>
5:31 pm - Tuesday November 13, 0306

"እዚያ ቤት የተመከረ ምክር እኛም ይመከራል!?!" ከአማራ  ተረቶች (በ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

“እዚያ ቤት የተመከረ ምክር እኛም ይመከራል!?!” ከአማራ  ተረቶች

በ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት 

የኦሮሞ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ?  ፣  የአማራ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ ጉዳይ  አይደለም  እንዴ? ፣  የሲዳማ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ፣  የሶማሌው፣ የሀረሪው፣ የጋምቤላው  ጉዳይ የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ?  ለምንድን  ነው  ጠብበን  እና  አጥብበን  የመንደር  ጉዳይ የምናደርገው???
*      *     *
የፍየል  እና  የነብር  ግልገሎች  በአንድ  ሜዳ  ላይ  አብረው  ሲጫወቱ  ዋሉ፡፡  ማታ  ሁለቱም  ወደ የቤታቸው  ገቡና  ለእናቶቻቸው  ውሏቸውን  ነገሯቸው፡፡  «እማየ»  አለ  የነብር  ግልገል፡፡  «ዛሬ  ወደ ኋላ  የተቆለመመ  ቀንድ  ካለው፡፡  ከኋላው  ላይ  በቆዳ  የተሸፈነ  ሥጋ  ነገር  ከተንጠለጠለበት፤ ሲጮኽ ሚእእእእእእ  ከሚል  ግልገል  ጋር  ስጫወት ዋልኩ፡፡  እንዴት  ጨዋታ  ዐዋቂ  መሰለሽ»፡፡
እናት  ከንፈሮቿን  በምላሷ  አራሰችና  «የኔ  ሞኝ  እኔ  እናትህ  ቀኑን  ሙሉ  ስንከራተት  የምውለው ምን  ፈልጌ  መሰለህ፤  እርሱን  ፍለጋኮ  ነው፡፡  ለመሆኑ  ከማን  ጋር  እንደዋልክ  ታውቃልሀ?» አለችው፡፡ ግልገሉ  ባለማወቅ  አንገቱን  ነቀነቀ፡፡ «ሲበሉት  ከሚጥመው፣  ሲቆረጥሙት  አንጀት  ከሚያርሰው  ከፍየል  ግልገል  ጋርኮ  ነው» ግልገሉ  በፀፀት  አንገቱን  ነቀነቀ፡፡ «በል  ነገ  አብራችሁ  የምትጫወቱ  መስለህ  አንገቱ  ላይ  በጥርስህ  ትጨመድድና  እየጎተትክ ታመጣዋለህ»  አለችው፡፡  ተቀበለ፡፡  መሸም፡፡
በፍየልም  ቤት  እንዲህ  ነበረ፡፡ «ዛሬ  እማዬ  ዝንጉርጉር  መልክ  ካለው፣  ቁመተ  ሎግላጋ፣  ሲስቅ  ድመት  ከሚመስል፣  ረዣዥም ጥፍር  ካለው  ልዩ  ግልገል  ጋር  ስጫወት  ዋልኩ»  አላት፡፡  ክው  አለች  እናቱ፡፡  አሁን  የመጣ መስሏትም  በግራ  በቀኟ  ገልመጥ  ገልመጥ  አለች፡፡  ይሰማት  ይመስል  ወደ  ግልገሏ  ጆሮ  ተጠግታ «ከማን  ጋር  እንደዋልክ  ታውቃለህ?»  አለቺው፡፡ አንገቱን  ወደ  ቀኝ  እና  ግራ  ወዘወዘ፡፡ «እርሱኮ  የነብር  ግልገል  ነው፡፡  የነብር  ግልገል  ኮ  የነብር  ልጅ  ነው፡፡  እኔ  ነፍሴ  እስክወጣ  ስሸሽ የምውለው  ከርሱ  አይደለም  ወይ፡፡  የነብር  ዓይን  ወደ  ፍየል  የፍየል  ዓይን  ወደ  ቅጠል የሚባለውን  አልሰማህም  ወይ?»
ግልገሉም  ዕጢው  ዱብ  አለ፡፡  እዚያው  ባለበት  ቀዘቀዘ፡፡ «ታድያኮ  ነገም  ልንጫወት  ተቀጣጥረናል»  አላት፡፡ «ከነብር  ጋር  መጫወት  ከሞት  ጋር  መጫወት  ነው፡፡  የኛን  ዘሮች  አድነው  የፈጇቸው  የርሱ  አያቶች እና  ቅድመ  አያች  ናቸው፡፡  ስለ  ነብር  ስንት  ተዘፍኗል፤  ስንት  ተተርቷል፡፡  ስንት  ተብሏል፡፡  ዛሬ  ዛሬ  ነው ትንሽ  ተንፈስ  ያልነው  ልጄ፡፡  ምንም  ቢሆን  የትናንቱን  አትርሳ፡፡  አንተ  ተደብቀህ  ለብቻህ  ተጫወት፡፡ በድንገት  ካየኽው  ሽሽ፣  ከተከተለህም  ሮጠህ  አምልጥ»  አለቺው፡፡ እህ  በሚል  ስሜት  አንገቱን  ወደላይ  እና  ታች  ወዘወዘ፡፡  መሸም፡፡
በማግሥቱ  የፍየሉ  ግልገል  ቀስ  ብሎ  ግራ  ቀኝ  እያየ  ወደ  መስክ  ወጣ፡፡  ምንም  ነገር  የለም፡፡ እየፈራ  እየቸረ  ቅጠል  መቀንጠስ  ጀመረ፡፡  ጥቂት  እንደቀነጣጠበ  ድምፅ  ሰማ፡፡  ዘወር  ሲል  የነብሩ ግልገል  ወደርሱ  እየመጣ  ነው፡፡  ፊቱን  ወደ  ነብሩ  ግልገል  አዙሮ  ወደ  ኋላው  ማፈግፈግ  ጀመረ፡፡ «የት  ትሄዳለህ?  ና  እንጫወት  እንጂ»  አለው  የነብሩ  ግልገል «አይ  እናቴ  ትፈልገኛለች፤»  እያለ  ወደ  ኋላው  ማፈግፈጉን  ተያያዘው፡፡
«ትናንት  ለዛሬ  ተቀጣጥረን  አልነበረም  እንዴ»  የነብሩ  ግልገል  ጠየቀ፡፡ «ተቀጣጥረን  ነበር» «ታድያ  ለምን  ትሸሻለህ  » «አየህ  እናንተ  ቤት የተመከረው  ምክር  እኛም  ቤት  ተመክሯል»  አለውና  ፈረጠጠ፡፡
ዛሬ  ዛሬ  በየኮሌጆቻችን  እና ዩኒቨርሲቲዎቻችን  የሀገሬ  ልጆች  በሁለት  ቤት  በሚመከር  ምክር ተጠምደው  ይታዩኛል፡፡  ዩኒቨርሲቲዎቻችን  የነብር  እና  የፍየል  ግልገል  አብረው  የሚውሉባቸው ተቋማት  መሆን  ነበረባቸው፡፡  ነብርም  አዳኞቹን  ፍየልም  አራጆቹን  ሳይፈራ፣  ፍየል  በነብር ሳይጠቃ፣  ነብርም  በፍየል  ጌቶች  ሳይታደን  የሚውሉበት  መስክ    ነበረ፡፡
ግልገሎቻችን  ግን  ለዚህ  አልታደሉም፡፡  አማራው  ለብቻው፣  ትግሬው  ለብቻው፣  ኦሮሞው ለብቻው፣  ሶማሌው  ለብቻው፣  ወላይታው  ለብቻው፣  ሲዳማው  ለብቻው፣  አፋሩ  ለብቻው፣ ሌላውም  ለብቻው  ሲመክርበት  የሚያድር  ቤት  እየሆነ  ነው፡፡  መምከሩ  ብቻውን  ደግሞ  ባልከፋ፡፡ የሚመከረው  ስለ  ሌላው  መሆኑ  እንጂ፡፡
እገሌ  ጠላትህ  ነው፣  ጨቋኝህ  ነው፣  የሚንቅህ  ነው፣ ከርሱ  ራቅ፣  አብረህ  አትዋል፣  አብረህ  አትጠጣ፣  በርሱ  ቋንቋ  አትናገር፣  እየተባለ  ነው  ሲመከር የሚያድረው፡፡ በሀገሪቱ  የመጀመርያው  ዩኒቨርሲቲ  በአዲስ  አበባ  ሲቋቋም  በአሮጌው  ሕንፃ  ግድግዳ  ላይ  እንዲህ የሚል  ቃል  ተጽፎ  ነበረ፡፡  «ኩሎ  አመክሩ  ወሠናየ  ግበሩ  ሁሉን  ፈትኑ  መልካሙንም»  ያዙ፡፡
የትምህርት  ተቋማት  መርሕ  ይሆን  ዘንድ  ነበር  የተለጠፈው፡፡  ታድያ  ይህ  ጥቅስ  ሁሉን  የሚፈትን ሳይሆን  የራሱን  ብቻ  የሚያይ፣  ሌላውንም  በጥላቻ  የሚቃኝ፣  ብሎም  ስለ  ሌላው  የነብር  እና  ፍየል ምክር  በየጎሬው  ሲመክር  የሚያድር  ተማሪ  ሲያይ  ምን  ይል  ይሆን» የነብሩም  የፍየሉም  እናቶች  ለግልገሎቻችው  የነገሯቸው  የእነርሱን  ቁርሾ  ነው፡፡
ፍርሃታቸውን  ነው፡፡
የነብር  እና  የፍየል  ግልገል  አብረው  የመዋላቸው  ጥቅም  አልታያቸውም፡፡  አብረው  የመዋላቸው አዲስ  ታሪክ  አልተሰማቸውም፡፡  አብረው  የመዋላቸው  ሀገራዊ  ጠቀሜታ  አልተዋጠላቸውም፡፡   ምንጊዜም  ትውልድ  ካለፈው  የተሻለ  ካላሰበ፣  ያለፈውን  ችግር  ፈትቶ፣  የተሻለ  ዓለም  ካላሳየ ትውልድነቱ  ምኑ  ላይ  ነው?  ግልገሎቹ  ለየብቻ፣  ያም  በጉሮኖው  ይኼም  በዋሻው  የተመከረውን ብቻ  የሚያስፈጽሙ  ከሆነ  እነዚህ  አሮጌ  ግልገሎች  እንጂ  አዲስ  ትውልዶች  እንዴት  ይሆናሉ፡፡ ለመሆኑ  ስለ  ኦሮሞ  ጉዳይ  ኦሮሞዎች  ብቻ  መነጋገር፣  መምከር፣  መጨነቅ  አለባቸው?  የኦሮሞ ጉዳይ  የአማራ፣  የትግሬ፣  የአፋር፣  የሶማሌ፣  የወላይታ  ጉዳይ  አይደለም  ያለው  ማን?  ማነው ይህንን  አጥር  የሠራው?  የትግሬን  ጉዳይ  ማነው  የትግሬ  ብቻ  ነው  ያለው?  ሌላው  አያገባውም? አያስጨንቀውም?  አይመለከተውም?  ለምንድን  ነው  በየጉሮኗችን  እና  በየዋሻችን  ብቻችንን የምንመክረው፡፡
የኦሮሞ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ?  የአማራ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ ጉዳይ  አይደለም  እንዴ፣  የሲዳማ  ጉዳይ  የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ፣  የሶማሌ  ጉዳይ የኢትዮጵያ  ጉዳይ  አይደለም  እንዴ?  ለምንድን  ነው  ጠብበን  እና  አጥብበን  የመንደር  ጉዳይ የምናደርገው፡፡  ጎበዝ  እዚያም  ቤት  እንደ  ሚመከረውኮ  እዚህም  ቤት  ይመከራል፡፡  እነ  እንቶኔ እንደሚያስቡትኮ  እና  እንትናም  ያስባሉ፡፡   ለምን  አብረን  አንመክርም?  የነብርም  ሆነ  የፍየል  ግልገል  ጠላትነቱ  የሚቀጥልበትን  መንገድ  ብቻ ነው  በየበኣታቸው  ሆነው  የመከሩት፡፡
እኛምኮ  ከእነርሱ  አልተሻልንም፡፡  ለየብቻ  ተሰብስበን  ከተቻለ ስለ  ነባሩ  ጠላታችን  እንመክራለን፤  ካጣንም  ጠላት  እንፈጥራለን፡፡
ዛሬ  ኢትዮጵያ  ውስጥ  በየበኣቱ  ብቻ  የሚመከርባቸውና  የበኣት  ጠላት የሚፈራባቸው  ሁለት ጉዳዮች  አሉ፡፡  ዘር  እና  እምነት፡፡  በክርስቲያኑም  ዘንድ  ነብር  እና  ፍየል  አለ፡፡  በሙስሊሙም ዘንድ  ነብር  እና  ፍየል  አለ፡፡  እነዚያንም  ለብቻ  ጠርተው  በቤታቸው  የሚመክሯቸው  አሉ፡፡ እነዚህንም  ለብቻ  ጠርተው  በቤታቸው  የሚመክሯቸው  አሉ፡፡  የነብር  እና  የፍየል  የማያውቁትን ጠላትነት  የገዛ  ወላጆቻቸው  እንደተከሉባቸው  ሁሉ  እነዚህንም  «እገሌ  ጠላትህ  ነው  ተጠንቀቀው» እያሉ  ጠላት  ተክለው  ጠላት  የሚያበቅሉ  ሞልተዋል፡፡
መጀመርያ  ክርስቲያኑ  እና  ሙስሊሙ  ለየብቻ  እንዲመክሩ  አድርገው  የጠላትነትን  መንፈስ  ዘሩ፡፡ ቀጠሉና  በሙስሊሙ  መካከል  ነብር  እና  ፍየል  ፈጠሩ፤  በክርስቲያኑ  መካከልም  ነብር  እና  ፍየል አፈሩ፡፡  ግን  እስከ  መቼ  ከነብር  ተጠንቀቅ፣  ፍየልን  እነቅ  እየተባልን  እንኖራለን?  አሁን  በሁላችንም ልብ  ውስጥ  የተጠቂነት  ሥነ  ልቡና  እየሠረፀ  ነው፡፡
ሁሉም  ተበድያለሁ፣  ተገፍቻለሁ፣  ተጠቅ ቻለሁ፣  ተጨቁኛለሁ፣  ተደፍሬያለሁ፣  ተዋርጃለሁ  እያለ  ብቻ  ነው  የሚያስበው፡፡ በአንድ  ወቅት  ከወንዝ  ወዲህ  እና  ወዲያ  የሚኖሩ  መንደርተኞች  ነበሩ  አሉ፡፡  ታድያ  የሁለቱ መንደርተኞች  ልጆች  ወንዙ  ጋ  ሲገናኙ  ያዩ  ወላጆቻቸው  እየጠሩ  «እነዚያ  መንደርተኞች  ቡዶች ናቸውና  አትቅረቧቸው»  እያሉ  ልጆቻቸውን  ይመክሩ  ጀመር፡፡
የዚህኛውም  መንደር  ሆነ  የዚያኛው መንደር  ምክር  ተመሳሳይ  ነበረ፡፡  እነዚህም  እነኛን  እነኛም  እነዚህን  ቡዶች  ናቸው  ብለው  ፈርተው በየመንደራቸው  ቀሩ፡፡ ይህንን  ያዩ  የሁለቱ  መንደር  ሽማግሌዎች  አንድ  ቀን  ተነጋገሩና  ወንዙ  ዳር  ተገናኙ፡፡  እናም  እንዲህ ብለው  ጠየቁ  «ለመሆኑ  ቡዳው  ማነው)?»  ያን  ጊዜ  አንዲት  እናት  ተነሡና  «እነርሱም  እኛን ይላሉ  እኛም  እነርሱን  እንላለን½  ቡዳው  አልታወቀም  ግን  እንበላላለን»  አሉ  አሉ፡፡
የየእምነቱ  ሰዎች  ችግሩን  ከሌላ  ቦታ  እየፈለጉት  እነዚያኞቹን  ቡዶች  እያልናቸው  ነው  እንጂ  ችግሩ ያለው  ከራሳችን  ነው፡፡  ኢትዮጰያ  ውስጥ  አማኞቹን  የሚመጥን  የእምነት  ተቋም  እና  የእምነት አባት  እጥረት  ተከስቷል፡፡  በእስልምናም  እንሂድ  በክርስትና  አማኞች  በእምነት  አመራሮቻቸው  እና አባቶቻቸው፣  ተቋሞቻቸው  እና  አሠራሮቻቸው  ሊረኩ  አልቻሉም፡፡ አሁን  በአማኞች  መካከል  በየጉሮኗችን  እንድንመክር  እና  ቡዶቹ  እነዚያኞቹ  ናቸው  እንድንል ያደረገን  ተቋማዊ  ችግሮቻችንን  መፍታት  ባለመቻላችን  ነው፡፡  የአስተዳደር  በደል፣  ሙስና፣  ዝርፊያ፣ ለሥልጣን  መሯሯጥ፣  የእምነት  ሕግጋትን  ለጥቅም  ሲሉ  መሸጥ፣  እግርን  ቤተ  እምነት  አድርጎ  ራስን
ፖለቲካ  ላይ  መንተራስ፣  የዘመድ  አዝማድ  አሠራር፣  ለታሪክ፣  ባህል  እና  ቅርስ  ግዴለሽ  መሆን የኢትዮጵያ  ቤተ  እምነት  ተቋማት  የጋራ  ጠባያት  እየሆኑ  ነው፡፡ እነዚህ  አካላት  እኛ  ተስማምተን  ወደ  እነርሱ  እንድናይ  ስለማይፈልጉ  በየጉሮኗችን  ለየብቻ ይመክሩናል፡፡  እኛም  የማናውቀውን  ጠላት  እናውቃለን፣  መንገዳችንም  እምነት  ተኮር  መሆኑ  ቀርቶ ጠላት  ተኮር  ይሆናል፡፡
ይመስለናል  እንጂ  አንደኛችን  አዝነን  ሌላችን  ልንደሰት  አንችልም፡፡ አንዳችን  አንገታችን  ደፍተን  ሌላችን  ቀና  ልናደርግ  አንችልም፡፡
ነፍስ  ኄር  አባ  እንየው  ውቤ ዘአሶሳ  በደርግ  ጊዜ  ከዞኑ  ኢሠፓ  ጽ/ቤት  ለሠፋሪ  ሙስሊሞች  የመስጊድ  መሥሪያ  ቦታ  ሊያስፈቅዱ ሲገቡ  የኢሠፓ  ጸሐፊው  «እርስዎ  ክርስቲያን  ሆነው  ስለ  ሙስሊሙ  የሚከራከሩት  ለምንድን ነው?»  ብሎ  ሲጠይቃቸው  «ወዳጄ  ሙስሊሙ  እያዘነ  ክርስቲያኑ  ሊደሰት  አይችልም፣  እምነት የግል፣  ደስታ  ግን  የጋራ  ነው»  ነበር  ያሉት፡፡ ይልቅስ  ጎበዝ  ሞኞች  አንሁን፡፡
በጋራ  እንምከርና  ጠላትነቱን  ትተን  ፊታችንን  የየራሳችንን  ቤት በጋራ  ወደማስተካከል  እንምጣ፣  ተቋማዊ  አሠራሮቻችንን  እንፈትሻቸው፡፡  ለምንድን  ነው  በእምነት ተቋሞቻችን  እና  በእምነት  መሪዎቻችን  እኛ  ኢትዮጵያውያን  ልንረካ  ያልቻልነው?  ለዚህ  ጥያቄ የጋራ  ምላሽ  እንፈልግ፡፡ ያን ጊዜ ነብር እና ፍየል አብረው ይውላሉ፡፡
Filed in: Amharic