>

ያልተዘመረላቸው [በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን]

ያልተዘመረላቸው

_______
[በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን]
__
እንደ መግቢያ
____
ቴሌቪዥኔ ተከፍቷል:- በቅርቡ የተሰራው “ቅኔ ነው ሀገር” የሙዚቃ ክሊፕ  እየታየ ነው።በጥሞና፣ በመደመም፣ በመደነቅ። ክሊፑን እያየሁ ሳለ፣ ጭንቅላቴ ውስጥ አንዳች ትውስታ ብቅ አለ። እንደገና ላየው ወሰንኩ።
.
እናም ወደ YouTube ጎራ አልኩ። በንፋስ ውስጥ የሚጓዝ የሚመስል ውብ ዜማ በቀስታ መጣ፤ ወዲያው እጆቹን እያመሳቀለ የሙዚቃውን ፍሰት የሚያቀጣጥል ፈርጠም ያለ ወጣት ዕይታዬ ውስጥ ገባ። የሙዚቃው ደራሲ እና ቀማሪ ነው፦ ኢዩኤል መንግስቱ።
.
የኢዩኤልን እጆች በዐይኔ ተከተልኩ። በለሰስታ የጀመረው ሙዚቃ ወደፒያኖው ድምፅ አሻገረኝ። ዕዝራ አባተ (ዶ/ር)- ፒያኖውን በተመስጦ እና በ”ዝማሜ” ሲዳብስ ክሊፑን አቆምኩት። ምክንያቱም፤ ልክ እዚህ ጋ ስደርስ ነው ጭንቅላቴ ውስጥ የተጫረው ትዝታ፣ ግዘፍ ነስቶ ወለል ብሎ የተከሰተልኝ።
 ——— ❶ ———
ትውስታ
ከሁለት አስርት ዓመት በላይ የኋሊት  የሚወስድ ነው። አንድ ሰፈር ነን። ቤታችን ብዙም አይራራቅም። አልፎ አልፎ ወደ  እነሱ ቤት ጎራ እል ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን …
እንደወትሮው ሄድኩ። የግቢውን በር አንኳኳሁ። ተከፈተልኝ። ከዋናው ከተም በር ትይዩ ሰርቪስ ክፍሎች አሉ። በስተቀኝ በኩል ደግሞ ዋናው ቤታቸው ተገሽሯል። የግቢውን በር አልፌ ወደ ሰርቪስ ክፍሎቹ መራመድ ስጀምር “ማንም የለም” አለችኝ፦ ከተም በሩን የከፈተችልኝ ሰራተኛቸው። “ጓደኞቻችንን” ማለቷ ነው። ቆም አልኩ። በዚያው ቅፅበት ለሰስ ያለ የፒያኖ ድምፅ ወደ ጆሮዬ ጥልቅ አለ። ድምፁ የሚመጣው ከዋናው ቤት ሳሎን ነው። ወደዚያው አመራሁ። የሳሎኑን በር በቀስታ ከፍቼ አንገቴን ወደ ውስጥ አሰገግኩ።
.
በሳሎኑ አንደኛው ጥጋት ፒያኖ ይታየኛል። ከፒያኖው ኋላ ማርታ ተቀምጣለች። ማርታ ተፈራ የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ናት። በግራ እጇ የፒያኖውን ጥቁር ቁልፎች ጫን ጫን እያረገች፣ የቀኝ እጇን ጣቶች ነጫጮቹ የፒያኖ ቁልፎች ላይ ታረማምዳለች። የማውቀውን ዘፈን ነው የምትጫወተው። ለደቂቃዎች ያህል በፀጥታ ስሰማ ቆየሁና “ሰው አለ” ለማለት ያህል ጉሮሮዬን ሳልኩ።  ማርታ የሰማችኝ አልመሰለችም፤ በተመስጦ ፒያኖዋን መጫወት ቀጠለች። እንደገና ጎላ ባለ ድምፅ ጉሮሮዬን ሳልኩ።  ይኼኔ ፊቷን ወደ ኋላ ዞር አድርጋ አየችኝ። አየኋት። ደነገጥኩ። የምናገረው ጠፋኝ። ያስደነገጠኝ ጉንጮቿን ያራሰው እምባዋ ነው። እምባዋ በጉንጮቿን ላይ ኩልል ብሎ ወርዷል፤ እንዲያም ሆኖ የእጆቿ ጣቶች በፒያኖውን ቁልፎች መረማመድ ቀጥለዋል። በድንጋጤ ውስጥ ሆኜ ልብ ብዬ አየኋት። በረቀቀው ሙዚቃ ውስጥ ርቃ ሄዳለች፦ በሕይወት የሌሉትን አባቷን እያሰበች። የኋላ ኋላ ነው የሙዚቃውና የእንባዋ ሚስጥር የገባኝ። ይህ “የእንባዋ ምስጢር” በርካታ ዓመታት  የኋሊት ያነጉዳል።
——— ❷ —-
አባቷ፤ ወርቃማ በሚባለው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ድርሻ ከነበራቸው ቀደምት ከሚባሉት የሙዚቃ ሰዎች መሃል የሚጠቀሱ ነበሩ፦ ከቀደምትም ቀደምት።
አባቷ፤ በወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን መባቻ፣ የማይደበዝዝ አሻራቸውን ማኖር ከቻሉ፣ በዚህም አንቱታን ካተረፉ፣ ከፊተኞቹ ተርታ ነበሩ፦ ከፊተኞችም ፊት።
አባቷ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ቀደምት የነበረው፣ ህያው አሻራውን መተው የቻለው፣ የዝነኛው ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ባልደረባ ነበሩ።
አባቷ፤  የክቡር ዘበኛ 1ኛ  ኦርኬስትራ i”የመጀመሪያው” ኢትዮጵያዊ ፒያኒስት ለመሆን የበቁ ድንቅ ባለሙያ ነበሩ። ይህ የአንደኛው ኦርኬስትራ ፒያኒስት የመሆናቸው አጋጣሚ ደግሞ አስገራሚ ታሪክ  አለው። አጋጣሚው ወደ 1940ዎቹ ዓ.ም የመጨረሻ ዓመታት ይወስደናል።
——– ❸ ——
ታሪክ እንደሚነግረን፤ የክቡር ዘበኛ ሙዚቀኛ ክፍል እንደገና የተቋቋመው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  ነው። (በመስከረም ወር 1934 መመስረቱን ነው የታሪክ ሰነዶች የሚነግሩን) በቅድሚያ የተመሰረተው ደግሞ ሰልፈኛ ሙዚቃ ክፍል ነበር።
ከዓመታት በኋላ ነው “አንደኛ ኦርኬስትራ” ምስረታ ዕውን የሆነው። “የአንደኛ ኦርኬስትራ አጀማመር ለኢትዮጵያውያን ጆሮ የታሰበ አልነበረም” ይላሉ የሀገሪቱን የሙዚቃ ታሪክ ያጠኑ ፀሐፊዎች። ንጉሱ በውጭ ሀገራት እንዳዩት በእራት ግብዣ እና ከፍ ባሉ ድግሶቻቸው ላይ ተገኝተው የቻምበርና የጃዝ ዜማዎችን እንዲያሰሙላቸው ነው እንዲቋቋም ያዘዙት። በዚህ መልኩ የተመሰረተው አንደኛ ኦርኬስትራ የውጭ እንግዶች ሲመጡ ቤተመንግሥት እየተገኘ ዝግጅቱን ያቀርብ ነበር።
——— ❹ ——-
በ1940ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት…
ከዕለታት በአንደኛው ቀን:-
የክቡር ዘበኛ 1ኛ ኦርኬስትራ እንደተለመደው ቤተመንግሥት መድረክ ላይ ተገኘ፦ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማቅረብ።
በዚያ ቀን ንጉሱ ከፊት ረድፍ ታድመው የኦርኬስትራውን ዝግጅት እየኮመኮሙ ሳለ አንዳች ነገር ቅር አላቸው። እናም ወደጎን ዞር አሉ፤ ዞር ብለው መለሎውንና ታማኝ ጄኔራላቸውን በዐይን ጥቅሻ ጠሩት። የክቡር ዘበኛቸው ዋና አዛዥ መንግስቱ ንዋይ ከወገቡ እጥፍ አለና ጆሮውን አዋሳቸው። ንጉሱ አንዳች ነገር በጆሮው እየነገሩት ወደሙዚቀኞቹ መድረክ ጣታቸውን ቀሰሩ፦በተለይ ወደፒያኖ ተጫዋቹ  እያመለከቱ። ፒያኖ ተጫዋቹ የውጭ ሀገር ዜጋ ነበር፦ ፈረንጅ።
“ቀይረው!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ነበር የሰጡት። መንግስቱ ንዋይ ትዕዛዛቸውን ተቀብሎ ወደቦታው ተመለሰ።
ጄኔራሉ ወዲያውኑ አንድ ወጣት ትዝ አላቸው። በእሳቸው ዕዝ ስር ባለው የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ ወጣቱ ቤዝ የተባለውን የሙዚቃ መሣሪያ ሲጫወት አስተውለውታል። ጎበዝ ነው፦ ችሎታው የረቀቀ። እስከ 1947 ዓ.ም እዚያው ክፍል ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ሆኖ ነው የተማረው።
አገኙት! ወጣቱን የሙዚቃ ሰው። ተቀያሪውን ፒያኖ ተጫዋች፦ ተፈራ መኮንንን። በዚህ ዓይነት አስገራሚ ነበር የክቡር ዘበኛ የአንደኛው ኦርኬስትራ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፒያኒስት ለመሆን የበቃው፦ ተፈራ መኮንን።
——– ❺ ——-
አንደኛ ኦርኬስትራ ከፈረሰ በኋላ እሱና ጓደኞቹ የመጀመሪያውን የግል ባንድ መሰረቱ፦ “ራስ ባንድ”ን!
ከራስ ባንድ መስራቾች ውስጥ ሶስቱ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ባልደረቦች ነበሩ፦ ተፈራ መኰንን፣  ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ።  ሌሎችንም መሣሪያ  ተጫዋቾችንና ድምፃውያንን ይዘው ዝነኛውንና ቀደምቱን ራስ ባንድ መሰረቱ። ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) ነበሩ፦ የባንዱ አባላቶች።
.
አንጋፋው ድምፃዊ ባህታ ገ/ሕይወት በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለምልልስ “የማይረሳና ድንቅ”  ሲል ነበር “ራስ ባንድ”ን የገለፀው።
ባህታ፤ እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን ዘፈኖቹን ከራስ ባንድ ጋር ነው የሰራቸው።
“…የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፍኩት ራሴ ነኝ፤  ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የፃፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር።” ይላል ባህታ።
.
በእርግጥ ተፈራ መኮንን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ንጋት ላይ ብቅ ያሉ፣ ድንቅ ባለሙያ ነበሩ። የመጀመሪያው ራስ ባንድ እስኪፈርስ እስከ 1956 ዓም መጨረሻ ድረስ የእነ ባሕታ ገ/ህይወትን፣ የእነ ግርማ በየነን እና የሌሎችንም ድምፃውያንን ዘመን አይሽሬ ዘፈኖች የቀመሩ (የፃፉ) የሙዚቃ ባለሙያ ነበሩ።
—- — ❻ — —
እኚህ ያልተዘመረላቸው የሙዚቃ ባለሙያ፣ ፒያኖ ተጫዋችና ሙዚቃ ቀማሪ ብቻ አልነበሩም። ቀደምት እና የተዋጣላቸው የሙዚቃ መምህርም ነበሩ። በርካታ “አንቱ” ለመባል የበቁ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያፈሩ መምህር።
“…. አስታውሳለሁ ከ5ኛ ወደ ስድስተኛ ክፍል ስሸጋገር ነበር የክረምት ወራት ኮርስ እንድወስድ እናቴ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የወሰደችኝ፤ ጊዜው በ1965 ዓም ይመስለኛል። ያኔ 3  አስተማሪዎች ነበሩ። አንደኛዋ ወ/ሮ አስቴር ይባላሉ፤ ሌላኛዋ ሩስያዊት ናቸው። ብዙ ልጆች ወደ ሩሲያቷ ነበር የሚሄዱት ። እናቴ ‘ይዤህ የመጣሁት እሳቸውን ብዬ ነው፣ እሳቸው እንዲያስተምሩህ ነው ምፈልገው’ ብላ አቶ ተፈራን በመምህርነት የመረጠችልኝ” ይላል እውቁ ፒያኒስት ቴዎድሮስ አክሊሉ።
ቴዎድሮስ አክሊሉ፤  ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካተረፉ የአፍሪካውያን፣ የካሪቢያንና የአበሻ ባንዶች ወዘተ ጋር የሠራ የሙዚቃ ባለሙያ ነው። በአሁኑ ወቅት በቴዲ አፍሮ ባንድ ውስጥ እየሰራ ይገኛል።
“…. ከክረምቱ ኮርስ በኋላበሳምንት አንድ ቀን ፕሮግራም ይዘውልኝ ጀርመን ስኩል እየሄድኩ ነው  የተማርኩት። በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ፒያኖ መጠቀም ስላልቻሉ ነበር ይህ የሆነው። እሳቸው እዚያም ያስተምሩ ነበር።” የሚለው ቴዎድሮስ አቶ ተፈራ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያስተማሩት ያስተዋለውንና አሁን ድረስ የሚገርመውን ትውስታ እንዲህ ይተርከዋል።
“……እስካሁን ድረስ የሚገርመኝ ፒያኖ ለመማር ጀርመን ስኩል በሄድኩ ቁጥር እሳቸው  ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ቁጭ ብለው ክላሲካል ሙዚቃ ሲጫወቱ ወይም ሲቀምሩ ነበር የማገኛቸው። ይገርምሃል፤ አሁን እንኳ ክላስካል ሙዚቃ ልጫወት ብዬ ብቀመጥ ወደህሊናዬ የሚመጣው እና መጫወት የምችለው እሳቸው ያኔ የቀመሯቸውን የእነ ባህታን ሙዚቃ ብቻ ነው። ምናልባት ይህ የሆነው ያኔ በፍቅር ያስተምሩኝ ስለነበር ነው። በጣም ይወዱኝ ነበር።….”
በኢትዮጵያ ክላሲካል መስመር እንዲገፋ ፍላጎታቸው እንደነበር የሚያስታውሰው ቴዎድሮስ፤ “አቶ ተፈራ ታላቅ ሰው ናቸው። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ስለጃዝ ሙዚቃና ባንድ  ሲነሳ ሰዉ ሁሉ የሚያስታውሰው ሙላቱ አስታጥቄን ነው። ጃዝ ሙዚቃን የጀመሩት ግን አቶ ተፈራ መኮንን ናቸው” ሲል ይመሰክራል።
——- ❼ ——
አቶ ተፈራ፤ እንደ ቴዎድሮስ አክሊሉ ያሉ፣ በሙያቸው “አንቱ” የተባሉ በርካታ ሥመ-ገናን የሙዚቃ ሰዎችን ያፈሩ መምህር ናቸው። የአብራክ ክፋይ ልጆቻቸው ጭምር በሙዚቃው ዓለም የእሳቸውን ፈለግ ተከትለዋል።
.
የመጀመሪያ ልጃቸው ትምክህት ተፈራ ትባላለች። ሚዩዚኮሎጂስት (Musicologist) ናት። ይኼ “ሚዩዚኮሎጂስት” የሚባለው ነገር፤ እኛ ሙዚቃ ብለን ከምናውቀው የተለየ ሰፋ፣ ቦርቀቅ፣ ረቀቅ ያለ የሙዚቃ ሳይንስ ነው። ስለሙዚቃ ያጠናል፤ ስለባህል መሳሪያ እና ጭፈራ ያጠናል፤ ስለዘፈኖቹ የትመጤነት እና ዕድገት ያጠናል። ታሪክንና ፍልስፍናን ወዘተ ጭምር ያካትታል። የእንግሊዝኛው ፍቺ የተሻለ ይገልፀዋል።
“The scope of musicology may be summarized as covering the study of the history and phenomena of music, including (1) form and notation, (2) the lives of composers and performers, (3) the development of musical instruments, (4) music theory (harmony, melody , rhythm, modes, scales, etc.), and (5) aesthetics, acoustics , and physiology of the voice, ear, and hand.”
ትምክህት ተፈራ በዚህ ዘርፍ ነው የዶክትሬት ዲግሪዋን ያገኘችው። ምናልባትም ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊ Musicologist ሳትሆን አትቀርም።
[ሁለተኛዋ ልጃቸው ሁላችንም በድምፅ ሳናውቃት አንቀርም። በሞባይላችን “ያለዎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው፣ መስመሩ ስለተያዘ እባክዎን ትንሽ ቆይተው ይደውሉ፣ ደምበኛው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው” የምትለን ሕሊና ተፈራ ናት።]
ጉልቱ ተፈራ የአክሱማይት፣ የመሐሙድ 3M ባንድ እና የሐገርፍቅር ዘመናዊ ባንድ (የረሳሁት ይኖራል?) ኦርጋን ተጫዋች ነበር። አሁን በሐገረ አሜሪካ የሕግ ባለሙያ ነው።
የመጨረሻዋ ልጃቸው በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ የጠቀስናት ማርታ ተፈራ ናት። እሷም የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ምሩቅ ናት።አሁን በሐገረ ጀርመን፣ እና በመላው አውሮፓ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ሙዚቃ በስፋት እያስተዋወቀች ትገኛለች። በክራር አጨዋወቷም፣ በድምፃዊነቷም አድናቆትን ያተረፈች ናት።
____ መውጫ ___
እነሆ ልንሰነባበት ዘንድ ግን ሆነ። ስንሰናበት ግን “ያልተዘመረላቸውን” እኚህን ቀደምት የሙዚቃ ባለሙያ እናስታውሳቸው ሰበብ የሆነንን “ቅኔ ነው ሀገርን” ማድነቅ ግድ ይለናል።
ምክንያቱም የትሮምቦንን የሚያርድ፣ የኩራት” ስሜት ከሚፈጥረው የትራምፔት፣ ጎርናናውን የቴነር ሳክስፎንን፣ የሚመስጠውን የቫዮሊንን እና የሌሎች ሙዚቃ መሳርያ ድምፆች አሰናስኖ፣ አዋህዶ፣ አጣፍጦ …ከዘመናት በኋላ ጥዑመ ዜማ  አሰምቶናልና።  ከአንድ ኦርጋን እና ቆርቆሮ ድለቃ ከሚመስል ኳኳታ አውጥቶ፣ ወደ ሙዚቃችን ከፍታ ዘመን አመላክቶናልና በ “ቅኔ ነው ሃገር” ሕብረ ዜማ የተሳተፉትን ባለሙያዎች ሁሉ ልናመሰግን እንወዳለን።
በመጨረሻም የምንሰነባበተው በታዋቂው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ የተዘፈነውንና  ሙዚቃው በአቶ ተፈራ መኮንን የተቀመረውን “የሀገሬ ሽታ” በመጋበዝ ነው። እነሆ፦
.
ትዝታው ገንፍሎ ዕንባዬ እያነቀኝ
የሀገሬ ሽታ ጠረኑ ናፈቀኝ
.
ትኩስ ድፎ ዳቦ የምጎረምደው
ትዝ አለኝ አሹቁ ንፍሮ የምወደው
የመንጋው ትርምስ ሜዳው ሸንተረሩ
ምንጭና ፏፏቴው ናፈቀኝ አየሩ ።
.
ሻሎም!
Filed in: Amharic