>
9:31 am - Saturday December 10, 2022

አጣሪ ጉባዔው የይስሙላ አሳታፊነት!?! (በፍቃዱ ኃይሉ)

አጣሪ ጉባዔው የይስሙላ አሳታፊነት!?!

በፍቃዱ ኃይሉ


የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ለፌዴሬሽን ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባለሙያዎችን ማሳተፉን የመሰለ ጥሩ ነገር አልሠራም። ሆኖም፣ ባለሙያዎቹን ለማሳተፍ የተደረገው ጥሪ ጨምሮ በብዙ እንከኖች የተሞላ ሒደት ነበር። 

ምርጫው ጊዜ መራዘሙ ቁርጥ ሲሆን የሕገ መንግሥት ምሁራን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ መጣጥፎችን በብዙኃን መገናኛዎች ላይ ሲያትሙ ከርመዋል። መንግሥትም ምሁራኑን ሰብስቦ በማነጋገር «ይህንን ሁኔታ በምን ዓይነት መንገድ እንፍታው?» ብሎ አማክሯል። በስተመጨረሻ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊዎች ከምክክሩ አገኘናቸው ያሏቸውን ሦስት ሕገ መንግሥታዊ አማራጮች ይዘው ብቅ ብለዋል። ሦስቱ አማራጮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንደመሸጋገሪያ መጠቀም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን ወይም ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መፈለግ የሚሉት ነበሩ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሦስቱ አማራጮች «ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ» የሚለውን በመምረጥ ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ኃላፊነቱን ይፋዊ ጥሪ በማድረግ የባለሙያዎችን አስተያየት ሲያዳምጥ እና ሲያስደምጥ ከርሟል። እስከዚህ ድረስ ያለው ሒደት ባመዛኙ ተስፋ ሰጪ ነበር።

ምርጫው በኮቪድ 19 ምክንያት መራዘሙን በግልጽ የተቃወመ የፖለቲካ ቡድን የለም። ነገር ግን ምርጫው በምን ዓይነት መንገድ ይራዘም የሚለው ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያየ አቋም እያራመዱ ነበር። የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ያንን ሁሉ ምክር አድምጦ ሲያበቃ፥ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው ጥቆማ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሲያነሷቸው የነበሩት ጥያቄዎች አግባብ ነበሩ የሚያስብል ከመሆኑም ባሻገር፣ ከዚያ በፊት የነበረው የሕጋዊ መፍትሔ ፍለጋ ሒደት ላይ በሙሉ ውኃ ቸልሶበታል።

የፖለቲካ ድርጅቶቹ ምን ብለው ነበር?

የፖለቲካ ድርጅቶቹ እና መሪዎቻቸው መንግሥት ከያዘው አቋም የተለዩ መፍትሔዎችን ነበር የጠየቁት። ከሁሉም ቀድሞ መናገር የጀመረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ «ጥያቄው የፖለቲካ እንጂ የሕገ መንግሥት አይደለም፣ ማግኘት ያለበትም ፖለቲካዊ ምላሽ ነው» የሚል ነበር። የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ እና የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የጋራ የሆነው ትብብር ለኅብረ-ብሔር ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም መንግሥት ሥልጣኑ እና ጊዜው ተገድቦ እንዲቆይ መክረዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ በበኩሉ ሕገ መንግሥታዊ መሻሻል እንደ ሁነኛ መፍትሔ ከጠቆመ በኋላ፥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጓሜን ስለመረጠ፣ ምርጫው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም እና የአስፈፃሚው አካል በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው አካል ላይ ያልተገባ ሸክም የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን እንዳያሳልፍ ጠይቋል። የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲም ተመሳሳይ አቋም አራምዷል። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ ጊዜያዊ የባለሙያዎች መንግሥት እንዲቋቋም ጠይቋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ ምርጫው ለአገር ሰላም እና ደኅንነት ሲባል ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንዲቆይ ጠይቋል፤ ሆኖም በሒደቱ በርካታ የማሻሻያ ሽግግሮች እንዲካሔዱ እና በዚህም የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሲቪክ ማኅበራት የተሳትፎ ዕድል እንዲሰጣቸው አሳስቦ ነበር።

የፖለቲካ ድርጅቶቹ እንዲህ ያሉ በርካታ ጥያቄዎችን ቢያነሱም ቅሉ፥ በቅጡ ተሰብስበው እንዲመክሩ ዕድል አልተሰጣቸውም ነበር። በመጨረሻው ውሳኔም ምክረ ሐሳቦቻቸው አልተካተቱላቸውም።

የአጣሪ ጉባዔው ፋይዳ ቢስነት

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ለፌዴሬሽን ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባለሙያዎችን ማሳተፉን የመሰለ ጥሩ ነገር አልሠራም። ሆኖም፣ ባለሙያዎቹን ለማሳተፍ የተደረገው ጥሪ ጨምሮ በብዙ እንከኖች የተሞላ ሒደት ነበር። ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን በሕገ መንግሥት ጥናት ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውን ብቻ ሲሆን፥ ይህም አግላይ እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ የሚመለከታቸው በመስኩ ጥናት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱትን ብቻ አስመስሎታል። ከባለሙያዎቹ በመቀጠል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እና የጤና ሚኒስቴርን እንደ ባለድርሻ አካላት ካደመጠ በኋላ፣ የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑትን የፖለቲካ ድርጅቶች ግን እንደ ባለ ድርሻ አካላት መርጦ ሳያደምጣቸው አልፏል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን በዘርፉ ብዙ የተመራመሩ ምሁራንን ጋብዞ ካዳመጠ በኋላ፥ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ያሳለፈው ምክረ ሐሳብ ተሳትፏቸውን የይስሙላ ያደረገ መሆኑ ነው። እውነቱን ለመናገር፣ የይስሙላ ተሳትፎን ማረጋገጥ ካልሆነ በስተቀር፥ የዚያን ዓይነት ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ የሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ባለሙያዎች መመረጣቸው አስፈላጊነቱ ምን እንደሆነ በራሱ ግልጽ አይደለም።

በወቅቱ የቀረቡት ባለሙያዎች በሙሉ በጥንቃቄ እንዲታይ ሲያሳስቡ የነበረው ምርጫው በተራዘመበት ጊዜ የመንግሥት እና የምክር ቤቶቹ ሥልጣን እንዴት መገደብ አለበት እንዲሁም የምርጫው መራዘሚያ ጊዜ ገደብስ መቼ ድረስ ነው የሚል ነበር። እንዲያውም ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፣ «ምርጫው መካሔድ ካለበት በእንዲህ ባለው ቀውስ ጊዜ ነው» ብለዋል፤ ይህንን ያሉት በቀውስ ወቅት መንግሥታዊ ተጠያቂነትን ማጠናከር ስለሚያስፈልግ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ ተቋም ነው። ምንም እንኳን አባላቱ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች ናቸው ተብሎ ቢታሰብም፥ ወክለው የተገኙት ግን የፖለቲካ ድርጅታቸውን ነው። ስለሆነም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ለስህተት ይዳርጋል። ምርጫው የሚራዘምበትን ውሳኔ ባሳለፉበት ዕለት የታየው ክርክርም የሚያመላክተው ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ነው። የሕወሓት ተወካዮች የተቃውሞ ድምፃቸውን ሲያሰሙ የሌሎቹ ክልሎች ተወካዮች ደግሞ (የብልፅግና ፓርቲ አባላት እንደመሆናቸው) ደግፈውታል። ስለዚህ ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አመቻችቶ የሰጠውን ምክረ ሐሳብ ያለ ጥያቄ ማፅደቁ የሚያስደንቅ አይደለም።

ውሳኔው ገደብ የሚባል ነገር አያውቅም። ምርጫው ሊካሔድ የሚችልበት የጊዜ ገደብ በጭራሽ አልተቀመጠም። የክልል እና የፌዴራል ምክር ቤቶች እንዲሁም የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣን ገደብ የሚባል ነገር አልተጣለባቸውም። በአጭሩ ለአምባገነንነት የተመቻቸ ነጻ ፈቃድ ቢባል ይቀላል። እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ለማሳለፍ ባለሙያዎችን ማማከር ትርፉ ማድከም ነው።

Filed in: Amharic