>
6:37 pm - Thursday February 2, 2023

መጣላትስ ማንም ይጣላል፤ እውነተኛ እርቅ ግን የጨዋዎች ብቻ ናት፤ መቀሌና አዲስ አበባ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መጣላትስ ማንም ይጣላል፤ እውነተኛ እርቅ ግን የጨዋዎች ብቻ ናት፤ መቀሌና አዲስ አበባ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

መቀሌ እና አዲስ አበባ በከተሙት ኢሃዴግዎች መካከል እርቅ መጀመሩ እጅግ ቢዘገይም ከሰመረ የሚበረታታ እርምጃ ነው። ዋናው ጥያቄ እና እኔን የሚያሳስበኝ ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ ግልግሎች ፍትህ እና እውነትን ጭዳ አድርገው ማለፋቸው ነው።
በሽግግር ጊዜ የሚደረግ እርቅ ምህለቁን የሚጥለው እውነት እና ፍትህ ላይ ነው። እውነቱ በአግባቡ ተነግሮ፣ ጥፋተኛ የጥፋቱ ልክ በአደባባይ ተገልጾ፣ አጥፊ ይቅርታ ጠይቆ፣ ተበዳይ በጉዳቱ ልክ ተክሶ እና ከልቡ ይቅር ብሎ፣ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር እውነትና ፍትህ ብቻ ወደ ላይ ከፍ ብለው፣ አሸናፊ ሆነው፣ ለትውልድ እና ለታሪክ ጥሩ የፖለቲካ ዳራ ትቶ የሚያልፍ ነው። ይህ አይነቱ ሽምግልና የተለያዩ እውቀቶች ያላቸው ሰዎች የሚያከናውኑት የባለሙያዎች ስራ ነው። እቅድ ተሰርቶ፣ ጥናት ተደርጎና በጀት ተበጅቶ የሚሠራ ነው።
ብዙ ጊዜ በሃይማኖት አባቶች እና በአገር ሽማግሌዎች የሚደረግ ግልግል መሠረቱ እውነት እና ፍትህ ሳይሆን አንተም ተው፣ አንችም ተይ ብሎ ሁለት አሸናፊ ወይም ሁለት ተሸናፊ ፈጥሮ እንደ ተኩስ አቁም ስምምነት የጸቡን እረመጥ አመድ አለባበሶ አንጻራዊ ሰላም መፍጠር ነው። ይህ አይነቱ ሽምግልና ብዙ ጊዜ ፍትህና እውነትን ቀብሮ ያልፋል። ሽምግልናው ካስፈለገ እንደውም ‘ዋሽቶ ማስታረቅ’ የሚለውን ሞራላዊ ክሽፈትንም ታሳቢ ሊያደርግ ይችላል። ምክንያቱም ግቡ እውነትና ፍትህ ሳይሆን እርስ በርስ በሚራገጡ ጠበኞች መካከል ሰላም ማውረድ ነው።
እውነተኛ እርቅ ግን እውነተኛ ሸምጋዮች እና ጨዋ ጸበኞች ይፈልጋል:-
ለማንኛውም እርቅ ጥሩ ነው። እውነተኛ እርቅ ደግሞ የጨዋዎች እና የሥልጡኖች ነው። እውነተኛ እርቅ ግን እውነተኛ ሸምጋዮች እና ጨዋ ጸበኞች ይፈልጋል። መቀሌና አዲስ አበባ የመሸጉት ባልንጀሮች በእውነትና በፍትህ የሚቆምሩ ፖለቲከኞች ናቸው። የእርቅ ሂደቱን ሆን ብለው ይመስላል ከእውነትና ከፍትህ አርቀው ወደ አንተም ተው አንተም ተው ሽምግልና የገፋት። በተለይም የአብይ አስተዳደር ዛሬም እውነትና ፍትህን የፈራቸው ይመስላል። እንግዲህ በባልንጀሮች እርግጫ አገር እና ሕዝብ ከሚጎዳ እውነትና ፍትህን ጭዳ አድርጎ በሚገኘው ጊዜያዊ ሰላም መክረም ይሻላል በሚል ሽምግልናው እንዲሰምር እመኛለሁ። ፍትህና እውነት አንድ ቀን ዋጋ ያገኙ ይሆነናል።
ሽማግሌዎቹ ወደ ህወሀት ብቻ ሳይሆን ወደ ምዕራብ ‘ሸኔ’ ይሄዳሉ ተብሏል:- 
 
 በተለይ የም/ወለጋ ነዋሪዎች ላለፉት ሁለት አመታት ያሳለፉት የስቃይ ጊዜ እንዲያቆም ማንኛውንም አይነት ጥረት መደረግ አለበት። በርካታ ዜጎች ሸኔ ለመንግስት ትሰራላችሁ እያለ፣ መንግስት ሸኔን ትደግፋላችሁ እያለ በመሀል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ገሚሱ ወደ ጋምቤላ አቅሙ የቻለ ወደ አዲስ አበባ ገብቶ ይኖራል። በርካታ ወጣቶችም እንዲሁ ከሰፈር ርቀዋል። ዛሬም ድረስ እስሩ እንደ ቀጠለ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ በህዝቡ ስም የተደራጀ እልፍ የፖለቲካ ቡድን እርስ በእርሱ ለጥቅሙ የሚራኮትና የሚጓተት እንጂ ለህዝቡ ፋይዳ ያለው ነገር ያመጣ አይደለም። ህዝቡ ግን ዛሬም ችግሩ እየባሰበት እንጂ እየቀነሰ አይደለም። እንድያውም ሽምግልና ችግርን የሚፈታ ከሆነ ከዚህ አካባቢ ነው መጀመር የነበረበት። እና ከመቀለ መልስ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚሄዱትን ሽማግሌዎች ውጤት በጉጉት እንጠብቃለን።
Filed in: Amharic