>

"ግብፅ እና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያራምዱት አቋም ከኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው!!!" (አቶ አማንይኹን ረዳ)

 

“ግብፅ እና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያራምዱት አቋም ከኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው!!!”

 አቶ አማንይኹን ረዳ በናሁ ቲቪ በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በነበራቸው ቃለመጠይቅ ካነሷቸው ነጥቦች ፦
እዮብ ሰለሞን

♦ የሚታረስ ሰፊ መሬት፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እና ከ25 ሚሊየን በላይ ስራ አጥ ወጣት ይዘን ሽንኩርት ከሱዳን የምንገዛበት አሳፋሪ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡
♦ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርና እና የገጠር ልማት ስትራቴጂን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ የሚከተል መንግሥት ላለፉት 29 አመታት ሥልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ስልት ግን ለውጥ አላመጣም፡፡ ገጠሩም ግብርናውም አልለማም፡፡ ፖሊሲው ሰርቶ ቢሆን ቢያንስ በሽንኩርት ራሳችንን እንችል ነበር።
♦ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የህዳሴ ግድብ ከማንም በላይ የሚጠቅመው ግብፅና ሱዳንን ነው፡፡
♦ መንግሥት ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ ከሆነ ሜንስትሪም ሚዲያዎች እንዲጠነክሩ መሥራት አለበት፡፡ አለበለዚያ ሀላፊነት የማይሰማቸው አክቲቪስቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቅመው በተለይ ለጋ ወጣቶችን ለግጭት ሊያነሳሱ ይችላሉ፡፡ ሀገርንም ለቀውስ ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ የተረጋገጠ መረጃ ይዘው የሚወጡ ሚዲያዎች መብዛት አለባቸው፡፡
♦ የሜንስትሪም ሚዲያዎች ህልውና መጠበቅ ያለበት ሁለት መሠረታዊ ጥቅሞች ስላሉት ነው፡፡ አንደኛ ሚዲያዎች የዴሞክራሲ ስርአት ምሰሶ ስለሆኑ ጠንክረው እንዲቀጥሉ መደረጋቸው ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡ ሁለተኛ ሀሰተኛ መረጃ እየረጩ ህዝብን ወደ ግጭት የሚከቱ ሰዎችን ድምፅ መቀነስ እና ሚናቸውን ዜሮ ማድረግ የሚቻለው ሜንስትሪም ሚዲያው እንዲዳብር ሲደረግ ነው፡፡ ይሄ ለሀገር መረጋጋት ትልቅ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም መንግስትና ሌሎች አካላት የሚዲያዎች ህልውና እንዲጠበቅ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡
♦ 15 ሚሊየን ህዝብ በየአመቱ ከመንግስት አስቸኳይ የእለት ደራሽ እርዳታ በሚጠብቅበት ሁኔታ፤ በተደራቢነት የኮሮና ወረርሽኝ እና የበረሀ አንበጣ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱብን ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው የኢኮኖሚ ጫና ምክንያት አሁን ላይ ከ25 እስከ 30 ሚሊየን ህዝብ አስቸኳይ የእለት ደራሽ እርዳታ የሚጠብቅበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ በከተሞች አካባቢ እስከ ሰኔ ወር ብቻ ከ2 ሚሊየን ህዝብ በላይ ስራ አጥ ሆኗል፡፡ ይህ ቁጥር በቀጣዮቹ ወራት እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡
♦ መንግሥት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመሻገር ለቀጣዩ አመት ከ400 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ይዟል፡፡ ይህ ለችግሮቹ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ቢሆንም፤ ይህ ሁሉ ብር ገበያ ውስጥ ሲረጭ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በቀጣይ አመት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲጨምሩ እና የምርት እጥረት እንዳይፈጠር በስፋት መስራት አለበት፡፡ አለበለዚያ የኑሮ ውድነት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ አይቀርም፡፡
♦ ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ እውነታውን መቀበል አለብን፡፡ የኮሮናን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርነት በልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በጣም አሳሳቢ ችግር መሆኑን መቀበልና አስፈላጊ ጥንቃቅ መደረግ አለበት፡፡ እንኳን እኛ ደሀ ሀገሮች አሜሪካና አውሮፓም ኮሮናን መቋቋም አቅቷቸው እየተንገዳገዱ ነው፡፡ በሽታው ሳይዘን በፊት የምንችለውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ከተያዝን በኋላ እጅግ ውድ ዋጋ እንከፍላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ቬንትሌተር (የመተንፈሻ መሣሪያ) አራት መቶ ምናምን ነው፡፡ በኮሮና የሚያዘው ሰው ቁጥር ደግሞ 2ሺ አልፏል፡፡ ስለዚህ አቅም ስለሌለን አስቀድሞ መጠንቀቁ ላይ መበርታት አለብን፡፡
♦ ግብፅ እና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያራምዱት አቋም ከኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ፖለቲካዋ እየተናጋች ነው ብለው ባመኑበት ጊዜ ሁሉ የህዳሴ ግድብን አጀንዳ ያጦዙታል፡፡ አሁንም እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው፡፡ ነገር ግን በሀገር ጥቅም ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሆኖ ስላስቸገራቸው አላማቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡
♦ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የህዳሴ ግድብ ከማንም በላይ የሚጠቅመው ግብፅና ሱዳንን ነው፡፡ ግድቡ ሁለቱ አገራት የሚቸገሩበትን የጎርፍ እና የደለል መሙላት ሁኔታ ያስወግድላቸዋል፡፡ ሱዳን ይህን ስለምታውቅ ግድቡ እንደተጀመረ የቁሳቁስ ድጋፍ እስከመስጠት ደርሳ ነበር፡፡ ግብፅም ግድቡ እንደሚጠቅማት ታውቃለች፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንድትለማ እና በኢኮኖሚ የግብፅ ተገዳዳሪ እንድትሆን አትፈልግም፡፡
♦ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨርሳ በአባይ ወንዝ ላይ ሌላ ልማት እንድትሰራ ግብፅ ስለማትፈልግ እንቅፋት እየሆነች ነው፡፡ መፍትሄው ግን ግብፆች የአባይ አመንጪ የሆነችውን ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በመደገፍ የአባይ ወንዝን ህልውና ማስጠበቅ ነው፡፡ ግብፅ ስለ አንድ ግድብ ነው የምታወራው፡፡ አጠቃላይ የአባይ ወንዝ ግን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተጎዳ ስለሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ የአካባቢ ጥበቃ ላይ መሥራት አለባት፡፡
♦ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርና እና የገጠር ልማት ስትራቴጂን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ የሚከተል መንግሥት ላለፉት 29 አመታት ሥልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ስልት ግን ለውጥ አላመጣም፡፡ ገጠሩም ግብርናውም አልለማም፡፡ ግብርናው ዳብሮ ቢሆን ኖሮ ሽንኩርት ከሱዳን፣ ብርቱካን ከግብፅ፤ የዶሮ ሥጋ ከብራዚል፣ ስንዴ ከሩሲያ አናስመጣም ነበር፡፡ ፖሊሲው ሰርቶ ቢሆን ቢያንስ በሽንኩርት ራሳችንን እንችል ነበር።
♦ ኢትዮጵያ ከአለም ቶፕ 5 ሰሊጥ አምራች ሆና 90 በመቶ ህዝቧ ለዛውም የሚረጋ ዘይት ከማልዢያ ነው የሚመጣለት፡፡ በርካታ ወንዝና ሀይቅ ያላት ኢትዮጵያ ሱፐር ማርኬቶቿ ከቬትናም በማመጣ አሣ ነው የተሞላው፡፡ የቲማቲም ድልህ ከጣልያን ነው የምናስመጣው፡፡ የህፃናት ወተት ከኒውዚላንድ ነው የሚመጣው፡፡
♦ የኢትዮጵያን ገቢና ወጪ ምርት አሳፋሪና አሳሳቢ የሚያደርገው ሯሷ ማምረት የምትችለውን በውድ ዋጋ ከውጭ መግዛቷ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ፖሊሲ ለመክሸፉ ይሄ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ የሚታረስ ሰፊ መሬት፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እና ከ25 ሚሊየን በላይ ስራ አጥ ወጣት ይዘን ሽንኩርት ከሱዳን የምንገዛበት አሳፋሪ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡
♦ የግብርና ምርት ችግር የተፈጠረው በመሬት ፖሊሲው ምክንያት ነው፡፡ መሬት አይሸጥም በመባሉ ገበሬው ትናንሽ መሬቱን ይዞ በበቂ ሁኔታ እያመረተ አይደለም፡፡ መሬት እንዲሸጥ ከተፈቀደ ግን አቅም ያላቸው ሰዎች ሰፊ መሬት ገዝተው ብዙ ምርት ማምረት ይችላሉ፡፡ የምርት እጥረትም አይኖርም፡፡ ችግሩ የፖሊሲ ነው መፍትሄውም የፖሊሲ ነው፡፡
♦ 29 አመት መሉ ግብርና ግብርና እየተባለ ተወራ እንጂ ምንም ትኩረት ያልተሰጠው ዘርፍ ግብርና ነው፡፡ በሀይለሥላሤ ጊዜ እኮ የግብርና ባንክ የሚባል ተቋም ተመሥርቶ ነበር፡፡ ያ ባንክ አሁን የለም፡፡ ባለሀብቶች በቂ ማበረታቻ ካልተሠጣቸው ወደ ግብርና ዘርፍ አይመጡም፡፡ ስለዚህ ባስገዳጅ ሁኔታም ቢሆን ባንኮች በግብርና ዘርፍ ለሚሠማሩ ሠዎች ገንዘብ እንዲያበድሩ በማድረግ ዘርፉ እንዲዳብር ማድረግ ያሥፈልጋል፡፡
Interview video links፦
Filed in: Amharic