>

ተመስገን ደሳለኝ እና አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛቱ   (ክፍል ሁለት)

ተመስገን ደሳለኝ እና አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛቱ

  ክፍል ሁለት
 
ለሰገጤ አይመከረም
6)  እጅ አለመስጠት፤
 
ሟቹ ኢህአዴግ ‹‹መሠረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ›› በሚለው ድርጅታዊ ሰነዱ ላይ የአብዩታዊ ዲሞክራሲን የአስተሳሰብ የበላይነት ለማረጋገጥ… ዜጎች በሁሉም ማዕዘናት ከዚህ አስተሳሰብ ውጭ እንዳያስቡ ለማድረግ የሚዲያ ቁጥጥሩም ሆነ የይዘት አቀራረቡ ከዚህ ቅኝት እንዳይወጣ ማድረግ እንደሚገባ በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይህ ርዕዩ ‹‹የሶቪየት ሕብረት ኮምዩኒስት የፖለቲካ ሚዲያ ሞዴል› ጋር ያቀራርበዋል፡፡ ይህ አንድ ሃሳብ፤ ጸረ-ዕውቀት የሆነ አተያይ በሕገ-መንግሥቱ ካሰፈራቸው የዴሞክራሲ መብቶች ጋር ይጋጭበታል፡፡ ሚዲያን ለሥርዓት ልዋጤ የትግል ዓላማ የሚያውለው ተመስገን ደሳለኝ የተለያየ ስያሜ ያላቸው አራት ሚዲያዎቹ በአፈና ተዘግተውበታል፡፡
 ሐምሌ 2004 ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ፣ ጥር 2005 ‹‹አዲስ ታይምስ››፣ መጋቢት 2005 ‹‹ልዕልና›› ጋዜጣ፣ ነሐሴ 2006 ‹‹ፋክት›› መጽሔት በትሕነግ/ኢህአዴግ የአፈና መዋቅር ተዘግተውበታል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በርካታ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክሶችን አስተናግዷል፡፡ ለሁሉም ክሶችና አፈናዎች ግን እጅ አለመስጠትን በተግባር አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ከአፈና ጋር ተያይዞ እጅ አለመስጠት/ተስፋ ቆርጦ ከገበያ አለመውጣት ‹‹የተመስገን ደሳለኝ ሞዴል›› በሚል ሊገለጽ ይችላል፡፡
 
7)  ፖለቲካዊ ራሮት (ጠላት እንደመቀነሻ)፤
 
ተመስገን በጽሁፍ ሥራው በሥልጣን ላይ ካለው ኀይል እና ከተገንጣይ ብሄርተኞች በስተቀር ለሌላው የፖለቲካ ኀይል የመራራት፣ ብዕሩን ያለማጥበቅ አካሄድ ይታይበታል፡፡ በተለየ ሁኔታ ለያ-ትውልድ የሚያሳየው ራሮት በግልጽ ይታይበታል፡፡ በተማሪው ንቅናቄ ጊዜ ጽንፈኛ ብሔርተኞች የሰለለ ድምጽ ነበራቸው እንጅ ያን ያህል ጉልበተኞች አልነበሩም የሚል ግምገማ አለው፡፡ ለዛሬዎቹ መሠረት የጣሉ መሆናቸውን ቢያውቅም ስርነቀላዊነትና ባህላዊ ብዥታቸው የፈጠረውን አገራዊ ቀውስ በለሆሳስ ያልፈዋል፡፡ ‹ባለፈ ዘመን የፖለቲካ እርግማን ለዛሬ ችግራችን መፍትሔ አይሆንም› በሚል ፖለቲካዊ ራሮትን እንደመፍትሔ ይወስዳል፡፡ በዚህ አቀራረቡ የያ-ትውልድ ጉማጅ ራዕይ አስፈጻሚዎችን፣ የቀጠለ ጥፋት ጠላት በመቀነስ ሰም ‹ለምጣዱ ሲባል…› ይላቸዋል፡፡ በጥፋታቸው ልክ ከመተቸት ይቆጠባል፡፡  ከመገንጠል በመለስ አቋም ይዘው ግን ደግሞ ፖለቲካውን የጅብ እርሻ ያስመሰሉትን እንደ ፕ/ር መረራ  ያሉ የዕድሜ ዘመን የፓርቲ ሊቃና መናብርት ተፈጥሮ መፍትሔ አለው በሚል ንቆ ትቷቸዋል፡፡ የዚህ ራሮት መዳረሻ አማካይ የፖለቲካ ኀይል ለመፍጠር ያለመ ይመስላል፡፡
8)  ልግስናን እንደ ነጻነት መንገድ፤
 
ከቀዳሚዋ ፍትሕ ጋዜጣ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ፍትሕ መጽሔት ድረስ (የኮቪድ ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ) የህትመት ይዘት አቀራረቡ ተመራጭ በመሆኑ ገበያው ላይ ተመራጭ ሆኖ ዘልቋል፡፡ በአምደኝነት ክፍያ ትልቁ ከፋይ/ የሚዲያ ባለቤት ተመስገን ነው፡፡ በርግጥ ይህ ለጸሐፍት ድካም ዋጋ መስጠት እንጅ  ልግስና አይደለም፡፡ ልግስናው በቀዳሚው ጊዜ የህትመት ሚዲያውን ትርፍ ተከትሎ ለሲቪክ አደረጃጀቶች (በተለይ ለወጣቶች) እንዲሁም ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች (በዋናነት ለአንድነት ፓርቲ)  የቢሮ ክራይ ክፍያ በተደጋጋሚ ከፍሏል፡፡ ይህ ለተመስገን ጽድቅ ሳይሆን የነጻነት መንገድ ጠረጋ ነው፡፡ በእስራት ላይ ይገኙ ለነበሩ ጋዜጠኖችና ፖለቲከኞች የዋስትና ብር በማስያዝ አጋርነቱን ስለማስመስከሩ ብዙዎች የሚመሰክሩለት እውነታ ነው፡፡ በዚህ ምግባሩ ‹ፍጡነ ንዋየ ረድዔት› የሚሉት ቢኖሩም፣ የእርሱ ዓላማ የነጻነት ኃይል ማሰባሰብን ያለመ ነው፡፡
 
9)  በቅንጫቢ ጩኸት አለመደናገጥ፤
 
አራት ያህል ሚዲዎችን ስም በማቀያየር ሲጠቀም የቆየው ተመስገን፣ በሚዲያዎቹ የተስተናገዱ ጽሁፎችን ተከትሎ ከባለሃብቶች እስከ ፖለቲከኞች ከጋዜጠኞች እስከ ተራ ግለሰቦች ያላስተናገደው የስድብና ዛቻ አይነት የለም፡፡ የግድያ ዛቻን ጨምሮ ሁሉንም ተብሏል፡፡ ተመስገን በቅንጫቢ ጩኸት (Sound bites) ከመደናበር ይልቅ፣ የሥርዓት ልዋጤ ላይ አተኩሮ መታገልን መርጧል፡፡ ለእርሱ ቀዳሚ የትግል ዓላማው የሥርዓት ለውጥ እንጅ የግለሰቦች መቀያየር አልነበረም፡፡ እዚህም እዚያም ይሰሙ የነበሩ የጥቂቶች ኩርፊያና የግራ ጥፍር ሚና በሂደቱ የሚዋጡ ቅንጫቢ ጩኸቶች እንደሆኑ ያምናል፡፡ ሰሞነኛው ሆይ ሆይታም በዚሁ አተያይ የሚጠቃለል ነው፡፡
 
10)   ለመረጃ ምንጭ መታመን፤
 
የተመስገን ደሳለኝ ጽሁፍ፣ ዋና ለዛ ለአደባባዩ እንግዳ የሆኑ መረጃዎችን ከትንታኔ ጋር ማቅረቡ ነው፡፡ እጅግ ጥብቅ ማዕከላዊነት መለያው የሆነው አገዛዙ፣ ድርጅታዊም ሆኑ ወታደራዊ መረጃዎቹ እንዲህ በቀላሉ የሚገኙ ባይሆኑም ተመስገን እጅ ላይ ቀድመው ደርሰው የአገሬው መነጋገሪያ ለመሆን የበቁ ጉዳዩች አሉ፡፡ በቀዳሚው ጊዜ (ቅድመ 2007) የግንባሩን የኃይል አሰላለፍና ድርጅታዊ መተጋገል፤ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በፍትሕ መጽሔት በኩል፣ ወታደራዊ ጉዳዩችን የተመለከቱ መረጃዎችን (የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በማይጎዳ መልኩ) በሪፎርም ስም የተፈጠረውን የፈረቃ ጉዞ ለሕዝብ ያደረሰባቸው ሁነቶች ‹ተመስገን ደሳለኝ ይለያል› ለማለት ያስገድዳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት የመረጃ ምንጮቹን አሳልፎ አለመስጠቱ፣ ምስጥራዊነታቸውን የሚጠብቀው ከመንግሥታዊ አካላት ብቻ ሳይሆን ከራሱ የስራ ባልደረቦች ጭምር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ የመረጃ ኦሜርታ ህግን አንብሯ!
ሲጠቃለል፤
 
ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ መድረክ ላይ ‹‹ብዙ ጽፎ ካልተሳሳተው ዣን ዠክ ሩሱ ይልቅ፤ ብዙ ጽፎ ከተሳሳተው ሄግል የበለጠ ተምረናል›› ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ አዎ! ተመስገን ባለፋት አስራ አንድ ዓመታት በአራት የተለያዩ ሚዲያዎች ሞጋች ሚናውን ይዞ ሲታገል፣ በሂደቱ ያስከፋቸው ሰዎች ቢኖሩ እንኳ በጥቅል አበርክቶው ግዝፈት የሚነሳ የሀገር መምህር ነው፡፡ ትላንት ለባለ ብረት መዳፉ ትህነግ ያልተንበረከከው ታጋይ ዛሬ በመንጋ ጩኹት ይሸበራል ማለት የተመስገንን አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛት አለመዋቅ ነው፡፡ ሰውዬው ላመነበት ነገር እስከ ቀራኒዮ (ቂያማ) ድረስ እንደሚጓዝ የስሜን ያህል እርግጠኛ ሆኘ እመሰክራለሁ! ቼ ጉቬራ አንድ አባባል አለው፡- ‹You can live by your own rules› ተመስገን እንዲህ ነው፡፡
I SALUTE OLD COMRADE.
Filed in: Amharic