>
5:18 pm - Thursday June 15, 2073

የአገር ቤት ጨዋታ...!!! (ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር)

የአገር ቤት ጨዋታ…!!!

ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር

ቅኔው ገብቶኛል ውስጠ ወይራ ነው!!!
 አንድ ተማሪ ቅኔ  ለመማር ወደቅኔ ቤት ቢሄድም ትምህርቱ ሊገባው ስለአልቻለ  በአንድና በሁለት ወር በምትፈጀው ጉባዔ ቃና  አልገባው ብላ  ለአንድ ዓመት  ያህል ይቆይባታል። ጉባዔ ቃና ቅኔ እየቆጠረ ወደ መምህሩ ለመቅረብና ለመቀኘት ቢሞክርም መሥጢር አልባ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ዓይነት ወደ ሁለተኛውና ወደ ባለ ሦስት ቤቱ እርከን ወደ ዘአምላኪየ ሊሸጋገር አልቻለም፡፡ በጉባኤ ቃና ለአንድ ዓመት ከቆየባት በኋላ  መምህሩ ወደ ዘአምላኪየ አልፈሃል ካላሉት የሚያደርገውን ለማድረግ ወሰነ፡፡መምህሩ   ዘአምላኪየ ከአልሠጡት በደበሎው ውስጥ ደብቆ በያዘው የወይራ ከንተሮ አናታቸውን ፈጥፍጦ ወደ አገሩ ለመመለስ ወሰነ።
 በአሰበው መሠረት በደበሎው ሥር የወይራ ከንተሮውን ይዞና ወደ መምህሩ ቀርቦ ” የንታ ቅኔ ልንገር” ይላል። የቅኔ መምህሩም ” እሺ ይሁን” ይላሉ።” ቂርቆስ ወኢየሉጣ ተጋደሙ ግድመ አምጣነ አኮኑ ወእስመ ወእስመ” ይላል። ቅኔው ምንም አይነት ምሥጢርና የሰምና የወርቅ  ጎዳና/ይዘት/የለውም። መምህሩ ግን ቅኔውን ካላደነቁለትና ዘአምላኪየ ከአልሠጡት በደበሎው  ሥር በያዘው የወይራ ከንተሮ እንደሚመታቸው አስቀድመው ከአንድ ተማሪያቸው ስለተረዱ ቅኔውን ሲሰሙ ” ይበል መልካም ነው ማለፊያ ቅኔ ነው። እሰይ የእኔ አንበሳ (አንበሳ አይባልም መሰለኝ) እሰይ የእኔ ፒኮክ  ዘአምላኪየ ሠጥቼሃለሁ” ይሉታል። በዚህ ጊዜ  የቅኔውን ጅልነት የተረዱት ሌሎች ተማሪዎች ” የንታ ይኸኮ ይበል የሚያሰኝ ቅኔ አይደለም። ምሥጢር አልባና ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው ቅኔ ነው” ይላሉ። በዚህ ጊዜ የቅኔ መምህሩ ” የለም ቅኔው ማለፊያ ነው መልካም ነው። ለእኔ ገብቶኛል ። ውስጠ ወይራ ነው” ብለው ተናገሩ። ውስጠ  ወይራ አንደኛው የቅኔ መንገድ ሲሆን  በሌላ በኩልም ንግግራቸው ተማሪው የወይራ ከንተሮ በደበሎው ሥር መያዙን ይጠቁማል። እና የሰው ልጅ  በልቡ ቂም ቋጥሮና አድብቶ  ሀገሩንም ሆነ ወገኑን መጉዳት እንደሌለበትና የፈተናንም ወቅት የየኔታን ብልኃት ተበድሮ  ክፉ ጊዜን    በዘዴ ማለፍ  ይገባል፡፡

አካሔድ ምንድን ነው?

       በአማርኛ ቋንቋ አረዳድ  አካሔድ አረማመድ፤አጓጓዝ ፤የጉዞ ስልት ቄንጥ — ተብሎ ሊፈታ ይችላል፡፡ ይህ ቃል ትክክለኛ ትርጉሙን የቀየረ  የሚመስለኝ  በዘመነ ኢሕአዴግ  ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ስሠራ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ኢሕአዴግ  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችን በተቆጣጠረን ጊዜ አማርኛንም እኛ በማናውቀው መንገድ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ብሎ ተቆጣጥሮት ነበርና አዳራሽ ውስጥ ሁለት ታጋዮች  ሰብስበውን ፤‘ እኛ እምንለው ያለው፤ እኛ እያልን ያለነው፤ እንዳካሔድ ፤ እንደ ቀበሌ ፤ እንደ ሕዝብ፤ እንደ መንግሥት ፤ የተገማገምንበት ሁኔታ ነው ያለው ፤ እኛ እምንለው ያለነው ፤እኔ እያልኩ ያለሁት የሚለው ሰዋስው አልባ ንግግር ወይም ወይም ይህንኑ  ፈሊጥ ተከትሎ ጋዜጣው ላይ የሚጻፈው ጽሑፍ ዛሬ ነጻ የወጣ ቢመስልም  አንዳንዱን ካድሬ ግን  ስለተወሐደው  ‘ እኔ እያልኩ ያለሁት ፤አካሔድ? ሥራው እየተሠራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ’ ሲል ይሰማል ፡፡
  አካሔድ በካድሬዎች ቋንቋ ሥነ ሥርዓት ፤ ስለደንብ  አቁም፤ አትናገር ለማለት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ዓይነት በ1993 ዓ ም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችን  ኢሕአዲጎች  በተቆጣጠሩን ወቅት  በተለይ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በተወሰኑ ጋዜጠኞች ላይ ግምገማ  ይካሔድ  ተብሎ  እናንተ የደርግ ኢሠፓ አፈቀላጤዎች በሚል ዱላ ቀረሹ  ስድብ አከል ግምገማ ከተደረገ በኋላ የመምሪያ ኃላፊውን እውቁን ጋዜጠኛ አቶ ሙሉጌታ ሉሌንና አቶ ክፍሌ ሙላትን ጨምሮ 11   ነባር ጋዜጠኞች  ቁልፍ እያስረከቡ ድርጅቱን እንዲለቁ ተደረገ፡፡
    በሌላም ቀን ገምጋሚውና የ8ኛ ክፍሉ ታጋይ የሽብ የክብ ይዞ ሲያስጨንቀን በዋለበት ሰዓት  በጣም የምወዳቸውንና የማከብራቸውን የሕግና ሕብረተሰብ ዐምድ አዘጋጅ  የነበሩትን የአቶ ታደሰ ውቤን (በኋላ ሊቀ ጠበብት)ስም እያነሣ ሲገመግማቸውና  ውንጀላ ሲያቀርብባቸው ብድግ አሉና  ‘ ይህ የቀረበብኝ ውንጀላ በእኔ ዘንድ ተቀባይነት የለውም  ምን ይላል? ከመሬት ተነሥቶ በእኔ ላይ አራሙቻ ሊያለብሰኝ ነው እንዴ የፈለገው ? ሲሉ ካድሬው ‘አካሔድ’  ብሎ ጮኸ፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና  በአለባበስ እንደፍቅረ ሥላሴ ወግ ደረስ ሽቅርቅር የነበሩት ጋዜጠኛና በካድሬዎች ውሳኔ መሥሪያ ቤቱን የለቀቁት  የሕግ ባለሙያ ‘ እኔ ታደሰ ውቤ  ስጓዝኮ ሸፋፋ አይደለሁም፤ አካሔዴ ቄንጠኛ ነው፡፡
  ድፍን የዑራኤል ሕዝብ ይመስክርብኝ፤ እናንተም ዜንጦ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ አካሔዴ ምን ችግር አለው ?’ ሲሉ ተሰብሳቢው በሣቅ ፈረሰ፡፡ድፍን የዑራኤል ሕዝብ ይመስክርብኝ ያሉት ዑራኤል አካባቢ ተወልደው እዚያው ስላደጉ ነው፡፡ አካሔድ፤ እንደ አቅጣጫ ፤ ኢሕአዴግ እንደ ኢሕአዴግ ፤ ጋዜጣ እንደ ጋዜጣ፤ በሽታ እንደ በሽታ፤ እንደ እንዳመለካከት—የሚለው የካድሬው ቃል ለሊቀ ጠበብት ታደሰ ውቤ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ታጋዩ  ካድሬ አካሔድ ብሎ ሊያስቆማቸው የነበረው የስብሰባ ሥነ ሥርዓት አላከበሩም ለማለት  ነበር፡፡ ያ ካድሬ ዛሬ በብልጽግናው ዘመን  የለምና ነው እንጂ ቢኖር ኖሮ ፤ ‘የትምክህት ኃይሎች ተላላኪ  የሆነው ኮረና እንደ ኮረና መጥፎ ነው፤የኮረና አካሔድ ጅምላ ጨራሽ ነው ፤እንዳካሔድ ኮረናን እንደ ደርግ ኢሠፓ ታግለን ማሸነፍ አለብን’  ብሎ ኦሬንቴሽን ከመስጠት አይመለስም ነበር፡፡
“እናንተን ባላውቃችሁ እኽሉን አውቀዋለሁ!”
    አንድ የዜማ ተማሪ ወደአንድ ትልቅ  ከተማ ሔዶና የዲቁና ማዕረግ ተቀብሎ በእግሩ ወደአገሩ  ገጠር ሲመለስ ረሀብ ልቡን ያጠፋዋል። እንዳጋጣሚ ግን ሰዎች በደቦ ጤፍ ሲያጭዱ ውለው በግምት ስምንት  ሰዓት ሲሆን ሽውታ እንዳይመታቸው ነጠላ ተሸፋፍነው  ምግብ ሲመገቡና ጠላም ሲጠጡ  ይደርሳል። ተማሪውም ” እንዴት ዋላችሁ ወገኖቼ ” ሳይል ሰዎቹ የተሸፋፈኑትን ነጠላ ገለጥ አድርጐ አብሯቸው መብላት ይጀምራል። ገበሬዎቹም ተገርመው” ተሜ አብረኸን ማዕድ የምትቀርበው የት ታውቀናለህ?” ብለው ይጠይቁታል። ተማሪውም ደበሎውን  እያንጓፈፈ ” እናንተን ባላውቃችሁ እህሉን አውቀዋለሁ።” ብሎ እየቆረሰ ሲጎርስ ሰዎቹ ” እውነቱንኮ ነው” ብለው ተገረሙበት።እና በዚህ ክፉ የኮረና ዘመን  ዐቅም ለሌላቸው ወገኖቻችን  እኽል ምግብ ተካፍለን  አካፍለን  ተረዳድተን መመገብና ክፉውን ዘመን መሻገር   ይኖርብናል፡፡

ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ 1997 ከተባለው መጽሐፌ የተወሰደ ፡፡ 

Filed in: Amharic