>

የነገሥታት ጋብቻ - የእኩዮች አምቻ ! (አሰፋ ሀይሉ)

የነገሥታት ጋብቻ – የእኩዮች አምቻ !

አሰፋ ሀይሉ

 

 ጋብቻ እንደ ሥልጣን ማስጠበቂያ! 
‹‹ጋብቻ›› የሀጢያት ፍሬ ነው ወይ? አዎ ነው፡፡ ድብን አድርጎ! ታዲያ ጋብቻ እንዴት የተቀደሰ ሊሆን ቻለ? ሐይማኖቱ እንደሚለው ፈጣሪ አምላክ አዳምና ሄዋንን ያቺን የጾታን ልዩነት ያሳየቻቸውን ፍሬ ከበሉ በኋላ ረግሞ ብቻ አላበቃማ! መርቆና አጣምሮምኮ ነው ወደ ምድር የሰደዳቸው፡፡ እና ይሄ የጋብቻ ጥምረት የፈጣሪ ፈቃድም የታከለበት የኃጢያት ፍሬ ነው ማለት ነው? ዓላማውንስ የተቀደሰ ያደርገዋል ማለት ነው?፡፡ ሳይሆን አይቀርም!የሚሉ አሉ፡፡
በሌላ በኩል ጋብቻ የሰውን ልጅ ትውልድ በኃላፊነት ስሜት የሚፈጥርና በምግባር ኮትኩቶ አሳድጎ ከሰፊው የሰውልጅ ማኅበር (ከማኅበረ-ሰብ) ጋር አላምዶ – ለወግ ለማዕረግ የሚያበቃ – የሰው ልጅ የመጀመሪያውና ዋነኛው ሰብዓዊነትን የማሠልጠኛ ማኅበራዊ ተቋም በመሆኑ – ጋብቻን በዓላማ ደረጃ – ከብዙ የሽርክና ጥምረቶች በተለየ – የተቀደሰ ጥምረት ያደርገዋል፡፡ የሚሉ አሉ፡፡
(በእርግጥ ልጅ መውለድ ተቀዳሚ ዓላማቸው ያልሆኑትስ – በከፍተኛ የስሜት ወላፈን ምሪት የሚፈጸሙት ‹‹የፍቅር›› ጋብቻዎችስ? – እነርሱስ የተቀደሱ ላይሆኑ ነው ማለት ነው? – አይ እንግዲህ! የቅድስናና የእርኩስና ፈራጅ አይደለሁም! እንዲያውም የዚያ የትዳር-ሰፈር ሰውም አይደለሁም! እና – በቃኝ ተሰናበትኩ፡፡)
ለማንኛውም ስለ ጋብቻዎች ስናወሳ አብረን የምናወሳው አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ያም ነገር ጋብቻዎች – በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥም – በኛ በራሳችን በሀገራችን ታሪክ ውስጥም – ለተቀደሰም፣ ላልተቀደሰም ዓላማ ውለው የመገኘታቸው ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በዓለም ጸሐፊያን ዘንድ – ‹‹የፖለቲካ ጋብቻዎች›› ወይም ‹‹የሥልጣን ጋብቻዎች›› የሚል ስያሜን ስላገኙት – እና በአንድ ሀገር ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሀገሮች መካከል ባሉ ገዢዎች (እና የገዢነት መነሳሳት ያደረባቸው ተስፈኛ ገዢዎች) መካከል ለረዥም ዘመን ጸንቶ የቆየውን የሥልጣን ሥሪት አስጠብቆ ለመቆየት – ጋብቻ ወይም ትዳር – እንደ ዓይነተኛ መሣሪያ በመሆን አገልግሏል፡፡
በውጪውም ዓለም ታሪክ እንደምናውቀው – (በተለይ በአውሮፓ ታሪክ – ኢንግላንድ-ስኮትላንድ-ዌልስ-አየርላንድ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ስፔን፣ ኦትሪያ-ሃንጋሪ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊስ፣ ኧረ ሀገረ አውሮፓ ሁሉ) – ነገሥታቱ ሁሉ ሴት ልጁን ከሌላ ነገሥት ወንድ ልጅ ጋር በጋብቻ ሲያጣምድ ነው የኖረው፡፡ በጋብቻ ማጣመድና ባላንጣን ማምከን ራሱን የቻለ ትልቅ የዓለም ታሪክ የሚወጣው ‹‹ታላቅ አስደማሚም አስገራሚም የነገሥታት ሴራና መደሰቻ›› ነበረ ማለት ይቀላል፡፡ ‹‹ዲፕሎማሲያዊ ጋብቻዎች›› (“Diplomatic Marriages”) እየተባሉም እስከመጠራት ደርሰዋል፡፡እስከ 19ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ የነበረው የአውሮፓ ታሪክ ባጠቃላይ የ‹‹Royal Marriages and Intermarriages›› ታሪክ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት የዓለም መንግሥታት ታሪክ የደም እና የወንዴ-ዘር ርጭት ታሪክ ነው የሚሉ ሂሰኞች አጋጥመውኛል፡፡ በጋብቻ ድራማው ውስጥ ደግሞ የጳጳሳት ሚናም ሳይዘነጋ ነው፡፡
ጋብቻ በትዳሩ ጥምረት በተጋቢዎቹ መሐል የሚፈጠረው ዝምድና ነው፡፡ አምቻ ደግሞ በጋብቻው የተነሳ በወንድ አማቾቻቸው መካከል የሚፈጠረው ዝምድና ነው፡፡ ልክ እንደ ውጪው ዓለም ሀሉ – በእኛም ሀገር የነበረው ጉልታዊ (ወይም የነገሥታት/የመኳንንት) አምቻ ጋብቻ ታሪክ ያው ነው፡፡ በኛ ሀገርም በተለይ በቀደመው ዘመን በዘር ሃረግና በደም ዝምድና ቆጠራ የተመሠረተው የገዢነትና የተገዢነት ሥሪተ-ሥልጣን በህዝባችን ዘንድ ያለው ቅቡልነት ሥር ከመስደዱ የተነሳ – አንድ የታሪክ ተቺ በስላቅ አነጋገር እንዳለው – የንግሥና ዘር ያለው ወንድ ልጅ ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ ሽንቱን ራሱ መንገድ ዳር ቆሞ እንደልቡ መሽናት እማይችልበት ደረጃ ተደርሶ ነበር፡፡
ምክንያቱ? ምክንያቱማ – ያም ይሄም እየመጣ እባክህ ከሴት ልጄ ጋር የዛሬን እደርልኝ (ተዳደርልኝ፣ ተዳርልኝ) እያለ እያስቸገረው – የሚል፡፡ ‹‹ወይ ካለው ተወለድ ወይ ከደህና ተጠጋ›› በሚል ፈሊጥ ከነገሥታቱ ተዛምዶ ጥዋቸውን መቃመስ የብዙው ሰው ህልም በሆነበት በዚያ ዘመን – አዳሜ ሴት-ልጁንና ወንድ-ልጁን የንጉሥ ዘር እንዲሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሳልፎ በመስጠት ሽሚያ ውስጥ ገብቶ ነበር ማለት እኮ ነው! አያድርስ ‹‹ሽሚያ›› ነው ይሄስ?!
(በእርግጥ እውነቱን ለመናገር፡- ‹‹ዘንድሮስ ጨዋታው ከዘውድ ወደ ሀብት መቀየሩ ነው እንጂ ያው እንደ ድሮው አይደል ወይ ሽሚያው?›› ለሚለኝ አጥብቆ ጠያቂ – መልስ የለኝም! ስምንተኛው ሺህን ይዘዝብህ ከማለት ሌላ! በ8ኛው ሺኅ የተነገረ ትንቢት አለ፡- ‹‹የጃንተከል ዋርካ – መሬቱን ከነካ – ወንዱ እምቢኝ እምቢኝ – ሴቱ እንካ እንካ››! ኧረ የ8ኛው ሺህ ያለህ!)
በነገሥታቱ ወይም በገዢዎቹ ዘመን ጋብቻ እንደ ሥልጣን ጥቅም ማስጠበቂያ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በታሪካችን እንደታየው – የነገሥታት ልጆች – ሳይወዱ በግዳቸው ከባድ ሃላፊነት ወድቆባቸው ኖረዋልም ማለትም ይቻላል፡፡ ሁለት ባላጋራ ባላባቶች ቢኖሩና ልጆቻቸውን በማጋባት በመካከላቸው እርቅ ለማውረድ ቢፈልጉ – እርቁን እውን የማድረግ መከራው የሚያርፈው በባላንጣዎቹ ልጆች (በተጋቢዎቹ) ላይ ይሆናል፡፡
በተለይ ሴቶቹ – በባላንጣነት ስሜት የደነደነን የሸፈተን ልብ የመግራት ልዩ ተሰጥዖ ስላላቸው ይመስለኛል – እንደ አሪፍ ወጌሻ ተቆጥረው – ወደ አማፂው፣ ወደ ኃይለኛው፣ ወደ ተስተካካዩ ባላንጣ ነገሥት/መስፍን ወንድ ልጅ ቤተሰብ – በትዳር ለሚስትነት ተላልፈው የሚሰጡት፡፡ የነገሥታቱ ሴቶች – ከአባታቸው ባላንጣ ወንድ ልጅ ጋር አብረውት በትዳር እየኖሩ በውበታቸው፣ በግርማቸውና በመንፈሳቸው እንዲያፅናኑት፣ ያን በል-በል የሚለውን መንፈሱን በዝምድና እንዲገሩት – ከባዱን ኃላፊነት ተሸክመው ይሄዳሉ፡፡
በነገራችን ላይ የቀደመው የመኳንንት ጋብቻ የሥልጣን ማስጠበቂያ ብቻ ሳይሆን ‹‹እኩያዬ›› የሚልም ዓላማ (‹‹ራሽናል››) ያነገበም ይመስላል፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌላ ዘንድ የነበሩ የሥሪት ማስጠበቂያ ጋብቻዎችም ተመሳሳይ የ‹‹ስቴተስ ሲምቦል››ነት ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህ አንጻር ካየነው – እኩያን የማሳወቂያ ማኅበራዊ ተቋም ሆኖ አገልግሏል ጋብቻ፡፡ ከነተረቱ ‹‹ያላቻ ጋብቻ ቆይ ብቻ ቆይ ብቻ›› ይባል የለም? እንደዚያም ሆኖ አገልግሏል፡፡
የራስ እገሌ ልጅ የምትዳረው በ‹‹ስቴተሱ››ከፍ ላለ ሰው ልጅ ነው፡፡ አሊያም ለኃያል ጉልበታም ነው፡፡ አሊያም ተመሣሣይ ‹‹እኩያነትን›› ለሚገልጽ ቤተሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ጋብቻ የእኩያነትን ማሳወቂያ በሚሆንበት ወቅትም ቢሆን በድብቅ የሚጫወተው የሥልጣን ማስጠበቂያነት ሚናም ነበረው፡፡ በሀብት በሥልጣን በተሰሚነት እኩያ በሆኑ ገዢዎች መካከል የሚፈጸም አምቻ-ጋብቻ – ለዘመናት በጥቂቶች እጅ የዘለቀውን ‹‹ሳክሬድ ሩሊንግ ሶሳየቲ›› በጥቂቶች እጅ ብቻ ቆይቶ እንዲቀጥል – የማድረጊያ – ሥልጣን ከዚያ ‹‹ሩሊንግ ሰርክል›› ውጪ እንዳይወጣ የመከላከያ አንዱና ዓይነተኛው የ‹‹ክሎዝድ ሶሳየቲ›› ስልት ወይም መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል የእኩዮች ጋብቻ፡፡
በአጠቃላይ እስከ 20ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ በሀገራችን የቀጠለውና (አሁንም ቢሆን በብዙ የነገሥታት ሥርዓትን ባላስቀሩ በርካታ የዓለማችን ሀገሮች ዘንድ እየተተገበረ ያለው) ይሄ የመካከለኛው ዘመን ባህል ነፀብራቅ የሆነው ‹‹የሥልጣን ሥሪት ማስጠበቂያ ጋብቻ›› – በኛ ሀገር የነበረው መልክ ምን ይመስል እንደነበረ ሲታይ – ጉድ ነው የሚያሰኝህ! ጥቂት የሀገራችንን የታወቁ የነገሥታት ሥልጣን ማስጠበቂያ ጋብቻዎች ለአብነት አንስቼ – ሀሳቡ እጅግ ብዙ ሆኖ በአንድ ቋት አልሰበሰብ ብሎ ያስቸገረኝን ጽሑፌን አሳርጋለሁ፡፡
ለምሳሌ አጼ ዮሀንስን ውሰድ፡፡ የአጼ ዮሐንስ ባላጋራ ሊሆኑባቸው የሚችሉት በእምነታቸውም የተለዩት እና በአኗኗር ዘይቤያቸው የተነሳ ሰጥ-ለጥ ብለው ለአንድ አካል መገበርን ፈጽሞ የማይሹት ‹‹ኢንዶሚቴብልስ›› አፋሮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ አጼ ዮሐንስ ያደረጉት ነገር የአፋር የጎሳ መሪ ሴት ልጅ የነበረች ሴት መርጠው – ክርስትና አንስተው – ስሟን ቀይረው ማግባት ነበረ፡፡ “ምሥጢረ-ሥላሴ” አፄ ዮሐንስ ክርስትና አንስተው ያገቧት የአፋር ጎሳ መሪ ልጅ ናት፡፡ ራስ አርዓያ ሥላሴ ዮሐንስ ከምስጢረሥላሴ የሚወለድ የአፄ ዮሐንስ ልጅ ነው፡፡ ይሄ ራስ አርዓያ ሥላሴ የዘውዲቱ ምኒልክ የመጀመሪያ ባል የነበረ ሲሆን እሷንም ባገባ ጊዜ ወሎን ተሾሟል፡፡
የአርዓያ ሥላሴ ብቸኛው ወንድ ልጅ የነበረው ራስ ጉግሣ አርአያ ሥላሴ ደግሞ አለ፡፡ በወቅቱ የትግራይ አስተዳዳሪ የነበረው ወጣቱ ደጃች ጉግሳ አርዓያ ሥላሴ ዮሐንስ ደግሞ የራስ ተፈሪ መኮንንን የቅርብ ዘመድ የነበረችውን ሉሊት የሻሽወርቅ ይልማን አግብቶ በዝምድና ተሳስሮ ነበር፡፡
ልዕልት ዘነበወርቅን ደግሞ አስባት፡፡ ይቺ ዕድሜዋ በአስራዎቹ የነበረች ቆንጆ ወጣት ‹‹ዘነበወርቅ›› ትባል ከነበረችው የሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ እናት ስም ተወስዶ የተሰየመችው ይቺ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሴት ልጅ – ገና በልጅነቷ የአፄ ዮሐንስ ልጅ የራስ አርዓያ ሥላሴ የልጅ ልጅ ለሆነው (ማለትም ለራስ ጉግሣ አርዓያ ልጅ ለሆነው) ለደጃች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ተድራ ወደ ትግራይ ሄደች፡፡ ነገር ግን የ7ወር እርጉዝ እያለች በህመም በለጋ ዕድሜዋ ተቀጠፈች፡፡ ንጉሥ ተፈሪ በዚህች ልጁ ሞት በሀዘን ክፉኛ ቅስሙ ተሰብሯል፣ በትግራይ ገዢዎች ላይም ከባድ ቂም ቋጥሯልም ይባላል!
(በእርግጥ ሴት ልጅን ያህል ማጣት የመጀመሪያው ክፉ ገጠመኝ አልነበረም – ሌላም በወሊድ የሞተች ልጅ ነበረችው ንጉሥ ተፈሪ፡፡ ልዕልት ፀሐይ፡፡ ይቺ ልዕልት ፀሀይ ኃይለሥላሴ ደግሞ ለወቅቱ ኃያል መስፍን ለራስ አበበ አረጋይ ልጅ – ለጄነራል አብይ አበበ የተዳረች ነበረች – በወሊድ ምክንያት በ23 ዓመቷ ባጭር ተቀጨች እንጂ፡፡)
ራስ መንገሻ ዮሐንስን ደግሞ ውሰድልኝ፡፡ ራስ መንገሻ ዮሐንስ የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ከሆኑት የጎንደሯ ወ/ሮ ከፋይ ወሌ ብጡል ጋር ተጋብተዋል፡፡ የሚገርምህ ራስ መንገሻ ከጣሊያኖች ጋር አብሮ ምኒልክ ከከዳ በኋላ (ወይም ከዳ ከተባለ በኋላ) ተይዞ ታሰረና እቴጌ ጣይቱ በክብር ያጋቡትን የእቴጌይቱን የወንድም ልጅ የሆነችውን ወ/ሮ ከፋይን አፋተውት – መልሰው ለራስ ናደው ዳሯት፡፡ አየህ – ያንን ሥሪተ ሥልጣን የመጠበቅ ኃላፊነትህን ሳትወጣ ስትቀር – ጋብቻህም ይፈርስብሃል – ወይም አለዛቢዋን የነገሥታት ልጅ አጋርህ ትወሰድብሃለች፡፡
ራስ አሉላን ውሰድ፡፡ ራስ አሉላ ሁለት ጊዜ ጋብቻ ፈፅሟል፡፡ የመጀመሪያ ሚስቱ ወ/ሮ ብትወጣ የምትባል ሴት ልጆችን ያፈራችለት ሴት ነበረች፡፡ አሉላ እጅግ ጉልበታም ሲሆንና ዝናው እየገነነ ሲመጣ ግን – በአፄ ዮሐንስ ትዕዛዝ የመጀመሪያ ሚስቱን ፈትቶ – ወ/ሮ አምለሱ አርዓያ የተባለችውን የአፄ ዮሐንስ የቅርብ ዘመድ አገብቶ አንድ ወንድ ልጅ ወልደዋል፡፡
የወሎውን ንጉሥ ሚካኤልን ውሰድ፡፡ መጀመሪያ ስማቸው መሀመድ አሊ ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ ክርስትና አንስተው የክርስትና ልጅ አደረጓቸው፡፡ ከዚያ የወይዘሮ ባፈናን ልጅ ወይዘሮ ማናልሞሽን አገቡ፡፡ ከዚያ ምኒልክን ሴት ልጃቸውን ወ/ሮ ሸዋረገድን ዳሩለትና የሥልጣኔ ወራሽ ነው ያሉትን የወንድ በኩር የልጅ ልጃቸውን – ልጅ እያሱን ወለደ – እያሱ ሚካኤልን፡፡ እንግዲህ የቀድሞው መሀመድ አሊ – የኋላው ራስ ሚካኤል – አንዴ በጋብቻ ተዛምዷልና ሥሪተ ሥልጣኑን የመጠበቅ ኃላፊነት በትከሻው ላይ ይወድቅበታል፡፡ ለዚህ ነው ኋላ ልጅ እያሱ ከዙፋኑ ሲሻር – ንጉሥ ሚካኤል እንዴት ብደፈር ብለው የወሎውን ጦር አዝምተው ‹‹ሰገሌ›› ላይ ከእነ ተፈሪ ጋር የተዋጉት፡፡ ግን ተሸነፈ እንጂ የጋብቻ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡
የሚገርምህ ነገር – የልዑል መኮንን ልጅ የነበረው የእያሱ አብሮአደግ እኩያ – የተፈሪ መኮንን ነገር – እነ ልጅ እያሱንና ራስ ሚካኤልን ከጅምሩም አላማራቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ልጅ እያሱ ተፈሪን በበለጠ ዝምድና ለመያዝ የቅርብ ዘመዱ (የእያሱ የእህት ልጅ) የነበረችውን የወሎዋን መነን አስፋውን ለተፈሪ ሚስት አድርገው ዳሩለት፡፡ አጅሬ ግን ያ ብቻ የሚከለክለው አልመሰለም፡፡ በእርግጥ የእርሱ የግል ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ብዙ ግፊትም ነበረበት፡፡
ድግምግም አድርጎ የሚገርምህስ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ጋብቻ ነው፡፡ የምኒልክ ልጅ ዘውዲቱ ሶስት ጊዜ ተድራለች፡፡ መጀመሪያ ገና በ6 ዓመቷ ለትግሬው ራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ተዳረች – ግን ከ5 ዓመታት በኋላ ባል ስለሞተ ተመለሰች፡፡ ድጋሚ ደግሞ ደጃች ውቤ አጥናፍሰገድ ለተባለው ጉልበታም ተዳሩ – ያም ጋብቻ ፈረሰ፡፡ ይሄ የሥልጣን ጋብቻ ቀጥሎ – ዘውዲቱ በመጨረሻ ለእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ (እና የበጌምድር/ጎንደር ገዢ) ለነበሩት ለራስ ጉግሳ ወሌ ተዳሩ፡፡
የሚገርመው ነገር ራስ ጉግሳ ከዘውዲቱ ጋር ከተፋቱም በኋላ – በጋብቻው የተጣለባቸውን የሥልጣን ሥሪቱን የማስጠበቅ ቃልኪዳናቸውን ያልረሱ ሰው ነበሩና – ተፈሪ መኮንን ንግሥት ዘውዲቱን ከቤተመንግሥት ሲያስወጡ – ራስ ጉግሳ ወሌ ‹‹እንዴት እደፈራለሁ›› ብለው ጦርነት ገጠሙ – በጎንደር ‹‹አንቺም›› በተሰኘው ጦርነት – ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ የአውሮፕላን ቦምብ የጣለበት ጦርነት ተከፍቶ – ተፈሪ መኮንን ድል አደረጉ እንጂ!
በጣም ከሁሉም የምትገርመኝ ለየት ያለች የጋብቻ ታሪክ የአጼ ቴዎድሮስ ነች፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በጎንደር ቋራ ተነስቶ – ቱርኮችን እየተፋለመ፣ ያካባቢውን ባላባቶችም ድል እያደረገ ገበሬውን እንዳሳመጸባቸው ያወቀችው – የቀድሞው የጎንደሩ ሽማግሌ ንጉሥ የአፄ ዮሐንስ (የትግሬው ዮሐንስ ማለትም በዝብዝ ካሳ አይደሉም እኚህ) ሚስት የነበረችው መነንን ውሰድ፡፡ መነንን ከወሎ እስላም ቤተሰብ አውጥተው አሊማ የሚል ስሟን ቀይረው ‹‹መነን›› በሚል ስም ክርስትና አንስተው ያገቧት – ቀዳሚዋ እቴጌ መነን – ያዘመተችበትን  ጦር ድል ላደረገባት ለካሣ ኃይሉ (ለአፄ ቴዎድሮስ) የልጇን ልጅ – የራስ አሊን ልጅ እቴጌ ተዋበችን ዳረችለት፡፡
ቴዎድሮስ ተዋበችን ያገባው በቀዳማይት እቴጌ መነን ትዕዛዝ ቀድሞ ያገባትን እንግዳወርቅ የተባለ የታወቀ የቋራ ሽፍታ ልጅ የነበረች በሠላም በትዳር አብሯት ይኖር የነበረችውን ሚስቱን ፈትቶ ነው፡፡ ሲፈታት እና ተዋበችን ሲያገባ እንግዳወርቅ እንዴት ብትደፍረኝ ብሎ ተነሳበት – እና ከእሱ ጋር የጠና ውጊያ አድርጎ ድል ማድረግ ነበረበት ቴዎድሮስ፡፡
ታዲያ በመሐሉ በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ በውጊያ ቆስሎ (አንዳንዶች ‹‹ኮሶ ታየኝ›› ብሎ ይላሉ) ‹‹ታመምኩ›› ብሎ መልዕክት ሲልክ – እቴጌ መነን ‹‹ለፍየል ጠባቂ ቆለኛ ደግሞ አንድ ብልት መች አነሰው?›› ብላ አንድ ብልት፣ ከ30 እንጀራና ከ1 ገምቦ ጠጅ ጋር ትልክለታለች፡፡ ይህን ያየችው የካሣ ሚስት – ፈሪ ወንድ አልወድም፣ እንዴት ቢንቁህ ነው አንድ ብልት የሚልኩልህ፣ ተነስ ቆርጠህ – ብለዋቸው ነው ተዋበች – አጼ ቴዎድሮስን ለታላቁ ንግሥና ላበቃቸውን የአመጽ ጉዞ ያነሳሷቸው ይባላል – በብዙ የታሪክ ድርሳኖች እንደሰፈፈው ከሆነ፡፡
እንግዲህ – ይህቺኛዋ እቴጌ ተዋበች ደግሞ – የተጣለባትን የሥልጣን ሥሪትን የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቷን ዘንግታ፡- ‹‹ሙሽሪት ለምዳለች፣ ሙሽሪት ለምዳለች – ከናቷም ካባቷም ባሏን ትወዳለች›› ሆኖባት – ጭው ብላ በፍቅር የበነነች ለየት ያለች የጋብቻ ታሪክ ሆና እናገኛታለን፡፡
በአጠቃላይ እንግዲህ እስከ 20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ድረስ የቀጠለው የሀገራችንን ለዘመናት የኖረ የሥልጣን ሥሪት ማስጠበቂያ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው የጋብቻ ትስስር – ከብዙው በጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል አስደማሚ ነገር አለው፡፡ ብዙ ጋብቻዎች ብዙ የደም መፋሰስን አስቀርተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሥልጣን ሽኩቻዎችና ሽሚያዎች የህዝብ ለህዝብ ጠብ ሳይሆኑ ከፍ ያለ የሥልጣን ፍላጎትን ባነገቡ ግለሰቦች መካከል ተወስነው የኖሩ እንደነበርና – ጋብቻዎቹም የእነዚያን ግለሰቦች የሥልጣን ጉዞ በጠብ መንገድ እንዳይፈታ ለማርገብ ከፍተኛ ሠላም የማውረድ ‹‹ፓሲፋዪንግ›› አስተዋፅኦ እንደተጫወቱ ታሪክ የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡
ጥቂቱን ከዚህም ከዚያም ተቀነጫጭበው ከላይ ቢቀርቡም የቀደመው ዘመን በሌሎችም ብዙ የሥልጣን አምቻ ጋብቻዎች የተሞላ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አስደማሚ የሥልጣን ጋብቻ ጥምረቶች አለን የምትሉ – ወዲህ ብትሉ – በሙሉ ልብ እናመሰግናለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለክቡርነታችንም ወደ ሁነኛ ሥልጣን ልታውጣጣን የምትችል አንዲት በገድ የተሞላች ጉብል ጀባ ብትሉን – ምስጋናችን እጥፍ ድርብ እንደሚሆን በፈገግታ ተሞልተን እየተናገርን – በዚሁ ተሰናበትን!
ለሁላችሁም በረካው በያላችሁበት ይድረሳችሁ!
Filed in: Amharic