>

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ - የአቋም መግለጫ!!! የተግባር እርምጃ ስለመውሰድ

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ – የአቋም መግለጫ!!!

 

የተግባር እርምጃ ስለመውሰድ


በፌዴሬሽን ም/ቤት፣ በሕግ ትርጉም ሽፋን የተላለፈውን የፖለቲካ ውሳኔ በመቃወም የተግባር እርምጃ ስለመውሰድ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የወጣ የአቋም መግለጫ
የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ፣ 6ኛው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በውል ላልታወቀ ዘመን እንዲራዘም እና እድሜያቸው መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ/ም የሚያበቃላቸው ሁሉም ም/ቤቶች በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ መወሰኑን መሠረት አድርጎ፣ የባልደራስ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰፊ ምክክር አድርጓል፡፡
ከመነሻው፣ ገዢው ፓርቲ ለአገራችን የሚጠቅም የፖለቲካ አማራጭ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ከሂደቱ እና ከውሳኔው አግልሎ፣ የስርዓቱ መጠቀሚያ በሆነው የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እና ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ውክልና በነፈገው ፌዴሬሽን ም/ቤት ት ብቻውን የሰጠው ውሳኔ፣ አገራችን ያለችበትን ውስብስብ ወቅታዊ ሁኔታ በቅጡ ያላገናዘበ እና በቀጣይም ከባድ አደጋ የሚጋብዝ አካሄድ እንደሆነ ፓርቲያችን ተገንዝቧል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ዳግም እያቆጠቆጠ የመጣውን የገዢው ፓርቲ አምባገነናዊነት፣ ህሊናቸውን በሸጡ  የፍትህ ስርዓቱ ቀለብተኞች እና ምሁራን ተብዬዎች ዲሞክራሲያዊና ህጋዊ ገጽታ እንዳለው አስመስሎ  ለማስቀጠል የተሞከረ ቢሆንም፣ በፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ የተጀመረው ሂደት የመጨረሻ ውጤት ተረኛ ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት የሚፈጥር ነው፡፡ የተወሰነው ውሳኔ የጠ/ሚ/ር ዐብይ አህመድ መንግስት፣  በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት እንደታየው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኃይል ስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያስችለውን መደላደል የሚፈጥርለት እርምጃ ነው፡፡
1. የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔና እንደምታው
1. 1—-ወቅታዊው የኮረና ወረርሽኝና የአባይ ጉዳይ የፈጠረው ችግር
የህዝባችንን ህልውና ለዘመናት ሲፈትኑ በነበሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ላይ ወቅታዊው የኮሮና ወረርሺኝ የፈጠረው ችግር፣ ምርጫን በጊዜው ለማድረግ የማያስችል ከባድ ሁኔታ መፍጠሩን ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ አገራችን ባነሳችው ፍትሃዊ የአባይ ውሃ አጠቃቀም መብት ጋር በተያያዘ ብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች እንደተደቀኑብን ምስክርነት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡
 እነዚህን መጥፎ አጋጣሚዎች ተጠቅሞ፣ የዜጎችን መብት የማያከብር አምባገነናዊ ስርዓት ለመፍጠር በገዢው ፓርቲ እየተወሰደ ያለው እርምጃ፣ የአገራችንን ልማትም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በእጅጉ የሚያቀጭጭ እና ወደ ግጭት የሚያመራ፣ አስተዋይነት የጎደለው አካሄድ ነው፡፡
1.2  የአገራችንን አንድነትና ሠላም የማይፈልጉ ኃይሎች
ይህ ሕገ-ወጥ ውሳኔ፣ ዶሮ  “ካልበላሁት ጭሬ ላፍሰው” እንዳለችው፣ የአገራችንን አንድነት እና የህዝብን ሰላም ለማይፈልጉ ኃይሎች “ሠርግና ምላሽ” በመሆን ለብጥብጥና አለመረጋጋት በሩን ወለል አድርጎ የሚከፍት ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም የሚቀርቡበትን እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ፣ ችግሮችን ውጫዊ በማድረግ የአገሪቷን የመለወጥ እድል የሚያጨልም የጥፋት ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ህዝብ ታግሎ የጣላቸውን ያለፉትን ስርዓቶች ታሪክን ከመድገም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
2 የመፍትሄ ሃሳቦች
ስለሆነም፣ የመንግስት ሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ሁሉንም ኃይሎች ያሳተፈ፣ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ጉባኤ /ኮንፈረንስ/ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ በባልደራስ እምነት፣ ኢትዮጵያ በቀጣይነት  የሚያስፈልጋት  የባለሙያዎች ባለአደራ መንግስት  ነው።
 ነገር ግን፣ ከዚያ አስቀድሞ ሁሉም ኃይሎች በአገራቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸውን አማራጭ ይዘው በአንድነት ሊመክሩና ሊወስኑ እንደሚገባ ፅኑ እምነታችን ነው፡፡
አሁን የፌዴሬሽን ም/ቤት የሰጠው ውሳኔ ግን፣ በሕግ ትርጉም  የተላለፈ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ ፓርቲያችን ይህን ፖለቲካ ውሳኔ በጽኑ ይቃወማል፡፡ ኢትዮጵያን በፍጥነት ወደ ብሔራዊ መግባባት መድረክ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው  የአገሪቱን መፃኢ እድል ገዢው ፓርቲ  ሌሎችን የፖለቲካ ኃይሎች አግልሎ በብቸኝነት እወስናለሁ የሚል ከሆነ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ህጋዊና ሠላማዊ እርምጃዎችን ይወስዳል።
በአጠቃላይ ፓርቲያችን የአገራችንን ህልውና ለማስቀጠልና ወደ ሀቀኛ ዲሞክራሲ ለመሻገር የሚከተሉትን አቋሞች ይዟል፡-
2.1.የፌዴሬሽን ም/ቤትን ውሳኔንና ጽንፈኞችን በመቃወም ሕጋዊ ሠላማዊ ሠልፍ ስለማድረግ
 የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲያበቃ እና ህዝቡ መስዋዕትነት የከፈለለት የመድበለ ፓርቲ  ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ፓርቲያችን ሰላማዊ እና ሕጋዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህም                    ሕገ-ወጡን የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ እና አገሪቷን ለማፍረስ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎችን በመቃወም፣ የመንግስት የሥልጣን ዘመን ከሚያበቃበት መስከረም 30/2013 ዓ.ም በኋላ ሕጋዊና ሠላማዊ ሠልፍ እንዲካሄድ ጥሪ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
 የሠላማዊ ሠልፉ ጥሪው የኮረና ወረርሽኙን፣ የአገሪቱን አንድነትና ሠላም በዋናነት ግምት ውስጥ ያስገባ ይሆናል፡፡
2.2 የአንድነት ኃይሎችን ትብብርና ቅንጅት በሚመለከት
ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ እየተጠናከረ ያለውን አምባገነናዊ ስርዓት በጋራ ለመታገል፣  የአንድነት ኃይሎች በሙሉ ወደ ትብብር እንድንመጣ ፓርቲያችን ልባዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 2.3.በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን
በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የዚህ አገርን የማዳን ትግል ተካፋይ እንድትሆኑ ፓርቲያችን ልባዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
 2.4 የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአገራችን ወዳጅ የሆናችሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋር አገራት፣  ኢትዮጵያና እና የአፍሪካ ቀንድ ሊገቡበት የሚችለውን ሁሉን አቀፍ ቀውስ በመገንዘብ፣ በገዢው ፓርቲ ላይ ጫና በማድረግ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች አሳታፊ የሚያደርግ ውይይት እንዲደረግ ድጋፍ እንድታደርጉ ፓርቲያችን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
ሰኔ 9/2012 ዓ/ም ፣ አዲስ አበባ
Filed in: Amharic