>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6152

« የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በበላይነት ተቆጣጥረው የሚጠቀሙበት እንደ አባይ ያለ ወንዝ በዓለም ላይ የለም» -  (ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ)

« የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በበላይነት ተቆጣጥረው የሚጠቀሙበት እንደ አባይ ያለ ወንዝ በዓለም ላይ የለም»

ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የአ.አ ዩ. መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ
*************************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- እንደ ናይል የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በበላይነት ተቆጣጥረው የሚጠቀሙበት ወንዝ በዓለም እንደሌለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ አስታወቁ፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ በዓለም ላይ ከ240 በላይ ወንዞች ሁለትና ከዚያ በላይ ሀገራትን አቋርጠው ያልፋሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ቁጥር215 አካባቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
አብዛኞቹን ወንዞች የላይኞቹ እና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ህብረት ፈጥረው እና ተባብረው ወንዞችን እንደሚጠቀሙ የገለጹት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፤ በአንዳንድ ተፋሰሶች ግን የውሃው አመንጪ የሆኑ እና አቅም ያላቸው ሀገሮች አብዛኛውን ውሃ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ማብራሪያ ሀገራት ህብረት ፈጥረው እያለሙ ካሉት ወንዞች መካከል ኢንዱስ ወንዝ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንን ወንዝ ሕንድ እና ፓኪስታን ህብረት ፈጥረው እየተጠቀሙት ነው፡፡ በአውሮፓ የሚገኘውና 13 ሀገራትን የሚያቋርጠው ዳኑብ ወንዝም ሀገራት በትብብር እያለሙት ካሉት ወንዞች ተጠቃሽ ነው፡፡ በተመሳሳይ ስምንት ሀገራትን የሚያቋርጠው ራይን ወንዝም በተመሳሳይ ሀገራቱ በትብብር ያለማሉ፡፡
በምዕራብ እና በደቡብ አፍሪካ አካባቢዎች የሚገኙ ወንዞችንም እንዲሁ ሀገራት ተግባብተው እንደሚያለሙ የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ ለአብነት ያህል ሴኔጋል ወንዝን ሴኔጋል፣ ማሊ እና ሞሪታኒያ የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመው ያለማሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኒጀር ወንዝን 10 የሚሆኑ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ባለብዙ ወገን ስምምነት ተፈራርመው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው የዓለም ሀገራት ወንዞችን ተግባብተው እየተጠቀሙ ሲሆን የማይስማሙባቸውን ጉዳዮችን ግን በይደር እያቆዩ ወንዞችን በማልማት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ አንዳንድ እንደ ናይል ያሉ ትላልቅ ወንዞችን ደግሞ ውሃውን የሚያመነጩ እና አቅም ያላቸው ሀገራት የበለጠ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ወንዞች መካከል በመካከለኛ ምሥራቅ የሚገኘው የጢግሮስና ኤፍራጦስ ወንዝ፣ በአሜሪካ የሚገኘው ኮሎራዶ እና ሪዮ ግራንዴ ወንዞች እንዲሁም በሩቅ ምሥራቅ የሚገኘው ሜኮንግ ወንዞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የጤግሮስና ኤፍራጦስ ወንዞች የአንበሳውን ድርሻ የምትጠቀመው አመንጪዋ ቱርክ መሆኗን የተናገሩት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፤ በኮሎራዶና ሪዮ ግራንዴ ምንጭ ዩ ኤስ ኤ ስለሆነች አብዛኛውን የወንዙን ውሃ ስትጠቀም ለሜክሲኮ ግን ውሃ ታጋራለች፡፡ የሜኮንግ ወንዝ አብዛኛውን ውሃ የምታመነጨው ቻይና ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የጠበቀ ህብረት ባይኖራትም ከሌሎች ጋር ተግባብተው መጠቀምን አትቃወምም ብለዋል፡፡
Filed in: Amharic