>

"የአባይ ውሃ ጉዳይና የህዳሴ ግድብ የተለያዩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል" (ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላቸው)

“የአባይ ውሃ ጉዳይና የህዳሴ ግድብ የተለያዩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል”

ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላቸው
የጂኦግራፊ መምህርና በአባይ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የጥናት ሥራዎችን የሰሩ
ኢ.ፕ.ድ

የአባይ ውሃና የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን ሁሉም ሊያውቅ እንደሚገባ የጂኦግራፊ መምህርና በአባይ ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያ ገለጹ::
ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላቸው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ርዕሰ ጉዳዩ የአባይ ወንዝ ሲሆን የ11 አገሮች ይሆናል:: የግድብ ጉዳይ ሲሆን ደግሞ የሶስት አገሮች ጉዳይ ብቻ ነው፤ መደራደር ያለብንም ይህንን መሰረት በማድረግ ሊሆን ይገባል::
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ይህንን ሁኔታ ለይታ የገባች ይመስላል›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ግብጾች ጉዳዩ የሶስት አገሮች መሆኑን ወደ ጎን በመተው ሌሎቹን አገሮች ለመጎተት ጥረት ስለሚያደርጉ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል::
ረዳት ፕሮፌሰሩ ‹‹የህዳሴው ግድብ በስንት ዓመት ይሞላ የሚለው ሃሳብ ሊያነጋግር የሚገባው ሶስቱን አገራት ቢሆንም ግብጾች የምናገኘው የውሃ ድርሻ እንዳይነካብን በማለት ሌሎች የተፋሰሱን አገራት ወደ ጉዳዩ በማስገባትና እኛን ከእነሱ በመነጠል እነርሱን የሚያስቀይም ሥራ እንድንሰራ ሊገፋፉን ይችላሉ፤ ሆኖም የውሃ ሙሌቱ የቴክኒክ ጉዳይ ስለሆነ በባለሙያ እንዲታይ ማድረጉ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል›› ብለዋል::
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ እስካሁን ጥሩ ተጉዘናል፤ ይህንን መስመር ስተን ወይም ቴክኒኩን ትተን ወደፖለቲካው ከተገባ ግብጾች አሁን እንደሚያደርጉት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ወደ አረብ ሊግ ፤ ወደ አፍሪካ ህብረት በመሄድና አሁን እንዳለው ቀደም ሲል የታየውን ዓይነት የአሜሪካን አሸማጋይነትን በመጠየቅ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲይዝ ያደርጋሉ፤ በመሆኑም በምንም መንገድ ወደእነሱ ሃሳብ መሳብ አያስፈልግም::
‹‹ግብጾች ኢትዮጵያ የግድብ ግንባታዋን እንድታቆም ሦስት መንገዶችን ይጠቀማሉ›› ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ድሮ በማስፈራራት፤ እርዳታና ብድር እንዳይገኝ ጫና በማሳደር ሥራውን ማስተጓጎል ፤ አሁን ደግሞ እኛ ያለ ብድርና እርዳታ መስራት የሚያስችል አቅም እንዳለን አሳይተናል፤ ከዚህ በኋላም ጉዳዩ ከሶስቱ አገራት ውጪ እንዳይወጣ ጥረት ማድረግና አቋም መያዝ እንዳለበት ተናግረዋል::
ረዳት ፕሮፌሰሩ ጉዳዩ ከሶስቱ አገሮች መውጣት ካለበት በተፋሰሱ ያሉ አገሮችን ሁሉ ጨምሮ መነጋገር፤ እነሱም አይበቁም ከተባለ ደግሞ የአፍሪካ አገራት ተሳትፎ እንዲያደርጉበት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ ወደአሜሪካና አረብ አገራት ከሄድን ግን ወደግብጽ ፍላጎት የምንጎተትበትን ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል::
ረዳት ፕሮፌሰሩ “ወደ አሜሪካና ዓለም ባንክ ከሄድን ግብጾች በዛ በኩል ጥቅማቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ስለሚያውቁት ለእነሱ ተገዢ ያደርጉናል፤ አሁን የሚያስፈልገው ከአሜሪካን ድርድር እንደቀረነው ሁሉ የቴክኒክ ጉዳዩን ሶስቱ አገሮች ሊጨርሱ ይችላሉ ብሎ መዝጋት ነው :: ስለዚህ ትኩረት ማድረግ ያለብን ጉዳዩ ከተፋሰሱ አገራት ውጪ እንዳይወጣ ማድረጉ ላይ ነው” በማለት ያብራራሉ:: (EPA)
Filed in: Amharic