አስቀድማችሁ የህዝቡን ትግል ተርጉሙልን !!
ክፍል ሁለት
ተማም አባቡልጉ (የህግ ባለሙያ)
በህጉ መርህ መሰረት የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔውም እንደ ፍርድ ቤት ያለ ገለልተኛ ውሳኔ ሰጪ መሆን ስለሚገባው፤ አማካሪ ድርጅት ባለመሆኑ ፓርላማው ሕጉን ለማውጣት እንኳን መምከር ያለበት ከሌሎች አካላት እንጂ ከጉባዔው ጋር ሊሆን አይገባም። ጉባዔውም በቀጥታ ምክር መስጠት ይቅርና በቀጥታም ባይሆን ምክር መስጠት የሚመስል ነገር እንኳን ለፓርላማው ማቀበል መሰረታዊውን የህግ መርህ ተቃርኖ መቆም ነው፡፡
የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም ከሚደረግ የፖቲካ ውዝግብ እራሱን አርቆ በገለልተኛነት ህግ ለመተርጎም የተሰጠውን ኀላፊነት ሊወጣ ይገባል ስል በይሁናል ግምት ወይም ቢሆን ይሻላል ከሚል የግል እምነትና ፍላጎት በመነሳት ሳይሆን ህጉ የሚለው ያንኑ ብቻ በመሆኑ እንደሆነ ጥቂት ማስረጃ ጠቅሼ ልልፍ ፡-
1ኛ. የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በህግ የተሰጠው የሥራ ደርሻና ኀላፊነት. . . አንድ አሠራር ድርጊት ሕግ ወይም ውሳኔ ሕገ-መንግስታዊ መሆኑን ወይም ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ይሄድ/አይሄድ አይቶ መወሰን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕገ-መንግሥቱ አንፃር ታይቶ ትርጉም የሚሰጥበት ድርጊት፤ አሠራር፤ ሕግ ወይም ውሳኔ ሊኖር ይገባል፤ ከዚያም ከአቤቱታው ጋር ለተርጓሚው አካል መቅረብም ይኖርበታል፡፡
2ኛ. በማያሻማ መንገድ በሚመለከተው አንድ ባለሥልጣን/ መስሪያ ቤት ወይም ሌላ አካል ‹‹ይህና ያ ድርጊት ተፈፅሟል›› ወይም ‹‹ይህና ያ ውሳኔ ተሠጥቷል›› ወይም ‹‹ይህና ያንን አሰራር እንዲህ የሚባል አካል (ስሙን ጠቅሶ) ስለተከተለ›› ወይም ‹‹ይህና ያንን ሕግ የሆነ አካል ስላወጣ እነዚህን አቅርበናልና የእነዚህን ሕገ-መንግሥታዊነት
እንዲወስንልን (እንዲተረጉምልን) እናመለክታለን›› መባል ይኖርበታል፡፡
3ኛ. ህግ የጣሰ ድርጊት ህጋዊ ውጤት አይኖረውም ከላይ ከተጠቀሰው ውጪ የሚኖር አካሄድ የሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም መጠየቅ/መስጠት መሆኑ ይቀርና ምክር እና አስተያየት መጠየቅ ወይም መስጠት ይሆናል፡፡ ተርጓሚ አካል ከዳኝነት ስራው ወጥቶ ምክር ሰጪ ከሆነ ህግ ተረጎመ ሊባል አይችልም፡፡ አሁን የሚታየው የመንግስት አቅጣጫ በሕገ-መንግስት ትርጉም ሥም በዚያ ጉዳይ ላይ አዲስ ሕግ አውጣልኝ የሚል የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡ ይህ ማላት ህግ አውጪውም ሆነ አሥፈጻሚው አካል ተርሚው የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ የሌለ አንቀፅ ጨምሮ በትርጉም ሥም ህግ ያውጣ እያለ መሆኑን ከሚያስረዳ በቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
4ኛ. የህግ አስተያየትን በተመለከተ ፓርላማው የሕግ አስተያየት መጠየቅ ያለበት የራሱን የሕግ ክፍል ወይም የሚመለከተውን ቋሚ ኮሚቴ ወይም ሌላ አካልን ነው፤ ለአጣሪ ጉባኤው ያቀረበውን ጥያቄ ማቅረብም ያለበት ወይም የነበረበት በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ ለማውጣት እንዲያስችለው ለሚረዱት ህግ አመጪ ወይም አሥተያየት ሰጪ ተቋማት መሆን ነበረበት፤ ያ ባለመሆኑ መጓተቱ በህጋዊነት እና ህገ ወጥነት መካከል መውደቁን ቀጥሎ በምጠቅሳቸው ማስረጃዎች እንመልከት፡፡
5ኛ. የአጣሪ ጉባዔው ጉዳይ አህን መንግስት በመረጠው አካሄድ (የፌዴሬሽን ም/ቤት) ውሳኔ ሰጥቶ እንዲያስፈጽም ለማን ይላካል? ያስ አካል ውሳኔውን እንዴት አድርጎ ያስፈጽማል የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ምላሹ ምን ይሆናል ? የመንግሥት ምላሽ ፓርላማው ነው የሚል ከሆነ ፡- ፓርላማው የሕገ-መንግስት አጣሪዉ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ምን ያደርጋል? ውሳኔውንስ እንዴት ያስፈፅማል የሚል ጥያቄ ይነሳል፤ ይህንን ውሳኔ ለማስፈፀም ወይም በዚህ ውሳኔ መሠረት ለመፈፀም እንዲቻል በሚል ፓርላማዉ ሕግ ቢያወጣ የአጣሪውን ውሳኔ እንደ ሕግ ምክር ተቀበለ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እስካሁን በጠቀስነው መሰረታዊ የህግ መርሆ እና አሰራር መሰረት ሕገ ወጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ፓርላማዉ የፌዴረሽን ም/ቤቱን ውሳኔ ተቀብሎ ምን ያደርገዋል፤ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ሁሌም የፓርላማው ነውና ፓርላማው እንዲሁ ምንም ሳይልበት ውሳኔውን ሥራ ላይ ቢያውለውና በዚያ ውሳኔ መሠረት መተርጎም ቢጀምር በግልፅ አጣሪው ህግ አውጪ ህግ አውጪው ፓርላማ ደግሞ አሥፈጻሚ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለቱም አካላት በሕገ- መንግሥቱ ከተሰጠው ኀላፊነት ውጪ ስለሆነ ሕገ-መንግስቱ ተጣሰ ማለት ይሆናል፡፡
ከዚህ ባሻገር ፓርላማው ከገባበት ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት ወይም በዘዴ ለማለፍ ውሳኔውን ተቀብሎ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታተም ቢያዝ ወይም በውሳኔው መሠረት ሁሉም ይፈፅሙት ቢል የጉባዔው ውሳኔ የሕግ ምክር ስለሚሆን በማያሻማ መንገድ ህገ-ውጥ ይሆናል፡፡ ይሄኛውን ህገ-ወጥነት ለመሸሽ ምንም ሳይል ውሳኔው በራሱ መንገድ ሕግ ቢሆን ደግሞ ፓርላማው በሆነ ጉዳይ ላይ ሕግ የማውጣት ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣኑን አሳልፎ ሰጥቶ በሆነ ጉዳይ ላይ አጣሪው ሕግ ማውጣት መቻሉን (በሕገ መንግሥትና በሕግ ያልተሰጠውንና የሌለውን ሥልጣን እንዳለው አድርጎ) መቀበል ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው የሚለውን እውነታ ከማረጋገጥ በቀር ሌላ ትርጉም ሊያሰጠው አይችልም፡፡
ከዚህ በግልጽ የምንረዳው ፓርላማው የራሱን ሥልጣን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ግራ ስለተጋባ፤ ከመሰረታዊው የህግ አተረጎም መርሆ እና አላማ ውጪ፤ በሕገ-መንግሥት ተለክቶ ከተሰጠው ስልጣን ተሻግሮ ምን ማድረግ እንዳለበት መወሰን ሲገባው የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ማቅረቡ በራሱ ሕገ-ወጥና ሕገ-መንግስቱን የሚጥስ መሆኑ ለክርክር መቅረብ ያለበት ጉዳይ ሳይሆን የበለጠ ሳይረፍድ መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም ‹ለዚህ ዓላማ ወይም አገልግሎት ማውጣት ያለብኝን ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ ሕግ አላወቅሁምና ንገረኝ› ማለት በሆነ ጊዜ የሕግ ምክር መጠየቅ ስለሚሆን ይህ አካሄድ በራሱ ሕገ ወጥ ስለሚሆንና ፓርላማው ይህንን ሁኔታ በሚመለከት የአጣሪ ጉባዔው (የፌዴሬሽን ም/ቤቱ) ሕግ እንዲያወጣለት (አስገዳጅ ውሳኔ የመስጠት ሕግ ነውና) የራሱን ሥልጣን አሣልፎ መስጠትና ሕገ-መንግስቱን መጣስ ስለሆነ ፈጥኖ ሊታረም የሚገባው እንጂ የሌለ የህግ ከለላ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡
ስለሆነም በፓርላማው የቀረበው ጥያቄ መቅረቡም ሆነ የሚሰጠው ውሳኔ (በተለይም ውስጡን ይዘቱን (content) አይቶ የወሰነ ከሆነ) ሕገ-ወጥና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ናቸው ብሎ ለሚከራከር ማንኛውም አካል በቂ ህጋዊ አመክንዬ ማቅረብ ይችላል፡፡
6ኛ. የተሻለው መፍትሔ የትኛው ነው ? ይህንን ጊዜ ለመሻገርና ዛሬ ያለንበትን (የገጠመንን) ሁኔታ ተቆጣጥረን በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 8 እና አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት ሥልጣን በሕዝብ ምርጫ ብቻ የሚያዝበትን ሁኔታ ለማስቻል አስፈላጊነት (necessary) መሆኑን ማብራራትና ማስረዳት እስከተቻለ ድረስ ህጉ ዝግ ነው ሊባል ስለማይችል ፖለቲካዊና ህጋዊውን በአንድ ላይ የሚያሟላ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፡፡ (ለምሳሌ የሁሉንም ትብብር ፈጥሮና ሁሉም የተከሰተውን ወረርሽኝ (ኮረና) በማጥፋትና በሌሎችም ችግሮቻችን ላይ በሙሉ ልብ ለማስተኮር ያስችላል፤ ጠንካራ (ሁሉን ያቀፈ) መንግሥት እንዲኖር ያደርጋል፤ ለአገር አንድነት ይጠቅማል ወ.ዘ.ተ በሚል) የሽግግር ወይም የብሔራዊ አንድነት. . . መንግሥት መመስረት የሕገ-መንግሥቱን አንቀፅ 8 እና 9 ንዑስ አንቀጽ (3) የሚቃረን አይሆንም፡፡
መንግሥት የመረጠው መንገድ ግን ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን መርምሮ ችግሩን የሚፈታ አዋጅ ማውጣት (መወሰን) ሳይሆን ከአጣሪ ጉባዔው ምክር መጠየቅ ሆኗል፡፡ የሕገ-መንግሥቱን ክፍተት ለመሙላት እንደዚህ creative ሆኖ ሠርቶ አዋጅ ማውጣት እና አዋጁም የሕገ -መንግስቱን ክፍተት ለመሙላትና ሕገ-መንግስቱን በሚገባ ሥራ ላይ እንዲውል ለማስቻል የወጣ ሕጋዊና ሕገ-መንግስታዊ መሆኑን በፍርድ ቤት ይሁን በአጣሪ ጉባዔው ማስወሰን እንጂ አጣሪ ጉባዔውን የሕግ ምክር መጠየቅን የመሰለ የፓርላማው ድርጊት የወረደ ወይም ዝቅ ያለና ለአገሪቷና ለሁላችንም የማይመጥን ነው፡፡
አጣሪ ጉባዔውም {The God Fathers} የችግራችን ምንጭ የሆነውን ግህ የቀረጹ {the framers} የተባሉትን ጭምር እየፈለገ አስተያየት ስጡበት ማለቱም አስተዛዛቢ ነው፡፡ ለዚህ ቀዳዳ መፍትሔ ያለንን ወገኖች (ባለሙያዎች) ለማግለል የሄደበት መንገድም አሳፋሪ ነው፡፡ ለዚህ ሁኔታ መቅረት መቀየርና ለዚያና እስከዚያው ተገቢ የሆነ ሌላ ዓይነት መንግሥት መፍጠር ወይም ያለውን መንግሥት ማስቀጠል መሆኑን የሚያብራራ ምክንያት ማስረጃና መርህ (ሕግ) ጠቅሶ ይህንን መንግሥት በአዋጅ መፍጠር ወይም ማስቀጠል ከሁሉም ሊቀድም ይገባ ነበር፡፡
ይህንን ካደረጉ በኋላ ከሳሽ/ተቃዋሚ ቢመጣ የተፈጠረዉ ሁኔታ (የምርጫ ቦርዱ የገጠመው ችግር ከአቅም በላይ መሆኑንና በዚህ የተፈጠረው ሁኔታ ደግሞ የአስፈላጊነት (necessity) ሁኔታ መሆኑንና የፓርላማው አዋጅ ደግሞ ያ ሁኔታ አስፈላጊ (ግዴታ) ያደረገው መሆኑን) በፍርድ ቤት ማስወሰን ይቻላል፡፡ እነዚህን መከላከያ አድርጎ አቅርቦ መከራከር ይቻል ነበረ፡፡
ያኔ ምርጫ ማድረግ የሕዝብን ጤናና ህልውና አደጋ ላይ መጣል ስለሆነ ያለመደረጉ ህጋዊ ይሆንና ያንን ያደረጉ (የሚያደርጉ) ካሉ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ በመጣል ሊከሰሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ያለመሆኑ ያለው መንግሥት በሕግ ለመግዛት እንኳ ፍላጎት እንጂ ብቃት እንደሌለዉ የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡
መንግሥት በዙሪያው የሰበሰባቸውና የሚሰማቸው አካላት አብዛኛዎቹ መስማት የሚገባውን ሳይሆን መስማት የሚፈለገውን ባቻ የማያቀብሉት እንደሆኑ ይስተዋላል፡፡ በዙሪያው ያሉት ከባቢዎች በሙሉ ልባቸው አብረውት ስለሌሉ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ይዘው ጊዜ ስለሚጠብቁለት ወይም ገዢው ወገን ቢነግሩትም ሃሳብ ስለማይሰማ ወይም አቅም የሌለው ስለሆነ ወ.ዘ.ተ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ይህ መንግሥት በራሱ መንገድና አካሄድ ብቻ ሕጋዊ ሆኖ (መስሎ) እስከ ምርጫዉ ድረስ እንኳ የሚቀጥልበትን ዕድል አሳጥተውታል፡፡
መንግሥት ከመሰረቱ ሃዲዱን ከሳተ በኋላ ሕገ-መንግሥቱን አስተርጉሜያለሁ ቢል ወይም ተርጓሚው በሰጠው መመሪያ (ሃሳብ) መሠረትም ቢሠራ ያው ሕጋዊ አይደለም ሕጋዊ ሊሆንም አይችልም፡፡ መንግስት ከገባበት አጣብቂኝ መውጣት የሚችልበት አንድ ቀዳዳ ቢኖር የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ‹የሚተረጎም ነገር የለም› ብሎ በፍጥነት ጉዳዩን እንዲመለስ አድርጎ ወይም የመንግሥትን አቤቱታ (ውሳኔውን) የሚሽር ሌላ ውሳኔ በማሳለፍ ፓርላማው እኔ ከላይ ያቀረብኩትን ማድረግ (ያልኩትን አዋጅ ማውጣት) የሚችልበትን እድል መፍጠር ይችላል፡፡ ይህ በራሱ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፡፡ እንደ አንድ መልካም አባት ሕግንና ሕገ- መንግሥቱን መሠረት አድርገን ለገጠመን የአስፈላጊነት ሁኔታ (ነሰሲቲ) የሚመጥነውን ይህንን አዋጅ አውጀናል በማለት መጀመር ከሁሉ በላይ አዋጪና የቀራቸው አንድ ብቸኛ ህጋዊ መስመር ነው፡፡
ክፍል ሦስት ይቀጥላል . . .