“እምቦጭ ለልዩ አገልግሎት ሊውል ስለታቀደ አትንቀሉ” – የአማራ ክልል መንግሥት
አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
በአንድ የዜና አውታር ሰሞኑን እንደተከታተልኩት የአማራ ክልል መንግሥት የእምቦጭን መጥፋት አይፈልግም ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እንዲስፋፋ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ ለምን? እጅግ ሲበዛ አጠያያቂ ነው! ይህ ጉዳይ መላውን የሀገሪቱ ሕዝብ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ በተለይም በቅርቡ የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ለምን ብሎ ይጠይቅ፡፡ ወጣቱም ዝም አይበል፡፡
እንደተባለው የባህር ዳር ዩንቨርስቲ ወጣቶችን አሰልጥኖና አስፈላጊውን የማሽኖች አቅርቦት አሟልቶ እምቦጭን እንዲያጠፉ ያሰማራል፡፡ ወጣቶቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ሰፊ ቦታ ከእምቦጭ ነፃ ያደርጋሉ፡፡ ይህን ስኬት የተመለከተው የአማራ ክልል ወጣቶቹን እንደመሸለምና ዩንቨርስቲውንም እንደማመስገን የክልሉ ባለሥልጣናት አማራን ለማጥፋት ከሌላ የጠላት ግዛት የተላኩ በሚያስመስል ሁኔታ ከበላይ በተላከ ቀጭን ትዕዛዝ “እምቦጭ ለሌላ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውል ስለተፈለገ ሥራችሁን አቁሙ” ተብለው ወጣቶቹ እንዲበተኑ እምቦጭም እንዲስፋፋ ተደረገ፡፡ ይህ ትዕዛዝ ከፌዴራል መንግሥት ወይም ከትግራይ ክልል የሕወሓት መንግሥት ቢመጣ አሣማኝ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ለአማራ ያላቸው ዕይታ ሸውራራ በመሆኑና ሊያጠፉትም እንደሚያሤሩ ስለሚነገር፡፡ የአማራ መንግሥት ተሁኖ ግን በአማራ ክልላዊ መንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኝን ሀብትና ንብረት ለማጥፋት መነሣት ስም የሌለው ህመም ነው፡፡ ይህ ክስተት ብቻውን ብአዴን የጠላት ሠርጎ ገቦች ስብስብ መሆኑን ያሳያል፡፡
በመሠረቱ ጣና የአማራ ብቻ አይደለም፡፡ አንድ የተፈጥሮ ሀብት ንብረትነቱ ከክልልና ከአንድ አገር አልፎ የመላው ዓለም የጋራ ንብረት ነው፡፡ አማዞን ቢቃጠል ብራዚል ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያም ትጎዳለች፡፡ ጣና ቢደርቅ በትንሹ ወደ 12 የሚጠጉ ሀገራት ይጎዳሉ፡፡ ላሊበላ ቢጠፋ የመላው ዓለም ቱሪስት ማየት ከሚፈልገው ነገር አንዱ ስለሚቀንስ ተፅዕኖው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የሰው ዘር ነው፡፡ ተጠየቁ በዚህ መልክ የሚቀጥልና አፍንጫ ሲመታ ዐይን እንደሚያለቅስ በግልጽ የሚናገር እውነት ነው፡፡ በሀገራችን ግን ብዙ የተወለጋገዱ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ ለአንድ በሽታ መድኃኒት ብታገኝ ዕዳ ነው፡፡ እምቦጭን የሚያጠፋ ዘዴ ብትፈጥር ዕዳ ነው፡፡ ብትሠራ ችግር፤ ባትሠራም ችግር፡፡ “ከጓደኞቿ ወጣ ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ” እያለ በሚተርት ማኅበረሰብ ውስጥ መልካም ሥራም ያስቀስፋል፡፡ ይህም ፍራቻን በመፍጠር አብዛኞቻችን ወደ ክፋት እንጂ ወደ ልማት ፊታችንን እንዳናዞር አንገት አሳጥቶናል፡፡ ችግሮቻችንና መባቀያቸው ኆልቁ መሣፍርት የላቸውም፡፡ በዚህም ሳቢያ ባለንበት መቆምም ሆነ መራመድ ሲያምረን የሚቀር ሆኖብን ቁልቁል የሽምጥ ግልቢያውን ተያይዘነዋል፡፡ ሰው ሰው አንሸትም ባጭሩ፡፡
ወደነገሬ ተመለስኩ፡፡ በሀገራችን የገባው የዘረኝነት ሰይጣናዊ መንፈስ እጅግ በጣም እየጎዳን ስለመሆኑ ጣና አንዱ ማስረጃ ነው፡፡ ሴትዮዋ ባለቤቷን የጎዳች መስሏት በሰውነቷ ላይ የፈረደችውን የተዛባና ራስን የሚጎዳ ፍርድ የሚያስታውስ ብዙ የጅልነት ተግባር በሀገራችን እየተመለከትን ነው፡፡ ብዙ ዐዋቂ ነው የተባለለት ጠ/ሚኒስትሩ ራሱ እንኳን ስለዚህ እምቦጭ ሲናገር አልሰማሁም – ተናግሮ ሊሆን ይችላል – እኔ አልሰማሁም ነው አባባሌ፡፡ ለተክሎችና ለከተማ ውበት ከሚሰጠው ትኩረት ትንሽ ቀንሶ ለጣና ሐይቅ ቢሰጥ ችግሩ ይሄኔ ታሪክ በሆነ ነበር፡፡ ጣና በውኃነቱ ከሚሰጠው ጥቅም በዘለለ ሐይቁን ለመጎብኘት ከሚመጡ ቱሪስቶች የሚገኘው ገንዘብ የውጭ ምንዛሬያችንን ያጎለብታል፡፡ የተፈጥሮ ሚዛንን ይጠብቃል፡፡ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲዘንብ የራሱን አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ የዐይን ማረፊያ ይሆናል፡፡ የሐይቅ ጥቅም ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ በጥቅሉ አማራው የተረፈው ስሙ ሆኖ ጥቅሙ ግን ለሀገርና ለፌዴራል ተብዬው መንግሥት መሆኑ ተረስቷል፡፡
አሁንም ቢሆን ካልረፈደ ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ጠ/ሚኒስትር አቢይ ለዚህ አንብጋ የእምቦጭ አረም ዘመቻ ይክፈት፡፡ ያስተባብር፡፡ ሕዝቡ ንቅል ብሎ በአንዴ በመሄድ ቢረባረብበት በቀናት ውስጥ የሚጠፋ ይመስለኛል – በቅድሚያ በአካባቢው የሚገኝ ሕዝብ በዘመቻ መልክ ለተወሰነ ጊዜ ይዝመትበት፡፡ ከመሀል አገርም የትራንስፖርትና የምግብ አገልግሎት በመንግሥት ቀርቦላቸው በጎ ፈቃደኞች እንዲዘምቱ ይደረግ፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታና ለታይታ ሣይሆን ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ ሁሉም በቅንነትና በቀናነት ይሣተፍ፡፡ ሀገራዊ ጥቅሞችንና የሀብት ምንጮችን ከፖለቲካ አስተሳሰብና ከዘረኝነት ልክፍት እናውጣቸው፡፡
የፖለቲካ ሸፍጥ ካለ አንድም ስኬት አይመዘገብም፤ እያየነው ነው፡፡ ለኮሮና ተጎጂዎች የእርዳታ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋለው አስቂኝ የልጆች ድራማ ብዙ እያስተማረንና እያስደመመንም ይገኛል – የፖለቲካውን ልጓም የጨበጡትን ልጆች ምንነትና ማንነት ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ነው፡፡ ታከለና አቢይ ዘይትና ዱቄት ሲሸከሙ ዙሪያ ገባውን እየቃኘ የሚጠብቃቸው ፖሊስ እስክንድርና ስንታየሁ ያንኑ ተግባር ሲፈጽሙት ግን እንደወንጀል ተቆጥሮ ዘብጥያ ያወርዳቸዋል፡፡ እርዳታውም ይነጠቃል፡፡ ከዚህ የበለጠ አስቂኝ ተውኔት ሊኖር አይችልም፡፡ አእምሮ ወደሆድ ሥር ወርዶ ሲወተፍ ይሉኝታ ከሰውነት ይሰደዳል፡፡ የዝነኝነትና የሥልጣን ሱስ ጭንቅላትን ሰንጎ ሲይዝ ሀፍረትንና ሰብኣዊነትን ከግለሰቦች ይነጥቅና የለዬለት ዐውሬ ያደርጋቸዋል፡፡ እሚገርም ነው!
ለማንኛውም በጀመርኩት የሃሳብ ምህዋር ላይ የሚሰማኝን አዋጭ የሆነ ምክረ ሃሳብ ልሰንዝርና ለሰናበት፡፡ እናም የወል ችግሮቻችንን ከአሁኑ በከፋ ሁኔታ ጉዳት ሳያድርሱብን ማስወገድ ከፈለግን “ ላሊበላ የኔም ነው፤ የፋሲል ግምብ የኔም ነው፤ ሶፉመር ዋሻ የኔም ነው፤ አክሱም ጽዮን የኔም ናት፣ የጀጎል ግምብ የኔም ነው፤ ወዘተ. “ ብለን በጋራ እንነሳ፡፡ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ዘረኝነቱ በቅርብ ይጠፋል፡፡ የራቀን ፍቅርና አብሮነትም ይመለሳል፡፡ ራስ ወዳድነትና አፍቅሮተ ንዋይ አደብ የሚገዙበት፣ ወገን ለወገኑ የሚጨነቅበትና ፍቅር የሚነግሥበት ዘመን ይብታል፡፡ የጋራ ዕሤቶቻችን ከጠፉ ግን በኋላ ጸጸት እንጂ መልሰን አናገኛቸውምና እንንከባከባቸው፤ እንጠብቃቸው፡፡ በአንድ በኩል ዛፍ እየተከልክ በሌላ በኩል ቅርስህን ማጥፋት ዕንቆቅልሻዊ ግንጥል ጌጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር የምንጠብቀውንና የሚያስፈልገንን እውነተኛ ሙሤ በቅርቡ ይላክልን፡፡ አሜን፡፡