>

ምጥ = (የኢትዮጵያ - ምጥ) [ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን]

ምጥ = (የኢትዮጵያ – ምጥ)

[ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን]

በአፍላ የወጣትነት ዘመኑ ወደዳት፡፡ መውደድ ቢሉ መውደድ ነው፡- ቅልጥ ያለ ፍቅር ያዘው፡፡ በፍቅሯ ቀለጠ፤ ተቅለጠለጠ፡፡ እሷም እንደሱ በፍቅሩ ተነደፈች፡፡
በየፊናቸው መፋቀርን ፈቀዱ፡፡ ተፈቃቀዱ፡፡ የእሷ እናት የአጋጣሚ ነገር ሆኖ እናት ዓለም ነው ስማቸው፡፡ “እናት” ይሏቸዋል ሲያቆላምጣቸው፡፡ “የዓለም ይሁንላችሁ” ብለው ፈቀዱላቸው፡፡ ዳሯቸው፡፡
ተጋቡ፡፡ በተክሊል፡፡ በቃልኪዳን፡፡
በዓመቱ አናት መልዕክተኛ መጣባቸው፡፡
“ሴት ልጅዎ …. ኢትዮጵያ ምጥ ይዟታል፤ ይድረሱላት” ተባሉ፡፡
ነጠላቸውን እንኳ በወጉ ሳያጣፉ እየበረሩ ወደልጃቸው ሄዱ፡፡
ሲደርሱ እሱ ኢትዮጵያን በመኪና ወደ ሆስፒታል ሊወስዳት አቆብቁቧል፡፡ አብረውት ሄዱ፡፡ ወዲያው ሐኪሞቹ ተቀብለው ወደማዋለጃ ክፍል አስገቧት፡፡
“እናት” ማዋለጃው ክፍል ብር አጠገብ ተቀምጠው እየተንቆራጠጡ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ እሱ ረዥሙ የሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ እየተመላለሰ መንቆራጠጡን ቀጠለ፡፡
ጠበቁ፡፡ ጠበቁ፡፡ የምስራች ጠበቁ፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ “እናት” የኢትዮጵያን የተፋፋመ የምጥ ጩኸት ብቻ ነው የሚሰሙ፡፡ እሱም የምጧ ጩኸት በሩቁ ይሰማዋል፡፡ ተጨንቋል፡፡ ጭንቀቱ ከወዲያ ወዲህ ያንቆራጥጠዋል፡፡
“እናት” ግራ ተጋቡ፡፡ ኢትዮጵያ ማዋለጃ ክፍል ቀገባች ሰዓታት አልፏል፡፡ በሃሳብ እና በጭንቀት እየናወዙ ወደ እሱ ሲመለከቱ ድንገት ቀበቶ መታጠቁን አዩ፡፡
“ና ና! ና እስቲ ወዲህ አንተ!…ና እኮ ምልህ?…እንዲህ ነችና!….ቀበቶ አልገህልኛል!?” አሉት ቆጣ ብለው፡፡
“አዎና!….. ካለቀበቶ ሱሪ ልታጠቅ ነው እንዴ!?…ምነው!?”
“በል ቀበቶህን ፍታ!!….ፍታና አውልቀው!….አንተ ቀበቶ አስረህ ነው ለካ የኢትዮጵያ ማህፀን አልፈታ ያለው!!” ሲሉ አዘዙት ካስተር ኮምጨጭ ብለው፡፡
እየገረመው ቀበቶውን ፈታና አጠገባቸው አስቀመጠው፡፡ እናም መንጎራደዱን ቀጠለ፡፡ “እናት” በተቀመጡበት ወገባቸውን ጭምቅ አድርገው ይዘው ይንቆራጠጡ ገቡ፡፡
አሁንም የኢትዮጵያ የምጥ ጣር ጩኸት ከማዋለጃ ክፍሉ ውስጥ እየሾለከ ከመሰማቱ በቀር መልካም የምስራች መስማት አልተቻለም፡፡
እንዲሁ በየፊናቸው ሲንቆራጠጡ ደቂቃዎች እንደዘበት ነጎዱ፡፡ እሱ ተበሳጨ፡፡ ጭንቀቱ የፈጠረው ብስጭት አንዳች ሃሳብ ወደ ህሊናው አመጣለት፡፡ ያን ሃሳብ እያሰላሰለ ወደ “እናት” ጠጋ ብሎ ጠየቃቸው፡፡
“እናት፤ ኢትዮጵያ ምጧ የበረታው እኔ ቀበቶ በማሰሬ የተነሳ ነው በለውኝ ቀበቶ ፈታሁ፡፡ ከፈታሁ በኋላም አልወለደችም፡፡ ለምን ይመስልዎታል!?”
“ቀድሞውኑ ብትፈታ ኖሮ ይኼኔ ኢትዮጵያ ወልዳ ነበር፤ ቀበቶ ማሰርህ ነው ማህፀኗን ያሰረው” አሉትና ፊታቸውን ወደማዋለጃው አዞሩ፡፡
“እንደዛ ከሆነ ጫማዬንም አስሬአለሁ ልፍታው”
“ፍ….ታ ….ው!!” አሉት በለበጣው ተናደው፡፡
ንዴታቸውን ላለማባባስ ፈታው፡፡
የጫማውን ክር ፈትቶ ቀና ሳይል የእልልታ ድምፅ ሲያስተጋባ ሰማ፡፡
ኢትዮጵያ ወለደች፡፡
ይኼኔ እሱ እንዲህ አለ ለራሱ፡-
“ኢትዮጵያ ቀበቶ የሚያወልቅና ጫማ የሚፈታ ትውልድ ወለደች” አለ፡፡
ሣቀ፡፡ በራሱ ሣቀ፡፡ በልጁ ሣቀ፡፡ በሣቁ ከ“ምጡ” ተገላገለ፡፡
Filed in: Amharic