ-መንግሥቱንና የአገርን ሕልውናና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥለውን የመንግሥት አልባነት ሁኔታን ማስቀረት ሕገ-መንግሥቱን የመጠበቅ የመከላከልና ተርፎ ሥራ ላይ እንዲውል የማስቻል ድርጊት ቅድመ-ሁኔታና በሰውነታችን በኢትዮጲያዊነትና በሕገ-መንግሥቱ የተጣለብን ግዴታ በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ አጠቃላይ መንፈስና በአንቀፅ 51 በተሰጠን ሥልጣን መሠረት በአንቀፅ 54 መሠረት ለመረጠን ሕዝብ ለሕገ-መንግሥቱና ለሕልውናችን በመገዛት የሚከተለውን አውጀናል፡
 
  የጨነቀ ዕለት አንቀጾች
የስልጣን ጊዜዉ፡- ኮሮና ጠፍቶ ወይም መድኃኒት ተገኝቶለት አደጋ መሆኑ ከቀረበት (ከአቅም በላይ የሆነው ሁኔታ ከቀረበት) አንስቶ ምርጫ ቦርድ በ6 ወራት ውስጥ ምርጫ አድርጎ አዲስ መንግስት ሥልጣን እስከሚረከብበት ድረስ ይሆናል፡፡
የመንግሥቱንም ሥልጣን በተመለከተ፡- የሚቀነስ ወይም የሚጨመር መሆኑን ከሌሎች ጋር በመደራደር ወይም በራስ ማቅረብ አሊያም በሕገ- መንግስቱ አንቀፅ 60 መሠረት lame dake government ማድረግ አሊያም ከነሙሉ ሥልጣኑ ማስቀጠል (በቂ ምክንያት ካለ) ምርጫ የሚደረግበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲመለስ፤ ሕገ-መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል የሚችልበትን ሁኔታ ለመመለስ የኮሮናን መድኃኒት መፈለግን ጨምሮ አስፈላጊውን ሁሉ መፈፀም፤ እስከዚያዉም የአገርን አንድነትና የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ፤ ሁሉም እንዲታዘዙት መደንገግ፡፡
በተለይም ይህ መንግሥት ለአገሪቷ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ችግሮች በሚቻል መንገድ (ኮሮና እያለም) ሁሉንም እያወያየ መፍትሔ እንዲፈልግ መደንገግ
ሥራዉን እንዴት እንደሚሠራ፡- በተለመደዉ ሁኔታ ወይም ሌላ ካለ መግለፅ፤ ትብብርን በሚመለከት ለዚህ መንግሥት ያለመተባበር ሕገ-መንግሥቱን መናድ እንደሆነ መደንገግ-ቅጣት መጣል-ወይም እስከ ዛሬ ካለው መንግሥት ጋር አንድ መሆኑን መጥቀስ፤
መንግሥት ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተደራድሮና ተስማምቶ የሚያመጣውን ከላይ የተጠቀሰውን አዋጅ ማድረግ፤ ይህንን አዋጅ ሕገ-መንግሥታዊነቱን ማስተርጎም ይቻል ይሆናል፤ ካልሆነ ግን ይህንን መፍትሔ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ቢያመነጭ እንኳ ሕገ ወጥና ዳኝነት መስጠት ሣይሆን ለመንግሥት የሕግ ምክር መስጠት (ሕገ ወጥ) ይሆናልና አይቻልም፡፡
መንግሥቱ በ decree (ፓርላማው ቀጥሎ)  በህጉ ያስተዳድራል፤ አለበለዚያ ደግሞ ቢበዛ በግልፅና በማያሻማ መንገድ {boldly} እነዚህን ሁሉ ጠቅሶ በዚህ ወቅት ሥልጣን ለቅቆ መበተን ኃላፊነት የጎደለው የአገርንና የሕዝብን ሠላም ደህንነትና ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የሚናድበትን ሁኔታ እያወቁ መፍጠር ስለሆነ ይህ ፓርላማና መንግሥት ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማድረግ እንዳይችል ያደረገዉ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ተወግዶ ከዚያን በኋላ በ6 ወራት ምርጫ አድርጎ የተመረጠው መንግሥት ሥልጣን መረከብ እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ (ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተቃጣው አደጋ ቆሞ ሕገ- መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል እስከሚቻልበት ድረስ) በሥልጣን ላይ እንዲቆይ አውጀናል› ማለት ነበረበት፡፡
2ኛ. ፓርላማው የምርጫ ቦርድን ሃሳብና ጥያቄ ከሰማ በኋላ ማድረግ የነበረበት ኮቪድ-19 ጠፍቶ አገሪቷ ምርጫ ማድረግ ችላ በምርጫ የቆመ መንግሥት ሥልጣን እስከሚረከብበት ባለው ጊዜ አገር እንዴት መመራት እንዳለባት ጠቅላይ ሚንስትሩን ወደ ፓርላማው ጠርቶ ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ የሚሆንን ሃሳብ ከሚመለከታቸውና ጉዳዩ ከሚያገባቸው ሁሉ ጋር ተነጋግረህ ተመካክረህ (ራስህ አመንጭተህ) አቅርብ በማለት በቀረበው ሃሳብ ላይ በሚያመች በሚቻልና ተገቢ በሆነ መንገድ መወሰን፡፡
(መንግሥት ከሚመለካታቸው ጋር በጋራ መክሮ አማራጭ ማቅረብ ያልቻለ ካልሆነ) ተቃዋሚዎችን፤ የሙያ ማህበራትን፤ የሲቪክ ማሃበራት  የሴቶች፤ የወጣቶች፤ የአካል ጉዳተኞች፤ የሐይማኖት አባቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ የሁሉንም ክልል ፕሬዘዳንቶች ጨምሮ  አወያይቶና ፓርላማው ራሱም ተወያይቶበት በሕግ መልክ መቅረፅ የተሸሉ አማራጮች ነበሩ፡፡ ይህ አልሆነም፤ ወይም ሊደረግ አልተፈለገም፡፡
  ክፍል ሁለት ይቀጥላል . . .
Filed in: Amharic