>

የማላውቅህ ወንድምዬ ፣ ማን ምን ብዬ ልጥራህ? (አሰፋ ሀይሉ)

ወንድምዬ የማላውቅህ፣ ማን ምን ብዬ ልጥራህ?

(የእውነተኞቹ አንበሶች የተሸነፈ ታሪክ)

አሰፋ ሀይሉ

ታሪክ ይሸነፋል እንዴ? ግጥም አድርጎ ነዋ ያውም! ታሪክ የአሸናፊዎች ወልጋዳ ጽሑፍ ናት፡፡ የተሸናፊዎች ታሪክ ተደፍጥጣ ትቀራለች፡፡ ታሪክ ሰሪ ትውልድ ሲፈጠር ታሪኩን መጻፍ ይጀምራል፡፡ ታሪክ ሰሪ ትውልድ የሌለው ሕዝብ ደግሞ የሌሎችን ታሪክ ‹ታሪኬ› ብሎ ሲያነበንብ ይኖራል፡፡ ‹ስልብ ባሪያ በጌታው ብልት ይፎክራል› እንዲሉ አበው፡፡
አንዳንዴ ዘወር ብለን ስናይ ልባችንን በሀዘን እና በቁጭት ከሚያደሙት የታሪካችን ጉድፎች አንዱ አርበኞቻችንን የረሳንበት ጉድፋችን ነው፡፡ ስለ እኛ ሲሉ የቆሰሉትን፣ የተጋደሉትን፣ የደሙትን፣ ያሸነፉትን፣ እና በመጨረሻም የተሸነፉትን ጀግኖቻችንን የረሳንበት መንገድ ነው፡፡ ያ ነው የሚያስቆጨው የታሪካችን ጉድፍ፡፡
እነዚህ ለመሆኑ ማን ናቸው? በድፍን ስም ‹‹ደርግ›› ብለን እንድንጠራቸው የተደረግነው – እናም ‹‹የደርግ ወታደር›› እያልን እየጠራናቸው ያሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ሠሪዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጠብቁ ብለው ኢትዮጵያን ያቆዩልንን አያት ቅድመ አያቶቻችንን አደራ በተግባር ተወጥተው – እና ተሸንፈውም – ተረስተውም ያለፉ ጀግና ትውልዶች ናቸው እነዚህ፡፡ እነዚህ ወያኔና ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ሕዝብ አሸንፈው ዋና ከተማችንን አዲስ አበባን በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሉ በኋላ – በቀይ መስቀል ድጋፍ ወደ ማገገሚያ ለመግባት ዕድሉን ካገኙ ጥቂት የ‹‹ደርግ›› ወታደሮች መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ ዘርና ብሔራቸው የማይገናኝ ከኢትዮጵያ ከስምንቱም ማዕዘን ተምመው ኢትዮጵያን ከጠላት እጅ ለማዳን የተፋለሙ – በመራር ፍልሚያ አስከፊ ዕጣን የተጎነጩ – ኢትዮጵያ የረሳቻቸው የኢትዮጵያ ተሸናፊ ልጆች ናቸው እነዚህ፡፡
እነዚያ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን እንዲህ የቆሰሉት፣ የተቆረጡት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱት ለመሆኑ ለምንድን ነበር? ይሄ እኔን የሚመስል ወገኔ እግሩን የተቆረጠው የት ነው? ከማን ጋር ሲፋለም ነው? መቼ? እንዴት? … ለምንድነው ያኛውስ ጉልበቱን የተሰበረው? እጆቹን ያጣው? ዓይኑ የጠፋው? ይሄኛውስ እግሩን ያጣው በምን ምክንያት ነው? ስሙ ማን ነው? እናቱስ ስሟ ማን ይባላል? አባቱስ በሕይወት ነበሩ? ሚስትስ አለችው ይሆን? ልጆችስ? ለሀገሩ ብሎ ወጥቶ እንዲህ ሆኖ ሲመለስ ማን አመስግኖታል? ማን ታሪኩን ጻፈለት? አካሉ ከጎደለ በኋላ – ይህ የተሸነፈ የኢትዮጵያ ልጅ – ምን ዋጠው? የሞቱትስ ጓዶቹ? ህይወት ለእርሱ እንዴት ነበረች? ምን ሆነ መጨረሻው? ለሀገር መሞት ውለታው ይሄ ነው? ለሀገር መቆረጥ፣ መጉደል፣ ሲያነክሱ መኖር – ይህ ነው የጀግንነት ውለታ? መረሳት ነው የጀግና ዋጋው?
እነዚህ ምስኪን የኢትዮጵያ ልጆች የተከፈላቸው የጀግንነት ዋጋ አስከፊ መረሳት ነው፡፡ ግን — መረሳትማ ብቻ ቢሆን ይሻል ነበር፡፡ ከመረሳት በላይ ደግሞ ምን አለ? ከምንድነው የሚሻለው መረሳት? መረሳት — ስምህ ከመጠልሸት ይሻላል! ለሀገር ያፈሰስከው ደም ለጣዖት እንደተገበረ ደም ከመቆጠር – መረሳት ይሻላል፡፡ አንተ ጀግና ሆነህ ሳለ – ሀገርህን ወገንህን ዳር ድንበርህን የወጉት ጀግና ተብለው ባደባባይ ከፍ ሲል ስማቸው – ታሪክህ መገላበጥ – ታሪክህ ሲገለባበጥ ከምታይ – ተረስቶ መቅረት ይሻላል! መረሳትማ በስንት ጣዕሙ!!! ይህ ሁሉ ከመረሳት የከፋ ዕጣ ፈንታ ነው የደረሰባቸው ለእነዚህ የአንድ ትውልድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፡፡
ይህ እኮ የአንድና የጥቂት ሰዎች ታሪክ አይደለም፡፡ ይህ የብዙ መቶ ሺህዎች ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡ እነዚህን ዳር ድንበራችንን እናስከብራለን ብለው ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በወያኔና ሻዕቢያ ጥይት ተበልተው እንደወጡ የቀሩትን፣ አካላቸውን አጉድለው የተመለሱትን፣ እና አንዳች የምስጋና ቃል ያላገኙትን፣ የጀግንነት ታሪካቸው ያልተወሳላቸውን፣ ውርደትና ድህነት፣ እንግልትና አስከፊ ህይወት የጠበቃቸውን እነዚህን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች የረሳች ሀገር – መቼውኑም ጀግና አይበቅልባትም፡፡ ዛሬ አርበኝነት ይፈለጋል፡፡ አርበኝነት ስሙ ይጠራል፡፡ ለሀገራቸው፣ ለህዝባቸው አርበኛ የነበሩትን ታሪክ ግን ለስማቸው አንዲት የአበባ ዝንጣፊ እንኳ ለመታሰቢያ ሳይኖርላቸው ተረስተው ቀርተዋል፡፡ ታሪካቸውን የሚጽፍላቸው፣ መታሰቢያ የሚያኖርላቸው፣ የሚገባቸውን የታሪክ ክብር የሚሰጣቸው ትውልድ ገና አልተፈጠረም፡፡
የትናንት አርበኞች ሳይከበሩ፣ እንዴት ዛሬ የተከበሩ አርበኞች ይፈጠራሉ? የትናንት አርበኞች በተረሱበት ሀገር፣ እንዴት ዳግም አርበኛ ይፈጠራል? ፈጽሞ አይፈጠርም! ለዚያ ነው – በዚህ አርበኞቹን በረሳ ትውልድ ዘመን – አርበኞችን ፈጥረናል ያሉ፣ አርበኞችን እንመራለን ያሉ ህልመኞች – አሁን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተሞዳሙደው የራሳቸውን ስምና ዝና ሲገነቡ – ስለ ራሳቸው መጽሐፍ ሲፅፉ – ስለ ራሳቸው በያገኙት አጋጣሚ ሲደሰኩሩ – ብቻ የምናያቸው፡፡ እነዚያስ ስም አልባዎቹ አርበኞች የት ደረሱ? እነዚያንስ ስም-አልባ አርበኞች ማን ስማቸውን ያንሳቸው? ስም አልባ መስዋዕትነት፡፡ ስም አልባ አርበኝነት፡፡ ስም አልባ ጉድለት፡፡ ስም አልባ ስብራት፡፡ ስም አልባ ሞት፡፡ ጀግንነታችን ስም አልባ ሆኗል፡፡ አርበኝነታችን እንደ አፈር መቀለጃ፣ መጫወቻ ሆኗል፡፡ ሙያችን ወሬ ብቻ ነው፡፡ ድርጊት እና ጀግንነት ዳግም በምድራችን ላይመለሱ ከአምላክ የተማማሉ ይመስል ከመካከላችን በንነው ጠፍተዋል፡፡ የጀግኖች ታሪክ እንዲህ በውርደት ተቀብሮ እየቀረ – ጀግንነት ከየት ይምጣ?
አንዳንዴ ይገርመኛል፡፡ አርበኛ አርበኛ እንላለን፡፡ አርበኝነት ይናፍቀናል፡፡ አርበኞቿን ከረሳች፣ ካላከበረች ሀገር – አርበኞቿን እንዳልተፈጠሩ ከረሳች ሀገር – የአርበኞቿን ታሪክ አሽቀንጥራ ከጣለች፣ የእውነተኛ አርበኞቿን ታሪክ ካጠለሸች፣ እበት ከለቀለቀች ሀገር – እንዴት ተሆኖ አርበኛ ይበቅላል? ያልተዘራ ይበቅላል ወይ? ‹‹ደርግነት›› ሆኗል መጠሪያው፡፡ ለሀገር ለወገን ለአንድነት ለድንበር ሲሉ ከጠላት ጋር በጀግንነት መፋለም፡፡ የአንድን ዘመን ትውልድ ጀግኖቿን ሁሉ ባንድ ስም አጠቃልላ ‹‹ደርግ›› በሚል የጥቅል መጠሪያ የምትጠራ አገር፣ እና ያሸነፋትን፣ የረገጣትን፣  ያደቀቃትን፣ ቀጥቅጦ በአረመኔ ክንድ የገዛትን ቀማኛ የሀገር ጠላት – ‹‹ጀግኞቼ›› ብላ ያነገሰች፣ ሕዝቦቿን የጀግና መካን አድርጋ ትናንት ባደሟት ቀማኛ ጠላቶቿ እጅ ሰጥ ለጥ ብላ የምትገዛ ሀገር፣ አርበኛ እንዴት ይኖራታል? መቼም አይኖራትም፡፡
የዛሬው ትውልድ – እነዚህን ተረስተው የቀሩ የትውልዳችን ታላቅ የኢትዮጵያ አርበኞች መስዋዕትነትና የሀገር ተጋድሎ የመዘከር ልቡንና አስተዋይነቱን ሊላበስ አይደለም፣ ያ ይቅርና… የጥንቶቹን እንኳ መቶ ዓመት የሞላቸውንም ጀግኖች አርበኞች – የእነ እቴጌ ጣይቱን ሀውልት እንኳ – ልሥራ ወይ እባካችሁ ተማለዱኝ – እባካችሁ ጌቶች ወንዱን ቢቀር ሴቷን እንኳ ጀግና የማስታውስበት መታሰቢያ ልስራ – ጌቶቼ እባካችሁ ፍቀዱልኝ – እያለ ገዢዎቹን ሲለምን ይኖራል፡፡ አንዳንዴ ላሰበው ጓድ መንግሥቱ ታዲያ መች ተሳሳተ? ወይ እኛን ‹‹ጀግና›› ብሎ የጻፈልን ታሪክ ዋሽቷል፣ ወይ ደግሞ ወኔያችንን በትክክልም አንጠፍጥፈን ሸንተነዋል፡፡
እነዚህ የአካል ቁስለኞች ናቸውና እስከቻሉት ድረስ እያነከሱ ይጓዛሉ፡፡ እኛ ደግሞ በአካል ባንቆስልም የልብ እና የመንፈስ እና የታሪክ ቁስለኛ ነንና ዕድሜ ልካችንን በየረገጥንበት ምድር ስናነክስ እንኖራለን፡፡ ጀግና ያለፈራ ትውልድ ሲያነክስ ይኖር ዘንድ ተፈርዶበታልና፡፡
‹‹እውነተኞቹ አንበሶች ታሪካቸውን መጻፍ እስኪጀምሩ ድረስ፣
የአይጦቹ ታሪክ ‹እውነተኛ ታሪክ› እየተባለ ሲዘከር ይኖራል!››
  አልቤር ካሙ
  (ትውልደ አልጄሪያ ፈረንሣዊ ደራሲና ጋዜጠኛ፣ የኖቤል የስነጽሑፍ ሎሬት)
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic