>

የፍጹም ተሀራሚው ሳልሳዊ ፓትርያሪክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ሐውልት ዳግም ተመረቀ!!! (ሀራ ዘ-ተዋህዶ)

  • የፍጹም ተሀራሚው ሳልሳዊ ፓትርያሪክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ሐውልት ዳግም ተመረቀ!!!

  • ሀራ ዘ-ተዋህዶ
  • እጅግ ፈታኝ በኾነ ወቅት ቤተ ክርስቲያኗን በመምራት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፓትርያርክ ናቸው::”
  • /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
  • ተወልጄ ያደግኹበት ቦታ ይህ ነው ብለው ከመናገር ይልቅ በፍጹም ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ያምኑ ነበር፡፡ አበ ብዙኃንነትን አጉልተው በማሳየት ኹሉን እኩል በመመልከት ብቃታቸው ብዙዎችን ሲያስገርሙ የኖሩ አባት ናቸው፡፡”
  • /ዜና ሕይወታቸው/
  • ሐውልቱን ለማስጠገን ስጀምር የቅዱስነታቸውን ታሪክና ሐዋርያዊ አገልግሎት አንብቤአለኹ፤ በእውነት ትልቅ አባት ነበሩ፤ ልቤ ተነክቷል፤ ይህን በመሥራቴም ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ፡፡” 
  • /በጎ አድራጊው በኵረ ምእመናን ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ/

*          *          *

በበጎ አድራጊው በኵረ ምእመናን ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ ድጋፍ ዕድሳት የተደረገለት የፍጹም ተኃራሚው ሣልሳዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ሐውልት

በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኘውና ሙሉ ጥገና እና ዕድሳት የተደረገለት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ሐውልት ነገ፣ እሑድ፣ ግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ዳግም ምረቃ እንደሚደረግለት ተገለጸ፡፡

ከጠዋቱ 3፡00፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት ዳግም ምረቃ የሚደረግለት የቅዱስነታቸው ሐውልት፣ ከ1ነጥብ 5 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጧል፡፡

ከ28 ዓመታት በፊት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተሠራው ሐውልት፣ አርጅቶና ፈራርሶ የቆየ ሲኾን፤ በኵረ ምእመናን ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ/ወልደ ዐማኑኤል/ በተባሉ በጎ አድራጊ ምእመን ድጋፍ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠግኖ ለዳግም ምረቃው መብቃቱ ታውቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የመታሰቢያ ሐውልቱን ለማስጠገን በዝግጅት ላይ እንደነበር የጠቀሱት የመንበረ ፓትርያርኩ የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፤ የመታሰቢያ ሐውልቱ፥ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክትትልና በበጎ አድራጊው ባለሀብት ሙሉ ድጋፍ ያማረና ጥንቃቄ የተሞላበት ዕድሳት እንደተደረገለት ገልጸዋል፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርከክ አቡነ ማትያስ፣ በመምሪያው በተዘጋጀና ለመታሰቢያ ሐውልቱ ዳግም ምረቃ ታትሞ በወጣ መጽሔት ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ እጅግ ፈታኝ በኾነ ወቅት ቤተ ክርስቲያኗን በመምራት፣ ሰበካ ጉባኤን በማጠናከርና ምእመናን ጊዜው በፈጠረው ፈተና ከሃይማኖት እንዳይናወጡ በማድረግ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፓትርያርክ ናቸው፤” ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባትንና መምህርን ማሰብ እግዚአብሔርን ማሰብና ሃይማኖትንም በተግባር መፈጸም እንደኾነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፤ በጎ አድራጊው በኵረ ምእመናን ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶላቸው ሥራውን ሠርተውና አጠናቀው በማስረከባቸው አመስግነዋቸዋል፤ የአባቶቻችን ታሪክ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መኾኑን ኹሉም ዐውቆ ይህን ዓይነቱን የተቀደሰ ተግባር መከተል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በፈቃደ እግዚአብሔር ተመርጠው ያገለገሏት ቅዱሳን አበው ፓትርያርኮች፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሕይወተ ሥጋ ሲያርፉ ታሪካቸውንና አገልግሎታቸውን በመጽሐፍ ለትውልዱ ከማስተማርና ከመግለጽ በተጨማሪ፣ የመታሰቢያ ሐውልት ሠርቶ ትውልድ እንዲዘክረው ማድረግ የተለመደ ተግባር መኾኑን በመልእክታቸው አስፍረዋል፡፡

ቅዱስነታቸውን ትውልድ ኹሉ እንዲያዘክራቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መመሪያ መሠረት በመካነ መቃብራቸው የመታሰቢያ ሐውልት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ተሠርቶ እንደነበር የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፤ ሐውልቱ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በመጎዳቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያስጠግነው በዝግጅት ላይ ሳለ እግዚአብሔር የፈቀደላቸው በጎ አድራጊ ምእመን፣ እኔ ላድሰው ብለው በቀና መንፈስ በመነሣሣት ያቀረቡት ሐሳብ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ ተሰጥቶበትና ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም የቀደመ ክብሩንና የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት በጠበቀ መልክ እንዲሠራ ከበጎ አድራጊው ባለሀብት ጋር በመመካከር ሥራው ተጠናቆ ለዚኽ በመብቃቱ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፤ ብለዋል፡፡ ለሥራው ቅን ትብብር ያደረጉትን የካቴድራሉን የሰበካ ጉባኤ አባላት አመስግነው፤ በጎ አድራጊው ባለሀብት ከነቤተሰባቸው ያደረጉትን ታላቅ መንፈሳዊ ሥራ በማሰብ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እንደምትጸልይላቸው አስታውቀዋል፡፡

“ሐውልቱን ሳየው ተጎድቷል፤ የተወሰነ አካሉም ወላልቋል፤” ሲሉ ከዕድሳት በፊት የነበረውን ገጽታ ያስታወሱት በኵረ ምእመናን ቁምላቸው፣ ለሥራው መቃናት ሐሳባቸውን ተቀብለው በፍጹም አባትነት ያስተናገዷቸውን አባቶች እና አገልጋዮች አመስግነዋል፡፡

“ሐውልቱን ለማስጠገን ስጀምር የቅዱስነታቸውን ታሪክና ሐዋርያዊ አገልግሎት አንብቤአለኹ፤ በእውነት ትልቅ አባት ነበሩ፤ በሚል ልቤ ተነካ፤ ይህን በመሥራቴም ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ፤” ብለዋል፤ ለመጽሔቱ በሰጡት አጭር ቃለ ምልልስ፡፡ በጎ አድራጊው ባለሀብት፣ ቀደም ሲል የሲ.ኤም.ሲ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በግል ገንዘባቸው ሠርተው ያስረከቡና በአኹኑ ወቅት ተስፋፍቶ በመሠራት ላይ ባለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም የአሠሪው ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር እንደኾኑ በመጽሔቱ ተጠቅሷል፡፡

ፍጹም ተኃራሚው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ በጾም፣ በጸሎት፣ በቀዊም እና በስግደት ተወስነው ቤተ ክርስቲያንን ለ12 ዓመታት በፓትርያርክነት ከአገለገሉ በኋላ በድንገተኛ ሕመም ያረፉት ግንቦት 28 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲኾን፤ ግንቦት 30 ቀን 1980 ዓ.ም. ነበር በካቴድራሉ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው፡፡

*          *          *

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዜና ሕይወትና ሥራዎች

ባ መልአኩ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መስከረም 10 ቀን 1910 ዓ.ም. የንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስ ታማኝ ወታደር ከነበሩት አባታቸው ከወታደር ወልደ ሚካኤል አዳሙ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘውዲቱ ካሳ በቀድሞው ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ማኅደረ ማርያም ተብላ በምትታወቀው ገዳም አካባቢ ጋዠን በምትባል ቦታ ነው፡፡

ወላጆቻቸው ገና በልጅነታቸው ነበር በሞት የተለዩአቸው፡፡ በማኅደረ ማርያም ጋዠን ከሚገኙት መሪጌታ ወርቅነህ ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ወደ ደብረ ታቦር ተሻግረው፣ እናቲቱ ማርያም በተባለች ደብር ያስተምሩ ከነበሩት አለቃ ቀለመ ወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ማዕርገ ዲቁና ተቀብለው ወደ ማኅደረ ማርያም በመመለስ በዲቁና አገልግለዋል፡፡

በጎጃም ናየረዝ ሚካኤል ከተባለው ቦታ ከመምህር ልሳነ ወርቅ ቅኔንና ዜማን ለስምንት ዓመታት ተምረዋል፡፡ የኢጣልያ ፋሽስት ጦር ኢትዮጵያን በግፍ መውረሩን ተከትሎ በሰላም ለማገልገል ባለመቻላቸውና ቀጣይ ሕይወታቸውንም በትኅርምት እና እግዚአብሔርን በማገልገል ለመኖር በመወሰናቸው፤ ራቅ ወደአለ ቦታ ለብሕትውና ለመሔድ ወሰኑ፡፡

ውሳኔአቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲያወጡ ሲያወርዱ፣ የጓደኞቻቸውን ምክርም ሲጠይቁ አንድ ባልንጀራቸው፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ አካባቢ፣ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጋደሉበት፤ ከጊዜ በኋላ ግን በጥምቀት የቅድስት ሥላሴን ልጅነት ያላገኙ ሰዎች የሚበዙበት ለብሕትውናና ለአገልግሎት የሚመች ቦታ እንዳለ ባመለከታቸው መሠረት፣ ዝናው ከጎንደር ስቦ ወደአመጣቸው ደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ገብተው በበዓት ተወስነው መኖር ጀመሩ፡፡

ከጥቂት ቆይታ በኋላም የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት መምህር ወልደ ኢየሱስ፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን በተለይም የማር ይሥሓቅንና የመጻሕፍተ ሊቃውንትን ትርጓሜያት በጥልቀት ተማሩ፡፡ ቅዱስነታቸው ከመማር ጋር በነበራቸው የቁም ጽሕፈት ችሎታ በመምህራቸው ታዝዘው ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጻፉ ለገዳሙ ማኅበር እንዲዳረስ አድርግዋል፡፡

በዚኽ መልኩ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር ሲመረምሩና ሲያጠኑ ቆይተው በዚያው ማዕርገ ምንኵስናን ተቀበሉ፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከግብጻዊው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ማዕርገ ቅስናን ተቀብለው ወደ ገዳሙ ተመልሰው፣ በጾም በጸሎት፣ በሰጊድና በትኅርምት በገድልና በልዩ ልዩ ትሩፋት ተወስነው እስከ 1940 ዓ.ም. ድረስ በዓታቸውን አጽንተው ቆይተዋል፡፡

ከ1940 ዓ.ም. በኋላ በዓታቸውን በዚያው በገዳም አድርገው በአውራጃው በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች እየተዘዋወሩ ሲያስተምሩ ከሊቀ ጳጳሱ አቡነ ጢሞቴዎስ ከተጻፈላቸው የፈቃድ ደብዳቤ በቀር የተቆረጠላቸው ደመወዝ ወይም የተሰፈረላቸው እኽል አልነበረም፡፡

በቅዱስነታቸው ትምህርት ከ300ሺሕ በላይ ኢአማንያን አምነው እንደተጠመቁ ይነገራል፤ ያመኑቱም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈጽሙባቸው በኹሉም ወረዳዎች 65 አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ እንዲኹም፤ ልጆቻቸው መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ትምህርት የሚማሩባቸው 24 ትምህርት ቤቶችን አቋቁመዋል፡፡

በወላይ ሶዶ ከተማ በደብረ መንክራት ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አካባቢ፣ 11 ክፍል የድኩማን ቤት በመሥራት፣ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በዚኹ ከተማ ከ400 ያላነሰ ሰው መያዝ የሚችል የወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አዳራሽ አሠርተው በአገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ አንድ ክሊኒክ አቋቁመው የከተማው ሕዝብ እንዲገለገልበት አድርገዋል፡፡ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው ቆንቶ በተባለው ቀበሌ በ1954 ዓ.ም. ያሠሩት የቃጫና የልዩ ልዩ ጥበበ እድ ሥራዎች አዳራሽ የአካባቢው ችግረኞች እየሠሩ ራሳቸውን እንዲረዱ አድርገዋል፡፡

አካባቢው በመናፍቃን የተጠቃ ስለነበር ባቋቋሙት ማኅበር አማካይነት ሰባክያንን በመቅጠር አባላቱም በገዛ ፈቃዳቸው እንዲሰማሩ በማድረግ ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በቤተ መንግሥቱ ዕውቅና የነበረውንና የሰባቱ አውራጃዎች ተወካዮችን በአባልነት የያዘውን የመገበሪያ ቦርድ የተሰኘ አካል በማቋቋም፤ ሕዝቡ ገንዘብ እንዲያዋጣ በማሳመን የአካባቢውን አብያተ ክርስቲያን አገልግሎት ማፋጠን ቀዳሚ ዓላማው ያደረገ ብርሃነ ሕይወት የተሰኘ ገባሬ ሠናይ ድርጅት አቋቁመው ነበር፡፡

ለፕትርክና ምርጫ ከቀረቡት አምስት አባቶች አንዱ መኾናቸውን ባላሰቡት ኹኔታ የሰሙት ቅዱስነታቸው፤ “መንበሩ ለእኔ አይገባም” ብለው ተቃውመው ነበር፡፡ በዚኽ የተነሣ ቅዱስነታቸው፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በምትገኝ አንዲት ክፍል ውስጥ ተቀምጠው በዘብ እንዲጠበቁ ተደርገው ነበር፡፡

በምርጫው ከተሳተፉት 909 ወኪሎች አብላጫ ድምፅ በማግኘት ሦስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኾነው ከተመረጡ በኋላ፣ ሐምሌ 11 ቀን 1968 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተብለው ማዕርገ ጵጵስና ተቀብለዋል፤ ነሐሴ 23 ቀን 1968 ዓ.ም. ደግሞ አባ ተክለ ሃይማኖት ሣልሳዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ተብለው በቅዱስ ሲኖዶስ ተሹመዋል፡፡

ከሢመተ ፕትርክናቸው በፊት ይኹን በኋላ በትግሃ ጸሎት፣ በገድል በትሩፋት የተፈተነ መንፈሳዊ ሕይወት የነበራቸው፤ ከፍቅረ ንዋይ የነጹ፤ ለተቸገሩት የሚሰጡትን ርዳታና በጎ አድራጎት ማንም እንዲናገርላቸው የማይፈልጉ፤ ሠርቶ የማሠራትና በየጊዜው አዳዲስ የሥራ መዋቅሮች እንዲከፈቱ የማበረታታት ልምድ የነበራቸው ደግ አባት እንደነበሩ የሚያውቋቸው ኹሉ ይናገራሉ፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መሠረቱ ተጥሎ የነበረውን የቃለ ዓዋዲ ደንብ በማሻሻልና ከወቅቱ ኹኔታ ጋር እንዲሔድ በማድረግ፣ ሰበካ ጉባኤያት በማዕከል እንዲመሩ ኾነው በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲቋቋሙ፤ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲኾኑ አድርገዋል፡፡

በየዓመቱ በሚካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በማስወሰን፣ ለበርካታ የአብነት መምህራን የወር ደመወዝ እንዲመደብላቸው እና ተማሪዎችም ተመሳሳይ ድጎማ እንዲታሰብላቸው አድርገዋል፡፡

በከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ለወሰኑ ዓመታት ሥራውን አቋርጦ የነበረው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት በ1974 ዓ.ም. ተከፍቶ ሥራውን እንዲጀምር አድርገዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት የካህናት ማሠልጠኛዎች እንዲቋቋሙና ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ለነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ለኾኑት የሰንበት ት/ቤቶች ተማሪዎች ከፍ ያለ አመለካከትና ትኩረት ነበራቸው፡፡ በዚኽም መሠረት በእያንዳዱ አጥቢያ የሰንበት ት/ቤቶች ተቋቁመው ሰፋ ያለ አገልግሎት እንዲያበረክቱ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች እየተዘዋወሩ ያስተምሩ ለነበሩ መምህራን በየወሩ 730 ብር ከደመወዛቸው አስተዋፅኦ ይሰጡ ነበር፡፡

በፓትርያርክነቱ የቅድስና መንበር ከመቀመጣቸው በፊት ይኹን በኋላ የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነት ሳያደርጉ ከየአቅጣጫው እያሰባሰቡ በምግበ ሥጋ እና በምግበ ነፍስ የሚረዷቸው ድኻ አደጎችና ድኩማን እጅግ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በየአህጉረ ስብከቱ 36 የዕጓለማውታ ማሳደጊያዎች በማቋቋም በርካታ ኢትዮጵያውያንን አሳድገውና አስተምረው በልዩ ልዩ ሞያ ተሰማርተው አገራቸውንና ወገናቸውን ለማገልገል በቅተዋል፡፡

በድርቅ የተጎዱ ወገኖች በሚገኙባቸው አካባቢዎች፣ ያለምንም የሃይማኖት ልዩነት ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉባቸው መሠረተ ልማቶችን፣ የአገልግሎት ተቋማትንና የጥበብ እድ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን አስፋፍተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ በርካታ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በየአቅራቢያው እንዲሠሩ፤ በውጭም ለምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማሟላትና እንዲኹም በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና እምነት አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ለሚፈልጉ የውጭ አህጉር አማንያን አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነፅና አገልጋዮችን በመላክ ከፍተኛ የኾነ የዕድገትና የጥንካሬ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡

በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም የሥራ ጉብኝት በማድረግ፤ ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጎበኙ በማድረግ፤ በዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤዎች ላይ በመገኘትና ስለ ሰላም አስፈላጊነት በመመስከር፤ የቤተ ክርስቲያን ልኡካን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ እንዲገኙ በማድረግ፤ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ስለሌላው የክርስትና ዓለም፣ ሌላውም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን በበለጠ እንዲያውቅ ለማድረግ ይከተሉት የነበረው አቋም ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ መታወቅን አትርፎላታል፤ ተፈላጊውን የተራድኦ ግንኙነት ለማጠናከር አስችሏታል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ተግባር የሚገልጹ መጽሔቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተሙ ለውጭው ዓለም እንዲሠራጩ አድርገዋል፡፡

በዘመነ ፕትርክናቸው ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት 28 ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመዋል፡፡

ለዘመናት የምእመናን ጥያቄዎች ኾነው ሲያነጋግሩ የነበሩ ጉዳዮች ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲያሳልፍባቸው በማድረግ በኩል የሚጠቀሱ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከሰባቱ አጽማዋት አንዱ የኾነው ጾም ገሃድ፣ ጾመ ነቢያት የሚገባው በየዓመቱ ኅዳር 15 እንደኾነና ዓሣ በጾም ወራት እንደማይበላ በምልዓተ ጉባኤ አቅርበው ያስወሰኗቸው ውሳኔዎች አይዘነጉም፡፡

ለቤተ ክርስቲያን የህልውና አደጋ ጋርጦ የነበረው የወቅቱ መንግሥት ርእዮተ ዓለም፤ በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ያደረሰው ጥፋት በእኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳያደርስ በጸሎት፣ በጥበብ እና በትዕግሥት በታለፈበት አመራራቸው ይታወሳሉ፡፡

ቅዱስነታቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገረ ሙላድ እያላቸው፣ ተወልጄ ያደግኹበት ቦታ ይህ ነው ብለው ከመናገር ይልቅ በፍጹም ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ያምኑ ነበር፡፡ የካህነ እግዚአብሔር መልከ ጼዴቅን አሰረ ፍኖት በመከተል፤ እንደ አብርሃም አበ ብዙኃንነትን አጉልተው በማሳየት ኹሉን እኩል በመመልከት ብቃታቸው ብዙዎችን ሲያስገርሙ የኖሩ አባት ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መቼም ቢኾን አልጋ ላይ ተኝተው የማያውቁ ፍጹም ተኃራሚ አባት እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በአመጋገብ በኩልም ቢኾን፣ በሀገር ውስጥ ይኹን በውጭ ከበሶ ወይም የተቀቀለ ድንች በስተቀር ሌላ ነገር ቀምሰው አያውቁም ነበር፤ ይባላል፡፡

ለዕረፍታቸው ምክንያት የኾነው፣ ሰፊ አገልግሎት እና ተጋድሎ ሲፈጽሙበት የቆዩበትን የወላይታ ደብረ መንክራት ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በመጎብኘት ላይ ሳሉ በድንገት መታመማቸው ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ በአስቸኳይ መጥተው በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቢቆዩም ሊድኑ አልቻሉም፡፡ በመኾኑም ከ12 ዓመታት የፓትርያርክነት አገልግሎት በኋላ ግንቦት 28 ቀን 1980 ዓ.ም. በተወለዱ በ70 ዓመት ዕድሜአቸው ከዚኽ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡

መላ ዘመናቸውን በጾም፣ በጸሎትና በሰጊድ ያሳለፉት ቅዱስነታቸው፣ ከሞተ ዕረፍታቸው ቀደም ብሎ የሰውነታቸው ክብደት 25 ኪሎ ግራም ነበር

 አስከሬናቸውም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ዐርፎ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ፍትሐት ሲደርስ ከቆየ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው፣ ግንቦት 30 ቀን 1980 ዓ.ም. ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ የቅዱስነታቸው አገልግሎት ሲዘከር ይኖር ዘንድም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ አስከሬናቸው ባረፈበት ሥፍራ የመታሰቢያ ሐውልት አቁሞላቸዋል፡፡

ሐውልቱ ከ28 ዓመት በኋላ በማርጀቱና በመፈራረሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ ለማስጠገን በዝግጅት ላይ ሳለ፣ ክቡር አቶ ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ/ወልደ ዐማኑኤል/ በግል ወጪአቸው ለማስጠገን በጠየቁት መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ተፈቅዶላቸው፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቅርብ መመሪያና ክትትል በ1.5 ሚሊዮን ያማረ ዕድሳትና ጥገና የተደረገለት ሐውልት ለዛሬ ዳግም ምረቃ በቅቷል፡፡ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ወልደ ዐማኑኤልን በሕይወትና በጤና ከነቤተሰቦቻቸው እንዲጠብቃቸው ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ትጸልይላቸዋለች፡፡

ምንጭ፡- ዝክረ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ የመንበረ ፓትርያርኩ የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ለመታሰቢያ ሐውልታቸው ዳግም ምረቃ ያዘጋጀው መጽሔት

Filed in: Amharic