>

አባዱላና ተወልደ የደፈሩት ዘ-ሐበሻን ሳይሆን የአሜሪካንን ሕገ-መንግስትንና እኛን ነው!  (ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

አባዱላና ተወልደ የደፈሩት ዘ-ሐበሻን ሳይሆን የአሜሪካንን ሕገ-መንግስትንና እኛን ነው!

ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ

ዘ-ሐበሻ በሰኔ 4 ቀን 2020 በለቀቀው ሰበር መረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበላይ ኃላፊዎች የአትላንቲክ ውቅያኖስ ተሻግረው “በስም ማጥፋት ወንጀል” የሚዲያ ተቋሙን ክስ እንደመሰረቱበት ይፋ አድርጓል። በክሱ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ ዘ-ሐበሻ በአየር መንገዱ ላይ የ25 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አድርሷል ተብሏል። እጅግ በጣም አስገራሚ ነው!
ከሁሉም በላይ አስደናቂው ደግሞ ክሱ የቀረበው በአገረ አሜሪካ መሆኑ ላይ ነው። በቅጥ ያጣ ፍርሃት ውስጥ ያሉት የአየር መንገዱ ቦርድ ሰብሳቢ አባዱላና ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወልደ ክሱን ሲመሰርቱ “የአሜሪካን ሕገ-መንግስት የሚነግራቸው አልነበረም ወይ?” ያስብላል። በዚህ መልኩ በድንቁርና መቀጠል ለገዥዎቹ የሚያስገኝላቸው አንዳች ጠቀሜታ ቢኖር ውርደት፣ ንቀትና ትዝብት መሆኑን እንዴት መረዳት አቃታቸው ያስብላል። ድርጊቱ ከተስፋ መቁረጥና ሕሊና መሞት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ለማስተማሪያ እንዲረዳ ከአሜሪካን ሕገ-መንግስት ጋር አያይዞ ማሳየቱ የተሻለ ስዕል ይሰጣል። የአሜሪካን አባቶች የሚዲያ ነፃነት ለማረጋገጥ የሔዱበትን ርቀት በአጭሩ መመልከት ያስፈልጋል።
                         ***
የአሜሪካን አባት ተደርገው ከሚቆጠሩት ግንባር ቀደሙ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን ናቸው። ታላቁ መሪ ቶማስ ጄፈርሰን ከ200 መቶ አመት በፊት ሚዲያ እና መንግስትን በተመለከተ አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ” ሚዲያ ከሌለው መንግስትና መንግስት ከሌለው ፕሬስ” የቱን ትመርጣለህ የሚል ነበር። ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን ምንም ሳያመነታ ፕሬስ አስቀደመ። የመንግስት መሰረት የሕዝብ አስተያየት እንደመሆኑ ያንን መጠበቁ የመጀመሪያ ግዴታ ነውና ፕሬስ የሌለበት መንግስት ባፍንጫዬ ይውጣ በማለት የሚዲያን የማይተካ ሚና አመላክተዋል።
ይህ የአሜሪካን አባት ንግግር እስከዛሬም ድረስ የሚዲያ ነፃነት ማህፀን ከፋች ተደርጐ ይወሰዳል። ስለ ሚዲያ ነፃነት መናገርም ሆነ መፃፍ የፈለገ ሰው ሁሉ ይህን ዘመን ተሻጋሪ ኃይለ-ቃል ይጠቀማል። ለአብነት ያህል ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በአመት አንድ ቀን ከሚዲያ ሰዎች ጋር በሚኖራቸው የእራት የመጨረሻው አመት ፕሮግራም ላይ የቶማስ ጄፈርሰንን ንግግር አስታውሰዋል። እኔም ምርጫ ቢቀርብልኝ ሚዲያን ያለ አንዳች ማመንታት እቀበላለሁ ብለዋል።
የአሜሪካን አባቶች የሚዲያ ነፃነትን በተመለከተ አንዳችም እንቅፋት እንዳያጋጥመው መሰረት የጣሉት ከዛሬ 224 አመት በፊት ነው። በ1776 የታወጀው “ቢል ኦፍ ራይትስ” የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ በማያወላውል ቋንቋ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፣
” የፕሬስ ነፃነት ዋናው የሰው ልጅ ነፃነት ማስከበሪያ መሳሪያ ስለሆነ ከአምባገነን መንግስታት በቀር በዚህ ነፃነት ላይ ተአቅቦ የሚያደርጉ ሊኖር አይችሉም” ይላል።
በማስከተልም ከ 15 አመት በኃላ በ1791 ” ዘ ፈርስት አሜንድመንት” በማወጅ የሚዲያ ነፃነትን ሕገ-መንግስታዊ ሽፋን ሰጥተውታል። የተሻሻለው የአሜሪካ ሕገ-መንግስት አንቀጽ አንድ ላይ፣
  ” የአሜሪካ ምክር ቤት የሃይማኖት ተቋማትና እንቅስቃሴያቸውን፤ የንግግር ነፃነት፤ የፕሬስ ነፃነትና የሕዝብ በሰላም የመሰብስብ መብት ወይም በሕዝብ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የሚቃወም ሕግ ሊያወጣ አይችልም” ይላል።
በመሆኑም በአሜሪካ ከ230 አመት በፊት የተካሄደው አብዬት ” ዘ ፈርስት አሜንድመንት” በመውለድ ኮንግረስ የሚዲያ ነፃነትን በመቀነስ ምንም አይነት ሕግ እንዳያወጣ ሕገ መንግስት እንዲከለክል አድርጓል። የሚዲያ ነፃነት ሕግ የሚወጣው የሕዝብን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ እንደመሆኑ በመርሖው መሰረት ሕግ የሚወጣው በመንግስት ላይ ነው። የአሜሪካ አባቶች ያደረጉት ይሄንኑ ነው። የሕዝቡን የማወቅ መብት በሕገ-መንግስት ማረጋገጥ።
ሌላው ቀርቶ የአሜሪካንን ብሔራዊ ደህንነት ሊጐዳ ይችላል ተብሎ የሚታሰብ መረጃ ሚዲያዎች እንዳያወጡ ለማድረግ ብይን የሚሰጠው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብቻ ነው። ለዚህ ማሳያ እንዲሆን በ1971 ዓ•ም• የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዋሽንግተን ፓስትና ኒዎርክ ታይምስ ላይ የሰጠው ውሳኔ የፕሬስ ነፃነት በተነሳ ቁጥር በአብነት የሚነሳ ነው።
 እንዲህ ነበር የሆነው፣
ከላይ በተጠቀሰው አመት ኒዎርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፓስት አንድ ተከታታይ ጽሁፍ ይወጣ ነበር። ጽሁፉ “ፔንታጐን ፔፐርስ” የሚል ሲሆን የአሜሪካ መከላከያ ዲፓርትመንት በቬየትናም የሚያካሂደውን ጦርነት የሚያጋልጥ ጽሁፍ ነበር። የአሜሪካ መንግስት በሁለቱ ጋዜጦች ላይ እየወጣ ያለው ጽሁፍ የአገር ሚስጥር ስለሆነና ብሔራዊ ደህነታችንን ይጐዳል በሚል ከመታተም እንዲታገድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ነበር። ይሁን እንጂ መንግስት ” ሚስጥርና ብሔራዊ ደህንነት” በሚል ሽፋን ከአሜሪካ ህዝብ የሚደብቀው መረጃ የለም በሚል የመንግስትን ክስ ውድቅ አደረገ።
ሌላ አንድ ምሳሌ ልጨምር። የአሜሪካን 37ኛ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኒክሰን የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ከነጩ ቤተ-መንግስት የተባረሩት ዋሽንግተን ፓስት የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ ከህዝብ የተሰወረውን እና በሴራ የተጐነጐነውን “የወተር ጌት ቅሌት” ፈልፍሎ ለአሜሪካ ህዝብ በማውጣት ነው። እዚህ ላይ ያለው ሌላ ቁምነገር የፕሬዝዳንት ኒክሰንን ቅሌት ያወጣው ጋዜጣም ሆነ ጋዜጠኞች የደረሰባቸው አንድም ነገር የለም። ይህ አሜሪካ ነው!
                         ***
እነሆ! አባት አገር አሜሪካ እንዲህ ናት። በዜጐቿ ሚዲያ አራተኛ መንግሥት ነው ሲባል ተራ ቃል አይደለም። የምድራዊው ቅዱስ ቃል ነው። የጨለማ ጠንቅ የሆነውን ሚዲያ እንደ አይናቸው ብሌን የሚጠብቁትም በዚህ ምክንያት ነው። በዚህ ምክንያት ጉራማይሌዋ አሜሪካ ከምንም በላይ ዴሞክራሲ እንዲያሸንፍ ሚዲያ ኃይልን የትቀዳጀበት አገር ናት። አይደለም ሙሰኞቹ አባዱላና ተወልደ ፕሬዝዳንት ትራምፕም ” ፌክ ሚዲያ” ብሎ ከመደንፋት ውጪ የሚዲያውን ዝንብ “እሽ!” ማለት አይችልም። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውሸት ሚዲያ በማለታቸው ራሳቸውን አዋረዱ እንጂ ፤ ለዘመናት ተገንብቶ የነፃነት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ዋና አራማጅ መሳሪያ ሆኖ የቆየውን ሚዲያ ምንም ማድረግ አልቻሉም።
 በነገራችን ላይ እኔም በአሜሪካ ዜግነቴ ከምኮራበት አንድ ሺህ አንድ ምክንያቶች አንዱ ይሄ ነው። እዚህ ላይ አንድ ሺህ አንድ ምክንያት ማለቴ ይሰመርበት።ባለፈው ጊዜ የአሜሪካ ዜግነት ከወሰድኩባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ ዶናልድ ትራምፕን የመሳሰሉ ዘረኛ፣ በራስ ፍቅር የወደቁና የአሜሪካንን ክብር የማይመጥኑ ፕሬዝዳንቶችን በድምጼ ለመጣል ነው በማለቴ የኩባያ ማዕበል አስነስቶ ነበር።
ዛሬ ዛሬ ግን ትራምፕን ለመጣል የአለም ህዝብ ሁሉ አሜሪካዊ የመሆን እድሉን ቢያገኝ አይኑን የሚያሽ አይመስለኝም። የፕላስቲክ ኩባንያ ማዕበል ያስነሱብኝም ሆነ የተሳለቁ የአገሬ ሰዎች ጭምር ማለቴ ነው። ለማንኛውም ትራምፕን ለመጣል የጆን ባይደን የአካባቢ የቅስቀሳ ቡድን ውስጥ በፍቃደኝነት ለመሳተፍ ይሁንታ ሰጥቻለሁ። አገር ሰላም ሲሆን የሰው ቤት እያንኳኳሁ ” ትራንፕን እንዳትመርጡ! አስተዋይና አርቆ አሳቢውን ጆን ባይደን ምረጡ!” በማለት እቀሰቅሳለሁ። ወደ ሚሊዬን ይጠጋል ተብሎ የሚገመተውን በአሜሪካ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ደግሞ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ለመድረስ እሞክራለሁ። “ቃል የእምነት እዳ ነው!” ይባል የለ!
                        ***
ወደተነሳሁበት ልመለስና የዝርፊያና ዘረኝነት ምሳሌ የሆኑት አባዱላና ተወልደ ውቅያኖስ ተሻግረው ሲፀዳዱ የበከሉት የአሜሪካንን አየር ብቻ አይደለም። የዘ-ሐበሻ ሚዲያንም ብቻ አይደለም። የሚዲያ ውጤቶችን ብቻ አይደለም። በአሜሪካ የሚኖረውን ዲያስፓራ ብቻ አይደለም። እንዲህ የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። ይልቁንስ የኮረኔሉን ዘመን ተሻጋሪ አባባል ልጠቀምና እያንዳንዳችንን ንቀውናል። ደፍረውናል። ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ቀብረውናል። በተለይም ለሚዲያ ተቋማትና በተቋሙ ለሚያገለግሉ ሰዎች ከዳግም ትንሳኤ በኃላ የተፈረደ የሞት ቅጣት ያህል ነው። ማናችንም በዚህ መስክ የተሰማራን ሰራተኞች የደናቁርቶቹ ድርጊት የጠመንጃ ቃታ እንደተሳበብን መቁጠር አለብን። በአንገታችን ላይ ጐራዴ እንደተጋደመ ማሰብ አለብን።
የአገራችን ሰው “ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” እንደሚለው የአባዱላና ተወልደ አካሄድ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በግል እምነቴ ሜኖሶታ የቀረበው ክስ ከፒኮኩ ቤተ-መንግስት አረንጓዴ መብራት ሳያዩ በአየር መንገዱ ቦርድና ስራ አስፈፃሚ ብቻ የተወሰነ ነው ለማለት ይከብደኛል። የቤተ-መንግስቱ ተሳትፎ መኖርና አለመኖር ጉዳዩ አደባባይ ከወጣ በኃላ ክሱ ይቀጥላል ወይንስ ይቋረጣል ከሚለው ጋር የተያያዘ ይሆናል። ምን ትገምታለህ ብትሉኝ “አልሰማሁም ነበር!” የምትል ምትሐተኛ ቃል ከቤተ-መንግስት ሾልካ የምትወጣ ይመስለኛል። የቤተ-መንግስት ሰዎች ከወዲሁ ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ቢኖር እንዲህ አይነት የእጅ አዙር የአፈና እርምጃ በሕዝብና በሥርአቱ መካከል የነበረውን መቋሰል እያባስበት ይሄዳል እንጂ እንዲሻሻል አያደርገውም።
ከዛም አልፎ በክስ ሂደቱ ላይ  86 ኢትዮጵያውያንን በጠራራ ፀሀይ ያስጨፈጨፈው የቀድሞ ሜኖሶታ ነዋሪው ምክረ-ሃሳብም ያለበት ይመስለኛል። የጥርጣሬዬ መነሻ ደግሞ አንድ ሰሞን የአየር መንገዱ ሚስጥራዊ መረጃዎች የሚወጡትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልተናነሰ የአየር መንገዱ አመራር የሚሽቆጠቆጠው “ለተከብቤያለሁ” ባዩ በመሆኑ ነው። በተለይ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነው አቶ ተወልደ ሲያሳየው የነበረው መረን የለቀቀ አድርባይነት እጅግ ይዘገንን ነበር።
                        ***
እንደ እኔ እምነት ከሆነ የአባዱላ እና ተወልደ ስርአት በእውቀት አልቦነት የጀመረውን ክስ በአስቸኳይ ማቋረጥ አለበት። ሚዲያዎችን በጠላትነት በመፈረጅ እየተከተለ ያለው በገንዘብ አቅም የማስፈራራት መንገድ የትም አያደርሰውም። በእነሱ የክስ ክምር ለተረገጡ ወገኖች ጠበቃ፣ አፋቸው ለተለጐሙ አንደበት፣ ምርኩዝ ላጡ መሪ የመሆን ግዴታችንን የማንወጣ ከመሰላቸው እጅጉን ተሳስተዋል። የህውሓት የማደጐ ልጆች የሆኑት እነዚህ ዘራፊ ግለሰቦች ከያዝነው አላማ የሚያናጥቡን ከሆነማ ከጅምሩ አላማ-ቢስ ነበርን። እነዚህ ለሁለት አስርተ አመታት በተዘፈቁበት የንቅዘት ህይወታቸው የዛፍ ላይ ኑሮ የሆኑ ግለሰቦች በህዝብ ገንዘብ የሚያስፈራሩን ከሆነማ በእናታችን ማህፀን ተጨናግፈን ብንቀር ይሻል ነበር።
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የውስጥ ገመና በተመለከተ ከተነገረው ያልተነገረው ይበልጣል። የአየር መንገዱ ባልደረቦች የነበሩ ሰዎችን በሚዲያ በጠየቅን ቁጥር የውስጣቸው የተዳፈነ እሳት ፈላፈኑ እኛንም ይገርፈን ነበር። በተቋሙ ውስጥ ያለው ዘረኝነት፣ የቤትና የእንጀራ ልጅነት፣ በዘመድ አዝማድና ጥቅም የተሳሰረ ኔትወርክ፣ የተደራጀ ሌብነትና ዝርፊያ፣ የሙያተኛ ተቋሙን ጥሎ መውጣትና መሰደድ፣ የሰው ሃይል አስተዳደርና ፋይናስ አሰራር መዝረክረክ፣ ሚዲያዎችን በጥቅም ለመደለል የሚኬድበት ረጅም ርቀት፣ የአውሮፕላኖቹ የሊዝና የባለቤትነት ጥያቄ፣ ቦርዱና ማኔጅመንቱ ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር የገቡበት እሰጣ-ገባ፣ የማኔጅመንቱ እርስ በራስ አለመተማመንና መሰደድ፣ የአገር ውስጥና የውጪ ብድር ጫናው…ወዘተ አየር መንገዱን ወደ ፀጉራም ውሻነት ቀይሮታል። እጅግ ያሳዝናል። የምንወደው፣ የምንኮራበትና ልዩ አርማችን የሆነው አየር መንገዳችን በአባዱላና ተወልደ እጅ ወድቆ በእጃቸው ላይ እንደ በረዶ እየቀለጠ ነው። ጐበዝ! አየር መንገዳችንን እንታደግ!
– አባዱላና-ተወልደ-ለፍርድ-ይቅረቡ!
– እውነት-ትመነምናለች-እንጂ-አትበጠስም!
– ክሱን-በተመለከተ-እኔም-ዘ-ሐበሻ-ነኝ!
Filed in: Amharic