>

የለውጡ መለስ ቀለስ...!!! (በፍቃዱ ኃይሉ)

የለውጡ መለስ ቀለስ…!!!

በፍቃዱ ኃይሉ


አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያለፈው ሳምንት ያወጣው ሪፖርት ብዙዎችን አስደንግጧል፣ አንዳንዶችን ግራ አጋብቷል፣ ሌሎችን ደግሞ አበሳጭቷል። አምነስቲ ብዙ ጊዜ አጫጭር መግለጫዎችን እንጂ ረዘም ያሉ ጥናታዊ ሪፖርቶችን አያወጣም። ለምሳሌ ያክል እንደዚህ ዘለግ ያለ ሪፖርት ከዚህ ቀደም ያወጣው እ.ኤ.አ. በ2014 የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ነው። ሪፖርቱ ‘ኦሮሞ ስለሆንኩ’ የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የኦነግ አባል የሆኑ ወይም በመሆን የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ግፎችን ያስነብባል። የአሁኑ ሪፖርት ደግሞ ‘ሕግ ከማስከበር ባሻገር’ የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞኖች እና አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር፣ በተለይም የቅማንት ተወላጆች ላይ የተፈፀሙ ግፎችን ያስነብባል።

በሁለቱ  ሪፖርቶች መካከል ያለው የጎላ ልዩነት የጊዜ ብቻ ነው። የዘፈቀደ ግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር፣ የዘፈቀደ እስር፣ የማፈናቀል እና የማሰቃየት ታሪኮች በሁለቱም ሪፖርቶች ውስጥ አሉ። ለዚህ ነው ላለፉት ሁለት ዓመታት ስናየው የነበረው የፖለቲካ ለውጥ ወደ ፊት ሔዷል ሲባል ወደኋላ መለስ ቀለስ እያለ አስቸግሯል ለማለት የሚያስደፍረው። ለመሆኑ ሪፖርቱ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

መሬት ወደ መርገጥ

የአምነስቲ ሪፖርት ያመጣው አዲስ ነገር ቢኖር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በሕሊናቸው እየካዱት የቆየነውን እውነት እንዲጋፈጡ መጋበዙ ነው። ያለፉት ሁለት ዓመታት የፖለቲካ ለውጥ ጉዞ መንገዱ ጨርቅ ያልተመላ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቃል። ሆኖም መንግሥትን እንደ ፍፁም ለውጥ ፈላጊ እና ቀና አካል ብቻ የመመልከት አባዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተንሰራፍቶ ነበር ማለት ይቻላል። “መንግሥት አቅም በማጣቱ ነው”፣ “ለውጡን ሊቀለብሱ የሚፈልጉ ሰዎች ሴራ ነው”፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት አይወድለትም” የሚሉትን ጨምሮ ሌሎችም ምክንያቶች እየተሰጡ መንግሥትን ከተወቃሽነት ለመከለል ሰበብ ሲሆኑ ነበር። ግጭቶችን፣ የደቦ ፍርዶችን፣ ስርዓተ አልበኝነቶችን እና ወዘተርፈ በተደጋጋሚ ዜና እያደመጡ ጥፋቱን ሁሉ መንግሥታዊ ላልሆኑ አካላት የመስጠት ዝንባሌ ከዚህ በኋላ የሚያስኬድ አይሆንም። የትኛውም የጎንዮሽ እርስ በርስ ግጭት እና ስርዓት አልበኝነት በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሕዝብን ተወቃሽ አድርጎ መንግሥትን ነጻ አያወጣም። በመሠረቱ መንግሥት የሚያስፈልገው እነዚህን ለመከላከል ሲባል ነው። በተለይ በሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ የመንግሥት ኀላፊነት በሦስት በኩል የሚመጣ ነው።

የመጀመሪያው የመንግሥት ኃላፊነት ሰብኣዊ መብቶችን ማክበር ነው፤ ዋነኛው የኃይል ባለቤት መንግሥት ራሱ እንደመሆኑ የዜጎቹን ሰብኣዊ መብቶች ማክበር ቀዳሚው ሕገ መንግሥታዊ ግዴታው ነው። ሁለተኛው ኃላፊነቱ ሰብኣዊ መብቶችን የማስከበር ነው። ሰብኣዊ መብቶችን የተደራጁ ቡድኖች፣ ታጣቂዎች እና ሌሎችም እንዳይጥሷቸው መንግሥት ጥበቃ እና የማስከበር ሥራ የመሥራት ኃላፊነት አለበት። ሦስተኛ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ የመሥራት ኃላፊነት አለበት። የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ድንገተኛ ክስተት አይደለም፤ ሁሌም ሕጋዊ ቸልተኝነት እና ክፍተት ባለበት የሚከሰት ነው። አሁንም በአምነስቲ ሪፖርት ውስጥ የምንመለከተው ቢያንስ ከሦስቱ አንዱ በመጉደሉ የተከሰቱ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ነው።

የፖለቲካ ለውጡ መታየት ከጀመረ ወዲያ በመጡት ወራት መንግሥታዊ ከሆኑ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ይልቅ መንግሥታዊ ያልሆኑት ማፈናቀሎች፣ የደቦ ፍርዶች፣ የታጣቂ ቡድን ጥቃቶች ይበዙ ነበር። እነዚህን በሕግ አግባብ መግታት የመንግሥት ሙሉ ሥልጣን እና ኀላፊነት ሆኖ ሳለ፥ ምንም በማይገናኝ መልኩ “አምባገነን ላለመሆን” በሚል ሰበብ በቸልታ ሲታለፍ ቆየ። ብዙዎቹ ጥሰቶች በቂ ክልከላ አልተደረገላቸውም፣ ከተፈፀሙም በኋላ ሕጋዊ እርምጃ አልተወሰደባቸውም። ይህ ጉዳዩን ከድጡ ወደ ማጡ በማድረጉ ከረፈደ በኋላ የመከላከያ ኀይል እንዲሰማራ ተደርጎ ከደቦ ፍርድ ያልተለየ ጥቃት አድርሷል። መንግሥት ሦስቱንም የሰብኣዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስከበር፣ እና እንዳይጣሱ ሁኔታዎችን የማስተካከል ኃላፊነቱን ሳይወጣ ቀርቷል።

ድሮ እና ዘን-ድሮ

የድሮውና የዘንድሮው የመንግሥት ባሕሪ በእጅጉ የሚመሳሰለው በሁለት ነጥቦች ነው። ይኸውም በአንድ በኩል ሰብኣዊ መብቶችን በመጣስ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ጥሰቶቹን ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ነው። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ፍፁም አይደለም። ከላይ ከጠቀስነው ሪፖርት ጋር ስናወዳድረው እንኳን የጥናቱ ጥልቀት ላይ ብዙ ክፍተቶችን እናገኛለን። ጥናቱ የሚሸፍነው የጊዜ ሰሌዳ እና ለሪፖርቱ የተመረጡት ርዕሰ ጉዳዮች የአንድ ወገን የፖለቲካ ትርክትን የሚደጉሙ መሆናቸው ጉድለቶቹ ናቸው። ምናልባትም የሪፖርቱ ግኝት የሚገባውን ትኩረት አጥቶ፥ በፖለቲካዊ ክርክር እንዲጠለፍ እነዚህ የጥናቱ ክፍተቶች አስተዋፅዖ አድርገዋል። ነገር ግን መዘንጋት የሌለበት በቂ የተጠቂዎች እና የዓይን ምስክሮችን የያዘ መሆኑ ነው። ሪፖርቱ የቤተሰብ አባላቸውን በግድያ የተነጠቁ፣ የታሰሩ፣ የተሰቃዩ፣ የተደፈሩ ሰዎች ምስክርነት ይዟል። እነዚህ ተጠቂዎች እና የዓይን እማኞች ፍትሕ ከማግኘት የበለጠ ምንም ጉዳይ አይኖራቸውም። ስለዚህ የክርክሮች ሁሉ መጀመሪያ መሆን የነበረበት “እንዴት እነዚህ ሁሉ የመብት ጥሰቶች?” የሚለው ነበር።

መንግሥት የሪፖርቱ መሰናዶ ላይ ያሉ ጥቃቅን ክፍተቶች የፈጠሩትን የፖለቲካ ክርክር ዕድል ተከልሎ የሪፖርቱን ውጤት በተለያየ መንገድ ክዷል። በአንድ በኩል ሪፖርቱ በተደረጉባቸው አካባቢዎች ያሉ ስርዓተ አልበኝነት በመጥቀስ፣ በሌላ በኩል የሪፖርቱ ሙሉ ምስል ከሳች አለመሆኑን በመጥቀስ፣ እንዲሁም ሌሎችም ሰብኣዊ መብት ጣሽ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስ የተጠቂዎቹን ጉዳይ አሳንሶ ወይም አድበስብሶ ለማሳየት ሞክሯል። ይህ በቀድሞው ስርዓትም የነበረ የተለመደ ዘዴ ነው። የመንግሥቱ ደጋፊዎችም ሪፖርቱ ላይ የጎደለው ቀርቶ የተጠቀሱት የተጠቂዎችን ምስክርነት አንብቦ መንግሥትን በመውቀስ እና በመጠየቅ ፈንታ እንደተለመደው ሪፖርት አውጭውን አካል ሲወቅሱ ሰንብተዋል። መለስ ቀለስ ማለትም ይኸው ነው።

ተስፋ እንዳንቆርጥ

እውነት ነው መለስ ቀለስ አለ። ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስትም የፕሬስ ነጻነትና የመደራጀት መብት በመፍቀድ ለዴሞክራሲ ፈር ቀዶ ነበር። የኋላ ኋላ ተቃውሞዎች ሲበረቱ ግን በሥማቸው ልጠራባቸው ሲላቸው የነበሩ ነጻነቶችን አቀጭጮ አቀጭጮ ጠባብ የፖለቲካ ምኅዳር ትቶ ተሰናብቷል። ይህም የፖለቲካ ለውጥ ይዞት የመጣው ቃልኪዳን የጠበበውን የፖለቲካ ምኅዳር መልሶ ማስፋት፣ በስፋት የሚጣሱትን ሰብኣዊ መብቶች ለማክበር እና ለማስከበር ቢሆንም፥ መጣሱ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። በመለስ ቀለሱ ውስጥ አዝጋሚ ለውጥ አለ። ለውጦቹ እየተመዘገቡ ያሉበት ፍጥነት እና የችግሮቹ አሳሳቢነት ያለው ክፍተት ግን የትየለሌ ነው።

በመለስ ቀለሱ ውስጥ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን ለውጥ አለ ስንል ከድሮ ጀምሮ የለውጥ ጭላንጭል ካየን በኋላ መልሶ ቢዳፈንም የተወሰኑ እርምጃዎች መኖራቸው ግን እውን ስለሆነ ነው። ከንጉሡ ወደ ደርግ በተደረገው ሽግግር የገባሩ ስርዓት ዳግም ላይመለስ ተሸኝቷል። ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ በተረገው ሽግግርም ለሕግ ተገዢነቱ ባይሳካላቸውም የዴሞክራሲ ተቋማት ተመሥርተዋል።  ከኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና የተደረገውን ሽግግር ውጤት ለመመዘን ጊዜው ገና ቢሆንም፥ ቢያንስ ነፍጥ ማንሳት ሳያስፈልግ መንግሥትን ለለውጥ ማስገደድ እንደሚቻል አሳይቷል። ቁም ነገሩ የለውጥ በሮች በተከፈቱ ቁጥር በአጉል ተስፋ አለመኖር ነው። ያልተገባ ተስፈኝነት አሁን እንደተፈጠረው ዓይነት መንግሥትን በዓይነ ቁራኛ ከመታዘብና ለውጡን የራስ ከማድረግ የመንግሥት ችሮታ አድርጎ በማሳየት፥ የኋላ ኋላ ተስፋ ለመቁረጥ ይዳርጋል።

Filed in: Amharic